
– አቶ መኩርያ መርሻዬ፤ የሃዋሳ ከተማ ከንቲባ
ሃዋሳ ፡- የሲዳማ ዘመን መለወጫ ፍቼ ጨምባላላ ለሀገራዊ ብቻ ሳይሆን ለአሁናዊ የዓለም ችግሮች መፍትሄ የሚሆን እሴትን የያዘ ነው ሲሉ የሃዋሳ ከተማ ከንቲባ ገለፁ።
የከተማዋ ከንቲባ አቶ መኩርያ መርሻዬ የሲዳማ የዘመን መለወጫ ፍቼ ጨምባላላ አብሮነትን ፣ ሰላምን እና አንድነትን ከትውልድ ወደ ትውልድ እያስተላለፈ የመጣ ነው ሲሉ ገልፀዋል ።
ይህ የሲዳማ ባህል በዓለም አቀፍ የማይዳሰሱ ቅርሶች ዩኔስኮ ከተመዘገበ 10ኛ ዓመቱን እንደያዘ አስታውሰው፤ ባህላዊ እሴቱ የኢትዮጵያውያን ከመሆን አልፎ የዓለምም ሀብት መሆን ችሏል ብለዋል፡፡ በዚህም ለሀገራዊ ብቻ ሳይሆን ለአሁናዊ የዓለም ችግሮች መፍትሄ የሚሆን እሴትን እንደያዘ ገልጸዋል፡፡
ባህላዊ እሴቱ በዩኔስኮ የተመዘገበበትን 10ኛ ዓመት አስመልክቶ በደማቅ ሁኔታ ለማክበር አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ገልፀው፤ በዚህም በዓሉ በሰላም ተከብሮ እንዲጠናቀቅ በፀጥታ ረገድ በቂ ዝግጅት ተደርጓል ነው ያሉት፡፡
የፍቼ ጨምባላላ ኩነትን ምክንያት በማድረግ የበዓሉን ይዘት አስመልክቶ ግንዛቤ ለመስጠት የተለያዩ ዝግጅቶችን በማድረግ ቅድመ ክብረ በዓሎች ሲደረጉ መቆየታቸውንም አስታውሰዋል፡፡
በሲዳማ ዘመን መለወጫ በዓል አስቀድሞ በዋዜማው ሁሉቃ ( መሽሎኪያ ) ተሠርቶ ሰዎች በዚያ ውስጥ እያለፉ ባለፈው ዘመን የሠሩት ሀጥያት ካለ ፈጣሪ እንዲምራቸው የሚማጸኑበት ሥርዓት ይከናወናል፡፡ በሁሉቃ ሥነ-ሥርዓትም አባወራ ቤተሰቡን፣ ከብቶቹን በዚያ ውስጥ ይዞ ያልፋል ። የተጣላና የተቀያየመ ካለም ‹‹አፊኒ›› ተባብሎ እውነት እንዲወጣ በማድረግ አዲሱን ዘመን በእርቅና በሰላም እንዲጀምር ይደረጋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የሃዋሳ ከተማ የሰላም ደሴት ነች ያሉት አቶ መኩርያ፤ በሲዳማ ባህልም አንድ ግጭት ሲነሳ ‹‹አፊኒ›› ተብሎ በተከሰተው ችግር ላይ በመምከር እውነት እንዲረጋገጥ ያደርጋል ብለዋል ። ይህ ባህላዊ ሥርዓት የከተማዋና የአካባቢው ሰላምና ደህንነት እንዲረጋገጥ አስተዋጽኦው ከፍተኛ ስለመሆኑም አመላክተዋል፡፡
አሁን ላይ ከተማዋ ሰላማዊ ሁኔታ ውስጥ ትገኛለች ያሉት ከንቲባው፤ ይህም በቱሪዝም ዘርፍ ተመራጭ እንድትሆን አስችሏታል ብለዋል፡፡ የከተማዋን ሰላምና ጸጥታ በማስጠበቅ ለልማትና ለቱሪዝም የበለጠ ተመራጭ እንድትሆን በትኩረት የሚሠራ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
ሰላም የሁሉም ነገር መሠረት እንደሆነ የጠቀሱት ከንቲባው፤ የተለየ ሃሳብ ያለው ሰው ካለም ችግሩን በጋራ ውይይት ይፈታል እንጂ እንደ ሀገር ወደፊት የሚደረገውን ጉዞ የሚገታ መሆን የለበትም ሲሉ ገልፀዋል።
በመጨረሻም አቶ መኩርያ ለሲዳማ ዘመን መለወጫ ጨምባላላ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክትን አስተላልፈዋል።
በተያያዘ ዜናም የሲዳማ ሕዝብ ፈጣሪ በዓልን ሲያከብር በአሮጌው ዓመት የተጣሉ ሰዎች በማስታረቅ፣ኀዘን ላይ ያለ ሰው ከነኀዘኑ ወደ አዲሱ ዓመት እንዳይገባ በማጽናናት እንዲሁም በአካባቢው የተነሱ ማንኛውም ችግሮችን ቀርፈው ወደ አዲሱ ዓመት ለመሸጋገር የተለያዩ ሥርዓቶችን በመከወን እንደሆነ ተገልጿል።
በፊጣራ በዓል በዋናንት ከሚከወኑ ሥርዓቶች ዋነኛው “ሁሉቃ” ሲሆን በዚህ ሥርዓት ሰዎች በክብ በተዘጋጀ እርጥብ ቅርንጫፍ ስር እንዲያልፉ ይደረጋል። የህም የሚደረገው ሕዝቡ ከአሮጌው ዓመት ወደ አዲስ ዓመት መሸጋገሩን ለማመልከት እንደሆነ ተጠቁሟል።
በፊጣራ ምሽት “ሻፌታ” የሚባል ባህላዊ ምግብ የሚበላ ሲሆን ከዛም ሽማግሌዎች አሮጌው ዓመት አልፎ ወደ አዲስ ዓመት መሸጋገራቸውን አስመልክተው ለፈጣሪያቸው ምስጋናና ምርቃት ያደርጋሉ።
የፊጣራ በዓል በሃዋሳ ከተማ ሲዳማ ባህል አዳራሽ ትናንት በርካታ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ፣ ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በተለያዩ ሁነቶች ተከብሯል።
ሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን ዓርብ መጋቢት 19 ቀን 2017 ዓ.ም