
የትግራይ ሕዝብ ለሰላም ስላለው ቦታ ብዙ ተብሏል። የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ጌታቸው ረዳም በቅርቡ ሰጥተውት በነበረ መግለጫ የሕዝቡን ሰላም ፈላጊነት ያብራሩበት መንገድም ይሄንኑ የሚያረጋግጥ ነው።
በእርግጥም፣ በሕዝቡ በኩል ያለውን እውነታም ሆነ አሁን ላይ በተጨባጭ መሬት ላይ የሚታየው ሐቅ ይሄው የሕዝቡን ሰላም ፈላጊነት የሚያንፀባርቅ ተግባር ነው። መጽሐፍ “ሰላምን እሽዋት፤ ታገኟታላችሁም፤” እንዳለ ሁሉ፤ ሰላም ከእርሱ ጋር እንድትሆን በብርቱ ሰላምን እየፈለገና እየናፈቀ ነው ያለው።
በተለይ ወጣቱ ሳይወድ በግድ በየጊዜው በሚገባበት ጦርነት ተሰላችቷል። ሕዝቡ በጦርነቱ ምክንያት ከልቡ ታሟል። ከዚህም በላይ ጦርነትን መጥላቱን፣ በጦርነት መታከቱን የሚያረጋግጡ ነገሮች ይታያሉ። ለዚህም ነው ወጣቱ፣ ከክልሉ በተለያየ መልኩ ወደ ውጪም፣ ወደ ሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎችም በርከት ባለ መልኩ እየተሰደደ የሚታየው።
ሌላው አሁን ላይ ክልሉ ውስጥ የሚገኘው ወጣት ከአሰቃቂ የጦርነት ድባብ ለመውጣት በጨዋነት ጥያቄውን እያቀረበ ይገኛል። ጦርነት ከበቂ በላይ ስላንገሸገሸው ሰላምን አጥብቆ ይሻል።
አሁን ላይ የትግራይ ሕዝብ እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ተረጋግቶ መኖርን ይፈልጋል። መማር፤ መሥራት፤ ሠርቶም የራሱን እና የቤተሰቡን ኑሮ ማሻሻል ይመኛል። ፍላጎቱ ይሄን ተሻግሮ ሲለካም ከራሱና ከቤተሰቡ አልፎ ተርፎ እንደ ክልል እንደ ሀገርም የሚጠቅም ሀብት ከማካበት ጋር ያሰናስለዋል።
ይሄ ፍላጎቱ በየጊዜው ከዚያው ከትውልድ ቀየው አካባቢ በተነሳ ጦርነት አቅሙ ለተሽመደመደው የኅብረተሰብ ክፍል፤ ብሎም በዚሁ ሰበብ እንደ ጦስ ዶሮ ጭዳ ለሆነው ወገኑ ያለው አበርክቶ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በእርስ በርስ ጦርነቱ ሰበብ የከፈለውን ዋጋ በማካካሱ ረገድ አስተዋፅዖ ይኖረዋል። በተለይ በጦርነት ሰበብ ዛሬ ላይ ተመፀዋች ለመሆን ለተገደደው የኅብረተሰብ ክፍል የጎላ ጠቀሜታ አለው።
በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች በጦርነቱ ምክንያት ድንኳን ውስጥ ከመኖራቸው ጋር ተያይዞ የሚያመጣላቸውን ትርጉም ያለው ውጤት ከወዲሁ መገመት ይቻላል። ለጊዜውም እንኳን ቢሆን ድንኳኑ ምቹ እንዲሆንላቸው ያደርጋል። በቂ ምግብና አልባሳት እንዲሁም ሕክምና እንዲያገኙም መደላደልን ይፈጥርላቸዋል። ይኸ ግን ዝም ብሎ በወሬ የሚሳካ አይደለም። ሥራን ይፈልጋል። ሕዝቡ ይሄን ችግሬን ይፈታልኛል ብሎ የሚያስበውን እና የሚመኘውን ሰላም ለማምጣት ምን እያደረገ ነው? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይገባል።
በክልሉ ሰላም እንዲሰፍን ግንባር ቀደም ተዋናይ ሕዝቡ ራሱ እንደመሆኑ መጠን ጥያቄውን መመለስ አለበትም። ሕዝቡ በክልሉ ሰላም እንዲሰፍን ራሱ ተረጋግቶ የመኖር ፍላጎት ያለው መሆኑ ብቻ በተግባር እስካልተረጎመው ድረስ በቂ አይደለም። ከጦርነት አባዜ፤ ጦርነት ቀስቃሽ ከሆኑ ተግባራት፤ ከሁከት፤ ግርግር፤ ውንብድና እና ዘረፋ ተግባራት ከተሰማሩ አካላት ኅብረተሰቡ ራሱን ማራቅ ይኖርበታል። በተለይ ከማዕድን ጋር ተያይዞ የሚሰማው ችግር፤ በወርቅ ዘረፋ በመሳተፍ ሕዝቡ ክልሉ የራሴ የሚለው ጥሪት አጥቶ ወደ ባሰ ድህነት እንዲያመራ ማድረግ የለበትም።
አሁን በተጨባጭ ትግራይ መሬት ላይ እንደሚታየውም ሆነ ጊዜያዊ አስተዳደሩ በመግለጫው እንዳመለከተው፤ ሁሉም በሚባል ደረጃ ሕዝቡ ከየትኛውም ሕገወጥ ተግባር ተሳትፎ ነፃ ነው። በእጅጉ ሰላምን እየፈለገም ነው። ምንም በጦርነቱ ቢፈናቀል፤ ምቹ ባልሆኑ ድንኳኖች ለመኖር ቢገደድም አመራሩ ከዚህ እንደሚያወጣው በትዕግስት ሲጠባበቅ ቆይቷል።
በተለይ ከፕሪቶርያው ስምምነት በኋላ ከዛሬ ነገ የተሻለ ነገር ያመጣልኛል በሚልም በጊዜያዊ አስተዳደሩ ላይ ተስፋውን ጥሎ ከርሟል። ይሄ ሕዝቡ ሰላምን አጥብቆ ለመሻቱ ጥሩ ማሳያ ይሆናል። በትግራይ ሕዝብ በኩል ሰላም ቅድሚያ ተሰጥቶት ለመገኘቱ ከዚህ በላይ ማስረጃ ማፈላለግ አያሻም።
ይሁን እንጂ ‹‹ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ“ እንዲሉ፣ በጊዜያዊ አስተዳደሩ ውስጥ ከፍ ያለ ድርሻ የተሰጠው ሕወሓት ግን ለሕዝቡ ከመሥራት ይልቅ በቡድን ፍላጎት ላይ የተመሠረተ መቧደን ውስጥ ገባ። መረጃዎች እንደሚያሳዩትም፣ አሁን ላይ አመራሩ በሦስት ቡድን ተከፍሎ ይገኛል። ይሄ መቧደንም የሕዝቡ ፍላጎት እና የአንጃዎቹ መንገድ ለየቅል መሆኑን በተግባር ጭምር እየተገለጠበት ያለ እውነት ሆኗል።
የዚህ ክፍፍል መነሻ ደግሞ የፕሪቶርያውን የሰላም ስምምነት እንዲፈጸም ከመሻት እና አለመሻት ጋር የተቆራኘ ነው። እዚህ ላይ ፌዴራል መንግሥትም ስምምነቱ አንቀፁ በሚያዘው መሠረት እንዲተገበር በማድረግ በኩል ኃላፊነት ያለበት፤ እና በዚሁ አግባብ እየሠራ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ስምምነቱን ከፈጸመው አካልም የሚጠበቀውን ግዴታ ከመወጣትና ሥራውን እንዲሳለጥ ከማገዝ ጋር በተያያዘ የሕወሓት አንጃ ቡድን እግር ሲጎትት፤ አለፍ ሲልም ጉዳዩ እንዳይፈጸም ከመሥራት ጋር የሚያያዝ ችግር መኖሩ ሊታወቅ የሚገባው ነው።
ይሄ የሆነው ደግሞ፣ ፖለቲከኞችም እንደሚሉት፣ የፕሪቶርያው ስምምነት አንቀጽ 10 አካታች የሆነ ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲመሠረት ያዛል። ሆኖም አሁን ጌታቸው ረዳ በጊዜያዊ ፕሬዚዳንትነት የሚመሩት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ይሄን አካታችነት መሠረት በማድረግ የተዋቀረ አይደለም። ይሄ ደግሞ ሕወሓት የአመራርነቱን ቦታ በብቸኝነት ሊያስብል በሚያስችል ደረጃ እንዲቆጣጠረው አድርጓል።
ይሄ የብቸኝነት ጉዳይ ደግሞ፣ የእርስ በርስ ፍትጊያና ጥቅም ማስጠበቅን አስቀደመ፣ የራሱ ሳይበቃ ሕዝቡን በየራሱ መስመር ለማሰለፍ የሚደረግ ሙከራ ውስጥ ገባ። ሆኖም ሰላም ፈላጊው በየአንጃው መቧደንን ሳይሆን፤ ስለ ክልሉ ሰላምና ልማት ቆም ብሎ በማሰብ አደብ እንዲገዙ ጥያቄ ማቅረብን መረጠ። እናም የትግራይ ሕዝብ የሰላም ጥያቄ በብዙ የክልሉ አካባቢዎች እየቀረበ፤ ይሄንኑ የሚያቀርበው ሕዝብ ቁጥርም እየተበራከተ መጥቷል።
ይሄ የሕዝብ የሰላም ጥያቄ ደግሞ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ነው። በመሆኑም የሕወሓት አፈንጋጭ አንጃም ሆነ፤ የፌዴራል መንግሥቱ በሕዝቡ ጥያቄ ልክ ምላሽ ሊሰጥ ይገባል። ያልተገናኘው የትግራይ ሕዝብ እና የሕወሓት አንጃ መንገድም፣ ስለ ሕዝቡ የሰላም ጥያቄ ሲባል ፈር እንዲይዝ ማድረግ ያስፈልጋል።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ መጋቢት 16 ቀን 2017 ዓ.ም