ፌስቲቫሉ ለቀጣናዊ ትውውቅና ትብብር ዕድል የፈጠረ ነው!

የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት የሕዝቦች ትስስርና ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ብሎም ሥነልቦናዊ ጉድኝቱ እጅጉን ከፍ ያለ ነው። ለምሳሌ፣ በኢትዮጵያ እና አጎራባች ሀገራት መካከል ያለውን ትስስር መመልከት ይቻላል።

ኢትዮጵያ በሰሜኑ ከኤርትራ ትዋሰናለች፤ በዚህ በኩል ትግርኛ እና አፋርኛ፣ በኢትዮጵያም በኤርትራም ይነገራል። የትግርኛም ሆነ አፋርኛ ተናጋሪ ማኅበረሰብ በሁለቱም ሀገራት ቢኖሩም፤ የሚጋሩትና የሚያስተሳስራቸው ሃይማኖታዊ፣ ማኅበራዊ እና ሥነልቦናዊ እሴት አላቸው።

በምሥራቁ በኩል ከጅቡቲ እና ሶማሊያ ጋር ትዋሰናለች። በዚህም በተለይም የአፋር፣ የሶማሌ ሕዝቦች በሦስቱም ሀገራት ይገኛሉ። እነዚህም የወል ባህል፣ ሃይማኖትና ሥነልቡናዊ እሴት ይጋራሉ። በምዕራብና ደቡብም ከሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ እንዲሁም ኬኒያ ጋር ትዋሰናለች። በዚህም የኦሮሞ ሕዝብን ጨምሮ በርካታ የማኅበራዊ፣ የሃይማኖት እና ሥነ ልቡናዊ እሴቶችን ትጋራለች።

ይሄ ለማሳያነት ያህል ተነሳ እንጂ፤ የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ከዚህም በላይ የሆነ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ መልክዓ ምድራዊ እና በሌሎችም ተፈጥሮም ሰው ሠራሽ ጉዳዮች በፈጠረላቸው ሁነት የተሳሰሩባቸው በርካታ የወል ጉዳዮች አሏቸው።

እነዚህ የወል ጉዳዮቻቸው እና እሴቶቻቸው ታዲያ የቀጣናውን ዕጣ ፈንታ እስከመወሰን የሚዘልቁ ናቸው። ምክንያቱም የተሳሰረ ማንነትና እሴት ብሎም ስሪት ያለው ሕዝብ፤ መነሳቱም ሆነ ውድቀቱ፤ ዕድገቱም ሆነ ድህነቱ፤ ሰላምና አለመረጋጋቱ፤ አጠቃላይም ወደ ሁለንተናዊ ብልፅግና የሚያደርሰው መንገዱ የሚወሰነው እርስ በርሱ ባለው መተባበርና አለመተባበር ላይ ነው።

እናም የቀጣናው ሀገራት እና ሕዝቦች አቅሞቻቸውን ደምረው፤ እሴቶቻቸውን አስተሳስረው፤ ሀብቶቻቸውን አቀናጅተው በጋራ መሥራት፤ በጋራ መልማት ሲችሉ፤ ወደ ሁሉን አቀፍ ብልፅግናቸው ይደርሳሉ። ይሄን ካላደረጉና በተቃራኒው ከሄዱ ግን ቀጣናው የጦርነት፣ የስደት፤ የድህነት እና ረሃብ መገለጫ ሆኖ መዝለቁ አይቀሬ ነው።

በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ የቀጣናውን ታሪክ የሚቀይሩ፤ የኖረ መገለጫዎቹን የሚሽሩ፤ ቀጣናው ተባብሮና ተደምሮ ወደ ከፍታና ሁለንተናዊ ብልፅግና እንዲሸጋገር የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን እየሠራች ይገኛል። ከእነዚህ መካከል ደግሞ ሀብትን ለይቶና በጋራ አልምቶ የመጠቀም መንገድን የመቀየስና የመጀመር ጉዳይ ሲሆን፤ ይሄን የሚያግዘውና ሕዝቦች እርስ በእርሳቸው ተቀራርበው እንዲተዋወቁ፣ ኅብረትና አንድነታቸውን እንዲገነዘቡ የሚያስችሉ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቶችን ማጠናከሩም በሌላ መልኩ የሚታይ ነው።

ከዚህ አኳያ፣ የቀጣናው ሕዝቦች ባህልና እሴቶቻቸውን የሚተዋወቁበት፤ አንዱ ስለ ሌላኛው የበለጠ የሚረዳበት፤ አንድነትና አብሮነታቸውን የሚያጎለብቱባቸውን፤ እንዲሁም የወል እሴቶቻቸውን የሚገላለጡበትን ዓውድ መፍጠር ተገቢ ነው። ይህ እንዲሆን ደግሞ ኢትዮጵያ በትኩረት እየሠራች ነው።

ለምሳሌ፣ ከሰሞኑ የተጠናቀቀው እና “ጥበባትና ባህል ለቀጣናዊ ትስስር” በሚል መሪ ሀሳብ ከመጋቢት 11 እስከ 14 ቀን 2017 ዓ.ም በሀገራችን በአዲስ አበባ ከተማ በአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ማዕከል የተካሄደው ሁለተኛው የምሥራቅ አፍሪካ የጥ በባትና ባህ ል ፌስ ቲቫል ለዚህ ጉል ህ ማሳያ ነው።

በዚህ ፌስቲቫል፣ ኢትዮጵያም ባህሎቿን፣ ታሪኳንና እምቅ የተፈጥሮ ሀብቷን አስተዋውቃለች። ከዚህ በላይ ግን የምሥራቅ አፍሪካ ሕዝቦች እርስ በርስ እንዲተዋወቁ፤ የወል ሀብቶቻቸውን እንዲገልጡና እንዲረዱ፤ በቀጣይ የወል እሴቶቻቸውን እና አቅሞቻቸውን አስተባብረው ለተሻለ አብሮነታቸውና እድገታቸው እንዲሠሩ የመነጋገርና የመወያየት ዕድልን የፈጠረላቸው ሆኗል።

ፊስቲቫሉ፣ የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት ሚኒስትሮች እና ከ140 በላይ የሚሆኑ የተለያዩ የባሕል ቡድኖችን አሳትፏል። የጥናትና ምርምር ሥራዎች ቀርበውበታል፤ ሲምፖዚየሞች፣ የባህልና የዕደ ጥበብ ምርት ዓውደ ርዕዮች፣ ሙዚቃዎች፣ የፊልምና የቴአትር ፌስቲቫሎች እንዲሁም የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራትን ብዝኃነት የሚያንጸባርቁ ሁነቶችን አስተናግዷል።

እነዚህን ሁሉ ሁነቶች ባስተናገደው ፌስቲቫል ላይም፣ ከኢትዮጵያ፣ ከጅቡቲ፣ ከሶማሊያ፣ ከደቡብ ሱዳን፣ ከሩዋንዳ፣ ከዩጋንዳ፣ ከታንዛኒያ፣ ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ከብሩንዲ የተውጣጡ ልዑካን የተሳተፉ ሲሆን፤ ሁነቱም የየሀገራቱ የዘርፉ ሚኒስትሮች ጭምር የተሳተፉበት ነው። ከዚህ አኳያ ሲመዘን ፌስቲቫሉ በሀገራቱ መካከል የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርን ለማጠናከር፣ የባህል ዲፕሎማሲና ቀጣናዊ ትስስር እንዲጎለብት ምቹ ሁኔታን የፈጠረ ነው!

አዲስ ዘመን ማክሰኞ መጋቢት 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You