
አዲስ አበባ ፡- በትምህርት ሚኒስቴር አዘጋጅነት ለኦሮሚያ ክልል አንደኛ ደረጃ እና ሁለተኛ ደረጃ መምህራን የተሠጠው የአቅም ግንባታ ሥልጠና የመምህራን አቅም ከማሳደግ አኳያ ውጤት ማምጣቱን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ፡፡
የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ቶላ በሪሶ (ዶ/ር) ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ በትምህርት ሥርዓት አተገባበር በተለይም በሥነ-ልቦና እና ማህበራዊ ድጋፍ፣ በሥራና ተግባር ተኮር ትምህርት እንዲሁም በአፍ መፍቻ ቋንቋ ትምህርት ማስተማር ሥነ ዘዴ ላይ የመምህራንን ብቃታቸውን መለየትና ትኩረት ተደርጎ መሠራት ይኖርበታል፤ ይህን ከሚያረጋግጡ መንዶች አንዱ ምዘና መስጠት ሲሆን፤ ቀደም ሲል በክልሉ በተደረገ ምዘና የሁለተኛ ደረጃ መምህራን ውጤት በጣም ዝቅ ያለ አፈጻጸም እንዳለው ታይቷል፤ የአንደኛ ደረጃ መምህራን ውጤትም ከ50 በመቶ በታች ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በክልሉ ያለው የመምህራን የፈተና ውጤት አስደጋጭ እንደነበር የገለጹት ቶላ (ዶ/ር)፤ ከተፈተኑት የአንደኛ ደረጃ መምህራን 41 በመቶ ብቻ ያለፉ ሲሆን፤ የሁለተኛ ደረጃ መምህራን ውጤት ከተፈተኑት ውስጥ ማለፍ የቻሉት 27 በመቶ ብቻ እንደነበር አውስተዋል፡፡
ከተሰጠው የአቅም ግንባታ ሥልጠና በኋላ የአንደኛ ደረጃ የፈተና ውጤት ከ41 ወደ 56 በመቶ ከፍ ያለ ሲሆን፤ የሁለተኛ ደረጃ መምህራን ውጤትም እንዲሁ ከ27 ወደ 42 በመቶ አድጓል ብለዋል፡፡ የትምህርት ሚኒስቴር ለሥልጠናው ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ ቢሆንም ክልሎች ካልደገፉት ሁሉንም መምህራን ማብቃት አይቻልም ነው ያሉት ፡፡
የኦሮሚያ ክልልም ቀድሞ በመተግበር ውጤት እንዳገኘ ገልጸው፤ የመምህራን የፈተና ውጤት መሻሻል ላይ አሁንም የበለጠ ትኩረት አድርጎ የሚሠራ ይሆናል ብለዋል፡፡
በሀገር አቀፍ ደረጃ የመምህራን ብቃት በወሰዱት ምዘና አማካኝነት ጥያቄ ውስጥ እንደገባ የትምህርት ሚኒስቴር መረጃ ማመላከቱን ገልጸው፤ በኦሮሚያ ክልልም ይህ ሁኔታ እንዳለና ችግሩን እልባት ለመስጠት በተሠሩ ሥራዎች የመምህራን የፈተና ውጤት በሁለቱም የክፍል ደረጃዎች መሻሻል እንዳሳየ ቶላ (ዶ/ር)፤ ተናግረዋል፡፡
ክልሉ የመማር ማስተማር ሁኔታውን ይገድባሉ ያላቸውን ዋና ዋና ተግባራት ለይቶ እየሠራባቸው እንደሆነ ገልጸው፤ ከእነዚህ ተግባራትም ውስጥ መምህራን በሚያስተምሩት ትምህርት ያላቸው ዝግጅት፤ በሥነ ማስተማር ያላቸው ብቃት ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛልና ክልሉ መምህራን የትምህርት አቅማቸውን ገንብተው የተሻለ መምህር እንዲሆኑ ማስቻል ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ ስለመሆኑ አስረድተዋል፡፡
በክልሉ መምህራን ራሳቸውን ለፈተና ዝግጁ አድርገው ያሉበትን ደረጃ እንዲያውቁ በስፋት እየተሠራ እንደሆነ ጠቅሰው፤ በዚሁ መሠረት መምህራን ራሳቸውን ወደ ፈተና እያስገቡ እንደሆነና ያሉበትን የትምህርት ብቃት እያሻሻሉ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
ውጤታቸው ምንም እንኳን አሳሳቢ ቢሆንም በሥልጠና እየተደገፉ መሻሻሎችን ማምጣታቸውን አመላክተው፤ የአቅም ውስንነት በነበሩባቸው አካባቢዎች ለሚያስተምሩ መምህራንና የትምህርት ቤት አመራሮች እየተሰጠ ያለው ሥልጠና መምህራን ተግዳሮቶችን ተቋቁመው ማስተማርና ሥራቸውን በአግባቡ መምራት እንዲችሉ ያግዛቸዋልም ብለዋል፡፡
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ዓርብ መጋቢት 19 ቀን 2017 ዓ.ም