
አዲስ አበባ፡- የፌደራል መንግሥት ለትግራይ ክልል ያቀረባቸው 585 ትራክተሮች የአርሶ አደሮችን ዘመናዊ የግብርና ልማት ሥራዎች እንደሚያቀላጥፉ የትግራይ ክልል ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ገለፀ፡፡
የትግራይ ክልል የግብርናና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ የሆርቲካልቸር ዳይሬክተር አቶ ሀይለ ታደለ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ የግብርና ሚኒስቴር ቀደም ሲል 500 ትራክተሮችን ፤ ቀጥሎም 85 ትራክተሮች ለክልሉ ድጋፍ አድርጓል፡፡ እነዚህ ትራክተሮችም ለአርሶ አደሩ በብድር ተከፋፍለዋል፡፡
ትራክተሮቹ አርሶ አደሩ ዘመናዊ የግብርና ልማት ሥራውን እንዲያቀላጥፍ በከፍተኛ ሁኔታ እየረዱት እንዳሉ ጠቁመው፤ በተለይም በተፋሰስ ሥራዎች ላይ ላቅ ያለ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ስለመሆኑ እና እስከ አሁንም የተፋሰስ ሥራዎች ተጠናክረው እየተሠሩ መሆኑን አቶ ሃይለ ተናግረዋል፡፡
ፌደራል መንግሥት ዘመናዊ የእርሻ መሣሪያዎችን እና የአፈር ማዳበሪያን አርሶ አደሩ በወቅቱ እንዲያገኝ በማድረጉ የግብርና ሥራዎች እንዲሳለጡ ማድረጉን አመልክተው፤ ክልሉ ከነበረበት ከፍተኛ ችግር እንዲላቀቅ እንደዚህ ዓይነት ድጋፎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ቀደም ሲል በተከሰተው የሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ጦርነት ከፍተኛ ውድመት ደርሶ እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን ላይ ክልሉ ከፌዴራል መንግሥቱ በድጋፍ ያገኛቸው ትራክተሮች አርሶ አደሩ እርሻውን ከማዘመን አንፃር ትልቅ ሚና እንዳላቸውም ተናግረዋል፡፡
ክልሉ በቴክኖሎጂ ግብዓት ጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ ከትራክተርም በተጨማሪ በድሮን የታገዘ ዘመናዊ የኬሚካል መርጫ መሣሪያን ጨምሮ ሌሎች ግብዓቶችንም ጭምር በወቅቱ እያገኘ ነው ሲሉ ገልፀዋል፡፡
በቀጣይም ምርጥ ዘር እና የአፈር ማዳበሪያ በበቂ ሁኔታ የሚገባ ከሆነ አርሶ አደሩ ምርታማነትን እንዲያሳድግ እና ተጠቃሚ እንዲሆን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርግለታል ነው ያሉት፡፡
በተያዘው በጀት ዓመት አመርቂ ሥራ መሠራቱን ያመላከቱት ኃላፊው፤ ይህም የሆነበት ምክንያት በዋናነት ግብዓቶች በወቅቱ በመቅረባቸው እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡
እስከ አሁንም ከምርጥ ዘር ውጪ ሁሉም ግብዓቶች ለአርሶ አደሩ ተደራሽ እንደሆኑ አመላክተው፤ በቀጣይም ምርጥ ዘር በወቅቱ እንደሚደርስ ተስፋ አለን ብለዋል፡፡
በሁለተኛው ዙር በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት በዓመት ሶስት ጊዜ ምርት ለማምረት መታቀዱን ገልጸው፤ በሁሉም አካባቢዎች የሚመረቱ የአዝርእት ዓይነት እና እንደሰላጣ፣ ቆስጣ፣ ቲማቲም፣ ድንች እና ሌሎችም ፤ ግብዓቶት በምን መልኩ ማሰራጨት እንዳለባቸውና የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በመለየት ወደ ሥራ እየተገባ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ከ21 ሺህ በላይ ገበሬዎችን ያሳተፈ ዘጠኝ ሺህ ሄክታር መሬት በክላስተር ማልማት እንደተቻለ ጠቅሰው፤ ከዚሁ ጎን ለጎን የክረምት ሥራ ንቅናቄ በማስጀመር በቀጣይ አመርቂ ሥራ ለመሥራት መታቀዱን አስረድተዋል፡፡
በሁለተኛው የሆልቲካልቸር ሥራ ላይ ከፍራፍሬ ልማት እንዲሁም ከአረጓዴ ዐሻራ (ግሪን ሌጋሲ) ጋር ተያይዞ የኢኒሼቲቭ ሥራዎችን ለመሥራት እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውንም ጠቅሰዋል፡፡ የተሰጠውን የስልሳ አርባ መመሪያ ከክልሉ ዕቅድ ጋር በማጣጣም በተፈጥሮ ሀብትና በአትክልትና ፍራፍሬ (ሆርቲካልቸር) የተሠሩ እና የሚቀሩ ሥራዎችን በመገምገም መሥራት ያለብንን እየሠራን ነው ሲሉ አቶ ሃይለ ገልፀዋል፡፡
ሔርሞን ፍቃዱ
አዲስ ዘመን መጋቢት 18 ቀን 2017 ዓ.ም