
የፋይዳ መታወቂያ በዓለማችን ለአገልግሎት ከበቃ ወደ ሁለት አስርት ዓመታት አለፉት። በሀገራችን አገልግሎት ላይ ከዋለ ስድስት ዓመታት ተቆጥረዋል። በዚህ ጽሁፍ ገሚሱን የፋይዳ መታወቂያ ገሚሱን የዲጂታል መታወቂያ ያልኩት ፋይዳ መታወቂያው ፋይዳውም ብዙ ስሙም ብዙ መሆኑን ለማመልከት ነው።
ዲጂታል መታወቂያ ሥር የያዘውና ያቆጠቆጠው በ እኤአ በ2000 በኢስቶንያ እና በሲንጋፖር ነበር። ነገር ግን በሀገራቱ በይፋ ዕውቅና ተሰጥቶት የተጀመረውም ከአስር ዓመት በኋላ ነው። ማለትም የዲጂታል መታወቂያ በ2014 በመጀመር ኢስቶንያ ቀዳሚ ነች። በኢስቶንያ በማንኛው ቦታ የሚኖር ማንኛውም ሰው በዲጂታል መታወቂያ ክፍያ ይፈጽሙበታል፣ ድምጽ ይሰጡበታል፣ ግዥም ያከናውኑበታል። በዚህም 99 በመቶ ኢስቶንያውያን የዲጂታል መታወቂያ አላቸው።
በአጠቃላይ ከ “beyondencryption.com ” ድረገጽ የወጣ መረጃ እንደሚያሳየው ፤ በኢስቶንያ ዜጎች ከ600 በላይ አገልግሎቶችን 2ሺህ 400 የንግድ ተቋማትም በዚሁ ፋይዳ መታወቂያ ይፈየዳሉ። ከአፍሪካ ደግሞ የዲጂታል መታወቂያ የተጀመረው በ2014 በናይጄሪያ ነው።
በአሁኑ ወቅት ከ90 በላይ ሀገሮች የዲጂታል መታወቂያ አገልግሎት እየተጠቀሙ ሲሆን እስካለፈው የፈረንጆቹ ዓመት መጨረሻ በዓለም 5 ቢሊዮን ሰዎች ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው የአፍሪካና የእስያ ሀገሮችን የዚሁ ፋይዳ መታወቂያ ተጠቃሚዎች እንደሆኑ “Digital Watch Observatory” ያወጣው መረጃ ያሳያል።
በኢትዮጵያ ፋይዳ መታወቂያ ከተጀመረ ስድስት ዓመት ሆኖታል። ፋይዳ መታወቂያው በሙከራ ደረጃ ሲተገበር ቆይቶ መጋቢት 21 ቀን 2015 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የወጣውን አዋጅን ተከትሎ በይፋ ተግባራዊ መሆን ጀምሯል።
ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያን ከሌሎች መታወቂያዎች የሚለየው አንድ ወጥ መሆኑና ከአንድ አካባቢ ከሌላ አካባቢ ካለ የነዋሪነት መታወቂያ ጋር በቀለም በመሳሰሉት ልዩነት የሌለው መሆኑ ነው። ሰዎች የቀበሌ ነዋሪነት፣ የትምህርት ቤት፣ የመሥሪያ ቤት መታወቂያ ይኖራቸዋል። በዘመናችን ብዙዎቹ መታወቂያዎች ቀድሞ ስንገለገልበት ከነበረው ከወረቀት መታወቂያ ጋር አጋርነት የነበራቸውን ‹የዲፕሎማቲክ ግንኙነት› እያቋረጡ ነው።
ከኢትዮ ቴሌኮም ድረገጽ የተገኘ መረጃ እንደሚያሳየው ፤ የዲጂታል መታወቂያ የነዋሪዎችን የባዮሜትሪክ (የጣት ዐሻራ፣ የዓይን ዐሻራ እና የፊት ምስል) እንዲሁም የግል መረጃዎችን በመሰብሰብ አንድን ግለሰብ ልዩ በሆነ መልኩ እንዲታወቅ የሚያስችል ነው። ኢትዮ ቴሌኮም መሪ የዲጂታል መፍትሄ (ሶሉሽን) አቅራቢ ድርጅት በመሆኑ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያን ራዕይ በአጋርነት ለማሳካት እና ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን የማድረግ ራዕይ ለማፋጠን በዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ፣ በመታወቂያ ህትመትና ስርጭት፤ ማንነትን በማረጋገጥ (Authentication) ሥራዎች ላይ በትኩረት እየሠራ ይገኛል።
ኢትዮጵያዊ እና ኢትዮጵያዊ ያልሆኑ የነዋሪነት ማረጋገጫ ያላቸው ፣ የመኖሪያ አድራሻ ማረጋገጫ ሰነድ ያላቸውም ሆነ የሌላቸው፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ነዋሪነታቸው “በአዋጁ መሠረት” የተሰጠ የት እንደሚኖሩ ምንም ዓይነት ሰነድ የሌላቸው ሰዎች የዲጂታል መታወቂያ ያለው ሰው እንደ ምስክር ይዞ በመቅረብ መመዝገብ እንደሚችሉ መረጃው ያሳያል።
በኢትዮጵያ የዲጂታል መታወቂያ ከፓስፖርትና ከቀበሌ ነዋሪነት መታወቂያ ጋር እኩል ተቀባይነት አለው። ከቀበሌ መታወቂያ የሚለየው ከሰውየው ማንነት በተጨማሪ ባዮሜትሪክ የታከለበት የመረጃ ቋት መሆኑ ነው። የቀበሌ ነዋሪነት መታወቂያ ለማግኘት የቤት ባለቤት ወይም በሚኖርበት ቤት ቋሚ ተከታይ መሆን አለበት። ካለበለዚያ ያለው አማራጭ ወደ ትውልድ አካባቢው ሄዶ የነዋሪነት መታወቂያውን ይዞ መምጣት ነው። በፋይዳ መታወቂያ ግን ይህ ግድ አይደለም። ስለዚህ የቀበሌ መታወቂያ የሌለው ግለሰብ የፋይዳ መታወቂያ ሲያገኝ ‘ሀገሬ መታወቂያ ከልክላ አገለለችኝ ‘ ከሚል ብሶት ይላቀቃል ።
ፋይዳ መታወቂያ ተጠያቂነትን ለማስፈን፣ የማጭበርበር ድርጊቶችን ለመቀነስ እና ግልጽነትን ለማስፈን ሁነኛ ፋይዳ እንዳለው ከኢትዮጵያ ዲጂታል መታወቂያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት የወጣ መረጃ ያሳያል። አሁን አሁን ብዙዎቹ መታወቂያዎች የፕላስቲክ ቁመና እና ወዘና ያላቸው ፈጣን ክፍያ ማሽን እንደምንለው የገንዘብ ማውጫ ካርድ ዓይነት እየሆኑ ነው ። የወረቀት መታወቂያ ካርዶች የአገልግሎት ዘመናቸው ብዙውን ጊዜ አጭር ነው። ቶሎ የመቀደድ ውሃ ላይ ቢወድቁ ወይም በአጋጣሚ በዝናብ ሊበሰብሱ ቢችሉ መታወቂያው የአገልግሎት ዘመኑ ይገታል።
አንዳንዴ ደግሞ መታወቂያ ላይ ያሉ ዋነኛ ማስረጃዎቹ ላይነበቡ ይችላሉ፤ ስሙ፣ አድራሻው የመሳሰሉት ፊደላቱ ሊደበዝዙ ፎቶውም ሊወይብ የሚችልበት ዕድሉ ሠፊ ነው። እዚህ ላይ ግን የዲጂታል ካርዶቹ መታወቂያ እንደዛ ዓይነት ችግሮች እንዳሉባቸው ከእራሴ መታወቂያ አገልግሎት መገንዘብ ችያለሁ። እጅ በጣም ሲበዛባቸው ሲተሻሹ መታወቂያው የሚመስሉ እንጂ የሰውየው ማንነት የማያሳዩ ይሆናሉ። ፎቶው ጠፍቶ ፊደሎቹም ወይበው በደንብ አይታዩም። የሚሻለው መታወቂያዎቹን በአንድ ቦርሳ በአግባቡ መያዝ ነው።
የፋይዳ መታወቂያ ሲጀመር ባንኮች ሁነኛ ሚና ነበራቸው። ከዚሁ ጎን ለጎን የኢትዮ ቴሌኮምና ፖስታ ቤትም ሰዎች የፋይዳ መታወቂያ አግኝተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ በትጋት እየሠሩ ይገኛሉ።
የዲጂታል መታወቂያ በኢትዮጵያ ያለ ማንኛውም ሰው ሊወስድ የሚችልበት ነው። ዜጎች የዲጂታል መታወቂያ እንዲወስዱ አዋጁ አያስገድድም። ነገር ግን አንዳንድ ድርጅቶች ሰዎች ለመገልገል ሲሄዱ የፋይዳ መታወቂያ ሊያስገድዱ ይችላሉ። ባንኮች ፣ ኢንሹራንስ ተቋማት፣ ፖሊስ፤ ለምሳሌ ብሔራዊ ባንክ ከያዝነው ዓመት ታህሳስ ወር ጀምሮ ሰዎች ከባንኮች የባንክ ደብተር ሲያወጡ የዲጂታል መታወቂያ እንደ ግዳጅ እንዲጠየቁ መመሪያ አውጥቷል።
ከኢትዮ ቴሌኮም የወጣ መረጃ እንደሚያሳየው ፋይዳ መታወቂያ ለግለሰቦችና ለነጋዴዎች፣ ለዜጎች ችግሮች በቋሚነት በመቅረፍ ያገለግላል። ማንነታቸውን በሕጋዊ መንገድ ያላረጋገጡ ግለሰቦች መሠረታዊ የዜግነት መብቶቻቸውን አለማግኘት፣ የዜጎችን ፍላጎት ያላገናዘበ አገልግሎት አሰጣጥ የተገልጋዮች ግላዊ መረጃዎች በአግባቡ ስለመያዙ ዜጎች ለዝርፍያና ለሌሎች አደጋዎች ተጋላጭ መሆን፣ ማንነትን ለማረጋገጥ ሰነዶችን ማገላበጥ የሚጠይቅ በመሆኑ የተጓተተ የአገልግሎት አሰጣጥ በመቅረፍ ያገለግላል።
ለነጋዴዎችም በሚገለገሉባቸው ተቋማት በተንዛዛ ሂደት ቅልጥፍና የጎደለው አገልግሎት አሰጣጥን ለመቅረፍ፣ በያዙት ፋይዳ መታወቂያ ነፃ ሆነው አገልግሎት ለማግኘት፣ አገልግሎት ተጠቃሚዎችም የተሳሳተ የማንነት መረጃ ይዘው ሲመጡ ለማጣራት እንዳይቸገሩ እና በዚህም ምክንያት የተቋማት መጭበርበር ለመቅነስና ያስችላል።
ለፖሊስ ደግሞ በወንጀል የተጠረጠረን ግለሰብ ቢይዙና ፋይዳ መታወቂያ ተጠቃሚ ግለሰብ ከሆነ በቀላሉ ማንነቱን የሚለዩበት ስለሰውየው ማንነት መረጃ ለማሰባሰብ የሚፈጅባቸውን ሰዓት የሚያባክኑትን ጉልበት ይቀንስላቸዋል። የጠቀስናቸው ነገሮች ፋይዳ መታወቂያ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ እንዳለው ያሳያሉ። እኛም ከፋይዳ መታወቂያ ጋር ወደፊት እንላለን።
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ዓርብ መጋቢት 19 ቀን 2017 ዓ.ም