በተስፋ እና ተስፋ በሚፈጥራቸው ብሩህ ነገዎች ራሱን እንደገራ የኪነጥበብ ባለሙያ!

ኪነ- ጥበብ ለአንድ ሀገር ማኅበራዊ ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያው ዕድገት የሚኖረው አበርክቶ ከፍ ያለ ነው። በተለይም በመለወጥ መነቃቃት ውስጥ ያለ ማኅበረሰብ የለውጥ ጉዞው ስኬታማ እንዲሆን ፣ የአስተሳሰብ ተሐድሶን በመፍጠር እና በማስፋት ሂደት ያለው አስተዋጽኦ መተኪያ የሌለው እንደሆነ የማኅበረሰብ ሳይንስ ምሁራን ይስማማሉ።

አሁን ላይ አንቱ የተባሉ ሀገራት የቀደሙ ታሪኮቻቸው እንደሚያመለክቱት ዛሬ ላይ ለደረሱባቸው ሁለንተናዊ ለውጦች ሆነ ለውጦቹ ይዘዋቸው ለመጣቸው ማኅበራዊ ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያው እመርታዎች የኪነጥበብ ሰዎች እና ሥራዎቻቸው ትልቁን ስፍራ ይይዛሉ። ከእያንዳንዱ የለውጥ ሂደት በስተጀርባም ጥለውት ያለፉት ዐሻራ ደማቅ እንደሆነ የታሪክ መዛግብት ይናገራሉ።

የኪነጥበብ ባለሙያዎች በሥራዎቻቸው ትውልድ ተሻጋሪ ሕልሞችን በማጋራት፣ ገዥ ማኅበረሰባዊ አስተሳሰቦችን በማስፋፋት ፣ የጋራ ትርክቶችን በመፍጠር፣ የጋራ ትርክቶች በማኅበረሰብ ውስጥ የጸና/ተጨባጭ መሠረት እንዲኖራቸው በማስቻል፤ ከእዚያም ባለፈ ዘመናትን የሚመጥኑ የአስተሳሰብ መሠረቶችን በመጣል እና በማስፋት ዓለም አሁን ለደረሰችበት የአስተሳሰብ ልዕልና የነበራቸው እና ያላቸው አዎንታዊ አስተዋጽኦ ከፍ ያለ ነው።

በአውሮፓም ሆነ በአሜሪካ ፣ከእዚያም ውጪ ባሉ የዓለም ሀገራት የተካሄዱ የማኅበረሰብ ተሐድሶዎች/የለውጥ መነሳሳቶች በአብዛኛው መሠረታቸው የኪነጥበብ ባለሙያዎች እና ደራሲዎች ናቸው። እነዚህ ደራሲያን እንደ አንድ የማኅበረሰብ ክፍል የማኅበረሰቡን የዕለት ተዕለት ሕይወት መሠረት ያደረጉ ማኅበረሰባዊ የለውጥ መነቃቃት መፍጠር ያስቻሉ ሥራዎችን አበርክተዋል።

ሥራዎቻቸው የለውጥ መነሳሳት ከመፍጠር ባለፈም የማኅበረሰብ የለውጥ መሻትን ተጨባጭ በማድረግ ሂደት ትልቅ አቅም የሆኑበት አጋጣሚም ብዙ ነው። ለእዚህም በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ካገኙ ማኅበረሰባዊ ለውጦች በስተጀርባ የሚጠቀሱ የኪነጥበብ ሰዎች ጥቂት አይደሉም። በለውጥ ታሪክ ውስጥ ጥለውት ያለፉት የደመቀ ታሪክም ለቀጣይ ትውልድ ክብር ሆኗል።

በእኛም ሀገር በቀደሙት ዘመናት የነበሩ የኪነጥበብ ባለሙያዎች በማኅበረሰቡ ውስጥ የለውጥ መንፈስ ለመፍጠር ሆነ የሕዝብን የለውጥ መሻቶች አደባባይ ይዞ በመውጣት የነበራቸው አበርክቶ ቀለል ብሎ የሚታይ አይደለም። ለእዚህ ደግሞ ከ1966ቱ አብዮት ዋዜማ ጀምሮ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ለውጡን በማዋለድም ሆነ ከተወለደም በኋላ ጠንክሮ እንዲወጣ ብዙ ጥረዋል።

በወቅቱ የነበረው የለውጥ አስተሳሰብ ሕዝቡ ውስጥ ሰፊ መሠረት እንዲኖረው የኪነጥበብ ባለሙያዎች እና ሥራዎቻቸው ያበረከቱት አስተዋጽኦ በሀገሪቱ ታሪክ ውስጥ ጎልቶ የሚታይ እና የሚደመጥ ነው። እያንዳንዱ የኪነጥበብ ባለሙያ በተሰጠበት የጥበብ ዘርፍ፤ ሕዝባዊ/ሀገራዊ ተስፋ ሰንቆ በብዙ መነቃቃት የተጀመረውን ለውጥ ደግፎ በመቆም ረጅም መንገድ ተጉዟል ።

በሀገሪቱ ታሪክ ውስጥ ኪነጥበብ በእዚህ ደረጃ ራሱን ለማኅበረሰብ /የሀገር የለውጥ መነሳሳት በተጨባጭ የሰጠበት እና በእዚህም ራሱን ያሳደገበት አጋጣሚ እንዳልነበርም ብዙዎች ይስማማሉ። በእርግጥ ኪነጥበብ እንደ አንድ የለውጥ መሣሪያነቱ እንደሀገር ለውጡን ተሸክሞ ለመሄድ የተጓዘበት የጽናት መንገድ የሚጠበቅ ቢሆንም፤ ቀደም ሲል ከነበረበት የአወዳሽነት ባህሪ ወጥቶ በእዚያ ደረጃ የሕዝብ አጀንዳ ይዞ መገኘቱ እንደ አንድ አዲስ የታሪክ ጅማሮ ተደርጎ የተወሰደ ነው።

እንደ ሀገር ኪነጥበብ የሕዝብ የለውጥ መሻቶችን አጀንዳ አድርጎ ረጅም መንገድ በጽናት የሄደበት መንገድ፤ በተለይም አሁን ላይ ላሉ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ትልቅ ሀገራዊ ተጨባጭ ተሞክሮ ነው። ግራ አጋቢ በሆነ የለውጥ መንገድ ውስጥ ብሔራዊ ጥቅሞችን እና የሕዝብ መሻቶችን አጀንዳ አድርጎ በስክነት መጓዝ እንደሚቻል ማሳያ ጭምር ነው ።

ይህ እውነታ እንደ ሀገር በ2010 ዓ.ም በተጀመረው ለውጥ ዋዜማ በተመሳሳይ መንገድ ለውጡን እና በለውጡ ውስጥ ያለውን የሕዝብ መሻት ይዞ ለመጓዝ የኪነጥበብ ባለሙያዎች መነቃቃት የተስተዋለበት ቢሆንም፤ በሂደት ተገማች በሆኑ የለውጥ ወቅት ፈተናዎች በጀመረበት መንገድም ሆነ በሚጠበቀው መልኩ ሊቀጥል አልቻለም።

የኪነጥበብ ባለሙያው ሀገርን አሻጋሪ ማኅበራዊ ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያው አጀንዳዎችን ይዘው የለውጡን አደባባዮች ሞልተው ከመገኘት ይልቅ፤ ባልተገባ ድባቴ ውስጥ ሆነው ተስተውለዋል። አንዳንዶችም የሕዝባዊ ለውጡ አካል እና አቅም ከመሆን ይልቅ ባልተገቡ አጀንዳዎች ተጠልፈው ከሙያዊ ተልዕኳቸው በተቃርኖ ቆመው የጥፋት ኃይሎች መሣሪያ ሆነው ተገኝተዋል።

የማኅበረሰባችንን ዘመናት የተሻገረ አብሮነት፣አብሮነቱ የፈጠረውን ፍቅር እና መተማመን በሚሸረሽሩ ተግባራት ላይ ተሰልፈው ሀገር እና ሕዝብን ያልተገባ ዋጋ አስከፍለዋል። ባልተገባ አሉባልታ እና የሀሰት ትርክቶች ውስጥ ገብተው ከሙያው ብቻ ሳይሆን ከሙያዊ ስብዕና ባፈነገጠ መልኩ ረጅም መንገድ ተጉዘዋል።

እንደ ሀገር አሁን ያለንበት የታሪክ ምዕራፍ የኪነጥበብ ባለሙያዎቻችን ከምንም በላይ ለብሔራዊ ጥቅሞቻችን ዘብ የሚቆሙበት ፣ የሕዝቡን የለውጥ መሻት አጀንዳ አድርገው የሚጓዙበት ፣ የሕዝባችንን አብሮነት የሚያጸኑ ፣ እንደ ሀገር በብዙ መስዋዕትነት ተጀምሮ ዛሬ ላይ የደረሰው ለውጥ ወደ ስኬት ምዕራፍ እንዲጓዝ በጽናት እንዲቆሙ የሚጠይቅበት ነው።

ለእዚህ ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ መስጠት እንደ ዜጋ፣ ከእዚያም በላይ በተስፋ እና ተስፋ በሚፈጥራቸው ብሩህ ነገዎች ራሱን እንደገራ የኪነጥበብ ባለሙያ ከሁሉም የሚጠበቅ ነው። የጥበብ መክሊታቸውም ሊያመጣላቸው የሚችለው እውነተኛ ሽልማት ከእዚህ እውነታ የሚመነጭ እና የሚሰላ ነው!

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 12 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You