የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ተስፋ እንጂ ስጋት ሊሆን አይገባም!

የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ምርት ዘርፍ ከአምራቾችና ከመንግሥታት ከፍተኛ ኢንቨስትመንትን በመሳብ በዓለም ፈጣን እድገት እያስመዘገቡ ካሉ ኢንዱስትሪዎች አንዱ ነው። ዓለም ነዳጅ ከሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎች እየተላቀቀ ወደ ኤሌክትሪክ እየተጓዘ ይመስላል። ኢትዮጵያም መንገዱን ጀምራለች።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎችን በተለይም በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ በብዛት ማየት እየተለመደ መጥቷል። ወደፊትም እነዚህ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ቁጥር እየጨመረ እንደሚሄድ ይጠበቃል። መንግሥትም የግሉ ዘርፍ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየናረ በመጣው ነዳጅ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች እየቀነሰ በኤሌክትሪክ የሚሠሩትን እንዲገዛ እያበረታታ ይገኛል።

ጠቅላይ ሚኒስር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በአንድ ወቅት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ “በብዙ መልኩ ለኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ቴክኖሎጂ ነው” ብለዋል። “ይህቺ ሀገር ኤሌክትሪክ የማምረት አቅም አላት። ከወዲሁ ይህንን መኪና (የኤሌክትሪክ) መገጣጠም እና ማምረት ከጀመርን የዛሬ አምስት እና አስር ዓመት የምንመኛትን፣ የበለጸገች ሀገር ለማየት የሚቻል መሆኑን ያመላክታል” ሲሉ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የትራንስፖርት ዘርፍ የ10 ዓመት ዕቅድ ውስጥ ታዳሽ ኃይል ቅድሚያ ተሰጥቶታል። በዚህ ዕቅድ በኤሌክትሪክ የሚሠሩ የሕዝብ ማመላለሻ እና አነስተኛ ተሽከርካሪዎች በብዙ ቁጥር ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ ታቅዷል። እየገቡም ይገኛሉ። በኢትዮጵያ የግሉ ዘርፍ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት የሚጣለው ግብር ዝቅ መደረጉ ይታወቃል።

ታዲያ የመንግሥት ፍላጎት እና የዓለም ጉዞ እንዲህ ከሆነ፣ በኢትዮጵያ ተሽከርካሪዎቹ ላይ ለምን ጥርጣሬ እና ጥያቄ በዛ? እውነታው ምንድን ነው? የሚለው ጉዳይ አሁንም ድረስ አነጋጋሪ ሆኖ ይገኛል። በዚህና በሌሎች ምክንያቶች የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን የሚገዙ ሰዎች ቁጥር እያደገ ቢመጣም በህብረተሰቡ ዘንድ የተለያዩ ውዥንብሮችን የሚፈጥሩ ሃሳቦችም መነሳታቸው አልቀረም።

ቢበላሹ የሚጠግናቸው ባለሙያ የለም፣ ባትሪያቸው ኪስ ያራቁታል፣ እድሜውም አጭር ነው፣ ቻርጅ ማድረግ ፈተና ነው፣ ወኪል የላቸውም፣ መለዋወጫቸውም ውድ ነው ይባላል። በተጨማሪም ይጓዙበታል የሚባሉትን ያህል ኪሎ ሜትር አይጓዙም፣ ለኢትዮጵያ አይሆኑም. . . ሌላም ሌላም ይባላል።

የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የአዋጭነት ጉዳይ ሲነሳ ብዙ ጉዳዮች ቢነሱም፣ ዋነኛው አከራካሪ ነገር የባትሪ እድሜና የመለዋወጫ እቃዎች ዋጋ መወደድ ነው። የተሽከርካሪዎቹ ባትሪ አምስትና ስድስት ዓመት ካገለገለ በኋላ(አንዳንዶች አስር ዓመትም ይላሉ) በአዲስ መቀየር ይኖርበታል። ይህም እስከ ግማሽ ሚሊዮን ብርና ከዚያም በላይ ወጪ ማድረግ ይጠይቃል የሚል ስጋት በብዙዎች ዘንድ አሳድሯል። የሌሎች የመለዋወጫ እቃዎች መወደድም ሌላኛው ጉዳይ ሲሆን የባትሪው ነገር ግን ገዝፎ የሚስተዋል ነጥብ ነው።

የባትሪ የአገልግሎት እድሜንና ዋጋን በተመለከተ እንደየተሽከርካሪዎቹ አይነት የሚለያይ ቢሆንም በውድ ዋጋ እንደሚገዛ ግን በብዙዎች የተስማሙበት እውነታ ነው። ይሁን እንጂ በነዳጅ ከሚሠሩት ተሽከርካሪዎች አንፃር በኤሌክትሪክ የሚሠሩት አዋጭ ናቸው የሚሉ ወገኖች ጥቂት አይደሉም። ይህንንም ባትሪ በሚቀየርበት ዓመት ለነዳጅ ከሚወጣው ገንዘብ አኳያ ያሰሉታል።

ለምሳሌ ያህል አንድ በነዳጅ የሚሠራ የቤት ወይም የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጥ ተሽከርካሪ አራት መቶ ኪሎ ሜትር ያህል መጓዝ የሚያስችለውን ነዳጅ ለመሙላት ሦስት ሺህና ከዚያ በላይ ብር ማውጣት ይጠበቅበታል። በተቃራኒው በኤሌክትሪክ የሚሠራ ተመሳሳይ ከንድ ተሽከርካሪ ግን ያን ያህል ርቀት መጓዝ የሚያስችለውን ኤሌክትሪክ ለመሙላት ከመቶ ብር ያልበለጠ ወጪ ብቻ እንደሚያደርግ ይጠቀሳል።

ይህንም በነዳጅ የሚሠራው ተሽከርካሪ በኤሌክትሪክ የሚሠራው ባትሪ መቀየር እስከሚያስፈልገው ዓመት ድረስ ከሚያወጣው ገንዘብ ጋር ሲነፃፀር የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪውን በብዙ እጥፍ የተሻለ ያደርገዋል የሚሉ ወገኖች ጥቂት አይደሉም። ያምሆኖ ይህን ሃሳብ በራሱ ሞጋች የሚያደርግ ነጥብ አለ።

ይህም የኤሌክትሪክ ዋጋ አሁን ላይ ትንሽ ቢመስልም የተጠቃሚው ቁጥር እየጨመረ ሲሄድ ዋጋውም መናሩ አይቀርም የሚሉ ብዙዎች ናቸው። ነገር ግን የኤሌክትሪክ ኃይል ዋጋ የቱንም ያህል እየጨመረ ቢሄድ በየጊዜው እየናረ ከመጣው የነዳጅ ዋጋ ጋር እንደማይደርስ ሌላ አከራካሪ ነጥብ ይነሳል።

እርግጥ ነው አሁን ባለው ሁኔታ የኤሌክትሪክ መኪኖች ከነዳጅ ወይም ከናፍታ መኪናዎች የበለጠ ውድ ናቸው፣ ይህም እንደ ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ውስጥ ለብዙ ሰዎች ሊገዙ የማይችሉ ያደርጋቸዋል። እንደ ኢትዮጵያ ነዳጅ ከውጪ ሀገራት በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር እያወጡ ለሚያስገቡ ሀገራት ግን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ከሚወራው ስጋት ይልቅ ተስፋቸው ሚዛን ይደፋል።

ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የመሠረተ ልማት አውታር አሁንም በበቂ ሁኔታ ያልተዘረጋ በመሆኑ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ባለንብረቶች ስጋት ቢገባቸው አይገርምም። የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ምርት ገና በእድገት ደረጃ ላይ እንደመገኘቱ ይህ ስጋት ምክንያታዊ ነው። ያም ሆኖ ኢንዱስትሪው በርካታ ፈተናዎች እንዳሉበት ሁሉ ብዙ እድሎች እንዳሉትም አርቆ ማሰብ ተገቢ ነው።

አፍሪካ በዓለም ላይ ፈጣን ዕድገት እያስመዘገቡ ካሉ ገበያዎች አንዷ ስትሆን ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ኢንዱስትሪው መስፋፋት ከፍተኛ እድሎችን ይፈጥራል። የአፍሪካ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ኢንዱስትሪ በመጪዎቹ ዓመታት ያድጋል ተብሎ ይጠበቃል። በ2030 በአፍሪካ የኤሌትሪክ ተሽከርካሪ ገበያ 100 ቢሊዮን ዶላር ሊደርስ እንደሚችል አንዳንድ ግምቶች ይጠቁማሉ። ኢትዮጵያም የዚህ እድል ተጋሪ ከሚሆኑ ሀገራት ቀዳሚዋ ነች።

የኤሌክትሪክ መኪና ብክለትን የሚቀንስ እና ኃይል የቆጣቢ መጓጓዣ ስለሆነ በጣም አስፈላጊ እንደሚሆን እሙን ነው። የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ለነዳጅ የሚወጣ ወጪን በመቀነስ እንዲሁም ከባቢ አየርን ለመጠበቅ ጠቃሚ መሆኑ አያከራክርም። እንደ ሀገር ለነዳጅ የሚወጣውን ወጪ ለመቀነስ እና የውጪ ምንዛሬን ለማዳንም እንዲሁ። ለዚህም ነው ብዙ የአፍሪካ መንግሥታት የፋይናንስ እና የቁጥጥር ማበረታቻዎችን በማቅረብ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ኢንዱስትሪን እየደገፉ የሚገኙት።

ይህንን ተስፋ የሚደግፉ በርካታ ምክንያቶች አሉ፣ ከእነዚህም መካከል፣ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ዋጋ መቀነስ፤ ቴክኖሎጂ እና ምርት እየዘመነ ሲሄድ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ዋጋ ይቀንሳል የሚል ተስፋ አንዱ ነው። ይህን ከግምት በማስገባት የኃይል መሙያ መሠረተ ልማቶችን ከወዲሁ ማሻሻልና መዘጋጀት ግድ ይላል።

የአፍሪካ መንግሥታት እና የግል ኩባንያዎች ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የኃይል መሙያ መሠረተ ልማት በማዘጋጀት ኢንቨስት እያደረጉ ነው። የኃይል መሙያ መሠረተ ልማትን ማዳበር፤ እንደ ፈጣን የኃይል መሙያ ጣቢያዎች ያሉ የኤሌክትሪክ መኪኖች የኃይል መሙያ መሠረተ ልማቶችን መንግሥትና የግል ኩባንያዎች በጋራ መሥራት ይጠበቅባቸዋል። በኢትዮጵያ መንግሥት ተስፋ የሚሰጥ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል። ግን በቂ አይደለም፣ የባለሀብቶችንም ሰፊ ተሳትፎ ይጠይቃል።

ከዚህ ጎን ለጎን የኤሌክትሪክ መኪና ተጠቃሚዎች እየጨመሩ በሄዱ ቁጥር የህብረተሰቡ ግንዛቤ እየጨመረ መሄዱ እንዳለ ሆኖ በተለያዩ አጋጣሚዎች የህብረተሰቡ ግንዛቤ ማሳደግ ያስፈልጋል። የህብረተሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ መንግሥታት እና የግል ኩባንያዎች ህብረተሰቡ ስለ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች እና ጥቅሞቻቸው ግንዛቤን ለማሳደግ በጋራ መሥራት አለባቸው።

በተጨማሪም የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ኢንዱስትሪ እድገትን ለማፋጠን በርካታ ርምጃዎችን መውሰድ ይቻላል። ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ አምራቾች የፋይናንስ ማበረታቻ መስጠት፣ መንግሥት ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እና የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ወጪ ለመቀነስ ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ አምራቾች የፋይናንስ ማበረታቻዎችን ለምሳሌ የታክስ እፎይታ መስጠትን የመሳሰሉ ርምጃዎችን ማሳደግ ይችላል።

ብሌን ከ6ኪሎ

አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 17 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You