«ኢትዮጵያ ታሪካዊ የቀይ ባሕር ተዋሳኝነቷን መልሳ ማግኘት አለባት» – አደም ካሚል (ረ/ ፕሮፌሰር)

የታሪክ ተመራማሪው ረዳት ፕሮፌሰር አደም ካሚል በውጭ ሀገር ለአጭር ጊዜ የነበራቸውን ቆይታ አገባድደው ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ ሁለት ሳምንታቸው ነው:: የዓድዋ በዓልን ለማክበር የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባቀረበላቸው ግብዣ ባደረጉት ጉዞ እግረ መንገዳቸውን ከሲኤንኤን ዓረብኛ ጋር በስድስት ክፍል የተላለፈ ቃለ መጠይቅ አድርገዋል:: በዛሬው ወቅታዊ ዝግጅታችን በውጭ ሀገር የነበራቸውን ቆይታ፣ ቀይ ባሕርን እና ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመንፈቅ ጊዜ ውስጥ እንደሚመረቅ የተናገሩለትን የዓባይ ግድብን የሚመለከቱ ጉዳዮችን እንዳስሳለን፤ መልካም ቆይታ!

አዲስ ዘመን፡- ከሲኤንኤን አረብኛ ጋር ባደረጉት ዘለግ ያለ ቆይታ ምን ምን ጉዳዮች ተነሱ ?

አደም (ረ/ፕ/ር)፡- ሲኤንኤን የአረብኛው ክፍል የሁለት ሰዓት ቃለመጠይቅ አድርጎልኛል:: ኢትዮጵያ ማን ናት ምንድን ናት፣ በአፍሪካ ቀንድስ ያላት ቦታ ምን ይመስላል፣ መረጋጋቷ እና አለመረጋጋቷ ምን ሊያስከትል ይችላል እንዲሁም የኢትዮ ዓረብ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት በቆይታችን የተዳሰሱ ጉዳዮች ናቸው:: ዓረብ ሀገራት ነዳጅ አምራች ይሁኑ እንጂ የምግብ አቅርቦትና የውሃ ዋስትና ችግር አለባቸው:: እነዚህን ሁለት ቁልፍ አቅርቦቶች ማሟላት ትልቅ የቤት ሥራቸው ነው::

ሳውዲዎች በአውሮፓውያኑ 2023 ብቻ 105 ሚሊዮን የሃይማኖት ጎብኚዎችን አስተናግደው 250 ቢሊዮን ሪያል ነው ያገኙት:: ለዚህ ሁሉ ጎብኚ የሚያስፈልገውን የምግብ ግብዓት ለማሟላት የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ያስፈልጓቸዋል:: በቂ ምርት ስለሌላቸው ከነዳጅ ብቻ ሳይሆን ከሃይማኖት ቱሪስቶች የሚያገኙትን ገቢ ተጠቅመው ከህንድ እና ላቲን አሜሪካ ከሚገኙ ሩቅ ምሥራቅ ነው ምግብ የሚያስመጡት:: በአላት ተፈጥሮ ፍላጎታቸውን ልታሟላ የምትችለውን በአንድ ሰዓት ከ45 የበረራ ርቀት ላይ ያለችውን ኢትዮጵያ ምን ያህል እንደተጠቀሙባት፤ ሳውዲዎች በእርሻ ሥራ መሠማራት የሚችሉበት የሕግ ማሕቀፍ ስለመኖሩ እንዲሁም ኢትዮጵያ ራሷ አምርታ ማቅረብ የምትችልበትን ዕድል የተመለከቱ ጥያቄዎች ነበር በብዛት የቀረቡልኝ:: ባነሱልኝ ጥያቄ ዙሪያ በቂ ግንዛቤ መያዝ የሚችሉበትን መልስ ሰጥቻቸዋለሁ ብዬ አምናለሁ::

በተጨማሪም ኢትዮጵያ በዓድዋ ጦርነት የራሷን ነፃነት ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም የሚኖሩ ጥቁሮችን መብት ማስከበሯን፤ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን በመመሥረት የነበራትን ተሳትፎ፤ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲመሠረት ቁልፍ ሚና መጫወቷን እንዲሁም በአሁኑ ወቅት ደግሞ ከኒዎዮርክ ቀጥሎ ሁለተኛዋ የዲፕሎማቶች መንደር መሆኗን ተናግሬያለሁ:: ኢትዮጵያ የውሃ ሀገር የዓባይ ምንጭ መሆኗ አልተነሳም:: ምክንያቱም አስተሳሰባቸው የተሞላው ኢትዮጵያ ኋላቀር እና የረሃብ ሀገር ስለመሆኗ ነው:: ስለዚህ ከሲኤንኤን አረብኛ ጋር በነበረኝ ቆይታ ቋንቋውን ለሚናገሩ ሰዎች ጥሩ ግንዛቤ የሚፈጥር ነው ማለት ይቻላል::

አዲስ ዘመን፡- የዓረቡ ዓለም ስለኢትዮጵያ ያለው ግንዛቤ እንዴት ያለ ነው ?

አደም (ረ/ፕ/ር)፡- ኢትዮጵያ በዓረቡ ዓለም የምትታወቀው በረሃብ፣ በኋላቀርነት እና በስደት ነው:: ከሞላ ጎደል በዚህ ተግባር ላይ የሚሳተፉት ግብጻውያን ናቸው:: ግብጻውያን በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚዲያ ደረጃ ያላቸው ቦታ የሚናቅ አይደለም:: ይህን ምስል ለመቀየር የሚያስችል ሥራ አልተሠራም:: ግብጾች ቀደም ብለው ባደረጉት እንቅስቃሴ ኢትዮጵያ ለዓረቡ ዓለም አደጋ ናት የሚል ግንዛቤ እንዲያዝ ነው የተደረገው:: ስደተኞችን የተቀበለችበት እስላማዊ ታሪኳ እንዲሁም የቢላል እና የነጃሺ ሀገር መሆኗን የማስገንዘብ ሥራ አልተሠራም:: የፍትህ እና የእውነት ምድር የሚሉት ነብያዊ ቃላትም እንዲንጸባረቁ አልተደረገም:: ይህን አለማድረጋችን የራሳችን ድክመት ነው::

እዚህ ላይ አንድ ገጠመኜን ባጋራህ ደስ ይለኛል:: አንድ ጊዜ ወደ ጅዳ የሚል ቲኬት ይዤ ወደ ካይሮ አምርቼ ነበር:: አንድ መቶ አለቃ ፓስፖርቴን ሲመለከት ቆይቶ ጥያቄ አቀረበልኝ:: ኢትዮጵያዊ ሆነህ እንዴት ቲኬት ቆርጠህ ባለአምስት ኮከብ ሆቴል ለማረፍ ትመጣለህ አለኝ:: የተፈጥሮ ድህነት የለብኝም የአስተሳሰብ ድህነት ነው ያለብኝ:: የአንተ ሀገር መሪዎች ጭምር ጭንቅላታቸው የተገነባው በእኔ ውሃ ነው:: እኔ ግን የአስተዳደር ችግር ነው ያለብኝ ብዬ በሚገባው በአረብኛ ቋንቋ ስነግረው ሁለት ጊዜ ሰላምታ ሰጥቶ አሳለፈኝ::

በእርግጥ ኢትዮጵያ ግብጽን መጉዳት ከፈለገች ዓባይን የሚመግቡ ስድስት መጋቢ ወንዞችን አቅጣጫቸውን ቀይራ ወደሌላ አካባቢ እንዲፈሱ ብታደርግ ዓባይ ደረቅ ወንዝ ሆኖ ይቀራል:: ስለዚህ በድርድር መግባባት ነው እንጂ በኃይልም ሆነ በተንኮል ኢትዮጵያን ማስኮረፉ አይበጅም ብለው የሚጽፉ የግብጽ ምሁራን አሉ:: ይህ ከግብጾችም ሀቀኞች መኖራቸውን ያሳያል:: ሰሞኑን ሰልማ የምትባል የአፍሪካ ቀንድን በተመለተ የምትመራመር አንዲት ግብጻዊት ኢትዮጵያና ኤርትራ ጦርነት ሊገጥሙ ይችላሉ ተብላ ስትጠየቅ ምላሽ የሰጠችው ኢትዮጵያን ማስኮረፍ አይበጅም ብላ ነው::

በአጠቃላይ ግን የውጭ ዲፕሎማሲያችን ድክመት ነበረው ማለት እንችላለን:: በአጼዎቹ ዘመን የውጭ ግንኙነታችን ከምዕራቡ ዓለምና ከአሜሪካ ጋር ሆነ:: ሶሻሊስት በነበርንበት ዘመን ደግሞ ምዕራባውያን ተገንጣዮችን ይደግፋሉ ብለን ፊታችንን ወደ ሶቪየት ሕብረት እና ሰሜን ኮሪያ አዞርን:: የኢህአዴግ ዘመን ለፓርቲ ያለ ታማኝነት ብቻ ሚዛን እየሆነ እውቀቱ የሌላቸው ሰዎች በዲፕሎማትነት የሚመደቡበት ሆነ:: ስለዚህ የኢትዮ ዓረብ ግንኙነትን በአግባቡ አልተጠቀምንበትም::

አሁን ግን በዓረቡ ዓለም ለውጥ መጥቷል:: 21ኛው ክፍለ ዘመን ሚዲያውም ቴክኖሎጂውም ብዙ ዕድል የሚሰጥበት ጊዜ ስለሆነ ኢትዮጵያ ማን ናት የሚለውን ግንዛቤ የመያዝ ሁኔታ ጅማሬ አለ:: ይህን ግንዛቤ በሕዝብ፣ በሃይማኖት ድርጅት፣ በመንግሥት፣ በሚዲያ እና በዲፕሎማሲ ደረጃ ማዳበር አለብን:: ብዙ የቤት ሥራ ይጠብቀናል ማለት ነው የምንችለው::

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ራሷን ለዓረቡ ዓለም የምታስተዋውቅበት በዓረብኛ ቋንቋ የሚተላለፍ ራሱን የቻለ የቴሌቪዥን ሥርጭት አያስፈልጋትም ?

አደም (ረ/ፕ/ር)፡- ሚዲያዎችን እባካችሁ ለዓረብኛ ቋንቋ ትልቅ ቦታ ይሰጠው ብለን ብንጠይቅም እስካሁን ድረስ የተሰጠው መልስ በጣም አሳፋሪ ነው ማለት እችላለሁ:: ዓረብኛ ቋንቋን ማወቅ ከእስልምና እምነት ጋር ምንም ግንኙነት የለውም:: የእስልምና ሃይማኖት ሌላ አጀንዳ ነው:: ዓረብኛ ቋንቋ ግን የኢኮኖሚ፣ የቱሪዝም እና የኢንቨስትመንት መሳሪያ ነው::

በዓረቡ ዓለም፣ በአውሮፓም ሆነ በአሜሪካ የሚገኙ ሚዲያዎችን የዓረብኛ ዘርፍ የሚመሩት ግብጻውያን ናቸው:: በየትኛውም የዓለም ክፍል በሚገኝ በዓረብኛ የሚተላለፍ ሥርጭት ላይ ግብጻውያን አሉ:: አንቀሳቃሾቹ እነርሱ ናቸው:: እንዲህ ዓይነቱን መዋቅራዊ ስም የማጥፋት ዘመቻ በተንጠባጠበ መንገድ ግለሰቦች በሚያደርጉት ጥረት መግታት አይቻልም:: የግድ 24 ሰዓት ለውጭው ዓለም በዓረብኛ፣ እንግሊዝኛ እና ፈረንሳይኛ የሚተላለፍ የተደራጀ ሚዲያ ያስፈልገናል::

በጥናት ላይ የተመሠረቱ ዘገባዎችን በማቅረብ የዓረቡ ዓለም ስለኢትዮጵያ ያለውን የተዛባ አረዳድ መቀየር ይቻላል:: ዓለማችን በጥናትና ምርምር ሥርዓት ነው እየተደገፈ ያለው:: በዓለማችን 8450 የጥናትና የምርምር ማዕከሎች አሉ:: ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ከናይጄሪያ ቀጥላ ትልቋ ሀገር ተብላ ነው የምትሰየመው:: 130 ሚሊዮን ከሚደርሰው አጠቃላይ ሕዝቧ 80 በመቶ ያህሉ ወጣት የሆነባት ይህች ታላቅ ሀገር ዩኒቨርሲቲዎቿ በሙሉ የጥናትና ምርምር ማዕከል መሆን አለባቸው:: ወጣቱ ስለኢትዮጵያ ተፈጥሯዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ምርምሮችን እንዲያደርግ መበረታታት አለበት::

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር የተገለለችበትን መንገድ ከታሪክ፣ ውሳኔውን ካሳለፈው የወቅቱ ገዢ ፓርቲ እና ከዓለም አቀፍ ሕግጋት አንጻር እንዴት ይታያል ?

አደም (ረ/ፕ/ር)፡– ቀይ ባሕር ለእኛ ምን ነበረ? እውነት ቀይ ባሕር የቅኝ ገዢዎች ተጽዕኖ አድሮበት ነው የተገነጠለው? ኤርትራ እንድትገነጠል ያደረገው የእነማን ሚና ነው? የሚሉትን ጉዳዮች የሚዳስስ ሰፋ ያለ ጥናት ሠርቻለሁ:: ኢትዮጵያ ቀይ ባሕርን ልታጣ የቻለችበት ውጤት ራሱን የቻለ የኋላ ታሪክ አለው::

ቀይ ባሕር ከጥንት ጀምሮ የአበሻ ባሕር በመባል ነው የሚታወቀው:: ሥልጣኔያችንም፣ ታሪካችንም፣ እምነታችንም፣ ብልፅግናችንም ሆነ ንግዳችን ከቀይ ባሕር ጋር የተያያዘ ነው:: ቅኝ ገዢዎች መጥተው አይደለም ይህቺን ሀገር የከፋፈሏት:: የኤርትራ ነፃ አውጪዎች አጀንዳ ላይ ራሱን የቻለ ሚና የተጫወተው ማን ነው? እውነት የኤርትራ ሕዝብ ፍላጎት ነው? የኢትዮጵያ ሕዝብ ተጠይቆ በጉዳዩ ላይ ተወያይቷል ? አልተጠየቀም እንዲህ ዓይነት ጥረት አልተደረገም::

ኤርትራ እንድትገነጠልና ቀይ ባሕርን እንድናጣ የተደረገው ለምንድን ነው ብለን በተለይ የግብጾችን ሚና ከፈተሽን የተሠራብንን ሸፍጥ መረዳት እንችላለን:: በተለይ የአሰብ ጉዳይ አነጋጋሪ ነው:: ኢትዮጵያን የሚመራው የወቅቱ መንግሥት ቀይ ባሕርን እንድታጣ የተደረገውን ደባና ሴራ አሜን ብሎ መቀበሉ አነጋጋሪና አከራካሪ ነው:: በወቅቱ የነበሩ አማጽያን የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው:: ሁለቱ የሚታገሉትን የደርግ ሥርዓት ለመጣል የትጥቅ ትግል ሲያደርጉ ከጀርባቸው የነበሩ ኃይሎች እነማን ናቸው? የሚለውን መመርመር ይገባል::

ቀይ ባሕርን እንድናጣ ያደረገው በወቅቱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ ይሠራ የነበረ አንድ ግብጻዊ ዲፕሎማት ነው:: ለአራት ዓመታት በድርጅቱ ውስጥ ያገለገለው ይህ ግብጻዊ በጊዜው በሰፊው ሲንቀሳቀስ እንደነበረ አስታውሳለሁ:: ሲንቀሳቀስ የነበረበት አላማም የቀይ ባሕርን ምዕራብ ክፍል የያዘችውን ኢትዮጵያ ከባሕር ዳርቻው ማራቅ የሚል ነበር:: ምንም እንኳን ዓረብኛ ባይናገሩም ጅቡቲና ሶማሌን የዓረብ ሊግ አባል አድርገናል:: የቀይ ባሕርን ዓረባዊነት ለማረጋገጥ ኤርትራ የምትባል ሀገር መወለድ አለባት:: ይህች ሀገር 23ኛ የዓረብ ሊግ አባል ሀገር ትሆናለች፤ ያን ጊዜ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር የቀይ ባሕር ምንም ድርሻ ስለማይኖራት ያልቅላታል የሚል ህልም ነበረው:: ይህን ህልሙን ለማሳካት ኢትዮጵያ ውስጥ የነበሩ ታጣቂዎችን በሁሉም መንገድ በመደገፍ ጉዞውን ጀመረ:: ኮድ ከሚባል የወቅቱ የአሜሪካን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የአፍሪካ ተጠሪ ጋር በመሆን የኤርትራን መገንጠል ተግባራዊ አደረጉ:: በዚህም ኢትዮጵያ ቀይ ባሕርን አጣች::

የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ገዢ ፓርቲዎች ውሳኔዎችን አሳለፉ እንጂ በሁለቱም ወገን ያሉ ሕዝቦች አልተወያዩበትም:: ሰላሳ ዓመት ታግለናል ነፃነታችንን ማግኘት አለብን አሉ አገኙ:: በዚህ ሂደት ቅኝ ገዢዎች ዐሻራ የላቸውም:: በዚህ መንገድ ነው አሰብና ምጽዋን እንድናጣ የተደረገው:: የኢሳያስ መንግስት ነጻነቱን ከወሰደ 31 አመታት ተቆጥረዋል:: በዚህ ጊዜ ውስጥ የኤርትራን ሕዝብ ድህነት ለመቅረፍ በአሰብ ወደብም ሆነ በመላ ሀገሪቱ የሰራው ምንም ነገር የለም::

አዲስ ዘመን፡- አሰብ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ግዛት መሆኑ እየታወቀ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ሕጎች ጭምር እውነታውን እየደገፉ ለእናት ምድሩ ባይተዋር ሆኖ የሚቀጥለው እስከ መቼ ነው ?

አደም (ረ/ፕ/ር)፡- አሰብ የኢትዮጵያ ንብረት መሆኑ ከጥንትም ጀምሮ የተረጋገጠ ነው:: ዓለም አቀፍ ሕግ የመሰከረበት ሁኔታ ነው:: ወጪያችንን ለመቆጠብ ያለን አማራጭ ይህን ታሪካዊ ንብረታችንን ማግኘት ነው:: ኢትዮጵያ የቀይ ባሕር ተዋሳኝነቷን መልሳ ማግኘት አለባት:: ስለዚህ በሰላማዊ መንገድ እነሱም እኛም ተጠቃሚ መሆን የምንችልበትን መንገድ መፍጠር አለብን:: ጦርነት አይበጅም::

የአሰብ ወደብን መጠቀም የምትችለው ሀገር ኢትዮጵያ ብቻ ናት:: ኬንያ ፣ ታንዛኒያ፣ ሱዳን ወይም ሌሎች ጎረቤት ሀገራት ሊጠቀሙበት አይችሉም:: አሰብን እንኳን ለኢትዮጵያ በማከራየት መጠቀም ይችል ነበር፤ ይሄንን እንኳን ማድረግ አልቻለም:: እኛ የወደብ አማራጮች አሉን::

ከፈለግን ደግሞ በዚህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ልክ የኮሪደር ልማት እንደምንሠራው ከቀይ ባሕር እስከ አሰብ ድረስ ያለውን ቦታ ቆፍረን ባሕሩን ስበን በማምጣት በራሳችን ክልል ውስጥ የራሳችን ወደብ መመሥረት እንችላለን:: በዚህ ረገድ የተጠና ጥናት አለ:: ነገር ግን የጋራ ተጠቃሚነት እንዲኖር በሰላማዊ መንገድ ተደራድረን ወደቡን ለመጠቀም እየሠራን ነው:: ኢትዮጵያ አሁን የ130 ሚሊዮን ዜጎች ሀገር በመሆኗ ወደቡን የመጠቀም አስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ ገብታለች:: ወጪያችንን ለመቆጠብ ወደብ ማግኘት አለብን::

አዲስ ዘመን፡- የተለያዩ ሀገራት ኢትዮጵያ የቀይ ባሕር ተዋሳኝ ለመሆን የምታደርገውን እንቅስቃሴ እንደሚደግፉ እየገለጹ ይገኛሉ:: ይህ ምን ማለት ነው ?

አደም (ረ/ፕ/ር)፡– የአካባቢውም ሆነ የዓለም ሀገራት ቀይ ባሕር አሁን ካለው ሁኔታ አንጻር ኢትዮጵያ በአካባቢው መኖሯ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ያደርጋል የሚል አመኔታ አድሮባቸዋል:: ይህንንም ሁኔታ መጠቀም መቻል አለብን:: ኢሳያስ አሰብ ወደብን ለሳውዲ ዓረቢያ አከራይቶ ለመጠቀም እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል:: ሳውዲዎችም በግንዛቤ ደረጃ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላምና መረጋጋት ከሌለ ወደቡን መጠቀም መቻላችን ምን ያህል ዋስትና አለው የሚለውን እየተነጋገሩበት ነው ያሉት::

እኛ በበኩላችን መረጃዎቻችንን አጠንቅረን እና አቋማችንን አጠናክረን የቀይ ባሕር አስፈላጊነት ለእኛ ምን እንደሆነ ለማስረዳት መንቀሳቀስ አለብን:: ወደብ ወይም የባሕር በር ልክ እንደ ዓባይ ግድብ ሁሉ የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድነት ሊጠቀምበት የሚገባ ጉዳይ ነው:: የወደብን ጉዳይ የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድ ጊዜ ብቻ በመነሳት የሚያረጋግጠው ሁኔታ ነው:: አራት ሚሊዮን ሕዝብ ያላት ሀገር ፍላጎት ተሟልቶ 130 ሚሊዮን ሕዝብ ይራብ ይቸገር ለከፍተኛ ወጪ ይጋለጥ የሚለውን ማንም የሚቀበለው አይደለም:: የሚደግፈን አካል ሞልቷል:: ነገር ግን እኛ አንድነታችንን ይዘን መነሳታችን አስፈላጊ የሆነበት ጊዜ ላይ ደርሰናል ማለት ነው:: ዲፕሎማሲያችን ጠንካራ ስለሆነ ብዙ እንቅስቃሴ ማድረግ እንችላለን::

አዲስ ዘመን፡- ግብጽ ኢትዮጵያና ሶማሊያ መካከል ንፋስ ገብቷል ብላ ባሰበች ጊዜ ሁኔታውን ለመጠቀም ምን ያህል ጥረት እንዳደረገች ተመልክተናል:: አሁን ደግሞ ኢትዮጵያ የቀይ ባሕር ተዋሳኝ ለመሆን የምታደርገውን እንቅስቃሴ ለማስተጓጎል ከኤርትራ መንግሥት ጋር በመሆን ሽርጉድ ማለቷ የሚፈይድላት ነገር አለ ?

አደም (ረ/ፕ/ር)፡- ግብጾች ከጥንትም በኢትዮጵያ ላይ ጥሩ አቋም የላቸውም:: አሁን የግድቡ ጉዳይ ሲያመልጣቸው በሶማሊላንድ ስምምነት መጡ:: የሶማሊያን መንግሥትን ረድተው በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት እንዲከፍት የማድረግ ውጥን ነበራቸው:: በጎረቤት ሀገራት ጉብኝት በማድረግ ጅቡቲን፣ ብሩንዲን፣ ዩጋንዳን እና ኬንያን ለመያዝ ጥረዋል:: ኤርትራ ሄደው ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ እና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጋር መክረዋል:: የቀራቸው ነገር የለም:: ዋናው ጉዳይ ለሶማሊ ሰላም ደማችንን በማፍሰስና አጥንታችንን በመከስከስ ትልቅ ሥራ የሠራነው እኛ ኢትዮጵያውያን ነን:: ግብጽ መቼ ነው የሶማሊያን ሰላም ለማስጠበቅ የሰላም አስከባሪ ጦር የላከችው? ስለዚህ በሶማሊ በኩል መጥተው ኢትዮጵያን ማጥቃት የማይሞከር ህልም ነው::

የኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር ያላትን ግንኙነት በቱርክ አደራዳሪነት መልሳ ማስተካከል በመቻሏ የግብጽ ፖለቲካ እጅግ አስቀያሚ አወዳደቅ ነው የወደቀው:: ኢትዮጵያና ሶማሊያ የተካረረ ሁኔታ ውስጥ በገቡበት ወቅት ከሚዲያዎች ጋር በነበረኝ ቆይታ የኢትዮጵያ ፍላጎት ሰላም በመሆኑ የሶማሊያ መሪዎች ወደ ግብጽም ሆነ ኤርትራ መመላለስ የተለየ ነገር እንደማያመጣ ተናግሬ ነበር:: ኢትዮጵያ በሶማሊያ ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣ ብዙ መስዋዕትነት ከፍላለች:: አሜሪካኖች ከሶማሊያ ምድር ተሸንፈው ሲወጡ የኢትዮጵያ ወታደሮች ግን ሞተውም ቆሰለውም ለሶማሊያ ብዙ መስዋዕትነት ከፍለዋል:: እንደ ጎረቤት ሀገር የሶማሊያ መረጋጋት ለኢትዮጵያም ወሳኝ ነው:: ይህን የሶማሊያ መሪዎች የተረዱ ይመስለኛል:: ሶማሊያና ኢትዮጵያ መካከል የነበረው ውጥረት በመርገቡ በአፍሪካ ቀንድ የተሻለ ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣ አድርጓል:: የሶማሊያ መሪዎችም ቢሆኑ ሥልጣናቸውን ለማስረከብ የአንድ ዓመት ተኩል ዕድሜ የቀራቸው በመሆኑ መካረሩን አልፈለጉትም:: በኢትዮጵያ በኩል በሳል የዲፕሎማሲ ሥራ ተሠርቷል::

የግብጽና ኤርትራ እንቅስቃሴ የከሰረ ፖለቲካ ነው:: በወቅታዊው ሁኔታ ያን ያህል የሚያሰጋን ነገር የለም:: የባሕር በር ጉዳይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍላጎት ስለሆነ አጠናክረን መቀጠል ይኖርብናል:: አሁን የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሞላ ጎደል ነቅቷል:: ያለፈውን ታሪኩን ረስቶ ድህነትን እና ኋላቀርነትን አሜን ብሎ ይቀበላል ማለት ሞኝነት ነው:: ግብጾች ሁልጊዜ የኢትዮጵያውያንን በቋንቋ እና በብሔር የመነጣጠል ሁኔታ መነሻ አድርገው ሊጠቀሙበት ሙከራ ያደርጋሉ:: እዚህ ላይ ነው ጥንቃቄ ማድረግ የሚገባን:: ስምምነታችን እና ሕብረታችን ካለ ማንም የፈለገውን ቢያደርግ የሚያመጣው ውጤት አይኖርም::

አዲስ ዘመን፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ በፓርላማ ባደረጉት ንግግር የዓባይ ግድብ ግንባታ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን ጠቁመው በአንድ መንፈቅ ጊዜ ውስጥ እንደሚመረቅ ገልጸዋል:: ኢትዮጵያ በግብጽ ሲደረግባት የነበረውን ፈርጀ ብዙ ጫና ተቋቁማ የጀመረችውን ታላቅ ፕሮጀክት ማጠናቀቋ የሚኖረውን አንድምታ እንዴት ይገልጹታል ?

አደም (ረ/ፕ/ር)፡- ኢትዮጵያውያን ከእንቅልፋችን ነቅተን በውሃችን ኤሌክትሪክ ለማመንጨትና በመስኖ ለመጠቀም መንቀሳቀስ ስንጀምር ግብጾች አትችሉም ሲሉን ነበር:: ግድቡን ለመገንባት የሚያስችል ብድር እንዳናገኝ ያደረጉት ጥረት ሲሳካላቸውም በድል አድራጊነት ስሜት ተውጠው ነበር:: ነገር ግን እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ከኪሱ ባወጣው ገንዘብ የግድቡ ግንባታ ሂደት ተጀምሮ 40 በመቶ ላይ ሲደርስ ግብጾች ደነገጡ:: ከዚህ በኋላ ነው ጩኸታቸውን የጀመሩት:: በድርድር ስም የግድቡን ግንባታ ለማደናቀፍ ያልቆፈሩት ጉድጓድ የለም:: ነገር ግን ኢትዮጵያ በተከተለችው ጠንካራ የድርድር መርህ እና ዲፕሎማሲ ምክንያት ሁሉም መክኖ ቀርቶባቸዋል::

ለአብነት ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ በሚል ባራመደችው አቋም ምክንያት ግብጾች ተገደው ወደ አፍሪካ ሕብረት ፊታቸውን ሲያዞሩ ይዘውት የመጡት አጀንዳ ሕብረቱም ሆነ አባል ሀገራቱ የሚቸገሩበት ነበር:: አንደኛው ጥያቄያቸው አውሮፓ እና አሜሪካ ታዛቢ ሆነው እንዲገቡ የሚጠይቅ ነው:: ይሄ ደግሞ ቅኝ ገዢዎች መልሰው ጣልቃ እንዲገቡ ዕድል መስጠት ነው:: ሁለተኛው ግድቡን ግብጾች እንዲያስተዳድሩት የሚጠይቅ ነው:: ይህም ከመብታችን እና ከነፃነታችን አንጻር ፈጽሞ የማንቀበለው ነገር ነው:: ሱዳኖች ደግሞ ይፍረስና እንደገና ይታይ የሚል የቴክኒክ ጥያቄ ነው ያነሱት:: ተቀባይነት የሌለው ነገር ነው:: ስለዚህ ስምምነት ላይ ሳይደርስ ቀርቷል:: በአሜሪካ አደራዳሪነት የተጀመረው ሂደትም መልኩን ሲቀይር ኢትዮጵያ ጥላ በመውጣቷ ተቋጭቷል:: የግብጽ ፖለቲከኞች ለሕዝባቸው ግድቡ የትም አይደርስም እያሉ ሲዋሹ ነው የከረሙት:: ኢትዮጵያ የግድቡን ግንባታ ቀጥላ ውሃ መያዝ ስትጀምር የግብጽ ሕዝብ በመቆጣቱ ፕሬዚዳንት አልሲሲ ባለሥልጣናቶቻቸውን ከኃላፊነት አንስተዋል::

ግብጾች የዓባይን ውሃ ብዙ ነገር ይሠሩበታል:: ኢትዮጵያ ነቅታ ግድብ እንዳትሠራ እንድትዳከም ምን እናድርግ ብለው ነው የሚመራመሩት:: ኢትዮጵያ ያልተሳተፈችባቸውን የቅኝ ግዛት ዘመን ስምምነት ለማጽናት ነው የሚንቀሳቀሱት:: ዋነኛዋ የዓባይ ወንዝ አመንጪ ሀገር በተገለለችበት ስምምነት እንድትገዛ አትገደድም:: የዓባይ ልጅን ውሃ ጠማው እንደሚባለው ኢትዮጵያውያን በ1977 በረሃብና በድርቅ ስቃይና ሰቆቃን አሳልፈናል:: ተርበናል፤ ተሰደናል፤ ሞተናል:: ይህ ሁሉ ሲደርስብን እኛ አፈርና ውሃ የምንገብርላቸው ሱዳኖችና ግብጾች ይሳለቁብን ነበር:: ውለታዋን አስበው ምንም ዓይነት ርዳታ አላደረጉም::

ስለዚህ ኢትዮጵያ የዓባይን ግድብ በማጠናቀቋ ታላቅ ድል ነው የተጎናጸፈችው:: በራሷ አቅም ግዙፍ ፕሮጀክትን ማሳካት የምትችል ታላቅ ሀገር መሆኗን ለዓለም አሳይታለች:: ግድቡን ለመገንባት ያሳየነውን ሕብረትና አንድነት ከያዝን ከድህነት መውጣት እንደምንችል ያየንበት ፕሮጀክት በመሆኑ የሚኖረው አንድምታ ብዙ ነው::

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያውያን ከውጭ የሚቃጣባቸውን የትኛውንም ዓይነት ትንኮሳና ጥቃት ለመመከት ምን ማድረግ አለባቸው ብለው ይመክራሉ ?

አደም(ረ/ፕ/ር)፡- አሁን ካለንበት ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር እንደ ሕዝብ ሰላም መረጋጋት አንድነትን ማምጣት ይጠበቅብናል:: እኔ እንደተገነዘብኩት ችግሮች ከመምጣታቸው በፊት የመነጣጠል ሁኔታ አለን:: ችግሮች ሲከሰቱ ደግሞ አንድነታችን ይጠናከርና የመከላከል ሥራ እንሠራለን:: ኢኮኖሚያዊም ሆነ ወታደራዊ ጥንካሬያችን ኢትዮጵያዊ መሆን አለበት:: የእዚያ ድክመት ውጤት ነው አንዳንድ ጊዜ ለአደጋ የሚያጋልጠን:: ለውጭ ጠላቶች በር የሚከፍተው ይሄ ነው:: ብሔር፣ ጎሳ እና እምነት የሚያለያየን መሆን የለበትም:: ክርስቲያኑም ሆነ ሙስሊሙ የሀገር ጉዳይ ሲመጣ አንድ ነው መሆን ያለበት:: የሀገር ጉዳይ አንድነትን ይጠይቃል:: በአንድነት ከቆምን ማንም ሰው ሊደፍረን አይችልም:: ከንዑስ ማንነት በፊት ሚዲያውም፣ ምሁራንም፣ ነጋዴውም፣ ፖለቲከኛውም ሁሉም በአንደኛ ደረጃ ኢትዮጵያዊነቱን ማረጋገጥ አለበት:: በጎሳና በብሔር የምንከፋፈል ከሆነ ለጠላቶቻችን እጅግ አደገኛ የሆነ ክፍተት እንተዋለን:: ክፍተቱን ተጠቅመው ነው እኛን የሚበታትኑን:: ለምሳሌ በሰሜኑ ጦርነት ላይ የግብጾችና የሱዳኖች ሚና ምንድን ነው የሚለውን ማየት አለብን:: ውጤቱን ስናየው አልተሳካላቸውም::

አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ እጅግ አድርጌ አመሰግናለሁ!

አደም(ረ/ፕ/ር)፡- እኔም አመሰግናለሁ!

ተስፋ ፈሩ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 20 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You