
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ በአዋጅ የተሰጠውን ተግባርና ኃላፊነት ከመወጣት አኳያ ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል። በተለይም ባለፉት አራትና አምስት ዓመታት፤ በዋናነትም ከገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻያው ማግሥት በወሰዳቸው ዘርፈ ብዙ ርምጃዎች ከፍ ያለ ውጤት እየተገኘ ስለመሆኑም መረጃዎች ያሳያሉ።
በተሻሻለው የባንኩ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1359/2025 አንቀጽ 23፣ መሠረት የተቋቋመው የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ ደግሞ የእዚህ ስኬታማ ጉዞውና ተግባሩ አንዱ ማሳያ ሆኖ ይጠቀሳል። ምክንያቱም ይሄ ኮሚቴ ባንኩ ዋጋን የማረጋጋትና የኢኮኖሚውን ዕድገት የመደገፍ ቀዳሚ ዓላማ ጋር የተጣጣሙ የገንዘብ ፖሊሲ ምክረ ሃሳቦችን ለባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ በማቅረብና በማጸደቅ በኩል ጉልህ ድርሻ አለው።
በዚህ መልኩ ከሚያቀርበው ምክረ ሃሳብና የውሳኔ መነሻ ሃሳቦች መካከል ደግሞ የኢትዮጵያን የዋጋ ግሽበት፣ የፊስካል፣ የውጭ ኢኮኖሚ፣ የገንዘብ አቅርቦትና የፋይናንስ ዘርፍ እንቅስቃሴዎችን በመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ ሲሆን፤ ለዚህም በተለይ በሀገር ውስጥ የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታዎች ላይ ጉልህ አንደምታ ያላቸውን ዓለም አቀፍ ሁኔታዎች በጥልቀት ይገመግማል።
በዚሁ አግባብም ሥራውን ሲከውን የቆየ ሲሆን፤ ቀደም ሲል አንድ የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ ስብሰባ ውሳኔ ማቅረቡም የሚታወስ ነው። ከዚህ በኋላም መሰል ሥራዎችን ሲያከናውን የቆየው ይሄው ኮሚቴ ታዲያ፤ የሂደቱን ውጤታማነት ከመገምገም እና የቀጣይ አቅጣጫን ከማስቀመጥ አኳያ፣ ሁለተኛ ስብሰባውን መጋቢት 16 ቀን 2017 አካሂዷል። ኮሚቴውም “የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ ስብሰባ ቁጥር 2” በሚል ባወጣው መግለጫ ዝርዝር የግምገማ ውጤቶችን እንዲሁም፤ የውሳኔ አቅጣጫዎችን እና ምክረ ሃሳቦችን አመላክቷል።
በዚህ መግለጫ መሠረትም ኮሚቴው በመጀመሪያ የተመለከተው በማሻሻያ ሂደቱ የታዩ ለውጦችንና የተገኙ ውጤቶችን ሲሆን፤ በዚህም አበረታች ውጤት ስለመገኘቱ አመላክቷል። ለምሳሌ፣ የሀገር ውስጥ ብድር በ19ነጥብ8 በመቶ መጨመሩ፤ በባንኮች መካከል ያለው የገንዘብ ግብይት መጠን በየካቲት ወር 2017 መጨረሻ ብር 338ነጥብ8 ቢሊዮን መድረሱ፤ በግብርናው ዘርፍ እየተወሰዱ ያሉ የአቅርቦት ማሻሻያዎች ከፍተኛ የሰብል ምርት እንደሚኖር ማመላከታቸውን፤ በዚህም ምግብ-ነክ ያልሆነ የዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ቀንሶ 15 ነጥብ 6 በመቶ መድረሱን፤ ነገር ግን ባለፉት ጥቂት ወራት ከፍ የማለት አዝማሚያ ማሳየቱን በመግለጫው አብራርቷል።
ይሄው የዋጋ ግሽበት ጉዳይም ኮሚቴው በመግለጫው በዝርዝር ካስቀመጣቸው የግምገማው ዐበይት ግኝቶች መካከል አንዱና ቀዳሚው ነጥብ እንደመሆኑም፤ ካለፈው የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ ስብሰባ ወዲህ፣ ዓመታዊ የዋጋ ግሽበት እየቀነሰ በመምጣት የካቲት ወር 2017 መጨረሻ 15 በመቶ መድረሱን ኮሚቴው ስለመገንዘቡ አመላክቷል።
በዚህ መልኩ ባለፉት ጥቂት ወራት የዋጋ ግሽበት በተከታታይ እየረገበ እንዲመጣ ካደረጉት ተግባራት መካከል ደግሞ፤ ብሔራዊ ባንክ ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ በመከተሉ፣ የግብርና ምርት በመሻሻሉና በአስተዳደራዊ ዋጋዎች ላይ እየተወሰደ ያለው ማሻሻያ ትግበራዎች ስለመሆናቸውም ኮሚቴው በመግለጫው ቀዳሚ ግምቱን አስቀምጧል።
እነዚህ የእርምት ርምጃዎች ደግሞ አንዱ አንዱን አጋዥ እና ችግሮችን ለማቃለል አቅም የሚፈጥሩ መሆናቸው እሙን ነው። ለምሳሌ፣ የገንዘብ ፖሊሲው ትግበራ ከግብርና (በተለይም ከምግብ ሰብል) ምርታማነት ጋር ተሰናስሎ እንዲተገበር መደረጉ በምግብ ነክ ምርቶች ላይ ያለው የዋጋ ግሽበት እንዲቀንስ አድርጎታል።
የኮሚቴው መግለጫም ይሄንኑ የሚያረጋገጥ ነው። ለምሳሌ፣ ምግብ-ነክ የዋጋ ግሽበት በየካቲት ወር 2017 መጨረሻ 14ነጥብ6 በመቶ የደረሰ ሲሆን፣ ይህም ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው ሦስት በመቶ ጋር ሲነጻጸር በእጅጉ ያነሰ መሆኑን፤ ነው ኮሚቴው በመግለጫው የገለጸው።
በሌላ በኩል ደግሞ ምግብ-ነክ ያልሆነ የዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ቀንሶ 15ነጥብ6 በመቶ የደረሰ ቢሆንም፤ ባለፉት ጥቂት ወራት የማንሰራራት አዝማሚያ እያሳየ መሆኑን ኮሚቴው ከመጠቆም አልተቆጠበም። ይሁን እንጂ፣ በዚህ በኩል የታየው የዋጋ መጨመር ሲታይ፣ በየካቲት ወር 2017 ላይ የ0ነጥብ5 በመቶ ወርሃዊ ዕድገት የታየበት፤ ለአራት ተከታታይ ወራት የተከሰተው በዚሁ አግባብ ዝቅተኛ ዕድገት እንደመሆኑም፤ በዚህ በኩል ያለው የዋጋ ግሽበት በኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድረው አዲስ ተጽእኖ ዝቅተኛ ስለመሆኑ አብራርቷል።
ኮሚቴው በስብሰባው የተመለከተው እና በመግለጫውም ሰፋ ያለ ማብራሪያ የሰጠው ሁለተኛው አንኳር ጉዳይ፣ እድገት እና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ነው። ዕድገት አኳያ ኮሚቴው ባስቀመጠው የግምገማ ምልከታ መሠረት፤ በአብዛኞቹ የሀገሪቱ አካባቢዎች የታየው ምቹ የመኸር ዝናብ ወራትና በግብርናው ዘርፍ እየተወሰዱ ያሉ የአቅርቦት ማሻሻያ ውጥኖች በዘንድሮው ዓመት ከፍተኛ የሰብል ምርት እንደሚኖር ያሳያሉ።
በተመሳሳይ በኢንዱስትሪ፣ በሸቀጦች ወጪ ንግድ (በተለይም በቡናና በወርቅ)፣ እንዲሁም በአገልግሎት ወጪ ንግድ (በተለይም በአየር ትራንስፖርትና በቱሪዝም) ዘርፎች በመሳሰሉ ሌሎች ዘርፎችም የተጠናከረ ዕድገት እንደሚኖር መገመቱን ኮሚቴው አመላክቷል። በዚህም መሠረት የሀገር ውስጥ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ አመላካቾች የተጠናከረ የዕድገት አዝማሚያ መኖሩን እንደሚያሳዩም ነው ኮሚቴው የገለጸው።
የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን በተመለከተም፣ የገንዘብ ሁኔታን፣ የባንኮች የእርስ በርስ መስተጋብር፣ የወለድ ተመንን፣ በጥቅሉም የባንክ እና የፋይናንስ ዘርፉን የመረጋጋት ሁኔታ በዝርዝር የተመለከተበት ነው። የገንዘብ ሁኔታን በተመለከተ፤ ከመጀመሪያው የኮሚቴው ስብሰባ ማግስት የብድር፣ የፊስካልና የውጭ ኢኮኖሚ ሁኔታዎች እንዲላሉ በመደረጋቸው ምክንያት መጠነኛ የገንዘብ ዝውውር እድገት ጭማሪ መታየቱን ኮሚቴው ተገንዝቧል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከወርቅ ሽያጭ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ክምችት በመያዙ፤ እንዲሁም ተመጣጣኝ የሀገር ውስጥ ገንዘብ ወደ ባንክ ሥርዓት እንዲገባ በመደረጉ መሠረታዊ ገንዘብ ፈጣን ዕድገት ሊያሳይ የቻለ ሲሆን፤ በዚህም፣ እስከ ጥር ወር 2017 ድረስ በኢኮኖሚ ውስጥ የሚዘዋወረው የጠቅላላ ገንዘብ አቅርቦት (broad money supply) የ22ነጥብ8 በመቶ፤ መሠረታዊ ገንዘብ (base money) 42 በመቶ ዓመታዊ ዕድገት ማሳየታቸውን፤ እንዲሁም፣ የሀገር ውስጥ ብድር በ19ነጥብ8 በመቶ መጨመሩን በመግለጫው ለአብነት አቅርቧል።
የሀገር ውስጥ ብድር ከመጨመሩ በተጓዳኝ ግን፣ በገበያ ላይ የተመሠረቱ የአጭር ጊዜ የወለድ ተመኖች ለመጀመሪያ ጊዜ ከዋጋ ግሽበት በላይ መሆናቸውን መገንዘብ ተችሏል። ለአብነትም፣ የ364 ቀን የመንግሥት የግምጃ ቤት ሰነድ የወለድ ተመን አምና ታኅሣሥ ወር መጨረሻ ላይ ከነበረበት 15ነጥብ9 በመቶ፤ ዘንድሮ የካቲት ወር 2017 መጨረሻ 17ነጥብ7 በመቶ መድረሱ ተጠቁሟል።
በሌላ በኩል፣ ባንኮች እርስ በርሳቸው በሚበዳደሩበት ገበያ አማካይ የወለድ ተመን የካቲት ወር ላይ 16ነጥብ7 በመቶ የደረሰ ሲሆን፣ ይህም ብሔራዊ ባንክ ባስቀመጠው የ15 በመቶ የወለድ ተመን ክልል (በሦስት በመቶ ያነሰ ወይም ከፍ ያለ ወሰን) ውስጥ ይገኛል። በባንኮች መካከል እየተደረገ ያለው የገንዘብ ግብይት መጠንም በፈጣን ሁኔታ ማደጉን ቀጥሎ በየካቲት ወር 2017 መጨረሻ ብር 338ነጥብ8 ቢሊዮን መድረሱን ነው ኮሚቴው በመግለጫው ያብራራው።
እነዚህ እና መሰል የግምገማ ግኝቶች ጋር በተያያዘ፤ ኮሚቴው የባንክ እና የፋይናንስ ዘርፍ መረጋጋት የታየበት ስለመሆኑም አንስቷል። በዚህ ምልከታውም፣ የባንክ ዘርፍ ዝቅተኛ የተበላሸ ብድር እና በቂ ካፒታል ያለው፤ ሂደቱም ጤናማና የተረጋጋ መሆኑን ገልጿል። ይሁን እንጂ፣ አንዳንድ ባንኮች በተወሰነ መልኩ የጥሬ ገንዘብ እክል (liquidity) እጥረት የሚታይባቸው ስለመሆኑም ጠቁሟል።
የዚህ ምክንያቱ ደግሞ፣ በተወሰኑ ባንኮች የብድርና የተቀማጭ ሂሳብ (loan to deposit ratio) ጥምርታ ከፍተኛ መሆኑን፤ ነገር ግን፣ የባንክ ለባንክ የገንዘብ ግብይት (Interbank Money Market) እና በብሔራዊ ባንክ በኩል ቋሚ የብድር አገልግሎት መጀመራቸው የአንዳንድ ባንኮች ችግር እየተቀረፈ እንደሚገኝም አመላክቷል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ ኮሚቴው ባወጣው መግለጫ ያስቀመጠው ሌላው ነጥብ፤ የፊስካል ሁኔታ ግምገማ ግኝትን ይመለከታል። በዚህ ግኝት መሠረት፤ ጥንቃቄ የተሞላበት የፊስካል ፖሊሲ ሥርዓት መተግበር መቀጠሉን፤ ጥብቅ የፊስካል ዲሲፕሊን መኖሩ በዘንድሮው በጀት ዓመት ለበጀት ጉድለት ማሟያ ከብሔራዊ ባንክ ብድር እንዳይወሰድ መርዳቱን፤ በዚህም ለማዕከላዊ ባንኩ የገንዘብ ፖሊሲ አቋም ከፍተኛ ድጋፍ የሚሰጥ ክስተት ሆኖ መገኘቱን መረዳት ተችሏል።
በሀገር ውስጥ ከታየው የገንዘብ ፖሊሲ ትግበራ ውጤት በተጓዳኝ፣ የውጭ ኢኮኖሚው ዘርፍ እንቅስቃሴ ላይ የታየውን መሻሻልም ኮሚቴው ገምግሟል፤ ውጤቱንም በመግለጫው አመላክቷል። በዚህም መሠረት፣ የውጭ ኢኮኖሚ ዘርፍ እንቅስቃሴ ትልቅ መሻሻል ማሳየቱን፤ ባለፈው ሐምሌ ወር 2016 በተደረገው የውጭ ምንዛሪ ተመን ማሻሻያ ምክንያትም የሸቀጦችና የአገልግሎቶች ወጪ ንግድና ሐዋላ፣ እንዲሁም የካፒታል ሂሳብ ከፍተኛ ዕድገት ማሳየታቸውን፤ የከረንት አካውንት በመጀመሪያው የበጀት ግማሽ ዓመት ትርፍ ማሳየቱን እና የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያ ክምችትም መጨመር መቻሉን አብራርቷል።
በመሆኑም ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ዕድገት እ.ኤ.አ በ2025 እና በ2026 ተጠናክሮ እንደሚቀጥል፤ በዚህም ሦስት ነጥብ ሦስት በመቶ ዕድገት እንደሚያሳይ የዓለም የገንዘብ ድርጅት የጥር ወር መረጃ እንደሚያመላክት ኮሚቴው በመግለጫው አስፍሯል።
በአንጻሩ፣ ዓለም አቀፍ የዋጋ ግሽበት እ.ኤ.አ በ2025 ወደ 4ነጥብ2 በመቶ፤ እ.ኤ.አ በ2026 ደግሞ ወደ 3ነጥብ5 በመቶ ዝቅ እንደሚል መተንበዩን አመላክቷል። ይሁን እንጂ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚንጸባረቁ የጂኦ ፖለቲካ እንቅስቃሴዎችና አለመረጋጋቶች በዓለም አቀፍ የታሪፍና የንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ በሚያሳድሩት ተጽእኖ የዋጋ ግሽበት ሊባባስ እንደሚችልም ጥቆማውን አድርሷል።
እንደ አጠቃላይ ሲታይ ግን አሁን ያለው የዓለም የሸቀጦች ዋጋ በጥቅሉ ለሀገራችን ምቹ ነው ሊባል የሚችል መሆኑን የጠቆመው መግለጫው፤ የነዳጅ ዋጋ የበጀት ዓመቱ ከተጀመረ ወዲህ 9 በመቶ ሲቀንስ፣ በአንጻሩ፣ የዋና ዋና የወጪ ምርቶች ዋጋ (የቡናና የወርቅ) ከመቼውም ጊዜ በላይ በከፍተኛ ደረጃ በመጨመሩ ለውጭ ክፍያ ሚዛን መሻሻል አስተዋጽኦ ስለማድረጉ ለአብነት አንስቷል።
ይሄንን የግምገማ ግኝት መነሻ በማድረግም ኮሚቴው ውሳኔ እና የውሳኔ ሃሳብ አቅርቧል። በዚህም መሠረት፣ የቅርብ ጊዜ የዋጋ ግሽበት ሁኔታ አበረታችና የመርገብ አዝማሚያ ቢያሳይም፤ አሁንም ቢሆን የዋጋ ግሽበቱ ከፍተኛና በመካከለኛ ጊዜ ሊደረስበት ከታሰበው የነጠላ አሃዝ ግብ በላይ በመሆኑ አሁንም ጠበቅ ያለ የገንዘብ ፖሊሲ መጠቀም አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝቧል።
ይሄ እውን እንዲሆንም፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክም የዋጋ ግሽበቱን ትርጉም ባለው መልኩ ለመቀነስ በሙሉ ቁርጠኝነት እየሠራ እንደመሆኑም፤ በመሆኑም የዋጋ ግሽበቱ በቀጣይ ባሉት ወራቶች ቅናሽ እንዲያሳይ ጥንቃቄ የተሞላበት አካሄድ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን አጽንዖት ሰጥቶበታል። ለዚህም ጠንቃቃ የገንዘብ ፖሊሲ መከተልን አስፈላጊ ከሚያደርጉ ማክሮ ገጽታዎች መገንዘብ እንደሚገባም ጠቁሟል።
የዋጋ ግሽበትን ከመቆጣጠር ባለፈም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚታየው የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ጉዳይ ልዩ ትኩረት ሊሰጠውና ወደ ኢኮኖሚው የሚገባው የገንዘብ መጠን በገንዘብ ፖሊሲው ላይ ያልተፈለገ እና አሉታዊ ተጽእኖ እንዳያሳድር ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባም አስገንዝቧል።
በጥቅሉም፣ ከእነዚህ እና ተያያዥ ጉዳዮች ከተወሰደ ግምት በመነሳት፤ የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴው ካቀረባቸው የግምገማ የውሳኔ ሃሳቦች በመነሳት፤ ኮሚቴው ለቦርድ አቅርቦ የሚከተሉትን የገንዘብ ፖሊሲ ምክረ ሃሳቦች አስወስኗል። እነሱም፡-
- አሁንም ቢሆን ከፍ ብሎ የሚታየውን የዋጋ ግሽበት ለመቀነስና በውጭ ምንዛሪ ተመን ረገድ የሚታዩ ግምታዊ አስተሳሰቦችን (expectations) ለመቆጣጠር ሲባል የብሔራዊ ባንክ የፖሊሲ ተመን (National Bank Rate) አሁን ባለበት 15 በመቶ እንዲቆይ፤
- በወለድ ተመን ላይ ወደ ተመሠረተ የገንዘብ ፖሊሲ አስተዳደር ሥርዓት የሚደረገው ሽግግር ገና በመሆኑ፣ በባንኮች የብድር ዕድገት ላይ የተቀመጠው 18 በመቶ ገደብ እንዲቀጥል፤
- በአሁኑ ወቅት ብሔራዊ ባንክ ለሚሰጣቸው ቋሚ የተቀማጭ ሂሳብ አገልግሎት (standing deposit facility)፣ ለቋሚ የብድር አገልግሎት (standing lending facility) የሚከፈሉ የወለድ ተመኖች ባሉበት እንዲቀጥሉ፣ እንዲሁም ባንኮች በብሔራዊ ባንክ የሚያስቀምጡት የግዴታ መጠባበቂያ ተቀማጭ ሂሳብ በነበረበት እንዲቆይ፤ የሚሉት ናቸው።
ኮሚቴው በመግለጫው ማጠቃለያ እንዳመ ለከተውም፤ የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴው ቀጣይ የገንዘብ ፖሊሲ ውሳኔዎች በቀጣይ ወራት በሚከሰቱ የዋጋ ግሽበት ውጤቶች ግምገማ ላይ የተመሠረቱ እንደሚሆኑ ግንዛቤ መወሰዱን በመጠቆም፤ ቀጣዩ የኮሚቴው ስብሰባ ሰኔ 2017 መጨረሻ ላይ እንዲሆን መወሰኑን አመላክቷል። በመሆኑም የኮሚቴው ግምገማ ውጤቶች እና ምክረ ሃሳቦች፤ እንዲሁም የቦርዱ ውሳኔዎች ለውጤት እንዲበቁ የሁሉም ባለድርሻ ሚና ወሳኝ መሆኑን በመገንዘብ፤ በዚሁ አግባብ ኃላፊነትን መወጣት የግድ ይሆናል።
ማሙሻ ከአቡርሻ
አዲስ ዘመን ዓርብ መጋቢት 19 ቀን 2017 ዓ.ም