
– ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር
አዲስ አበባ፡– ሥራችን ዘላቂ ሀገር የምንገነባበትና በተቻለን መጠን ስጋት የምንቀንስበትን መሠረት መጣል ነው ሲሉ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) ገለጹ። ቀጣዩ ምርጫና ሀገራዊ ምክክሩ በአንድ ዓመት ውስጥ መካሔዳቸው የሚያጋጫቸው ምንም ነገር እንደማይኖርም አመልክተዋል።
ኮሚሽነር ዮናስ (ዶ/ር) ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳስታወቁት፤ የሀገራዊ ምክክር ዋና ዓላማ አሸናፊና ተሸናፊ የሚለይበት ሳይሆን ሁሉም አሸናፊ የሚሆንበት ነው። በኢትዮጵያ ሰላም ባህል ሆኖ እንዲዘልቅ ጽኑ ፍላጎት አለ። እርስ በእርስ በመነጋገር እንጂ በመገዳደል ደግሞ መፍትሔ ስለማይመጣ ምክክርን ባህል ማድረግ ወሳኝ ነው። ኮሚሽኑም ሥራው ዘላቂ ሀገር የሚገነባበትንና በተቻለ መጠን ስጋት የሚቀነስበትን መሠረት መጣል ነው። ለዚህ ደግሞ ጊዜ ወሳኝ ነው ብለዋል።
ኮሚሽነር ዮናስ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ በተለያዩ ሀገራት ያለው ልምድ እንደሚያሳየው በምክክር ጉዳይ ጊዜ ማራዘም በጣም የተለመደ መሆኑን ነው። እንዲያውም የአንዳንድ ሀገሮች ልምድ የሚያመለክተው የሥራ ጊዜ ለአንዴ ሳይሆን ለሁለት፣ ሶስትና አራት ጊዜ መሆኑን ነው። ጊዜ ማራዘሙ ብቻ ሳይሆን የአንዳንዶቹ የሚዘወረው በውጭ አካል ጭምር ነው።
የእኛ ሀገራዊ ምክክር ግን ባለቤቱ እራሱ ሕዝቡ ነው። 99 በመቶ የሚሆነውም ገንዘብ የሕዝብ ነው። ከውጭ የሚሰጠን ገንዘብ ቢኖር እንኳ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚሰጥ እንጂ ለእኛ አይደለም ያሉት ኮሚሽነሩ፤ ለስኬታማነቱ ምንም የሚያጠራጥረን ነገር የለም ብለዋል። ዋናውና ትልቁ ግብ ግን ሁሉንም አሸናፊ በማድረግ ማሳካት መቻል ነው ሲሉም ገልጸዋል።
ዮናስ (ዶ/ር)፣ ምክክሩ በተጨመረለት የአንድ ዓመት ጊዜ ሥራዎቹን ለማጠናቀቅ እንደሚሠራ ጠቅሰው፤ ምክክሩ ኢትዮጵያ በቀጣይ ከምታካሒደው ምርጫ ጋር ምንም እንከን የማይፈጥር መሆኑን አስረድተዋል።
ቀጣዩ ምርጫና ሀገራዊ ምክክሩ በአንድ ዓመት ውስጥ መካሔዳቸው የሚያጋጫቸው ምንም ነገር አይኖርም ብለዋል። ምክንያቱም እኛ የተጨመረልን የአንድ ዓመት ጊዜ እስከ 2018 ዓ.ም ድረስ ያለው ነው። ምርጫው ደግሞ በ2018 ዓ.ም ግንቦት ወር ላይ የሚካሔድ መሆኑን ገልጸዋል።
እኛ ምርጫ ቢኖርም መስመራችንን ይዘን እንቀጥላለን። ፍርድ ቤት ይቀጥላል። ፖሊስም ይቀጥላል ብለዋል።
እርሳቸው እንደገለጹት፤ ሀገራዊ ምክክር ስሙ እራሱ እንደሚጠቁመን ሀገራዊ ነው፤ ምክክሩ የብልፅግና ፓርቲ ወይም የኢዜማ አሊያም የኦነግ አይደለም። ፓርቲዎች እንደየዘመኑና እንደየሁኔታው የሚፈጠሩ እና ኢትዮጵያን የሚያሳድጓት ናቸው። ኢትዮጵያ ግን ለዘላለም የምትኖር ናት። ከዚህ የተነሳ ሁሌም ወደፊት ለምትቀጥል ሀገር የየራሳቸውን ድርሻ የሚያበረክቱ ናቸው።
ሀገራዊ ምክክር እና ምርጫው አንዱ ለሌላው እንቅፋት አይሆንም፤ በሳይንሱ መሠረትም የሚያጋጫቸው ምንም ነገር እንደሌለ አመልክተዋል።
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 17 ቀን 2017 ዓ.ም