የአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጣናን በአግባቡ መጠቀም የሚያስችል ፕሮጀክት ሊተገበር ነው

አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጣናን በአግባቡ እንድትጠቀም የሚያግዝ ፕሮጀክት ሊተገበር መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴርና የአውሮፓ ኅብረት አስታወቁ።

በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወንድሙ ፍላቴ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር እና የአውሮፓ ኅብረት በጋራ የሚተገብሩትን ፕሮጀክት አስመልክተው በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነትን ፈርማ ወደ ሥራ ለመግባት በዝግጅት ላይ ትገኛለች። ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱም ከአውሮፓ ኅብረት ጋር በመተባበር ኢትዮጵያ በነፃ ንግድ ቀጣናው የሚኖራትን ተሳትፎ ውጤታማ ለማድረግ የሚያዝ ፕሮጀክት ሊተገበር ነው ብለዋል።

ኢኮ ትሬድ/ECOTRADE/ የተሰኘው ይህ ፕሮጀክት ለአራት ዓመት እንደሚተገበር ጠቁመው፤ የአውሮፓ ኅብረት ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ የሚሆን ስድስት ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል። የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ውስጥ ስንገባ የእኛ ገበያ ለሌሎች፣ የሌሎች ሀገራት ገበያም ለእኛ ነጋዴዎች ክፍት እንደሚሆን አመልክተው፤ ፕሮጀክቱ በዚህ ሂደት ውስጥ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመውጣትና ሀገራዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ተጨማሪ አቅም እንደሚፈጥር አብራርተዋል።

ፕሮጀክቱ የንግድ ሥርዓትን ከማሳለጥ ባለፈ የአመራረት ሂደታችን የአካባቢውን ሥነ ምሕዳር የማይጎዳ እንዲሆን አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት የተያዘውን ሀገራዊ ተልዕኮ ለማሳካት እንደሚያግዝም ጨምረው ገልጸዋል።

በአፍሪካ ሀገሮች መካከል ያለውን የንግድ ትስስርን ከማጠናከር ባለፈም ታሪፍን ለመቀነስ፣ የንግድ እንቅፋቶችን ለማስወገድ፣ የገቢና ወጪ ንግዱን ሚዛናዊ የቴክኖሎጂ እና የእውቀት ሽግግር ለማድረግ፣ የምርት ጥራትን ለማረጋገጥ እገዛ እንደሚያደርግ አብራርተዋል።

ፕሮጀክቱ ሴቶችና ወጣቶችን ጭምር ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ገበያ የማፈላለግ እና አቅም የመገንባት ሥራን እንደሚሠራ አመላክተው፤ በአጠቃላይ ፕሮጀክቱ የምርት ጥራትን ለማረጋገጥ፣ ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንዳለው አብራርተዋል። ፕሮጀክቱ የታለመለትን ዓላማ ማሳካት እንዲችል በመንግሥት በኩል ድጋፍና ክትትል ይደረጋል ነው ያሉት።

አያይዘውም ሀገራዊ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ትግበራ ስትራቴጂ በማስፀደቅ ወደ ትግበራ ለመግባት በትኩረት እንደሚሠራ አመላክተዋል።

በአውሮፓ ኅብረት የግል ዘርፍ ንግድ፣ ኢኮኖሚና አካባቢያዊ ትስስር ፕሮግራም ኦፊሰር አርድያን ካኖ በበኩላቸው፤ የአውሮፓ ኅብረት ለበርካታ ዓመታት የኢትዮጵያ የልማት አጋር ሆኖ ዘልቋል። ኢኮ ትሬድ ፕሮጀክትም ኢትዮጵያ በአፍሪካን ነፃ የንግድ ቀጣና የሚኖራትን ተሳትፎ ለማሳለጥና ለመደገፍ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የበርካታ ወጣቶች ሀገር መሆኗ አስታውሰው፤ ፕሮጀክቱ በቆዳ፣ በቡና እና በአትክልትና ፍራፍሬ (በሆልቲካልቸር) ዘርፍ ለተሰማሩ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች አረንጓዴ ኢኮኖሚን መገንባት በሚያስችል መልኩ እንዲያመርቱና ተወዳዳሪ ሆነው እንዲወጡ የሚያግዝ ድጋፍ እንደሚደረግ አመልክተዋል።

የኢኮ ትሬድ ፕሮጀክት ቡድን መሪ ሜሮን ዳኘው፤ ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያ የጀመረችውን አረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ባማከለ መልኩ ዕሴት የተጨመረባቸውን ምርቶች ለአፍሪካ ገበያ ማቅረብ የሚያስችል ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎችም የአፍሪካ ሀገራት የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣናን እውን ለማድረግ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ጠቁመው፤ ኢኮ ትሬድ ፕሮጀክት በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ ወጣቶችና ሴቶችን አቅም በማሳደግ የሚፈጠረውን የገበያ ዕድል በአግባቡ መጠቀም የሚያስችል አቅም መፍጠርን ዓላማ ያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የኢኮ ትሬድ (ECOTRADE) ፕሮጀክት ሰኔ 13 ቀን 2017 ዓ.ም ይፋ እንደሚደረግ ተመላክቷል።

ፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 12 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You