
አዲስ አበባ፤ ለ2017/18 የምርት ዘመን እስከ አሁን ከ836 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ የአፈር ማዳበሪያ ወደ ሀገር ውስጥ መጓጓዙን የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር አስታወቀ። የማዳበሪያ ሥርጭት በሕገ ወጥ ደላሎች እንዳይስተጓጎል የአቅርቦት ሥራን ዲጂታላይዝድ የማድረግ ሥራዎች መጀመራቸውን ተጠቁሟል፡፡
ለምርት ዘመኑ ግብዓት 60 ሺህ ሜትሪክ ቶን ዳፕ የተሰኘ የአፈር ማዳበሪያ የጫነችው 18ኛዋ መርከብ ጅቡቲ ወደብ ደርሳ የማራገፍ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ አመልክቷል።
በዚሁ መሠረት እስከ መጋቢት 14 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ 964 ሺ 118 ሜትሪክ ቶን የአፈር ማዳበሪያ በ18 መርከቦች ተጭኖ ጅቡቲ ወደብ መድረሱ ተገልጿል።
ከዚህም ውስጥ 836 ሺህ 253 ነጥብ 2 ሜትሪክ ቶን ወደ ሀገር ውስጥ መጓጓዙንና 127 ሺህ 865 ሜትሪክ ቶን ገደማ በወደብ ላይ እንደሚገኝ ሚኒስቴሩ አመልክቷል።
በ18 መርከቦች የተጫኑት እና ወደ ሀገር ውስጥ የተጓጓዙት ዩሪያ እና ዳፕ ማዳበሪያዎች ናቸው።
የአፈር ማዳበሪያ ወደ ሀገር ውስጥ የተጓጓዙት በደረቅ ጭነት ተሽከርካሪ እና ባቡር መሆኑን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል።
በተያያዘ ዜናም በአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት እና ሥርጭት ዙሪያ በሕገ ወጥ ነጋዴዎች፣ በደላሎች እና በማዳበሪያ ግዥ ሥርዓት ዙሪያ የነበሩ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ አሠራርን የማዘመንና ዲጂታላይዝድ የማድረግ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ በግብርና ሚኒስቴር የኢንቨስትመንትና ግብዓት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ሶፍያ ካሣ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
ግብርናን በተለይ የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦትና ስርጭትን ከተለምዶ (ከወረቀት) አሠራር ወደ ዲጂታል ማሸጋገር ወቅታዊና የመንግሥት የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ ይህንን ሥራ የሚያግዝ ሶፍትዌርም እየበለፀገ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
ሶፍትዌሩ የአርሶ አደሩ የማዳበሪያ ፍላጎት በመሬቱ ልክና በሰብል ዓይነት መሆኑን ከማረጋገጡም ባሻገር፤ በስርጭት ወቅት የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመቅረፍ ትልቅ ፋይዳ እንዳለውም ጠቅሰዋል። በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልልም በተሳካ ሁኔታ ሙከራ እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የአፈር ማዳበሪያና ምርጥ ዘር አቅርቦትና ስርጭትን ዲጂታላይዝ ከማድረግ ጋር ተያይዞ የተዘጋጀው ሰነድ ላይም ውይይት ተደርጓል። በቀረበው ሰነድ ላይ ተሳታፊዎች ሃሳብ የሰጡ ሲሆን፣ ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎችም ከመድረኩ ምላሽ ተሰጥቷል።
በመድረኩም ከተለያዩ ክልሎች ለተውጣጡ የዘርፉ ባለሙያዎችና የሥራ ኃላፊዎች እየለማ የሚገኘው ሶፍትዌር አስፈላጊነትና አተገባበር ላይ ያተኮረ በንድፈ-ሃሳብና በተግባር የታገዘ ሥልጠና እንደተሰጣቸውም የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ማክሰኞ መጋቢት 16 ቀን 2017 ዓ.ም