አፍሪካዊቷ የዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት

የስፖርቱ ዓለም አውራ የውድድር መድረክ የሆነውን ኦሊምፒክ የሚመራው ዓለም አቀፍ ተቋም አንድ ክፍለ ዘመን በተሻገረ ታሪኩ ሰሞኑን አዲስ ነገር አስተናግዷል። ዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪካዊት ሴት ፕሬዚዳንት ለመመራት አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል።

የቢሊዮኖች ትኩረት ማዕከል የሆነውና ቢሊዮን ዶላር በጀት የሚያንቀሳቅሰውን ተቋም ቁንጮ ሆኖ ለመምራት አፍሪካዊቷ እንስት ከተሰየሙ ቀናት ተቆጥረዋል።

ለ12 ዓመታት ኮሚቴውን በመሩት ጀርመናዊው ጎልማሳ ቶማስ ባኸ ምትክ 10ኛው የዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት በመሆን ክርስቲ ኮቭንትሪ የመጀመሪያዋ ሴት ከመሆናቸው ባለፈ፤ ከወደ ዚምቧቡዌ የተገኙ አፍሪካዊ ናቸው። የ41 ዓመቷ ጎልማሳ የትልቁን የስፖርት ተቋም የፕሬዚዳንትነት ቦታ በእጃቸው በማስገባት በርካታ ክብረወሰኖችን ለመጨበጥ በቅተዋል።

የቀድሞዋ የውሃ ዋና ስፖርተኛ በኦሊምፒክ የውድድር መድረክ ሜዳሊያዎችን ማሸነፍ የቻሉበት ታሪክ አላቸው። በአሠልጣኝነቱም አይታሙም። ይህም ዓለም አቀፉን ኦሊምፒክ ኮሚቴ በበላይነት ለመምራት ለቦታው የሚመጥን ክህሎት እንዲኖራቸው አድርጓል። በስፖርተኝነት ዘመናቸው እአአ በ2004 የአቴንስ ኦሊምፒክ የመጀመሪያ ተሳትፎ ያደረጉት ክርስቲ የወርቅ፣ የብርና ነሐስ ሜዳሊያዎችን ጠራርገው በመውሰድ ልዩ ታሪክ ሠርተዋል።

በቀጣዩ የቤጂንግ 2008 ኦሊምፒክም አንድ የወርቅና ሦስት የብር ሜዳሊያዎችን በማጥለቅ ትልቅ ስም አላቸው። በወቅቱም ዚምባቡዌያውያን ‹‹ብሔራዊ ሀብታችን›› ሲሉ አወድሰዋቸዋል። የሀገሪቱ ታሪካዊ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ በበኩላቸው የ100ሺ ዶላር ሽልማት ‹‹ወርቃማዋ ሴት›› ከሚል መጠሪያ ጋር አበርክተውላቸው ነበር። እአአ ከ2016 በኋላ ከዋና ስፖርት ተወዳዳሪነት ወጥተው ወደ ስፖርት አስተዳደር የገቡ ሲሆን፤ በዚምባቡዌ የወጣቶች፣ ስፖርትና ኪነጥበብ ሚኒስቴር ውስጥ አገልግለዋል። የዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አባል የሆነው የአትሌቶች ኮሚሽን ሊቀመንበር በመሆንም ወደ ትልቅ የኃላፊነት ምዕራፍ ተሸጋግረዋል። ይህም በዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ዕጩ ሆነው ለመቅረብ መደላድል ፈጥሮላቸዋል።

አዲሷ ፕሬዚዳንት ከሁለት ወር በኋላ የዓለም አቀፉን ግዙፍ የስፖርት ተቋም በትረ ሥልጣን ተረክበው በይፋ ወደ ሥራ የሚገቡ ሲሆን ለሚቀጥሉት 8 ዓመታት (ሁለት ኦሊምፒኮች) የሚመሩ ይሆናል። በ21ኛው ክፍለ ዘመን ከተነሳበት ዓላማና ከገነባው መልካም ትርክት ወጥቶ ፊቱን ወደ ፖለቲካ አዙሯል እየተባለ የሚወቀሰውን ኮሚቴ የመምራት ኃላፊነቱ ግን ቀላል እንደማይሆንላቸው ሲኤንኤን በዘገባው አትቷል። ከፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት እስከ የዘመኑ ፈተና እስከሆነው ፆታዊ ጉዳይ ምን ዓይነት ውሳኔዎችና ፖሊሲዎችን ሊከተሉ እንደሚችሉም የስፖርት ቤተሰቡ ትኩረት ሆኗል።

በተለይም ለውጥ ሊታይባቸው ይችላሉ በሚል ከሚጠበቁ ጉዳዮች መካከል አንዱ የሩሲያ ወደ ኦሊምፒክ መመለስ ሊሆን ይችላል። ስፖርታዊ ጥሰቶችን ፈጽማለች በሚል ሽፋን የምዕራባውያን ፖለቲካዊ ርምጃ ተወስዶባታል የምትባለው ሩሲያ ከየትኛውም ስፖርታዊ ውድድር ከተገለለች ዓመታት ተቆጥረዋል። በዚህም ዛሬም ድረስ አትሌቶቿ በግላቸው ኦሊምፒክ ላይ እንዲሳተፉ ቢደረግም እንደ ሀገር መወዳደር ግን አትችልም። በመሆኑም አዲሷ ፕሬዚዳንት በቀጣዩ ዓመት በሚደረገው የክረምት ኦሊምፒክ ሩሲያውያን እንዳሰቡት ወደ ውድድር እንዲመለሱ ታደርግ ይሆን ወይስ በፖለቲካዊው ጨዋታ ትቀጥላለች የሚለው ተጠባቂ ነው።

ቀጣዩ የ2028 ሎስአንጀለስ ኦሊምፒክ ዕጣ ፋንታም በምን መልክ ይቀጥል ይሆን የሚለው በአዲሷ ፕሬዚዳንት ጫንቃ ላይ የወደቀ የቤት ሥራ ነው ተብሏል። ይህም ሊገመቱ ከማይችሉት አዲሱ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶላንድ ትራምፕ ጋር የተያያዘ ሲሆን፤ ከቀድሞው የኮሚቴው ፕሬዚዳንት ቶማስ ባኸ ጋር የጀመሩትን ግንኙነት ይቀጥሉ አይቀጥሉ ማወቅ አይቻልም። ፕሬዚዳንቱ በትኩረት እየሠሩ ካሉበት የቪዛ አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ችግሮችን ሊፈጥሩና ከኦሊምፒክ ገለልተኛና ሁሉን አቀፍ ጽንሰ ሃሳብ ጋር የሚጋፋ ውሳኔ ላይ እንዳይደርሱ ያሰጋል። ስለዚህም አዲሲቷ ፕሬዚዳንት በዚህ ላይ የሚኖራቸው ቀጣይ አካሄድ በሥልጣን ዘመናቸው ላይ ፈተና ሊሆን ይችላል።

እስካሁን ውሉ ያለየውና በፓሪሱ ኦሊምፒክ መክፈቻ ወቅት የታየው ከፆታ ጋር የተያያዘ ጉዳይ በምን መንገድ ይቀጥላል የሚለው የፕሬዚዳንቷን ውሳኔ የሚጠይቅ ነው። በወቅቱ ዓለምን ለሁለት የከፈለው ጉዳይ እስከ ውድድር ተሳትፎ በሚኖረው ሂደት ወጥ አቋም መያዝ የኮሚቴውን ቅርጽ እስከወዲያኛው ሊቀይር አሊያም ሊገዳደር ይችላል።

ክርስቲ ኮቭንትሪ በፕሬዚዳንትነት መመረጣቸውን ተከትሎ ድምፅ ለሰጧቸው አካላት ‹‹አኮራችኋለሁ፤ በውሳኔያችሁም አስደስታችኋለሁ። ቀጣዩ የኦሊምፒክ እንቅስቃሴ ብሩህ ይሆናል›› እንዳሉት ቃላቸውን ይጠብቃሉ ብለው ብዙዎች ተስፋ አድርገዋል።

ብርሃን ፈይሳ

 

Recommended For You