የምግብ ዘይት ዋጋን ለማረጋጋት አምራች ኢንዱስትሪዎችን ማበረታታት ወሳኝ መፍትሄ ነው

አዲስ አበባ፡- የምግብ ዘይት ዋጋን በዘላቂነት ለማረጋጋት የሀገር ውስጥ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ማበረታታት ያስፈልጋል ሲል የኢትዮጵያ የምግብ ዘይት አምራቾች አንዱስትሪ ማህበር አስታወቀ።

የማህበሩ የቦርድ ሊቀመንበር አቶ መሃመድ የሱፍ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በየጊዜው እየጨመረ የሚሄደውን የምግብ ዘይት ዋጋ መቆጣጠር የሚቻለው የሀገር ውስጥ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ማበረታታት ሲቻል ነው። ከሰሞኑ በምግብ ዘይት ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪም አቅርቦቱ በገቢ ንግድ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ነው።

የምግብ ዘይት ከነጋዴ እጅ ወጥቶ ወደ ሀገር ውስጥ አምራቾች እንዲሸጋገር ማህበሩ ጥረት ሲያደርግ እንደቆየ አቶ መሃመድ ገልጸው፤ ማህበሩ የማምረት አቅምን በማሳደግ መሉ ለሙሉ የሀገር ውስጥ ፍጆታን በመሸፈን ምርቱን ወደ ውጭ ለማቅረብ አልሞ እየሠራ ቢሆንም ዛሬም ድረስ ወደኋላ ከሚጎትቱት ፈታኝ ሁኔታዎች አልተላቀቀም ብለዋል።

እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ ኢንዱስትሪው እንደታሰበው ውጤታማ እንዳይሆን ካደረጉ ምክንያቶች አንዱ የጥሬ እቃ አቅርቦት ነው። የቅባት እህሎች በበቂ ሁኔታ ያለመመረታቸውን እና ከሚመረተው ምርት የተወሰነው እሴት ሳይጨመርበት ለውጭ ገበያ የሚላክ መሆኑን እንደ ችግር ጠቅሰዋል።

ለአብነትም በጥሬ ምርት አቅርቦት ማነስ ምክንያት ከሰሞኑ በአንድ ኩንታል አኩሪ አተር ላይ የሶስት ሺህ ብር ጭማሪ መታየቱን ጠቅሰው፤ ምርቱ በስፋት ካለመመረቱም በላይ ያለው የጸጥታ ችግርም የተመረተውን ጥቂት ምርት ወደሚፈለገው ቦታ ለማድረስ አስቸጋሪ መሆኑን ተናግረዋል።

ነጋዴዎች ዋጋ ሊጨምር ይችላል በሚል በየመጋዘኑ ምርቱን ከዝነው ማስቀመጣቸውም ሌላው ተገማች ችግር እንደሆነ ጠቁመው፤ ጥሬ ሀብቱን በስፋት በማምረት በየጊዜው የሚከሰተውን የዋጋ ንረት መቆጣጠር አንዱ መፍትሄ እንደሆነም አስረድተዋል።

ከምግብ ዘይት ጋር ተያይዞ ባለቁ ገቢ ምርቶች ላይ የተጣለው የታክስ ሥርዓት በአምራች ኢንዱስትሪዎች ላይ ተጽዕኖ የሚፈጥር ሌላው ጉዳይ እንደሆነም ጠቅሰዋል።

የሀገር ውስጥ አምራቾች ከውጭ የሚያስገቧቸው ግብዓቶች ታክስ የሚጣልባቸው መሆኑና እና ያለቁ የምግብ ዘይት ምርቶችን ነጋዴዎች ከውጭ ሲያስገቡ ከቫት ውጭ ሌላ ዓይነት ታክስ የማይጣልበት መሆኑ የሀገር ውስጥ የምግብ ዘይት አምራች ኢንዱስትሪዎች ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ ማድረጉን ገልጸዋል።

አቶ መሃመድ፤ እንደ ዱቄትና ስኳርን በመሳሰሉ መሠረታዊ ፍጆታዎች ላይ ታክስ እየተጣለ ከውጭ በሚመጣ የምግብ ዘይት ላይ ታክስ አለመጣሉ አምራች ኢንዱስትሪዎች ከውድድር ውጭ እንዲሆኑ የሚያደርግ ነው ብለዋል።

የምግብ ዘይት ታክስ የማይደረገው መንግሥት ህብረተሰቡ እንዳይጎዳ በማሰብ መሆኑ ይታወቃል ያሉት ሊቀመንበሩ፤ ነገር ግን ምን ያህል ህብረተሰቡ እየተጠቀመ ነው? የሚለውም መፈተሽ አለበት ነው ያሉት። መንግሥት ገቢ የሚያጣበት፣ ህብረተሰቡ የማይጠቀምበት እና የሀገር ውስጥ አምራች ኢንዱስትሪዎችም ከውድድር ውጭ የሚሆኑበት ሁኔታ እንዳይፈጠር ጉዳዩን በጥልቀት መመልክትና የማስተካከያ ርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል ብለዋል።

በቅባት እህሎች እና በተረፈ ምርታቸው ላይ የሚጣለው ተጨማሪ እሴት ታክስም እንዲሁ በሀገር ውስጥ የማምረቱን ሁኔታ ፈታኝ ያደርገዋል። ጥሬ ምርቱን ከሚያመርተው አርሶ አደር ጀምሮ በፋብሪካ ውስጥ ተቀጥረው እስከ ሚሠሩ ዜጎች ድረስ ተጎጂ ያደርጋል ነው ያሉት።

የቅባት እህሎች ምርት ለሀገር ውስጥ ገበያ ሳይቀርብ እሴት ሳይጨመርበት ለውጭ ገበያ የሚላክበት ሁኔታ ስለመኖሩም አመልክተው፤ ይህ አሠራር ያለችውን ትንሽ ምርት የሚሻማ እንደሆነም ጠቅሰዋል።

የሀገር ውስጥ የምግብ ዘይት ኢንዱስትሪዎች ከ60 እስከ 70 እንደማይበልጡ ጠቅሰው፤ ምንም እንኳን አሁን ባለው ሁኔታ በጥናት ባይረጋገጥም የሀገር ውስጥ ፍጆታን የመሸፈን አቅማቸው ከአምስት እስከ አሥር በመቶ አይበልጥም ነው ያሉት። አሁን ላይ ባለባቸው ጫና ምክንያት አንዳንዶቹ ከሥራ ውጭ እየሆኑ ስለመምጣታቸውም ጠቁመዋል።

መንግሥት በዘላቂነት የምግብ ዘይት እጥረትን ለማስወገድና የዋጋ ንረትን ለማስቀረት የሀገር ውስጥ የምግብ ዘይት አምራች ኢንዱስትሪዎችን ማበረታታት እንዳለበት ተናግረው፤ ሀገር ውስጥ የሚመረተውን ጥሬ ሀብትም ለሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች የሚውልበት ሁኔታ ሊመቻች ይገባል፤ ይህ ሲሆን እያመረትን ራሳችንን የምንችልበት ሁኔታ ይፈጠራል ሲሉ አስረድተዋል።

ኢያሱ መሰለ

አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 17 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You