ኢንተርፕራይዞች ወደ ኢንዱስትሪ የሚያድጉበት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል

– በአዲስ አበባ 281 ኢንተርፕራይዞች ወደ መካከለኛ ኢንዱስትሪ ደረጃ ተሸጋገሩ

አዲስ አበባ፡- ኢንተርፕራይዞች ምርትና ምርታማነትን ከጥራት ጋር በማሳደግ ወደ ኢንዱስትሪ ማደግ የሚችሉበት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል ሲሉ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጥራቱ በየነ ገለፁ።

አቶ ጥራቱ በየነ የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ በ13ኛ ዙር ወደ መካከለኛ ደረጃ የተሸጋገሩ 281 ኢንተርፕራይዞችን በዓድዋ ሙዚየም ትናንትና ሲያስመርቅ በወቅቱ እንደተናገሩት፤ የኢንተርፕራይዞች ሽግግር ዓላማ የኢንተርፕራይዞችንና ጥቃቅን ኢንዱስትሪዎችን ምርትና ምርታማነትን በማሳደግና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ማስቻል ነው።

ይህም የፋይናንስ ፣ የቴክኖሎጂ ፣ የገበያ ትስስርና የሰው ሀብት ልማት ድጋፎችን የማግኘት እድል እንደሚሰጥ ጠቁመው፤ በተጨማሪም የመሥሪያና መሸጫ ማዕከላትን ተጠቃሚ የሚሆኑበት ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።

መንግሥት በፖሊሲው አዲስ የሥራ እሳቤዎችን በማካተት የሚፈጠሩ የሥራ እድሎች ከዳቦ በላይ እንዲሆኑ ትኩረት ተደርጓል ያሉት አቶ ጥራቱ፤ ቢሮው ሥራ ፈጣሪ ወጣቶችን በማደራጀት ወደ አምራች ኢንዱስትሪነት እንዲሸጋገሩ እየሠራ ይገኛል። በዚህም ዜጎች ቢያንስ በአንድ የሥራ መስክ ክህሎት እንዲኖራቸው በማድረግ ሀብት ፈጣሪ ኢንተርፕራይዞች እንዲበራከቱ የሚያደርግ እንደሆነም ተናግረዋል።

በውጭ ድጋፍና ርዳታ ሀገር እንደማይለወጥ እና ዘላቂ ዕድገት እንደማይኖር አይተናል ያሉት አቶ ጥራቱ፤ የሀገር ውስጥ ኢንተርፕራይዞች ይህንን በመረዳት ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት መሥራት እንዳለባቸውም ገልፀዋል። ኢትዮጵያን ከድህነት በማውጣት የአፍሪካ የብልፅግና ተምሳሌት ለማድረግ ሁሉም ዜጋ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ መሀመድ ልጋኔ በበኩላቸው፤ የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ምርታማነት፣ የሀብት መጠን፣ የመንግሥታዊ ድጋፎች አጠቃቀም፣ ትርፋማነት፣ የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም እና የገበያ መጠን የሸግግር መስፈርቶች እንደሆኑ ገልፀዋል።

ከተማ አስተዳደሩ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከሚሠራቸው ሥራዎች ውስጥ የኢንተርፕራይዞችን አቅም የማሳደግ ሥራ ተጠቃሽ መሆኑን አንስተው፤ ቢሮው እስከ አሁን ከአንደኛ እስከ 12 ዙር ድረስ ሁለት ሺህ 241 ኢንተርፕራይዞችን ወደ መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ደረጃ ማሸጋገር ተችሏል ብለዋል።

በዘንድሮ በጀት ዓመትም በ13ኛ ዙር 281 ኢንተርፕራይዞችን ወደ መካከለኛ ደረጃ ለማሸጋገር መብቃታቸውን ገልፀው፤ በዚህ የሽግግር ተግባር ቢሮው በርካታ ሥራዎችን ሠርቷል። በቀጣይም ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን ወደ መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ የማሸጋገር ሥራ እንደሚሠራ ጠቁመዋል።

ሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 17 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You