
አዲስ አበባ፡- በባህር ዳር ከተማ የተሠራው የኮሪዶር ልማት የከተማዋን የቱሪስት ተመራጭነት የበለጠ የሚያሳድግ እንደሆነ የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ጋሻው እንዳለው አስታወቁ፡፡
አቶ ጋሻው ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፤ ባህር ዳር ከተማ በጣና ሀይቅ እና በዓባይ ወንዝ ዳርቻ የምትገኝ ፤ በዙሪያ ገባዋ ገዳማትና ታሪካዊ ቦታዎችን የያዘች በመሆኗ ወትሮም የቱሪስትን ቀልብ የምትስብ ከተማ ነች፡፡ አሁን ላይ እየተሠራ ያለው የኮሪዶር ልማት ደግሞ ለከተማዋ የቱሪስት ተመራጭነት ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር ነው ብለዋል፡፡
ቱሪስቶች ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀሱት አዳዲስ ነገሮችን ለመመልክትና ለመዝናናት እንደሆነ የገለጹት አቶ ጋሻው፤ በሚጓዙባቸው ቦታዎች ሁሉ ለየት ያለ ነገርን ማየትና አገልግሎት ማግኘትን ይፈልጋሉ ብለዋል።፡
በባህር ዳርና አካባቢዋ 99 የሚደርሱ የእምነት ቱሪዝም መዳረሻዎች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ እነዚህን ቦታዎች ሊመለከቱ የሚመጡ የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎች በከተማዋ በሚኖራቸው ቆይታ የከተማዋ ጽዱና ምቹ መሆን ደስተኛ ሆነው እንዲሄዱ ያደርጋቸዋል ነው ያሉት፡፡
ከዓባይ ድልድይ አንስቶ እስከ መሃል ከተማው ተገንብቶ በመገባደድ ላይ ያለው የኮሪዶር ልማት ከአሁኑ ለከተማዋ ልዩ ውበትን እንዳጎናጸፋት ገልጸዋል።
የጣና ሀይቅና የዓባይ ወንዝ ለባህር ዳር ከተማ የውበት ምንጮቿ እንደሆኑ የገለጹት አቶ ጋሻው፤ የኮሪዶር ልማቱም ከእነዚህ የውሃ አካላት ጋር ተያይዞ የተሠራ መሆኑ ከተማዋ በተሰጧት የተፈጥሮ ጸጋዎች የበለጠ እንድትደምቅ አድርጓታል ብለዋል፡፡
የጣና ሀይቅ በአራትና አምስት አቅጣጫዎች ከኮሪደር ልማቱ ጋር ተሳስሮ እንዲለማ መደረጉ፤ ከዋናው አስፋልት ግራና ቀኝ ያሉ መንገዶች እንዲሰፉ መደረጋቸው፣ የእግረኛ እና የብስክሌት መንገዶች መለየታቸው፤ አዲሱ የዓባይ ደልድይም ከኮሪዶር ልማቱ ጋር ትስስር መፍጠሩ የከተማዋ ውበት እንዲጨምር ያደረጉ አዳዲስ ክስተቶች ስለመሆናቸው አንስተዋል፡፡
የኮሪዶር ልማቱን ተከትለው እጅግ በጣም ማራኪ የመዝናኛ ሥፍራዎች እየተሠሩ መሆኑንና ቀደም ሲል በነበሩት ላይ ሌሎች ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች፣ ሎጆችና ሪዞርቶች ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን ጠብቀው እየተገነቡ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
እነዚህም የከተማዋን ገጽታ እየቀየሩ ከመሆናቸውም ባሻገር ለቱሪስቶች ምቹ ሁኔታ የሚፈጥሩና ቱሪስቶች ቆይታቸውን እንዲያራዝሙ የሚያደርጉ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡
የኮሪዶር ልማቱ በአሁኑ ጊዜ በሥራ እድል ፈጠራ እና በኢኮኖሚ ዝውውሩ ላይ እያበረከተ ካለው አስተዋጽኦ በተጨማሪ በቱሪስቶች እንቅስቃሴ ወቅትም በቱሪዝም ሰንሰለቱ ውስጥ የሚገኙ በርካታ ሰዎችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እያደረገ የሚቀጥል ስለመሆኑ አስረድተዋል፡፡
የከተማዋ የቱሪስት ፍሰት እያደገ መምጣቱን የተናገሩት አቶ ጋሻው፤ የኮሪደር ልማቱ መሠራት ደግሞ ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው ሌላ አቅም እየፈጠረ የሚሄድ ነው ብለዋል፡፡
ሰላም የቱሪስቶች ፓስፖርት እንደመሆኑ ጎብኚዎች ወደ ባህር ዳር ከመምጣታቸው በፊት ስለ አካባቢው ሰላም ማረጋገጥ ቀዳሚ ሥራቸው እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡ ባህር ዳር ከተማ አሁንም ለቱሪስቶች ስጋት የሚሆን ነገር ስለሌለባት ጎብኚዎች መጥተው እንዲጎበኙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ለቱሪዝም ዘርፉ መጎልበት ህብረተሰቡ የከተማዋንና የአካባቢውን ሰላም በማስፈን በኩል የራሱን ሚና እንዲጫወትም አቶ ጋሻው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ መጋቢት 23 ቀን 2017 ዓ.ም