
ሀገር ያለ ሰው፣ ሰውም ያለ ሀገር መገለጫ አልባ ስለመሆናቸው በርካቶች ይናገራሉ፤ ድርሳናትም ያትታሉ። ይሄ የሰውና የሀገር የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታነት ደግሞ፣ በሰንደቅ ዓላማ አንድ ሆኖ ይወከላል። እናም አንድ ሰንደቅ ዓላማ የሀገርን ነፃነትና ሉዓላዊነት፤ የዜጎቿን ልዕልናና ገናንነት ወክሎ የሚገለጥ እንደመሆኑ፤ በሚወክላት ሀገር እና ሕዝብ ሉዓላዊነትና ክብር ልክ በሌሎች ፊት ግርማን ያገኛል።
ይሄ ግርማው ደግሞ ከሰው ልጆች (ከዚያች ሀገር ነዋሪዎችና ዜጎች) የሥራ እና የትጋት ባሕል ይወለዳል። ሕዝብ ሲተጋ፣ ሕዝብ ሲሠራ፣ ሕዝብ ለሰላምና አንድነቱ ሲቆም፣ ሕዝብ ስለ አጠቃላይ ሉዓላዊነትና ብልፅግናው ሲተባበር፤ ሕዝብ ስለ አንድነትና አብሮነት ከፍታው እያሰበ በሙሉ ልብ ለጋራ ሀገሩ ዋጋ ሲከፍል፤ ሀገሩን ከፍ ያደርጋል፣ ያገንናል፣ ሉዓላዊነቷን ያረጋግጣል፤ ሰንደቁም የሀገሩን ክብርም ከፍ አድርጎ በመግለጽ ለዓለም ሕዝብ ያስተዋውቃል።
ከዚህ በተቃራኒው ግን፣ ስለ አብሮነትና አንድነቱ፤ ስለ ሀገራዊ ሉዓላዊነትና ብልፅግናው፤ ስለ ሰላምና ሁለንተናዊ ከፍታው፤… የማይሠራ፣ የማይተጋ ዜጋና ሕዝብ ያሉባት ሀገር፤ ኢኮኖሚዋ በሚፈለገው ልክ የማይራመድ፤ ሰላምና መረጋጋት የነገሰባት፤ ዜጎቿ በተለይም ወጣቶቿ የሚሰደዱባት፤ ከአንድነት ይልቅ ልዩነትና መነጣጠል የሚሰበክባት፤ በሌሎች ዓይን መግዘፏን ሳይሆን አንሳ እንድትታይና የእነሱ የመከፋፈል መንገድ እንዲሳካ እንቅልፍ አጥተው የሚተጉባት አንጃዎች የሚፈለፈሉባት፤… ሀገር ትፈጠራለች።
ይሄ ሲሆን የአብሮነት መንገዱ ቀርቶ የየብቻ ሀዲዱ እንዲሰምር የሚያደርጉ አጀንዳዎች ይበዛሉ። አረጋውያን የሚጦሩበት፣ ሕፃናት በተስፋ ተሞልተው የሚያድጉበት፣ ሴቶችና አካል ጉዳተኞች ሙሉ መብታቸው ተከብሮ የሚኖሩበት፣ ወጣቶችን ስለ ሀገራቸው ሁለንተናዊ ልማት የሚሳተፉበት እና ከልማቱም የሚጠቀሙበት አውድ እየኮሰሰ ይሄዳል። ስደት፣ መፈናቀል፣ ጦርነትን የመሳሰሉትም ይነግሳሉ፤ ወጣቶች ለእልቂት፣ አጠቃላይም ሀገር ለከፋ ሰብዓዊም ቁሳዊም ኪሳራ ትዳረጋለች።
ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያንም ከሦስት ሺህ ዘመን በተሻገረው የሀገርና የሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደት እነዚህ ሁለት ገጾች የታሪካቸው አካል ሆነው ይነበባሉ። እንዴት ቢሉ፤ በአንድ በኩል በኅብር የተገለጠ እንዲያውም ለዓለም የተረፈ የኪነ ጥበብ፣ የኪነ ሕንጻ፣ የሥነ ጽሑፍ፣ የሥነ ፈለግ ፋና ወጊነታቸው፤ አለፍ ሲልም የነፃነት ቀንዲል ሆነው የተገለጡባቸው አያሌ አብነቶች ዛሬም ድረስ ደምቀውላቸው።
በተቃራኒው፣ በዘመናት ሂደት የተገነቡ ማንነቶችን፤ የገዘፉ ልኬቶችን፤ የገነኑ ታሪኮችን፤ ደምቀው የተገለጡ እሴቶችን፤ በዘመናት በብዙ መልኩ የተጋመደውንና በህብር ያጌጠውን የሕዝቦች አንድነትና አብሮነት፤ በደም መስዋዕትነት ጸንቶ የኖረውን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት፤… ለመናድና ለማፍረስ ሙሉ አቅማቸውን የሚጠቀሙ አንጃዎች እና ተላላኪ ባንዳዎችም ሆነው የተገለጡ የሀገር አረሙቻዎችም አልታጡም።
እነዚህ በስንዴ መሀል እንደሚበቅል እንክርዳድ ያሉ፤ ሀገርን ለማፍረስ፣ ሕዝቦችንም ለመነጣጠል የሚሠሩ አንጃዎች ታዲያ፤ ትናንትን ኢትዮጵያን ከክብሯም፣ ከግዛት አንድነቷም እንድታንስ ለማድረግ፤ ዜጎች እርስ በእርሳቸው እንዲዋጉ፤ ለማይጨበጥ ሕልማቸው ሲሉ ወጣቶች በየዘመኑ ወደ ጦርነት እንዲማገዱ ሲያደርጉ ኖረዋል። ዛሬም ከዚሁ መሰል ቅዠት ወለድ የምኞት አንጎበር ያልነቁ ስለመኖራቸው የቅርብ ጊዜ ትዝታችን፤ አሁናዊም ራስ ምታታችን ሆኖ ዘልቋል።
ለዚህ ደግሞ፣ ሩቅ ከሄድን ግማሽ ምዕተ ዓመት፤ ቀረብ ካልን ደግሞ ሦስት እና አራት ዓመታትን፤ እሱም ራቀ ከተባለ ደግሞ ሰሞንኛውን ግርግር በማሳያነት በማቅረብ ከብዙ አብነቶች አንዱን ማንሳት ይቻላል። ለምሳሌ፣ ከሃምሳ ዓመት በፊት ራሱን ነፃ አውጪ አድርጎ በመሰየም ጫካ ከገባበት ጊዜ አንስቶ፤ በኋላም በባንዳነት እንዲያገለግል ባደራጁት የውጭ ኃይሎች ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ታግዞ ለአቅመ መንግሥትነት የበቃው፤ በጊዜ ሂደትም ሀገር የመገንጠል የማይጨበጥ ምኞቱን ለማሳካት ሲተጋ እና አሁንም ይሄው ምኞቱ ቅዠት ሆኖ እንቅልፍ የነሳውን የሕወሓት አንጃ የሃምሳ ዓመታት መንገድ በወፍ በረር እንመልከት።
ይሄ አንጃ በነፃነት ስም ጫካ ከገባ ጀምሮ ለ17 ዓመታት የትግል ጉዞው በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ወጣቶችን ለሞት፣ ለአካል ጉዳት፣ ለስደትና ለከፋ ሥነ ልቡናዊ ጉዳት ዳርጓል። የሀገርን ክብርና ሉዓላዊነት በሚያጎድፉና አሳልፈው በሚሰጡ ተግባራት ተሰማርቶም ታይቷል። ከሱዳን፣ ከግብጽና ሌሎችም ኢትዮጵያን በማዳከምና በማፍረስ ውስጥ ጥቅም ከሚያገኙ አካላት ጋር ተባብሮ ሠርቷል።
በእነዚሁ ኃይላት ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እና በትግራይ ልጆች ብሎም ወጣቶች መስዋዕትነት ላይ ተረማምዶ ወደ መንግሥትነት ዙፋን ሲደርስም፤ የመጀመሪያው ተግባር የነበረው የሀገርን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት መናድ ነበር። በዚህም የኢትዮጵያን ጥቅም ባላስጠበቀ፤ ይልቁንም በቀጣይ ያስቀመጠውን ሀገርን የመበታተን ጉዞው ለእሱ የሚመቸውን አቅጣጫ ታሳቢ ባደረገ መልኩ፤ የኢትዮጵያን ምድር ቆረሰ፤ ጠላቶቿ እንደሚመኙትም ኢትዮጵያን ከባሕር በር ነጠለ።
በሂደትም ኢትዮጵያውያን እንዳይተማመኑ የሚያደርጉ የጠላትነት፣ የመነጣጠልና የቂም በቀል ትርክትን በማስፋፋት፤ ሕዝቦች እንዳይተማመኑና እንዳይተባበሩ ለማድረግ አብዝቶ ሠራ። ወጣቱ በጥላቻ፣ በመከፋፈልና በበቀል ስሜት ተሞልቶ ከሀገሩ ይልቅ ወደ ቡድን ወርዶ እንዲያስብ ለማድረግ ብዙ ርቀት ተጓዘ። ለኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ጥቅምና ፍላጎት ሳይሆን በውስጡ ላሉ አንጃዎች ጥቅምና ፍላጎት፤ ክብርና ብልፅግና አብዝቶ ትውልዱን ዋጋ አስከፈለ።
ለዚህ ደግሞ ከ2010ሩ ሀገራዊ ለውጥ ማግስት ያለውን እውነት መመልከቱ ተገቢ ነው። ይህ ጊዜ ዜጎች የዚህ ቡድንና አንጃ ግፍና በደል፤ ዘረፋና ጭቆና፤ ሰብዓዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብት አፈና፤…የመሳሰሉ ጉዳዮች አንገፍግፈውት በሕዝባዊ እንቢተኝነት ለውጥ የተወለደበት ነው። ይሄ ለውጥ ደግሞ የሕዝብ ፍላጎትን ተረድቶ መሥራትን፤ ለሕዝብ ራስን አሳልፎ በመስጠትን፣ የተሻለ ሀገርና ትውልድ መገንባትን፤ ሀገራዊ ክብርና ብልፅግናን በሙላት እውን ማድረግን አብዝቶ የሚሻ ነበር።
የወቅቱ የለውጥ ኃይልም በዚሁ ልክ የተቃኘ ነበር። የሕወሓት አንጃ ግን ስሪቱም፣ ኑረቱም ከዚሁ በተቃራኒ ስለነበር፤ በዚህ የለውጥ ሀዲድ ላይ የሚጓዝበት ሰብዕናም፣ ቁመናም አጣ። እናም ከነፃ አውጪነት አልፎ ለመንግሥትነት በቅቶ የነበረው ቡድን፤ ዳግም ራሱን ነፃ አውጪ ባደረገ የማታለያ ትርክት በመታገዝ ሕዝቡን ውስጡ ሆኖ እንደ ረመጥ ይለበልብ፤ ያቃጥለው ያዘ።
ቀድሞም የቡድናዊ ፍላጎትና ሕልም እንጂ የሕዝብ ጥያቄና ፍላጎት የማይገባው ይሄው አንጃ፤ በሌላ የነፃነት ካባ፣ በሌላ የሀገረ መንግሥት ምስረታ የሞቅታ ሕልም ተመርቶ ሌላ ጦርነት ቀሰቀሰ፤ ሌላ ትውልድ ወደ እሳት ማገደ፤ ሌላ በሀገርና ሕዝብ ሰብዓዊም ቁሳዊም ጉዳት ያስከተለ መንገድ መረጠ።
በዚህ መልኩ ሁለት ዓመታትን ከዘለቀ ጦርነት ማግሥት፤ ለሕዝብ እና ሀገር ጥቅም ሲባል በመንግሥት ከፍ ያለ ጥረት ፕሪቶሪያ ላይ የሰላም ስምምነት ተደረገ። በዚህ ስምምነትም ለመገዛት ተስማምቶ፣ ከመንግሥትነት ወደ አሸባሪነት ወርዶ የነበረው ቡድን ዳግም በክልሉ የሥልጣን ባለቤት እንዲሆን ያስቻለውን የጊዜያዊ አስተዳደርነት መንበር ተቆናጠጠ።
ይሁን እንጂ በቡድኑ መካከል በሞቅታ መሃል የሚቀሳቀስ የነፃ ሀገርነት ቅዠት የተጠናወታቸው አንጃዎች ረፍት አጡ። እናም በስምምነቱ ምክንያት ለሁለት ዓመታት የጥይት ድምጽ ሳይሰማበት የዘለቀውን ክልልና ከባቢ፤ ወደ ልማትና መረጋጋቱ፤ ወደ ነበረ ማህበራዊ ግንኙነቱ፣ ወደ ሀብት ማፍራትና የመበልጸግ ተስፋው የተመለሰውን ሕዝብ ወደ ዳግም አለመረጋጋት ለማስገባት ይተጋ ጀመር።
የፕሪቶሪያው ስምምነት እንዳይፈጸም እንቅፋት ከመሆን ጀምሮም፤ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ተረጋግቶ ሥራውን እንዳይሠራ ለማደናቀፍ ወደ ተራ ወንበዴነት ተግባር ተሰማራ። በዚህም ከተራ የማህተም ቅሚያ ጀምሮ ወጣቱ ተረጋግቶ ወደ ልማቱ እንዳይሳተፍም፣ ከልማቱ ተጠቃሚ እንዳይሆንም ዕረፍት ወደ መንሳት ገባ።
ይባስ ብሎ አሁን ላይ ከሕወሓት ያፈነገጡ የጥቂት አዛውንቶችን ጥቅምና ፍላጎት ብሎም የማይሳካ ቅዠት ማዕከል አድርጎ የሚንቀሳቀሰው የአንጃ ቡድኑ፤ በጊዜያዊ አስተዳደሩም ሆነ በፌዴራል መንግሥቱ በኩል ለሕዝቦች የላቀ ተጠቃሚነትም ሆነ ለፕሪቶሪያው ስምምነት በሙላት መፈጸም የሚያደርጉትን ጥረት በገሃድ ወደማስተጓጎል ገብቷል። ይሄንኑም ሃቅ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ፣ እንዲሁም የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ጌዴዮን ጢሞቲዎስ ገልጸዋል፤ ለዓለም አቀፉም ማኅበረሰብ አሳውቀዋል።
ይሄ የአንጃ ቡድኑ አካሄድ ደግሞ የሕዝብ ፍላጎትን በራስ ጥቅምና ምኞት የመተካት ብቻ ሳይሆን፤ ላለፉት ሁለት ዓመታት ሰላማዊ አየር የነፈሰበትን፤ የልማት መንገድ የተጀመረበትን ክልልና አጎራባች አካባቢዎች ወደ ሌላ ውጥረት የሚከትት፤ አለፍ ሲልም ከውጭ ኃይሎች ጋር በማበር ወደ ለየለት ጦርነት በማስገባት ቡድናዊ ሕልውናን ማቆየትን ታላሚ ያደረገ ነው።
ለምሳሌ፣ ከፕሪቶሪያው ስምምነት ማግሥት መንግሥት ተፈናቃዮች እንዲመለሱ አስፈላጊውን ሁሉ አድርጓል፤ በጦርነቱ የፈረሱ የጤና፣ የትምህርት፣ የመብራት፣ የመንገድና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት በብዙ ቢሊዮን ብር ፈሰስ አድርጎ ሠርቷል። የክልሉን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የሚያስችል የምርጥ ዘር፣ የማዳበሪያና የሜካናይዜሽን ሥራን የሚያሳልጡ ትራክተርና ኮንባይነር ሃርቨስተሮችን በስፋት ተደራሽ አድርጓል።
የኅብረተሰቡን ጤና ለማስጠበቅ የሚያስችሉ የጤና ተቋማትን ከማጠናከር ባለፈም፤ የመድኃኒት፣ የአምቡላንስና ሌሎችም ድጋፎችን አድርጓል። የሰብዓዊ ድጋፍ ለሚሹ የኅብረተሰብ ክፍሎችም ከአጋር አካላት ጋርም፣ በራስ አቅምም የሚያስፈልገውን ሁሉ እያደረሰ ይገኛል። መደበኛ የልማት ሥራዎች እንዳይስተጓጎሉም በጀት መድቦ በጊዜያዊ አስተዳደሩ በኩል እንዲከናወኑ እያደረገ ነው።
በጦርነቱ ውስጥ የተሳተፉና የታጠቁ ኃይሎችን ትጥቅ የማስፈታት እና መልሶ የማቋቋም ጅምሩም ከውጤት እንዲደርስ ከፍ ያለ ሚናውን ተወጥቷል። በዚህ እና መሰል ከስምምነቱ ማግሥት ባከናወናቸው ተግባራትም በመቶ ቢሊዮን የሚቆጠር ሀብት በክልሉ ፈሰስ አድርጓል።
ከዚህ በተቃራኒው ግን፣ ተገናጣዩ የሕወሓት አንጃ፣ በክልሉ ሰላም እንዳይሰፍን ውጥረትን በሚያነግሱ ተግባራት ላይ ሳይታክት እየሠራ ይገኛል። ለምሳሌ፣ የቀድሞ ተዋጊዎችን ትጥቅ የማስፈታትና መልሶ የማቋቋም ሂደቱ ውጤታማ እንዳይሆን ከመሥራት ባለፈ፤ ዛሬም ከ270 ሺህ በላይ ታጣቂዎች ትጥቅ ሳይፈቱ እንዲቀመጡ እና በመንግሥት በጀት ቁጭ ብለው እንዲቀለቡ እያደረገ ይገኛል።
ይሄ ደግሞ በአንድ በጀት ዓመት ብቻ ከስምንት ቢሊዮን ብር የሚልቀው የክልሉ በጀት ለዚሁ ጦርነትን ታሳቢ ተደርጎ ለሚቀለበው ኃይል እንዲውል መደረጉን፣ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንት በቅርቡ መግለጻቸው የሚታወቅ ነው። ይሄ ደግሞ አንጃ ቡድኑ ቀደም ሲል በነፃነት ስም መቶ ሺዎችን፤ ከአራት ዓመት በፊትም በሌላ የነፃነት የዳቦ ስም እና በሞቅታ በሚቀሰቀስ ሀገር የመመስረት ቅዠት ውስጥ፣ ብዙ መቶ ሺህ ወጣቶችን፤ አሁንም በመሰል የሞቅታ ውስጥ የሚራወጥ ያልተቋጨው የቅዠት ውስጥ ሆነው ወጣቱን በጦርነት ለመማገድና የጥቅማቸው ማስጠበቂያ የማድረግ ፍላጎት የወለደው የአዛውንት አንጃዎች ጫና ምክንያት የሚፈጸም ነው።
ሆኖም ይሄ ፍላጎታቸው አሁን ላይ የሚሰምርላቸው አይሆንም። ምክንያቱም፣ ሕዝቡ ልማቱን መመልከትና መጠየቅ ጀምሯል። ወጣቱም ሰርቶ መለወጥን እንጂ የአንጃዎች ጥቅም ማስጠበቂያ መስዋዕት እየሆኑ መኖርን በቃኝ ብሏል።
አንጃው የተፈናቀሉ ወገኖችን ወደ ቦታቸው እንዳይመለሱ እና ዓመታትን በድንኳን ውስጥ እንዲሰቃዩ በማድረግ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚታትር መሆኑን አብዛኛው የትግራይ ሕዝብ ስለተገነዘበም፣ ለዚህ አንጃ መሳሪያ የመሆንን ጉዞ ለመግታት የሚያስችለውን እንቢታ ከወዲሁ ማሰማት ጀምሯል።
ቀድሞ በነፃነት፣ ከዚያም በሀገረ መንግሥትነት፣ አሁንም በዘመቻ አንድነትና በሌላም የዳቦ ስም ለሚፈጸሙ ማደናገሪያዎች ቦታም፣ ጆሮም ነፍጎታል። ዛሬ ላይ ቡድኑ ሰላምና ልማት የሚያስከትሉበትን ቡድናዊ ኪሳራ ስለሚገነዘብ፤ ሕዝቡ ከልማቱ እንዳይቋደስ፣ በሰላም ጥላ ስር እረፍት እንዳያገኝ የሚችለውን ሁሉ እየጣረ ይገኛል። በአንጻሩ መንግሥት ለሰላምና ልማቱ ቅድሚያ ሰጥቶ እየሠራ፤ ዛሬም ለትግራይ ሕዝብ ምርጥ ዘር፣ ማዳበሪያ፣ ትራክተር፣ መድኃኒት እና አምቡላንስ እየላከ ይገኛል።
በመሆኑም አንጃው ከቡድናዊ ፍላጎትና ስሜት ከሚገፋው ምኞት በመራቅ፤ ወጣቶችን በሞቅታ ዲስኩር ለጦርነት ከማሰናዳት ራሱን ሊያቅብ ይገባል። ሕዝቡም የአንጃውን አካሄድ በግልጽ እየተገነዘበ እንደመሆኑ፤ ይሄንኑ ግንዛቤውን ሌላውም እንዲገነዘበው፤ ወጣቱም የዚህ ቡድን ሰለባ ላለመሆን የሚያደርገውን ትግል ሊያግዝ ያስፈልጋል።
ወጣቱም ለሞት ሳይሆን ለልማት፤ ለአንጃ ዓላማ ሳይሆን ለሀገርና ለሰንደቅ ዓላማው ክብር እንዲቆም መርዳትም የግድ ይላል። የሚመለከታቸው የፌዴራልም፣ የፕሪቶሪያው ስምምነት ባለድርሻ አካላትም፤ ለሕዝቡ ጥቅም፣ ሰላምና ልማት ሲባል የዚህን አንጃ አካሄድ በልኩ በመገንዘብ ከተሳሳተ መንገዱ እንዲመለስ ለማድረግ አስፈላጊውን ሁሉ ሊያደርጉ ይገባል። ለዛሬው አበቃሁ፤ ሰላም!
በየኔነው ስሻው
አዲስ ዘመን ማክሰኞ መጋቢት 16 ቀን 2017 ዓ.ም