ውሻ ነጋዴው ወጣት

የሰርኩን ነፋሻማ አየር ለመቀበል በእግሬ ሳዘግም በርከት ያሉ የጎዳና ውሾች አላፊ አግዳሚው ላይ ምክንያት እየፈለጉ ቢጮሁም አንድ የቆሎ ተማሪን ግን “ከእኛ ብታመልጥ ወገባችንን ለፍልጥ” ያሉት ይመስለኛል የያዘውን ቆመጥ ዱላ ከመጤፍ ሳይቆጥሩ እንደመዥገር እርር ብለው ተጣብቀውበታል። ከገላገልኳቸው በኋላ የቆሎ ተማሪና ውሻ ለምን እንደሚጣሉ ስጠይቀው “የሚጣልላቸውን ቁራሽ እንጀራ ስለምንወስድባቸው ይሆናላ” የሚል መልስ ሰጠኝ ከውሻ ንጥቂያ የተረፈ አኮፋዳውን እያስተካከለ። ይህን ሲለኝ የዕለት ጉርሱን ከመሻት አልፎ የሀገሩን ደህንነት ለመታደግ የተቀበረ ፈንጂ መኖሩን በመጠቆም ለሽልማት የበቃው የቻይናው ውሻ አስደንቆኝ የሀገራችንም ውሾች እንዲህ ቢሆኑ ብዬ መመኘቴ አልቀረም።

ያደጉ ሀገራት ውሾችን በማሰልጠን ለስለላ ከመጠቀማቸው ባሻገር ዓይነ ሥውራንን እንዲመሩ ያደርጓቸዋል፤ እኛ ሀገር ግን ግቢ ብቻ እንዲጠብቅ ለማድረግ «ድንገት እንኳን ሰው ቢለምድ ሌባ ላያስጥል ይችላል» ብለን በማሰብ ክሂላቸውን ለተሻለ ነገር ለማዋል የሄድንበት ርቀት እምብዛም ነው። በዚህ ሃሳብ እየተወዘወዝኩ ጉዞዬን ሳሰላ መቻል የቤት እንስሳት መኖና መገልገያ [መቻል ፒት ሾፕ] የሚል ጽሑፍ ከደረቱ የሰቀለ ቤት ተመለከትኩና ላፍታ ያህል ቆሜ አስተዋልኩት።

ከቤቱ ዘልቄ ዙሪያ ገባውን ስቃኝ ልማዳዊ አያያዛችንን አርቀን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ለመንከባከብ የሚያስችሉን የውሾች የምግብ ፍጆታዎች፣ መጫዎቻዎች፣ አልባሳትና የጽዳት መጠበቂያ ቁሳቁሶች የሱቁን ሼልፍ ሞልተውታል። በነገሩ ተደንቄ መቅረጸ/ድምጼን በማስተካከል ስለሁኔታው ቃለመጠይቅ እንዲሰጠኝ ስጠይቀው ሳያመነታ እሽታውን ሰጠኝና ቆይታችንን ጀመርን።

ከ21 ዓመታት በፊት 1996 ዓ.ም ከአባቱ አቶ አረጋይ ገብረኪዳንና ከእናቱ ከወይዘሮ የሺሐረግ ነጋ እዮብ አረጋይ ተወለደ። እትብቱን በተቀበረበት አዲስ አበባ መካኒሳ በድንቦስኮ የካቶሊክ ሚሽነሪ ትምህርት ቤት የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን የተከታተለው እዮብ፤ ለሻይ መጠጫ የሚሆን ፍራንክ ሁልጊዜ ቤተሰብን ማስቸገሩ ይሉንታ ፈጥሮበት አሁን ላይ ስም የገዛበትን የሥራ ፈጠራ እንዲያመነጭ መልካም አጋጣሚ ሆኖለታል። ለወላጆቹ ሶስተኛና የመጨረሻ ልጅ የሆነውን ወጣቱ እንግዳዬን ውሻን አርብቶ ከመሸጥ አልፎ ለዕለት ተዕለት ኑሯቸው የሚያስፈልጓቸው ግብዓቶችን እስከ ማቅረብ ድረስ ያለው ሂደት ምን ይመስላል? ስል ለወጋችን መግቢያ እንዲሆን ጥያቄ አቀበልኩት።

ወጣት እዮብ፤ “መጀመሪያ በአካባቢዬ ካሉ ውሻ ሻጮች ጋር በመሆን ኮሚሽን እያሰቡልኝ እንደደላላ አግዛቸው ነበር። በኋላም የማገኘው ጥቂት ገንዘብ ተጠራቅሞ አራት መቶ ሲሞላልኝ ራሴን ችዬ ገዛሁና ተገቢውን ያመጋገብና የጤና ክትትል በማድረግ ለገበያ ሳቀርብ ደህና ሂሳብ አገኘሁበት።” ሲል መነሻውን አስገነዘበኝ። ቀጥዬ ከቤተሰብ አንስቶ እስከ አካባቢው ማኅበረሰብ ድረስ ያለውን አመለካከት እንዴት አገኘኸው? ስል ሌላ ጥያቄ አከልኩለት። እዮብ ፊቱ በፈገግታ ተሞልቶ በኩራት እንዲህ ሲል መለሰልኝ። “ምንም እንኳን ወላጆቼ በትምህርቱ መስክ እንድገፋ ቢሹም ከልጅነት መሠረቴ ውሻ እወዳለሁና ፈቃዴን እንድፈጽም ከማገዝ የዘለለ ነቀፌታ አላደረሱብኝም፤ የአካባቢው ሰው ግን አላማዬ አድርጌ ይዤው ጥቅሙን አይቶ እስኪገነዘብ ድረስ “የሀረር ሰንጋ ተሸጦም ለውጥ አልመጣ” እያለ ያሾፍብኝ ነበር በማለት ሃሳቡን በተግባር መሬት ለማስነካት ሲፈጠር የነበረውን ፈተና አጫወተኝ።

አስከትዬ ያልተለመደና በማኅበረሰባችን የአኗኗር ባሕል እንደነውር የሚቆጠረውን የውሻ ሽያጭ የንግድ ዘርፍን ደፍረህ የገባህበት እንዲሁም ለመሥራት የሚያስችል የሞራል ጥንካሬ የታጠከው፤ ተሞክሮ የቀሰምክበት ነጋዴ የሆነ የቤተሰብ አባል አለ? በማለት የማወቅ ጉጉት ስሜት ያዘለ ጥያቄዬን አነሳሁለት።

“ነገን ለመኖር የዛሬን ዛሬን ለመኖር ደግሞ የትናንትን ፈተናዎች እንደሐይወት እዳ ሳይሆን እንደሕይወት ምንዳ በመቁጠር በእያንዳንዱ የምንነትና የማንነት ሽግግሮቻችን ላይ የሚታዩ ጎታች የአመለካከት ህጸጾችን በማረም በሚኖረን የሥራ እንቅስቃሴ ሂደቱን ለማሳለጥ ከአለት የጸና ሞራል እንላበሳለን። እኔም የተገነባሁት በዚህ አካሄድ ነውና ሰውኛ ምንነቴን ብሎም የሥራ ማንነቴን በአቅምና ክህሎት ሥልጠናዎች ራሴን አጎልብቼ፤ የዕለት እንጀራ ከመቁረስ ባለፈ የቤት እንስሳትን አያያዝ ለማስተማር ለሀገሬ ዜጎች ምሳሌ ሆኜ እገኛለሁ።

እኛ ወጣቶች ልብ ልንለው የሚገባው ትልቁና ዋነኛ ተቀዳሚ ተግባራችን መሆን ካለበት ምን አለኝ? ምንስ መሥራት እችላለሁ? የሚሉ ጥያቄዎችን በመፈተሽ ያለንን ውስጣዊ ጸጋችንን ማውጣት ነው፤ ይህን ያደረግን እንደሆነ አዲስ ነገሮችን ለመፍጠር እንጂ በተለመዱ የሥራ ዘርፎች ላይ ገንዘባችንንና ጊዜያችንን ስናባክን አንገኝም። ለራሳችሁ ያላችሁት ራሳችሁ ብቻ ናችሁና ማንም እንዲደርስላችሁ አትጠብቁ፤ “ሰው ያለ ሰው አይደምቅ እህል ያለመንጋጋ አይደቅ” የሚለው ብሂላችን እንዳለ ሆኖ ማለት ነው።

የኔ ቤተሰቦች በግልና በመንግሥት ተቋማት ተቀጥረው የሚሠሩ ናቸው። አሁን ላለሁበት የውሾች ርባታና የመገልገያ እቃዎች ሽያጭ ሥራ እንግዳ ስለነበሩ አይዞህ እያሉ ሞራል ከመስጠት በቀር ያዋጡት ሃሳብ የለም። ይሁን እንጂ በጀመርኩት አዲስ የሥራ ጽንሰ ሃሳብ ሳልመጻደቅ ሁልጊዜ ተማሪ ነኝና እግራቸው ስር ሆኜ ራሴን ለመቀየር እየታተርኩ እገኛለሁ።” አለ። በራስ መተማመኑ ከገጹ ላይ ጎልቶ እየተነበበ።

እሱ የሚያወራኝን እያዳመጥኩ በአንድ ጎኔ በማኅበራዊ የትስስር ገጹ የለጠፋቸውን ማስታወቂያዎች ተመለከትኩና አስተያየት መስጫ ሳጥኑ ላይ የሰፈሩትን ሃሳቦች ስበረብር የሚሠሩ እጆችን ከመሰብሰብም በላይ ሰውኛ ሞራልን እንደ ሸክላ አንኮታኩተው ከጥቅም ውጭ ያደርጋሉ። አዳዲስ ነገሮችን የሚፈጥሩ ወጣቶችን የማያበረታታና የሥራ ተነሳሽነታቸውን የሚቀብር እሳቢያችን እያለ ሥራ ፍጠሩ ብለን ብንለፈልፍ “ፈረስ ግዙ ጨው ላያግዙ” እንደሚባለው ተረት ይሆንብናልና ባነበብኩት ነገር ስሜቴ ክፉኛ ተጎድቶ ባየ ጊዜ ወጣቱና ብርቱ ሰው እዮብ አረጋይ “ትችት ፈርተህ ምስጋናና ሙገሳ ጠብቀህ ከሠራህማ ከሕይወት ገጽ ምኑን ተማርከው?” አለኝ ንግግሩን በሳቅ አጅቦ።

ለማርባት የምትመርጠው የትኞቹ ዝርዮች ናቸው? የከተማችንን ጎዳናዎችን የሞላው የውሻ መንጋ እጣ ፈንታውስ ምንድነው? ስል ሌላ ጥያቄ መዘዝኩ። “ከሁሉም አስቀድሞ ውሾችን መንከባከብ ባንድም ይሁን በሌላ መንገድ እንደ ዕብድ ውሻ ከመሳሰሉት በሽታዎች የማኅበረሰብን ጤና መጠበቅ ነው። አኒማል ኒድ አቴንሽን ከተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር በመተባበር በየጎዳናው የሚርመሰመሱ ውሾችን የጤና ክትትል በማድረግ ደህና መሆናቸውን ስናረጋግጥ ተረክበው ማሳደግ ለሚፈልጉ ሰዎች እንሰጣቸዋለን፤ መስጠት ብቻ ሳይሆን ጤናቸው ላይ አስጊ ነገር ቢመለከቱ ድጋፋችንን ማግኘት እንደሚችሉ በማስተማር ውሾችን ከሚረከቡ ሰዎች ጋር ሙሉ አድራሻ ልውውጥ እናደርጋለን። በዚህም አመርቂ ውጤት በማየቴ ሌሎች መሰል አጋር ድርጅቶችን እየሳብኩ የቤት እንስሳትን የምንይዝበትን የተሳሳተ ልማዳችንን ለማሻሻል እየሠራሁ ነው።” ሲል ከግል ጥቅሙ ባሻገር ውሾችን መንከባከብ ያለውን ሀገራዊ ፋይዳ አስገነዘበኝ።

ቀጠለና የሚያረባቸውን ውሾች እያስጎበኘኝ “በብዛት ለገበያ የምናቀርባቸው ውሾች የውጭ ዝሪያ ያላቸው ሲሆኑ፤ የሚሰጣቸውን ማንኛውንም ሥልጠና የመቀበል አቅማቸው ከፍተኛ በመሆኑ ዋጋቸውም ውድ ነው። በተፈላጊነት ደረጃ አብላጫውን ቁጥር የሚይዙት እንደማስቲቭ፣ ፉድል፣ ማልቴስ የመሳሰሉት ድንክ ውሾች ናቸው። ለሳሎን ጌጥነት ተመራጭ በመሆናቸው እስከ 15000 ብር ድረስ ይሸጣሉ። እንደነሱ አይሁን እንጂ እንደ ጀርመን ሺፐርድ፣ ቶለር ያሉትም ተፈላጊ ናቸው። የሀገር ቤት ውሾች ግን የሚሰለጥኑበት ትምህርት ቤት ካለመኖሩ ጋር ተያይዞ የመቀበል አቅማቸው አናሳ ነውና ለሽያጭ ሳይሆን ሥራዬን ለማስገንዘብ ይረዳኝ ዘንድ የምሰጣቸው በነፃ ነው። ለወደፊቱ ግን ፈጣሪ ቢረዳኝ እንደ ውጭዎች ሁሉ የእኛ ሀገር ውሾችም ሥልጡን የሚሆኑበትን ትምህርት ቤት ለመክፈት ከወዳጆቼ ጋር በመቀናጀት እንቅስቃሴ እያደረግን እንገኛለን” ሲል እንደ ውብ ጽጌሬዳ ተስፋና ጽናት ያፈካውን ህልሙን ገለጠልኝ።

የፍቃዱን ነገር ግን በምን መልኩ አወጣሃው? ለሚለው ጥያቄዬ ቅሬታ ውስጥ ሆኖ ተከታዩን መልስ ሰጠኝ። “እኛ ሀገር አስቀድመን ተዘጋጅተን የመጠበቅ ባሕላችን ገና ዳዴ ላይ ነው። የእንስሳት እርባታ ፈቃድ ሥራ ላይ ስላልዋለ ያወጣሁት የሱቅ የንግድ ፍቃድ ነው። ከዚህ በኋላ ላለው ጊዜ ግን መማሪያ እንዲሆን ከመንግሥት ጋር በቅርበት እየሠራንበት እንገኛለን” አለ ብሩህ መንፈሱ እያንጸባረቀ።

ሀገረ አሜሪካ ኑሮዋን ያደረገችው ሳራ አብርሃ ለዕረፍት አዲስ አበባ በተገኘችበትና መቻል ፒት ሾፕ በመጣችበት አጋጣሚ ስለእዮብ አገልግሎት አሰጣጥ ብቃትና ስለሥራ ባሕሉ የታዘበችውን እንድትነግረኝ ጠየኳትና ይህን አለችኝ። ለመጀመሪያ ጊዜ ያወቀችው በማህበራዊ ትስስር ገጾች ቢሆንም ማየት ማመን ነውና ባገኘችው አገልግሎት መርካቷን ገልጻ ምርቶቻቸውን ብንጠቀም ራሳችንንም፣ ወጣቶችንም፣ ሀገርንም ማሳደግ እንደሆነ በአጽኖት ትመክራለች። ብዙሃኑ ደንበኞቻቸውም ዲፕሎማቶች እንደሆኑ በቆይታዋ መመልከቷን ትገልፃለች።

ራሱ የሚያዘጋጀው የተፈጨ ዶሮና ከውጭ የሚያስገባው ደረቅ ምግብ በብዛት ተፈላጊ እንደሆነ የገለጸልኝ እዮብ፤ ከውጭ የሚያስገባቸውን ምግቦች ሀገር ውስጥ ለማምረትም የማሽን ግዢ ላይ እንደሚገኝ አጫውቶኛል። የአየር ንብረትን ያማከሉ ለሙቀትና ለብርድ የሚሆኑ የውሾች አልባሳት ከመኖራቸው በተጨማሪ ማለንቶስ የሚል ሻምፖ አይቼ ጠየኩት። “ሁሉም በሚባል ደረጃ ውሻቸውን በሰው ሻምፖ እያጠቧቸው ጸጉራቸው ረገፈ፤ ቆዳቸው ተላላጠ፤ ሰውነታቸው ሽታ ፈጠረ ይሉኛል። ስለዚህ ሻምፖ ከመሠረቱ የተዘጋጀው ለውሾች ብቻ ነውና የራሳቸውን ሎሽን፣ ጥርስ ብሩሽ፣ ጸጉር ማበጠሪያ፣ ጥፍር መቁረጫ፣ መመገቢያ ሳህን ማዘጋጀት ይኖርብናል” በማለት ከልምዱ ያካበተውን እውቀት አካፍሎኛል።

እንደፐርል ያለ ከታጠቡ በኋላ የሚቀቡት ቅንጡ የውሾች ዶድራንትም አይቼ መገረሜ አልቀረም። ውብ ማሰሪያ እንደ ጌጥ የሚያገለግሉ ቀበቶና ሰንሰለቶች፣ የሰውን የመኝታ ፍራሾችን የሚያስንቁ የውሾች መኝታዎች፣ መጫወቻ ኳሶች መኖራቸውንም ልብ ብያለሁ። መኝታቸውንና አልባሳቶቻቸውን ሀገር ውስጥ ማዘጋጀት መጀመራቸውን በቅኝቴ አረጋግጫለሁ። ከማኅበረሰባችን አቅም አንጻር የምትሰጡት አገልግሎት ዋጋው አልበዛም ወይ? ብዬ መጠየቄም አልቀረም። “ከውጭ የምናስገባቸውን ምርቶች በሀገር ውስጥ ምርቶች መተካት ያስፈለገው ለዚህም ነው።” ሲል አስተያየቱን እንደሚያምንበትና ለማስተካከል እየሠራ እንደሆነ በሙሉ ልብ ቃሉን ሰጥቶኛል።

በረዳትነት አብራው ስትሰራ ያገኘኋት እመቤት ገና ሥራውን እንደጀመረች አካባቢ ግንዛቤው እንዳልነበራትና አሁን ላይ ግን እየተለመደ መጥቶ እሷም ዳቦ ያበሰለችበት እንግዳ የሥራ ዘርፍ መሆኑን አወጋችኝ። በአሁኑ ሰዓት ወጣቱ እዮብ አረጋይ ስምንት ለሚጠጉ ዜጎች የሥራ እድል ከመፍጠሩም በላይ በበጎ አድራጎት ሥራዎችም ላይ በንቃት እየተሳተፈ እንደሚገኝ እመቤት አክላ አጫውታኛለች። በሥራው ዓለም ሲቆይ ጥሩም ይሁን መጥፎ አጋጣሚ ካለው እንዲያጫውተኝ በጠየኩት ጊዜ እስኪለመድ ድረስ ጓደኞቹ ለተወሰነ ወቅት ሸሽተውት እንደነበረና አሁን ግን ለሥራው ማደግ ቀኝ እጅ በመሆን ለስኬት እንዳበቁት ገልጾ ከሚያስበው ግብ ገና አለመድረሱንና ስኬት በጨመረ ቁጥር ፈተናዎችም አብረው ያድጋሉና ከጎኑ እንዲቆሙ በምስጋና ድጋፋቸውን ሽቷል። በመጨረሻም ይህን ሥራ ከኢትዮጵያ አልፎ በምስራቅ አፍሪካ ደረጃ ማስፋት እንደሚፈልግና ከዚህ ዘርፍ በተጨማሪ በቴክኖሎጂው መስክም ለሀገሩ የራሱን ዐሻራ ለማበርከት የጀመረው ሂደት እንዳለ መረዳት ችያለሁ።

በሀብታሙ ባንታየሁ

አዲስ ዘመን ዓርብ መጋቢት 19 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You