
አዲስ አበባ፡-እራስን የመቻል እና ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ እቃዎች በተተኪ ምርት ለመቀየር የመቻል ሀገራዊ ህልማችን የሚሳካው ቀጣይነት ባለው ፈጠራ እና ጠንክሮ በመሥራት ብቻ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በማህበራዊ ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ እራስን የመቻል እና ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ እቃዎች በተተኪ ምርት ለመቀየር የመቻል ሀገራዊ ህልማችን የሚሳካው ቀጣይነት ባለው ፈጠራ እና ጠንክሮ በመሥራት ብቻ ነው። በ ‘ክህሎት ኢትዮጵያ’ ውድድር እማካኝነት ወጣቶች ችሎታቸውን እና ሃሳባቸውን ወደ ትርጉም ያላቸው ተግባራዊ ፈጠራዎች ለውጠው እየተገበሩ በማየቴ ደስተኛ ነኝ ብለዋል።
በፈጠራ ሥራ ላይ የተሠማሩትን በርቱ እያልኩ፣ ሌሎች ወጣቶችም የማህበረሰባችንን አንገብጋቢ ፍላጎቶች እንዲመረምሩ እና ሀገራቸውን ለማገልገል የሚችሉ መፍትሄዎችን እንዲፈጥሩ አበረታታለሁ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በተጨማሪም የንግዱ ማህበረሰብን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት እነዚህን እና ሌሎች ወጣት ፈጣሪዎች የማምረት አቅማቸውን ያሳድጉ ዘንድ እንዲደግፉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 17 ቀን 2017 ዓ.ም