እያደገ የመጣው የስታርት አፖች አቅም

ወጣት ጌትነት ዘመነ ይባላል። የእፎይ ፕላስ ሐውሲንግ ሶሉሽን የተባለ የስታርት አፕ ድርጅት መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ነው። ድርጅቱ ከአምስት ዓመት በፊት እንደተመሠረተ፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ የስታርትአፕ ምሕዳሩ እያደገ መምጣቱ ለስታርትአፖች ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ መሆኑን ይናገራል።

ድርጅቱ ገና ስታርትአፕ ቢሆንም ከትንሽ ተነስቶ እያደገ ከመምጣቱ ባሻገር ከሌሎች ስታርትአፖች ተወዳድሮ በማሸነፉ በዓለም አቀፉ የቴክኖሎጂ ኤክስፖ ላይ ሳይቀር መሳተፍ መቻሉን ይገልጻል። ድርጅቱ የአዲስ አበባ ከተማ አጠቃላይ መኖሪያ ቤቶችን የሚያስተሳስር ዘመናዊ የኅብረተሰብ አስተዳደር ሥርዓት /ስማርት ኮሚኒቲ ማኔጅመንት ሲስተም/ ለመፍጠር ታልሞ እንደተመሠረተ ይናገራል።

እሱ እንደሚለው፤ በአዲስ አበባ ከተማ አፓርትመንቶችን ጨምሮ የጋራ መኖሪያ ቤቶች እና ኮምፓውንድ የሆነ የመኖሪያ ግቢዎች እየተበራከቱ መጥተዋል። በመሆኑም አሠራሩን /ሲስተሙን/ በማዘመን ከዘመናዊ ከተማ ጋር የተገናኘ ፕላትፎርም መዘርጋት አስፈላጊ ነው።

በቴክኖሎጂ በመታገዝ አሠራሩን ማዘመን እንደ ሚያስፈልግ አንስቶ፤ አሠራሩን ማዘመን አብዛኛውን በጋራ መኖሪያ ቤት ነዋሪዎችና ማኅበራት መካከል የሚስተዋለውን ከፍተኛ የግልጸኝነት ችግር ለመፍታት እንደሚያስችል እምነት አለው።

በሞባይልና በድረገጽ ፕላትፎርም ተጠቅሞ ዘመናዊ አሠራር መዘርጋት እንደሚቻል የሚገልጸው ወጣት ጌትነት፤ ይህም ነዋሪዎች የማኅበሩ ቢሮ ድረስ መሄድ ሳይጠበቅባቸው የተለያዩ ክፍያዎችንና ወርሐዊ መዋጮን ሳይቀር በቴሌ ብር በመሳሰሉት የክፍያ ሥርዓቶች ለመፈጸም የሚያስችል ነው።

ፕላትፎርሙ ብዙ ችግሮች የሚያቀልና ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው፤ የማኅበራቱንና የነዋሪዎችን ችግር የሚፈታ ነው። ከዚህ ባሻገር አሠራሮችን በማዘመን ዲጂታል ኢትዮጵያ እውን በማድረግ ረገድ የበኩሉን ሚና እየተወጣ እንደሚገኝ አመልክቷል።

መተግበሪያው በማኅበሩና በነዋሪዎች መካከል ያለው ግልጸኝነት እንዲፈጠር ያደረገ መሆኑን ጌትነት ይጠቁማል። አሠራሩ መዘመኑ መረጃዎች በዘመናዊ መልኩ እንዲያዙ፣ ክፍያዎች በኦንላይን እንዲሆኑና ሪፖርት በቀላሉ እንዲያገኙ፣ አጭር መልዕክቶች በአፋጣኝ እንዲያገኙ ያደርጋል።

ይህም በነዋሪውና በማኅበሩ መካከል መተማመን የፈጠረ ዘመናዊ አሠራር እንዲኖር የሚያደርግ መሆኑን፤ መንግሥትም ከነዋሪውና ከማኅበረሰቡ ጋር የሚያደርገው ግንኙነት ዘመናዊ እንዲሆን ያስችላል ብሏል።

በቀጣይ ድርጅቱ በአዲስ አበባ ከተማ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን በላይ አባወራና በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ10ሚሊዮን በላይ ነዋሪ በዚህ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ እንዲሆን ለማድረግ አቅዶ እየሠራ እንደሆነም ጠቁሟል ።

ሌላኛው ወጣት ሮቤል ፍቅር ይባላል፤ ‹‹ያስፈልጋል ኢትዮጵያ›› መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ነው። ‹‹ያስፈልጋል ኢትዮጵያ›› እ.ኤ.አ 2019 መጨረሻ አካባቢ እንደተመሠረተ ይናገራል።

ድርጅቱ ከተመሠረተ አምስት ዓመታት የሆነው ስታርትአፕ ድርጅት ቢሆንም ቀደም ሲል ከነበሩት ተግዳሮቶች የተነሳ በተፈለገው ፍጥነት መጓዝ እንዳልቻለ የሚገልጸው ሮቤል፤ የስታርትአፕ ሥነ ምሕዳሩ እየሰፋ በመምጣቱ ድርጅቱ በየጊዜው አሠራሮች እያሻሻለ እንዲሄድ ምቹ ዕድል ፈጥሮለታል።

አሁኑ ላይ ለስታርትአፖች የተፈጠረው ምቹ ሥነምሕዳር ድርጅቱ የተመሠረተበትን ዓላማ ግብ እንዲመታና ነጥሮ እንዲወጣ እያደረገ መሆኑን ጠቅሶ፤ በቀጣይ ከዚህ በላይ በመሥራት ትልቅ ደረጃ ለመድረስ ጥረት እያደረገ ነው።

‹‹ያስፈልጋል ኢትዮጵያ›› የተሰኘው ፕላትፎርሙ በየትኛው ቦታና ጊዜ ያለምንም ገደብ በቀላሉ በመጠቀምና በማዘዝ አገልግሎት ማግኘት እንድንችል የሚያግዝ ነው የሚለው ወጣት ሮቤል፤ ፕላትፎርሙ ከሌሎች ለየት የሚያደርገው በደንበኞች የሚታወቁ ተፈጥሯዊ የሆኑ ምርቶች የሚቀርብበት እንደሆነ አመልክቷል።

በተጨማሪም በጎ ፈቃደኞችን የሚያበረታታ የልዩ ቅናሽ አሠራር አለው የሚለው ሮቤል፤ ይህም በጎ ፈቃደኞች ለማበረታታትና በኅብረተሰቡ በጎ ሥራ በተሻለ መልኩ እንዲሰፋ ለማድረግ ታሰቦ የተሠራ መሆኑን ይገልጻል።

ፕላትፎርሙ ቢዝነስ ከቢዝነስ ወይም ቢዝነስን ከደንበኛ ጋር በአንድ ያስተሳሰረ መሆኑንም አንስቷል። ከሀገሪቱ የፋይናንስ ሕግ ጋርም አብሮ የሚሄድ እንደሆነ ጠቁሟል፤ ከፋይዳ መታወቂያ ጋር የተሳሰረ ስለመሆኑን አመልክቷል። አብሮነት የሚያበረታታና አሳታፊ የሆነ አሠራር እንዲኖረው እንደሚያስችል አስታውቋል።

አብነት ሲጠቅሱ በፕላትፎርሙ አንድ ደንበኛ እቃ ሲገዛ፤ ለሚፈልገው የበጎ አድራጎት ድርጅት፣ ማዕድ ማጋራት ሆነ እንዲሰጥለት የሚፈልገው ያህል የገንዘብ ማጋራት የሚችልበት አሠራር ያለው ነው። ከዚህም በተጨማሪም የወር ደመወዝተኞች ደመወዝ እስኪደርስ ድረስ የሚፈልጉትን አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል አሠራር የዘረጋ ነው።

ማኅበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት አንጻር የበጎ አድራጎት ድርጅቶች አብረውን እንዲኖሩ ተደርጓል የሚለው ሮቤል፤ የፕላትፎርሙ ተጠቃሚዎች ተቋማትንም ሆነ ሰዎች ለመርዳት ሲፈልጉ በቀጥታ በማስተር ካርድና በቪዛ ካርድ መርዳት የሚችሉበት ሥርዓት እንዳለውም አስታውቋል።

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 12 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You