
ዜና ትንታኔ
የአፍሪካ ቀንድ የዓለምን ጂኦፖለቲክስ ከመለወጥ አንጻር ያለውን ፋይዳ የተመለከቱ ኃያላን ሀገራት የሚራኮቱበት ሥፍራ ነው። ቀጣናው ብዙ አይነት ፍላጎቶች ያላቸው ኃያላን ሀገራት ዓይናቸውን የሚጥሉበት ነው። ሀገራት በቀጣናው ያላቸውን ጥቅም ለማረጋገጥ ሲሉ የሚነካካቿው በርካታ ጉዳዮች በመኖራቸው አካባቢው ሁሌም ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች የማያጣው እንደሆነ ምሑራን ይናገራሉ።
የድንበር ውዝግብ፣ የርስ በርስ ግጭት፤ ድርቅ፣ ስደት ፣ መፈናቀል ወዘተ ከበፊት ጀምሮ የአፍሪካ ቀንድ መገለጫ ሆነው የኖሩ ሳንካዎች ናቸው። የቀጣናው ሀገራት ዛሬም ድረስ ከችግሩ ሙሉ ለሙሉ ያልተላቀቁ ናቸው። ለመሆኑ ቀጣናው ከሌላው የዓለም ክፍል በተለየ ደረጃ የስጋት ምንጭ ሊሆን የቻለበት ምክንያት ምድን ነው ? ስንል ባለሙያዎች አነጋግረናል።
በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ አቶ ሙሉዓለም ኃይለማርያም እንደሚያብራሩት፤ በአፍሪካ ቀንድ እንደአጠቃላይም በምስራቅ አፍሪካ ለሚገኙ ሀገራት የሰላም መደፍረስ በርካታ ምክንያቶች አሉ። በዋናነት ግን ውጪያዊና ውስጣዊ ብሎ በሁለት ማየት ይቻላል። ከውስጣዊ ምክንያቶች መካከል በአካባቢው የሚገኙ ሀገራት የዲሞክራሲ ልምምዳቸው ዝቅተኛ መሆን ነው።
ከኢትዮጵያ ውጪ ያሉት ሁሉም የቀጣናው ሀገራት በጥቂቱም ቢሆን የዲሞክራሲ ጭላንጭል መታየት የጀመረባቸው ከቅኝ ግዛት ነጻ ከወጡ በኋላ ነበር። ነገር ግን በወታደራዊ እንቅስቃሴዎች በመፈንቅለ መንግሥትና ቅኝ ገዢዎች ባስቀመጧቻው ሌሎች አሻጥሮች የተጀመረው የዲሞክራሲ ልምምድ አልቀጠለም። ከዚህ ባለፈ ስር የሰደደ የመልካም አስተዳደር ችግር፤ ከኢኮኖሚ ጥያቄ ጋር በተያያዘ ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል አለመኖር፤ እንዲሁም በየሀገራቱ ያሉ የፖለቲካ ልሂቃን በተለይ በመንግሥትና በተፎካካሪ ፓርቲዎች መካከል ስር የሰደደ አለመተማመን መኖር ከምክንያቶቹ መካከል የሚጠቀሱ እንደሆኑ ይጠቅሳሉ።
ከውጪያዊ ምክንያቶች መካከል የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የሚገኙበት ቀይባሕርና አካባቢው ያለው ተፈላጊነት ነው። በዚህ ረገድ ከቀዝቃዛው ጦርነት በኋላ ቀጣናው የኃያላኑ አቅም የመፈታተሻ መድረክ ሆኖ ቆይቷል። በቀጣናው ያሉ ሀገራት አብዛኛዎቹ ድሆች በመሆናቸው ጣልቃ ለሚገቡ ሀገራት ምቹ ሁኔታ የፈጠረ ሲሆን የአቅም ማጣቱ ሀገራቱንም ጥቅማቸውን ማስጠበቅ እንዳይችሉ አድርጓቸዋል ነው ያሉት።
በመሆኑም ሀገራቱ የየራሳቸውን ፍላጎት ይዘው የሚገቡ ሲሆን የውክልና ጦርነት ሲያካሂዱም ይታያል። በቅርቡ በሶማሊያ አልሸባብን ለማጥፋት እንሠራለን በሚል ጦራቸውን ለማስገባት የሞክሩ ሀገራት ፍላጎታቸው የራሳቸው እንጂ የሶማሊያና የአልሸባብ ጉዳይ አልነበረም ይላሉ።
እነዚህ ክስተቶች ቀጣናውን ፖለቲካው ያልተረጋጋ ጦርነትና የእርስ በእርስ ግጭቶች የማይጠፉበት አድርገውታል። በዚህም ሀገራቱ ያላቸውን የተፈጥሮ ሀብት በአግባቡ መጠቀም ስላልቻሉ ያለመረጋጋት፤ የእርስ በእርስ ግጭት እና ለዜጎች ስደት ምክንያት ሆኗል። በየሀገራቱ ያሉ የዲሞክራሲ ተቋማትም በሕዝቡና በተፎካካሪ ፓርቲዎች እምነት የሚጣልባቸው እንዳልሆኑ ይገልጻሉ።
ችግሩ ስር የሰደደና ረጅም ዘመናት ያስቆጠረ ለመሆኑ የውጭ ጣልቃ ገብነት እንደ ምክንያት ቢነሳም፤ የየሀገራቱ መንግሥታት በቀዳሚነት የየራሳቸውን የውስጥ ችግር መፍታት ይጠበቅባቸዋል። በህብረት የመሥራት ልምድ መፍጠር፤ የውስጥ ችግሮቻቸውን በራስ አቅም የመፍታት ባህልን ማሳደግ፤ የዲሞክራሲ ባህልን እንደ መንግሥትም እንደ ሕዝብም ማዳበር መለማመድ አለባቸው። በተጨማሪ እንደ አፍሪካ ህብረት ካሉትና ሌሎች ቀጣናዊ ተቋማት ጋር ኢጋድን ጨምሮ በቅርበት መሥራት አለባቸው የሚል ሃሳብ አላቸው።
እነዚህ ተቋማት በየሀገራቱ ያሉ መንግሥታት ሕግ እንዳይጥሱ በማድረግ ረገድ ብዙ መሥራት ይችላሉ። ተቋማቱ ኃላፊነት በመውሰድ አቅማቸውንና ተሰሚነታቸውን በማሳደግ በአካባቢው ለሚፈጠሩ ችግሮች ከሌሎች አሕጉራት የሚመጡ አስታራቂዎችን ሳይጠብቁ ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ መስጠት በሚለው የህብረቱ መርህ መሠረት ሊሠሩ ይገባል። ሀገራቱ የየጎረቤቶቻቸውን አማጽያን በመደገፍ መጠላለፍ ሲሠሩ ይታያል ። ይህ ሊቀጥል የማይገባው ጉዳይ ሲሆን ለዚህ ደግሞ የመሪዎች የፖለቲካ ቁርጠኝነትና የኢኮኖሚ ትስስርን ማጠናከር ይገባል ብለዋል።
በተመሳሳይ በዚሁ በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ በታሪክ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ የሆኑት አስራት ኤርሞሎ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ችግሩ የጀመረው አውሮፓውያን የጀመሩትን የቅኝ ግዛት መስፋፋት ተከትሎ ነው ይላሉ።
አስራት (ዶ/ር) እንደሚገልጹት፤ አውሮፓውያን በቀይ ባሕር አካባቢ ወደብ በመያዝ ወደ መሀል ሀገራት ሲያደርጉት የነበረው መስፋፋት ትንንሽ ሀገራት እንዲፈጠሩ ምክንያት ሆኗል። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ግን አዲስ ታሪክና አዲስ ጎራ እየተፈጠረ ሲመጣ ቅኝ ግዛትም እየተዳከመ መጥቷል። የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ አውሮፓውያንን ከእስያ የሚያገናኝ ወሳኝ ኬላ በመሆኑ የአውሮፓ ቀኝ ገዢዎች በቀጥታ የነበራቸውን ግዛት ሲለቁ እነሱ በፈለጉት መልክ አርቴፊሻል ወሰን በመከለል ነበር። ይህም የፖለቲካ ብሶት እንዲፈጥር ምክንያት ሆኗል። ለምሳሌ በሶማሊያ በኩል የነበረው ታላቋን ሶማሊያ የመፍጠር ህልም በዚህ ሂደት የተፈጠረ ሲሆን የኤርትራም ጉዳይ ከዚሁ ጋር የሚያያዝ እንደሆነ ያነሳሉ።
የአፍሪካ አንድነት ድርጅትም በ1964 ዓ.ም እነዚህ ቅኝ ገዢዎች ያስቀመጧቸው ድንበሮች የጸኑ እንዲሆን ወስኗል። ይህ ውሳኔ ግን በየሀገራቱ ተቀባይነት ባለማግኘቱ የፖለቲካ አለመረጋጋት እንዲፈጠር የተለ ያዩ እንቅስቃሴዎችም እንዲጀመሩ በር የከፈተ ሲሆን፤ እንደ አልሸባብን ያሉ የሃይማኖት አክራሪዎችም ሊመሠርቱ በቅተዋል። አውሮፓውያን ይህንን ያደረጉት ከምስራቅ አፍሪካ ተነጥለው መኖር ስለማይችሉና ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት ሥርዓት መዘርጋት ስለነበረባቸው ነው ያሉት።
ከአውሮፓውያን በተጨማሪ የተወሰኑ የአረብ ሀገራት ፍላጎትም ለአካባቢው ሰላም ማጣት አንዱ ምክንያት ነው። እነዚህ ወሰን የአረብ ሀገራት አካባቢውን ከመቆጣጠር ባለፈ ስያሜው ራሱ ቀይ ባሕር ሳይሆን የአረብ ባሕር እንዲባል ብዙ ሲሠሩ ቆይተዋል። ይህንን ለማሳካት እንደ አንድ ጉዳይ የሄዱበትና የአረብ ሀገር ያልሆነን ከቀይ ባሕር የማግለል ሴራ አንዱ ኢትዮጵያን ባሕር በር አልባ ሆና እንድዘልቅ ግፊት እያደረጉ መሆኑን ያወሳሉ።
የምእራቡ ዓለምም ሆነ አረቦቹ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ጠንካራ ከሆኑና የባሕሩን አካባቢ መቆጣጠር ከቻሉ ተጠቃሚነት መኖሩ ግልጽ ነው። ከትናንት እስከ ዛሬ አካባቢውን ለማመስ እንደ መግቢያ በር የሚጠቀሙበት መንገድ ደግሞ የኢኮኖሚ ጉዳይ ሲሆን፤ እንደ የዓለም ባንክና አይ ኤም ኤፍን ያሉ የፋይናንስ ተቋማት ለዚህ ዋነኛ መሣሪያቸው ናቸው። ዛሬም ድረስ ሀገራቱን ጥገኛ ለማድረግ የሚሠሩት በዚህ መንገድ መሆኑን ይናገራሉ።
ለችግሩ አለመቀረፍም ሆነ እየተባባሰ ለመሄዱ መፍትሄ የሚፈለገው ከችግሩ ፈጣሪዎች መሆኑ ደግሞ ችግሩ እስከመጨረሻው እንዳይፈታ ያደረገ ነው። በምስራቅ አፍሪካ አካባቢዎች ለሚፈጠሩ ችግሮች ለሽምግልናም ሆነ የስምምነት ሃሳብ ለማቅረብ አውሮፓውያንና የተወሰኑ የአረብ ሀገራት ጣልቃ ሲገቡ ይታያል። ይህ ግን ፍጹም ስህተት እንደሆነ ገልጸዋል።
እነዚህ ሀገራት በአካባቢው የየራሳቸው ፍላጎት ያላቸው በመሆኑ የሚያቀርቡት ሃሳብም ሆነ የሚሠሩት ሥራ ፍላጎታቸውን መሠረት ያደረገ መሆኑ አይቀርም። ስለሆነም የአካባቢው ችግር እንዲቀረፍ ሃሳብ ማመንጨትም ሆነ መሠራት ያለበት በራሳቸው በሀገራቱና ከዚህም ከዘለለ በምስራቅ አፍሪካ ሀገራትና በአፍሪካ ስር በተመሠረቱ ተቋማት መሆኑን ይኖርበታል ይላሉ።
ይህንን ለማድረግ ደግሞ የእርስ በእርስ ግንኙነታቸውን ማጠናከርና የመሠረቷቸውንም ተቋማት ማብቃትና ውሳኔ ሰጪ ማድረግ ከየሀገራቱ የሚጠበቅ ይሆናል ሲሉ አስረድተዋል።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 17 ቀን 2017 ዓ.ም