ዘለንስኪ ሩሲያ ላስቀመጠችው ቅድመ ሁኔታ ከአሜሪካ ጠንካራ ምላሽ እንደሚጠብቁ ገለጹ

የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ሩሲያ በጥቁር ባሕር ላይ የተደረሰውን የተኩስ አቁም ስምምነት ለማክበር የተጣለብኝ ማዕቀብ ይነሳልኝ ስትል እንደቅድመ ሁኔታ ያስቀመጠችውን አቋም በመቃወም አሜሪካ በነዚህ ፍላጎቶች ፊት ጠንካራ ሆና ትቆማለች የሚል ተስፋ እንዳላቸው ተናገሩ።

ሞስኮ የንግድ መርከቦች ደህንነቱ የተጠበቀ እንቅስቃሴን እንዲያደርጉ ለመፍቀድ ማክሰኞ እለት የተደረሰው የባሕር ላይ ስምምነት ተግባራዊ የሚሆነው የምዕራቡ ዓለም በሩሲያ የምግብ እና የማዳበሪያ ንግድ ላይ የጣለው እገዳ ከተነሳ ብቻ እንደሚሆን ገልጻለች።

ቢቢሲ አሜሪካ የሩሲያን ጫና ትቃወም እንደሆነ ላቀረበው ጥያቄ ፕሬዚዳንቱ ሲመልሱ ‹‹ተስፋዬ እንደዚህ ነው፣ ፈጣሪ ይባርካቸው ግን እናያለን›› ብለዋል። ዋይት ሃውስ ባለፈው ማክሰኞ እንዳስታወቀው የሩሲያ እና የዩክሬን ልዑካን በሳውዲ አረቢያ ከአሜሪካ ባለሥልጣናት ጋር ለሶስት ቀናት የተናጠል ውይይት ካደረጉ በኋላ በጥቁር ባሕር ላይ የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ መስማማታቸው ሲታወቅ ከሰዓታት በኋላ ግን ሞስኮ የቅድመ ሁኔታ ዝርዝር የያዘ መግለጫ ማውጣቷ ተሰምቷል።

ከቀረቡት ቅድመ ሁኔታዎች መካከል በግብርና ንግድ ላይ በተሰማሩ የፋይናንስ ተቋማት ላይ ምዕራባውያን ያስቀመጧቸው ማዕቀቦች እንዲሰረዙ እና የስዊፍት ዓለም አቀፍ የክፍያ ሥርዓት ዳግም ተመልሶ መጠቀም መቻል የሚሉት ይጠቀሳሉ። ትራምፕ መንግሥታቸው መስኮ ላይ የተጣሉ ማዕቀቦች እንዲነሱ ያቀረበችውን ጥያቄ ‹‹እየተመለከትነው ነው›› ቢሉም የአውሮፓ ህብረት ግን ረቡዕ እለት የሩሲያ ወታደሮች ከዩክሬን ግዛት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ካልወጡ በስተቀር ማዕቀቡን እንደማያነሱ መናገራቸው ተሰምቷል።

ዘለንስኪ በፓሪስ ለተሰበሰቡ ጋዜጠኞች ሲናገሩ ‹‹አሜሪካ ለምታደርገው የሁለትዮሽ ድጋፍ በጣም አመሰግናለው›› ማለታቸው ሲገለጽ ‹‹ነገር ግን አንዳንዶች በሩሲያ ትርክት ተጽዕኖ ስር ናቸው›› ብለው እንደሚሰጉ አልሸሸጉም። ‹‹በነዚህ ትርክቶች መስማማት አንችልም›› ሲሉም አክለዋል።

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከእርሳቸው ወይም ከሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንደነበራቸው ለቀረበላቸው ጥያቄ ዘለንስኪ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ነው የተናገሩት። ‹‹አላውቅም፣ እንዲህ ነው ብዬ መናገር አልችልም፤ ምን አይነት ግንኙነት እንዳላቸው አላውቅም፤ ምን ያህል ጊዜ እንደተወያዩ የማውቀው የለም›› ሲሉ ተደምጠዋል።

የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ባለፈው ሳምንት የትራምፕ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ በአንድ ቃለ ምልልስ ላይ አውሮፓ ዩክሬንን ለመደገፍ የፍቃደኞች ጥምረት ለመመሥረት የምታደርገውን ጥረት ስለማጣጣላቸው ያላቸውን አስተያየት ተጠይቀው ሲመልሱ ‹‹በችኮላ ድምዳሜ ላይ እንደማይደርሱ ተናግረው ዊትኮፍ ያላቸው ልምድ በመኖሪያ ቤቶች ልማት ላይ መሆኑን በመጥቀስ ልምድ አልነበራቸውም ሲሉ ተናግረዋል።

‹‹እኔ እስከማውቀው ድረስ ሪል እስቴት እንዴት እንደሚገዛና እንደሚሸጥ ጠንቅቆ ያውቃል ነገር ግን ይህ በተወሰነ መልኩ የተለየ ነው። አውሮፓ በጦርነቱ ወቅት ራሷን በተሻለ ሁኔታ አጠናክራለች›› ብለዋል። ቢቢሲ ዘለንስኪ በታሪክ ውስጥ እንዴት መታወስ እንደሚፈልጉ ጠይቋቸው ‹‹የታሪክ መጽሀፍ ስለእኔ ምን እንደሚጽፍ አላውቅም። ያ ዓላማዬ ወይም ግቤ አይደለም›› ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

ዘለንስኪ አክለውም ‹‹ዓላማዬ ዩክሬንን መከላከል እና ልጆቻችን ሳይደበቁ በዩክሬን ጎዳናዎች ላይ ሲሄዱ ማየት ነው። ዩክሬንን በተቻለኝ መጠን ለመከላከል እስከዘመኔ መጨረሻ ድረስ የምችለውን ሁሉ አደርጋለሂ›› በማለት ተናግረዋል። ዩክሬን ኔቶን እንድትቀላቀል ይፈቀድላት ወይም አይፈቀድላት በሚለው ጉዳይ ላይ የተጠየቁት ዘለንስኪ ሲመልሱ ‹‹የትራምፕ አስተዳደር የኪዬቭ አባልነትን እንደማይቀበለው ቢያስታውቅም በግል የጠነከረው ሕዝባችን ጥምረቱን ይፈጥረዋል›› ሲሉ ተደምጠዋል። መረጃውን ከቢቢሲ አግኝተናል።

ዘላለም ተሾመ

አዲስ ዘመን ዓርብ መጋቢት 19 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You