ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት ቁልፍ ድርሻ አላቸው ተብሎ ከሚታመኑ ጉዳዮች መካከል የማኅበረሰብ ጤና በቀዳሚነት ይነሳል። ዜጎች ጤናቸው ተጠብቆና የኑሮ ደረጃቸው ተሻሽሎ ምርታማ ሲሆኑ በተመሳሳይ የሀገር ኢኮኖሚ እና እድገት እውን ይሆናል። በተቃራኒው ጤናን የሚያውኩ ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ዜጎችን በሚያጠቁበት ወቅት ከግለሰብ የተሻገረ ሀገራዊ የአደጋ ሥጋት ይደቀናል። ለዚህ ሁነኛ ምሳሌ የኮቪድ 19 (የኮሮና ቫይረስ) ነው። ወረርሽኙ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሚሊዮኖችን ሲገድልና በቢሊዮን የሚቆጠሩ የሰው ልጆችን ሲያጠቃ ከሰብዓዊ ጥፋቱ ባሻገር የየሀገራቱ ኢኮኖሚ ተሽመድምዶ ምድራችን ዓመታትን ወደኋላ ተመልሳለች። ኢትዮጵያም የዚሁ ወረርሽኝ ሰለባ እንደነበረች የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።
የማኅበረሰብን ጤና ማስጠበቅ ከሚቻልባቸው መንገዶች አንዱ የዜጎችን አመጋገብ (ሥነ ምግብ- Nutrition) ማሻሻል እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ። ማኅበረሰብ በቫይታሚን የበለፀገ፣ በቂ ተመጣጣኝ የምግብ ሥርዓትን የሚከተል ከሆነ በሽታን የመቋቋም (ተጋላጭነትን የመቀነስ) እድሉ ሰፊ መሆኑን ይናገራሉ። የተመጣጠነ የምግብ እጥረትን ተከትሎ የሚመጣን የሕፃናት መቀንጨርና ክብደት ማነስ በማስቀረት፤ መጪው ትውልድ የተሟላ ጤና እንዲኖረውና ሀገር ተረካቢ እንዲሆን ሥርዓተ ምግብ ከምንም በላይ ጉልህ ድርሻ እንዳለው እነዚሁ የዘርፉ ተመራማሪዎች ያስረዳሉ።
የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያ መለክተው ከሥነ ምግብ እጥረት ጋር ተያይዞ የሚመጣው መቀንጨርና የጤና መጓደል ምክንያቶች ዘርፈ ብዙ ናቸው። በዋናነት የሚነሱት ከድህነት እና ድርቅ መስፋፋት፣ ግጭትና መፈናቀል ተጠቃሽ ናቸው። በእነዚህ ገፊ ምክንያቶች በዓለማችን ላይ በርካታ ሚሊዮን ሕፃናት ከሚፈለገው ክብደት በታች ሆነው ይወለዳሉ፣ የመቀንጨር፣ የክብደት መቀነስ እና የቁመት ማጠር ያጋጥማቸዋል። ድርጅቱ ይህንን የጤና መጓደል ለመከላከል ዓለም አቀፍ ጥረቶችን የማድረግ፣ የአጭርና የረጅም ጊዜ ግቦችን በማውጣት ተግባራዊ ማድረግ ላይ ይገኛል።
እንደ መረጃዎቹ ከሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የመቀንጨር መጠንን የመቀነስ፣ የእናቶችን የእርግዝና ጊዜ የቫይታሚንና የፎሎክ አሲድ እጥረት መቀነስ፣ ሕፃናትን የእናት ጡት እንዲያገኙ የሚያበረታቱ ሆስፒታሎች፣ ክሊኒኮችና ጤና ጣቢያዎች ማስፋፋትን የመሳሰሉ ፕሮጀክቶችን ይዞ እየሠራ መሆኑን ያመለከታሉ። ለቀነጨሩ ሕፃናት የሚሰጥ አልሚ ምግብም ከሥነ ምግብ እጥረት ጋር ተያይዞ የሚፈጠረውን የጤና ጉድለት ለማከም እንደሚቻል ይናገራል። የዓለም አቀፍ የጤና ድርጅቱ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2020 ብቻ በምድራችን ላይ 149 ሚሊዮን ሕፃናት ለመቀንጨር ተዳርገዋል።
ኢትዮጵያ ሥርዓተ ምግብን ለማሻሻል እና በኢትዮጵያ የሚታየውን የመቀንጨር፣ ከክብደት በታች መወለድ እና የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ለመቀነስ በ2007 ዓ.ም የሰቆጣ ቃል ኪዳንን ተግባራዊ አድርጋለች። ስምምነቱ በበርካታ ወረዳዎችና ገጠራማ አካባቢዎች በስፋት የሚከሰተውን ቅንጨራ ለመቀነስ ያለመ ነበር። በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት መረጃ ላይ የተመሠረተ የፖሊሲ እርምጃ፣ ድጋፍ እና ችግሩ በስፋት የሚታይባቸውን ቦታዎች ለመለየት የሚያስችሉ ሳይንሳዊ የምርምር ሥራዎችን ያከናውናል። የሰቆጣ ቃል ኪዳን ፕሮግራም ውጤታማነቱ የታየ፣ በፍጥነት ወደ ትግበራ በመግባት ለውጥ ያሳየ ፕሮግራም መሆኑን የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ያወጣው መረጃ ያመለክታል። ሀገር አቀፍ ደረጃ የምግብ ሥርዓት እና ኒውትሪሽን ሥራዎችን ቅንጅታዊ አሠራር ለማጠናከር የሚያስችል በርካታ ፕሮግራሞች ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑንም መረጃዎቹ ያመለክታሉ።
ዶክተር እንዳለ አማረ የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የምግብ ሳይንስ ተመራማሪና ዲቪዥን ኃላፊ ናቸው። ከቀናት በፊት የዝግጅት ክፍላችን ባልደረባ የተሳተፈበት የሥርዓተ ምግብ ሥልጠና ላይ በኢንስቲትዩቱ እየተሠሩ ያሉ የምርምር ሥራዎችና ውጤቶቻቸውን የተመለከቱ ዳሰሳዎችን አቅርበው ነበር። እርሳቸው እንደሚሉት ኢትዮጵያ በተመጣጠነ ምግብ እጥረት የሚከሰተውን ረሃብን ለመከላከል ዘርፈ ብዙ ጥረት ታደርጋለች።
እንደ ተመራማሪው ገለፃ ሀገሪቱ ይህንን የሚደግፍ ፖሊሲ አውጥታ ተግባር ላይ አውላለች፤ በዚህም ደህንነታቸው የተጠበቀ፣ አልሚ ምግቦች፣ በሁሉም አካባቢ ተደራሽና ዘላቂ መሆናቸውን መረጋገጥ እንዳለበት፤ ከእርሻ እስከ ምግብ ጠረጴዛ ድረስ የምግብ ደህንነትን ማረጋገጥ፣ የግብርና ምርቶችን የምግብ ደህንነት ማረጋገጥ፤ ምግብንና የተመጣጠነ ምግብ ትስስርን ማጠናከር ላይ እየሠራች መሆኑን ይናገራሉ።
ከተመሠረተ 100 ዓመታት የሆነውን የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት (EPHI) የኢትዮጵያውያንን ጤና ለማሻሻል እየሠራ ስላለው ሳይንሳዊ ምርምር ሥራ የሚናገሩት ዶክተር እንዳለ አማረ ሀገሪቱ ረሃብን፣ የተመጣጠነ ምግብ እጥረትን እና የምግብ ደህንነትን ለመቅረፍ እያደረገች ስላለው ጥረት በዝርዝር ይናገራሉ።
‹‹ማንም ሰው የምግብ እጦት ወይም የተመጣጠነ ምግብ ማጣት የለበትም ፤ የእኛ ሥራ ሕይወትን በተለይም ሕፃናትን እና እናቶችን ማዳን ነው›› በማለት ከሥነ ምግብና ሥርዓተ ምግብ ጋር በተገናኘ እርሳቸው የሚሠሩበት ዲቪዥን እያከናወነ ስላለው ሳይንሳዊ የምርምር ሥራ ያብራራሉ።
ተመራማሪው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓለም አቀፍ ጥናትን መሠረት አድርገው እንደሚያስረዱት በዓለማችን ላይ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር 500 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በ2030 ስር የሰደደ ረሀብ ያጋጥማቸዋል። ኢትዮጵያም ይህንን ችግር ለመቅረፍ አበክረው ከሚሠሩ ሀገራት መካከል ቀዳሚዋ እንደምትሆን ይናገራሉ። ይህንን ዓለም አቀፍ ስጋት ተከተሎ እድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት በመቀንጨር፣ በምግብ እጥረትና ከሚፈለገው ከብደት በታች የመሆን ሥጋት አለባቸው። የኢንስቲትዩቱ ሀገር አቀፍ መረጃ እንደሚያሳየው በ2019 እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር 37 በመቶ ሲሆን በ2022 ያለው መረጃ የሚያሳየው ደግሞ ወደ 39 በመቶ ከፍ እንዳለ ነው። ከክብደት በታች ሆነው የሚወለዱት ደግሞ በ2019 ሰባት በመቶ የነበረ ሲሆን በ2022 ወደ 11 በመቶ ከፍ ብሏል።
ዶክተር እንዳለ ኢንስቲቱዩቱ በምርምርና የሥነ ምግብ ሥርዓት ላይ እያከናወናቸው ባሉ ሥራዎች ለጋዜጠኞች ባስተዋወቁበት አጭር ዳሰሳ ላይ እንዳመለከቱት፤ በኢትዮጵያ ከአምስት ዓመት በታች ከሆኑ ሕፃናት ከአራቱ አንዱ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ያጋጥማቸዋል። በዚህ ምክንያት በጤናቸው፣ በወደፊት ሕይወታቸው እና በትምህርታቸው ላይ አሉታዊ ጉዳት ያስከትላል። ይህንን ችግር በመረጃና ሳይንሳዊ የጤና መፍትሔዎች ላይ ትኩረት በማድረግ ኢንስቲትዩቱ የምርምር ውጤቶችን እያወጣ ይገኛል።
በኢንስቲትዩቱ እየተሠሩ ካሉና ተግባራዊ እንዲደረጉ ምክረ ሃሳብ ከተሰጠባቸው ጉዳዮች መካከል በጨው ውስጥ የሚቀላቀል በአዮዲን፣ በፎሎክ አሲድና የቤተሰብን የቫይታሚን አጠቃቀም የሚያሻሽሉ ምርቶች ማቅረብ ይገኝበታል። በዚህ መልኩ ጨውን አበልፅጎ ለምግብነት ማዋል የማኅበረሰብን ጤና መጠበቅ እንደሚረዳ የተደረገው የምርምር ውጤት ያሳያል። እናቶች በፎሊክ አሲድና በአዮዲን በበለፀገ ጨው ምግባቸውን አዘጋጅተው መመገባቸው ጤንነታቸው ከመጠበቁም በላይ የሚወልዱት ልጅ ከጨቅላነት ጀምሮ ጤናማ ሕይወትን እንዲያገኝ ያደርጋል።
የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቱ ከሚያከ ናውናቸው ሳይንሳዊ ምርምሮች መካከል የተመጣጠነ የምግብ እጥረት (malnourished) ያለባቸው ሕፃናትን ለማከም አዳዲስ መንገዶችን ማመላከት ነው። ከዚህ አንፃር ኢንስቲትዩቱ ከተወሳሰቡና ጊዜ ከሚወስዱ ሕክምናዎች ይልቅ የታሸጉ አልሚ ምግቦችን በየቀኑ መስጠት ውጤታማ እንደሚያደርግ እና ተስፋ ሰጪ ምልክቶች ማሳየቱን በሚያደርጋቸው ሳይንሳዊ ምርምሮች እያመላከተ ነው።
ኢትዮጵያ ከደቡብ እስከ ምስራቅ፤ ከምዕራብ እስከ ሰሜን ልዩ ልዩ ባሕላዊ ምግቦችና ሰብሎች የሚመረቱባት ሀገር ነች። እነዚህ ባሕላዊ ምግቦችና በሀገር ውስጥ በቀላሉ የሚመረቱ ሰብሎች በአግባቡ ጥቅም ላይ ቢውሉ አልሚ ነጥረ ነገሮችን የያዙና የተመጣጠነ ምግብ ፍላጎትን ሊያሟሉ የሚችሉ እንደሆኑ ዶክተር እንዳለ ይናገራሉ። በምሳሌነትም አተር፣ አንቾቴ፣ ባቄላ እና የመሳሰሉት ያነሳሉ። ሰብሎቹ በቫይታሚን የበለፀጉ ከመሆናቸውም በላይ የአየርን ንብረት ተፅእኖን የሚቋቋሙ መሆናቸውን ያስረዳሉ። ኢንስቲትዩቱ ሰብሎቹን ማኅበረሰቡ እንዲጠቀማቸው የማበረታታትና ጥቅማቸውን በሳይንሳዊ ምርምር ዘዴ የማረጋገጥ ሥራዎች እየሠራ ይገኛል።
የማኅበረሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከሚያ ከናውናቸው ተግባራት መካከል የዜጎችን ጤንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ ባዕድ ነገር የተቀላቀለባቸውን ምግቦች ማኅበረሰቡ እንዳይጠቀም ማሳሰብና ግንዛቤ መፍጠር ላይ ነው። ይህም የማኅበረሰቡን ሥርዓተ ምግብ ከማዛባቱ ባሻገር የተመጣጠነ ምግብ አወሳሰድ ሂደቱን የሚያዛባ መሆኑን ዶክተር እንዳለ ይናገራሉ። በተለይ በማር፣ በቅቤና ወተትን በመሳሰሉ ምግቦች ላይ የሚቀላቀሉ ባዕድ ነገሮች ላይ ጥንቃቄ እንዲወሰድ እንደሚሠራ ያስረዳሉ። ባዕድ ነገር የሚቀላቅሉ ነጋዴዎችን በማሰልጠንና ከድርጊቱ እንዲቆጠቡ ግንዛቤ የመፍጠር ኃላፊነት እየተወጣ ስለመሆኑም ይጠቅሳሉ።
በሌላ በኩል ኢንስቲትዩቱ የተማሪዎች ምገባ ሥርዓት ላይ የበኩሉን ኃላፊነት እየተወጣ መሆኑን በማንሳት በተለይ ምገባው የተመጣጠነና ሥነ ምግብ መስፈርትን ያሟላ እንዲሆን ከተቋማት ጋር መሥራቱን ይናገራሉ። በዚህም ተማሪዎች በምግቦቻቸው ላይ በቀን አንድ እንቁላል እንዲያገኙ ማድረግ በትምህርታቸው ላይ ንቁና ሙሉ አቅም መስጠት እንደሚችሉ በምርምሩ ማረጋገጡን ያነሳሉ።
ደካማ አመጋገብ ረሀብን ብቻ ሳይሆን በሽታ የመቋቋም አቅምን እንደሚያዳክም ዶክተር እንዳለ ይናገራሉ። የታዳጊዎችን የአንጎል እድገት ከመቀነሱም በላይ አዋቂዎች በሥራ ገበታቸው ላይ ውጤታማ እንዳይሆኑ ያደርጋል ይላሉ። ጤናማ አመጋገብ የጠንካራ ማኅበረሰብ መሠረት በመሆኑ በዚህ ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት ተገቢ መሆኑን ያነሳሉ። መንግሥትም ይህንን ግብ ለማሳካት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምግብና የተመጣጠነ ምግብ ስትራቴጂ (ከ2020-30) ባስቀመጠው ግብ መሠረት ሁሉም ዜጋ ደህንነቱ የተጠበቀ ልዩ ልዩና የተመጣጠኑ ምግቦችን እንዲያገኝ ማድረግ እንደሆነ ይናገራሉ። በዚህም ስለ ጤናማ አመጋገብ ማስተማር፣ የምግብ ብክለትን መከላከልና በአደጋ ጊዜ የሚፈጠር የምግብ እጥረትን ለመከላከል እንደሚሠራ ነው የተናገሩት።
መንግሥት እና በጤናው ዘርፍ ላይ የሚሠሩ ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ተቋማት ያስቀመጡት ግቦች ስኬታማ እንዲሆኑ፤ በምግብ እጥረት፣ በሥነ ምግብ ችግር የሚፈጠሩ የሕፃናት ሞት፣ መቀንጨር እና ከሚጠበቀው በታች ክብደት ይዞ መወለድን ለመከላከል የመገናኛ ብዙሃን በእውነታ ላይ የተመሠረተ መረጃን ለማኅበረሰቡ በማድረስ ሊተባበሩ ይገባል ይላሉ ዶክተር እንዳለ።
የመገናኛ ብዙሃን የኢትዮጵያ የአመጋገብ መመሪያዎችን እንዲዘምኑ፤ ገበሬዎች የአየር ንብረትን የሚቋቋሙ ሰብሎችን እንዲያመርቱ፤ የሥነ ምግብ ምክሮችን በሥነ ምግባር ለታዳሚያን ለማሰራጨትና ለማስተማር ከትምህርት ቤቶች፣ ክሊኒኮችና ከሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር መተባበር እንደሚኖርባቸው በምክረ ሃሳባቸው ያነሳሉ። በተለይ በመረጃ ላይ የተመሠረተ የጤና ምክሮችን ለማኅበረሰብ በማድረስ ዜጎች ለራሳቸው፣ ለቤተሰባቸው እና ለሀገር ልማት ሁለንተናዊ ጥቅም እንዲኖራቸው መሥራት ይገባል ሲሉ ይመክራሉ።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን መጋቢት 20 ቀን 2017 ዓ.ም