‹‹በዓላቶቻችን ትናንትን ያኖሩን፤ ዛሬን ያስተሳሰሩንና ነገ ላይ የሚያደርሱን ባቡሮች ናቸው›› – ኑረዲን ቃሲም (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፡- ዒድ አልፈጥርንና መሰል በዓላቶቻችን ትናንትን ያኖሩን፤ ዛሬን ያስተሳሰሩንና ነገ ላይ የሚያደርሱን ባቡሮች ናቸው ሲሉ ዓለም አቀፍ የቁርዓን ዳኛ ኑረዲን ቃሲም (ዶ/ር) አስታወቁ።

ኑረዲን (ዶ/ር) በተለይም ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደተናሩት፤ ዒድ አልፈጥር በሙስሊሙ ማኅበረሰብ ዘንድ ትልቅ የበረከትና የደስታ በዓል ነው። የተቸገሩ ሳይቀሩ ተደስተው እንዲውሉ የሚደረግበት ልዩ ጊዜ ነው። በዚህም ሙስሊሙ ይህንን የእምነቱን አስተምሮ ተግባራዊ ሲያደርግ በዓሉን በተለያየ አግባብ እንዲመለከተውና ነገውን እንዲሠራ ያስችለዋል። በመረዳዳት ውስጥ፤ በአብሮነት ውስጥ ያለውን ታላቅነት እንዲረዳውም ያግዘዋል ብለዋል።

በዓላቶቻችን እምነታችንን በተግባር እንድንኖረው የሚያስችሉን ናቸውም የሚሉት ኑረዲን (ዶ/ር)፤ በዒድ ጊዜ የሚደረገው ሰዎችን የማገዝ ተግባር አንዱ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

በዓሉ አንድም ሰው ወደ ልመና እንዳይወጣ በማገዝ አብሮነታችንን ማሳየት እንደሚገባ አመልክተው፤ ኢትዮጵያውያን ለበዓላት ልዩ ትርጉም የሚሰጡበት ዋነኛ ምክንያት በበዓላቶቻችን ውስጥ ትናንትን ማሰብ፤ ዛሬን መተሳሰርና ነገን አሻግሮ ማየት ስላለ መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ ኑረዲን ቃሲም (ዶ/ር) ገለጻ፤ በዓላቶቻችን ትናንትን በፍቅርና በደስታ አቆይተው ዛሬን አሳይተውናል። ዛሬን አስተሳስረው ደግሞ ነጋችን መልካም እንደሚሆን ይነግሩናል። ሁሌ ቅንና ለሰዎች የምንጨነቅም እንድንሆን መልካም ሥነምግባርን ያላብሱናል። በእነርሱ ውስጥ አብሮነትና መተጋገዝ የጎላ በመሆኑም ባቡሮቻችን በመሆን ነጋችንን አሻግረን እንድናይ ያግዙናል።

ሁሉም ኢትዮጵያዊ በተለይም ደግሞ የበዓሉ ባለቤት የሆነው ሙስሊሙ ማኅበረሰብ ከዒድ አልፈጥር በዓል ባሻገር ያሉትን በረከቶች አይቶ ለመሥራትና ለመጠቀም መትጋት እንደሚገባው ተናግረዋል።

እንደ ዒድ አልፈጥር ያሉ ትልልቅ በዓላት ከበዓልነት ባሻገር ሌላም አስተምሮና ማንነትን የሚያላብሱ መሆናቸውን ጠቁመው፤ ዛሬያችን ላይ መሥራት፤ ነጋችንን ማብራት እንደሆነ አስገንዝበዋል።

ኑረዲን (ዶ/ር)፤ ይህ በዓል የሁሉም ሰው የደስታ ዕለት በመሆኑ ሕዝበ ሙስሊሙም ሃይማኖት ሳይገድበው ሁሉንም የደስታው ተካፋይ ማድረግ ላይ ሊረባረብ እንደሚገባ አመላክተዋል።

ኢትዮጵያውያን በሕዝብ ቁጥራችን የላቅን በመሆናችን በሀገር ወዳድነታችንም ልቀን መውጣት ይኖርብናል። ያለችን ሀገር አንድ በመሆኗ ለእርሷ መሥራት እንጂ በእርሷ ውስጥ ሆነን መተራመስ አይገባንም ያሉት ኑረዲን ቃሲም (ዶ/ር)፤ በእርሷ ውስጥ ሆነን እውነቷን፤ ታሪኳን ልንገልጥና ለዓለም የመቻቻል፤ የመተሳሰብና የአብሮነት ተምሳሌት መሆኗን ልናሳይ ይገባልም ብለዋል።

ሀገር በምንም ነገር አይለካም፤ መስፈሪያም ወሰንም አይገኝለትም። ስለሆነም ልጆቻችንን የምንወዳቸው ከሆነ ለዘላለም ደስተኛ የሚሆኑባትን ሀገር ሠርተን ልናስረክባቸው እንደሚገባ ገልጸው በሃይማኖት፤ በብሔርና በጥላቻ መንፈስ አንቅረጻቸው። እኛ መልካሟንና ነፃ የሆነችውን ሀገር እንደተረከብን ሁሉ በኢኮኖሚውም፤ በማኅበራዊውም ተፅዕኖ የምትፈጥረውን ሀገር ልንሰጣቸው ይገባል ሲሉም ገልጸዋል።

ጽጌረዳ ጫንያለው

አዲስ ዘመን  መጋቢት 21 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You