ቢሾፍቱ:- በኦሮሚያ ክልል የተቋቋሙ የባህላዊ ፍርድ ቤቶች ኅብረተሰቡ በሚያውቀው ባህል እና ወግ መሠረት ጉዳዩን በቀበሌው እንዲፈጽም በማስቻል የመደበኛውን ፍርድ ቤቶች ጫና በማቃለልና የፍትሕ አገልግሎት እንዲዳረስ እያስቻሉ እንደሚገኝ የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ገለጸ፡፡
የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ገዛሊ አባሲመን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በፍርድ ቤት አሠራር የተቀመጡ ቀልጣፋ ተደራሽ እና ውጤታማ አገልግሎት የማዳረስ ተልዕኮን በመወጣት የኅብረተሰቡን አመኔታ ለማሳደግ በትኩረት እየተሠራ ይገኛል። በክልሉ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ በአዋጅ ቁጥር 240/2013 የወጣው የባህላዊ ፍርድ ቤት አዋጅ ኅብረተሰቡ በሚያውቀው ባህል እና ወግ መሠረት ጉዳዩን በቀበሌው እንዲፈጽም ማድረግ መቻሉን ጠቁመዋል።
በተግባሩ ከሰባት ሺህ በላይ የመጀመሪያ ደረጃ ባህላዊ ፍርድ ቤቶች ተቋቁመው 372 የሚሆኑ ይግባኝ ሰሚ ባህላዊ ፍርድ ቤቶችን በማቋቋም በሁሉም የኦሮሚያ ቀበሌዎች እና ወረዳዎች አገልግሎቶቹ እየተሰጡ መሆናቸውንም አመልክተዋል።
ኅብረተሰቡ ወደ ፍርድ ቤት እየተመላለሰ ጊዜውን እና ገንዘቡን ከሚጨርስ በቅርበት በመጠቀም በጊዜው አገልግሎቱን እንዲያገኝ በማስቻል በሂደቱ ተጠቃሚ ሆኗል ብለዋል።
በዚህ ተግባር ኦሮሚያ ክልል ለሌሎች ክልሎችም አርዓያ በመሆን ባህላዊ ፍርድ ቤትን በራሳቸው ተነሳሽነት አዋጅ እያወጡ ወደ ሥራ የገቡ ክልሎች መኖራቸውን አንስተዋል።
ባህላዊ ፍርድ ቤት ተግባራዊ በመደረጉ ሐሰተኛ ማስረጃን በመቀነስ ፍትሕን ማስፈን መቻሉን አመልክተው፤ በባህሉ መሠረት አንድ ሰው ወደ ባህላዊ ፍርድ ቤት ሲሄድ የራሱ ቃለመሐላ አፈጻጸም በመኖሩ መዋሸት አይቻልም ነው ያሉት።
በቀበሌው የሚሰጥ ፍትሕ በመሆኑ የተፈጸመው እና ያልተፈጸመው ምን እንደሆነ የሀገር ሽማግሌዎች ስለሚያውቁ እውነትን በማውጣት ሂደት መልካም ተፅዕኖ ማሳረፉንም ጠቁመዋል።
የባህላዊ ፍርድ ቤት ሽማግሌዎች ጉዳዩን የሚቋጩት ሁለቱን ወገን አስታርቀው መሆኑን ጠቁመው፤ እውነቱ ከወጣ በኋላ ታርቀው ስለሚለያዩ በኅብረተሰቡ ውስጥ መልካም ግንኙነት እንዲቀጥል ያደርጋል ብለዋል።
ደንበኛው ወደ ፍርድ ቤት በመመላለስ የሚያወጣውን ጊዜና ገንዘብ ማስቀረት ተችሏል። ፍርድ ቤት የሚመጡ ጉዳዮችንም እያቀለለ ነው። መደበኛ ፍርድ ቤት ቢሆን ግን አንዱ ላይ የሚወስን በመሆኑ የጠላትነት ስሜት እንዲቀጥል ያደርጋል ነው ያሉት።
የባህላዊ ፍርድ ቤቶች ከመቋቋማቸው በፊት በዓመት በአማካኝ ከ15 እስከ 20 በመቶ ጉዳዮች ይጨምሩ እንደነበር አውስተው፤ በኦሮሚያ ክልል የባህላዊ ፍርድ ቤት ከተቋቋመ በኋላ ወደ ፍርድ ቤት የሚመጡ ጉዳዮች እየቀነሱ መሆናቸውን አመልክተዋል።
ፍርድ ቤቱ ተደራሽነትን ለማሳደግ ቴክኖሎጂን በመጠቀም አገልግሎትን ለማሳደግ ትኩረት ማድረጉን በመጠቆምም፤ ቴክኖሎጂን በማልማት በጠቅላይ፣ በከፍተኛ እና በወረዳ ፍርድ ቤቶች ለማዳረስ በማቀድ ወደ ሥራ ተገብቷል ብለዋል።
አንድ ሰው ከጠቅላይ ፍርድ ቤት አገልግሎት ለማግኘት በአካል መቅረብ ሳይጠበቅበት፤ ባለበት ወረዳ ቀርቦ በኢ-ፋይሊንግ ሲስተም ጉዳዩን መላክ የሚችልበት ሥርዓት ተግባራዊ እንደሆነ ገልጸው፤ አሠራሩ ጉዳዩ ታይቶ መዝገብ ተከፍቶ ለዳኛ ከቀረበ በኋላ ባለጉዳዩና ዳኛው በቪዲዮ ኮንፍረንስ የሚገናኙበት መሆኑንም ጠቁመዋል።
የፍርድ ቤት ሥራ ነፃነትና ተጠያቂነት ተመጣጣኝ መሆን አለበት ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ነፃነት እንዳለ ሁሉ ለሚሠራቸውም ተጠያቂነት መኖሩንም ነው የገለጹት። ሥነምግባርን የተላበሰ ዳኛ እና ኅብረተሰብ ወሳኝ እንደመሆኑ ለትግበራው የተለያዩ ሥልጠናዎች እንደሚሰጡም ጠቁመዋል።
እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ፤ ሥራውን ለመሥራት የሚያስችል ጥቅማ ጥቅምና ደመወዝ ተመጣጣኝ መሆን አለበት። ይህ ሲደረግ በሀገር ደረጃ ሊከፈል በሚችለው መጠን ነው። በጥናት በተደገፈ መልኩ በዳኞች አስተዳደር ጉባኤ እየታየ ይፈጸማል።
የዳኞች ፍልሰትን ለመቀነስ ማስተካከያ ለማድረግ በማሰብ ጥናቶች እየተካሄዱ መሆኑን አመልክተው፤ ጥናቶቹ ሲጠናቀቁ ለመንግሥት ቀርቦ ውሳኔ ሲያገኝ ችግሩ ይፈታል። ለጊዜው በፌዴራል ደረጃ የተጀመሩ ሥራዎችም በቅርቡ ውሳኔ እንደሚያገኙ ተስፋ በማድረግ እየጠበቅን ነው ብለዋል።
የዳኝነት ሥርዓቱን ለማዘመን እና ጥራት ያለው አሠራር ተግባራዊ ለማድረግ የሕዝብ ተሳትፎ አስፈላጊ ነው። በዳኝነት ሥርዓቱ ማነቆ ሆኖ እያስቸገረ ያለው ከውሸት ማስረጃ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ናቸው ያሉት የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ገዛሊ አባሲመን፤ ኅብረተሰቡ የውሸት ማስረጃ የፍትሕ ሥርዓቱ ማነቆ፣ በሃይማኖትም የተከለከለ መሆኑን በመረዳት ሊያወግዘው ይገባል ነው ያሉት።
ዘላለም ግዛው
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 12 ቀን 2017 ዓ.ም