ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመግታት የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ

አዲስ አበባ፡– ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመግታት የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ በፍትህ ሚኒስቴር የመንግሥት ሕግና ፍትህ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ በላይሁን ይርጋ ገለጹ።

ሚኒስትር ዴኤታው ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ጥቆማ የሚስተናገድበት ነጻ የስልክ ጥሪ መስመር ትናንት ይፋ በተደረገበት ወቅት እንደተናገሩት፤ ሕገ ወጥ ስደትና የሰዎች ዝውውር ግለሰቦችን ተጎጂ ከማድረግ ባለፈ የሀገር ገጽታንና ዲፕሎማሲንም እያጠለሸ ይገኛል። በመንግሥት በኩል ኢመደበኛውን ፍልሰት በማስቀረት መደበኛውን ለማጠናከር የፖሊሲ፣ የሕግና የአደረጃጃት ሥራዎችን በማከናወን ላይ ነው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት የስደት መነሻ ምክንያት የተሻለ የሥራ እድል ለማግኘት የሚደረግ ጥረት መሆኑን ጠቁመው፤ ነገር ግን የተሳሳተ መረጃ መነሻ በማድረግ በሕገወጥ መንገድ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ዛሬም ድረስ በርካታ ዜጎችን በመተላለፊያና በመዳረሻ ሀገራት ለተለያዩ ችግሮች እያጋለጣቸው እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በማንኛውም መልኩ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች በሕጋዊ መንገድ የኢትዮጵያንም ሆነ የመተላለፊያና የመዳረሻ ሀገራት ሕጎችን ያከበሩ ሊሆን እንደሚገባ አመልክተው፤አብዛኛው ስደተኛ ለችግር የሚዳረገው በሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች የተሳሳተ መረጃ እንዲደርሰው ስለሚደረግ መሆኑንም አመልክተዋል።

በተለያዩ ቦታዎች በህብረተሰቡ ዘንድ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን የተመለከቱ መረጃዎች በህብረተሰቡ ዘንድ ቢኖሩም ከስጋት ነጻ ሆኖ ለሚመለከተው አካል ለማድረስ ምቹ ሁኔታዎች አልነበሩም ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ሥራውን የጀመረው ነጻ የስልክ ጥሪ ተጎጂዎችን ለመታደግ፤ ድጋፍ ለማድረግ መረጃ ተደራሽ ለማድረግ እና በሕገወጥ አዘዋዋሪዎች ላይ ተጠያቂነት ለማስፈን የሚረዳ ይሆናል ብለዋል።

ወንጀሎቹ ድንበር ተሻጋሪ በመሆናቸው ለመከላከል የሚደረገውም ትብብር በሀገር ውስጥ ብቻ የሚወሰን እንዳልሆነ ገልጸው፤ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን በተመለከተ እንደ ሀገር ከክልሎች፣ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንዲሁም ከሌሎች ሀገራት ጋር የተጀመሩት የትብብር ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

«ፍልሰት በራሱ ችግር ባይኖረውም በአግባቡ ቁጥጥር ካልተደረገበት የሚያደርሰው ተጽእኖ የከፋ ነው» ያሉት ደግሞ የብሔራዊ የፍልሰት ትብብር ጥምረት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብርሃም አያሌው፤ ከኢትዮጵያ በርካታ ፍልሰተኞች ወደ ተለያዩ ሀገራት ይሄዳሉ፤ በግጭትና በተፈጥሮ አደጋ ለስደት የሚዳረጉ ዜጎች ቁጥርም በየወቅቱ እየጨመረ ይገኛል። ይህም በዜጎች ላይ አካላዊ፤ ሥነ ልቦናዊ፤ ማህበረሰባዊና ኢኮኖሚያዊ ብሎም እስከ ሕይወት ማሳጣት የሚደርስ ጉዳት እያደረሰ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅትም ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር የደህንነት ስጋት ከሆኑ ወንጀሎች መካከል እየሆነ መምጣቱን ጠቁመው፤ በሰዎች የመነገድ ወንጀል በፍጥነት እልባት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው። ይህንን ወንጀል ለመከላከል ድርጊቱ ተፈጽሞ ሲገኝም ተጎጂዎችን ለመታደግና መልሶ ለማቋቋም የበርካታ አካላት ተሳትፎን የሚጠይቅ ተግባር እንደሆነም አመልክተዋል።

ሥራውን የጀመረው 8797 ነጻ የስልክ መስመር በዚህ ሥራ ተሳታፊ ለመሆን ፈቃደኛ የሆኑትን በሙሉ ሥራ የሚያቀል ይሆናል። ይህ የስልክ ጥሪ በአሁኑ ወቅት በአማርኛ ፤ በአፋን ኦሮሞ፤ ትግርኛና እንግሊዝኛ ቋንቋዎች የሚሠራ ሲሆን በቀጣይም ተደራሽነቱ የቋንቋ ብዝሃነቱንም ለመጨመር የሚሠራ ይሆናል ያሉት አቶ አብርሃም፤ ህብረተሰቡም የጉዳዩን አሳሳቢነት በመረዳት ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን በተመለከተ የሚያገኛቸውን መረጃዎች በነጻ የስልክ መስመሩ ተደራሽ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

ራስወርቅ ሙሉጌታ

አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 17 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You