“ትምህርት ቅንጦት ሳይሆን መሠረታዊ ሰብዓዊ መብት ነው” – ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የትምህርት ሚኒስትር

አዲስ አበባ፡- ትምህርት ቅንጦት ሳይሆን መሠረታዊ ሰብዓዊ መብት በመሆኑ ሕጻናትን እንዲማሩ ምቹ ሁኔታ መፍጠር እንደሚገባ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገለጹ፡፡

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የአማራ ክልል የትምህርት ንቅናቄ መድረክ ትናንት በባሕርዳር ከተማ ሲካሄድ እንዳሉት፡፡ ትምህርት ቤቶች ለልጆቻችን አመች፤ ዕውቀት መቀበል የሚችሉ ደስተኛ ልጆች ለማፍራት የሚያስችሉ እንዲሆኑ በመላው ሀገሪቱ እየሠራን ነው።

በተለያዩ ክልሎች የተነሱ ግጭቶች በትምህርት ዘርፉ እያደረግን ያለነውን የለውጥ ሂደት ከፉኛ እየተፈታተኑት ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ ግጭቶቹ በተፈጠሩባቸው አካባቢዎች ያሉትንም ሕጻናት እና ወጣቶች በትምህርት ሊያገኙት የሚችለውን የወደፊት ዕድል ክፉኛ ሲያጨናግፉት እናያለን ነው ያሉት።

እንደ ሀገር “ትምህርት ለትውልድ” የትምህርት ቤቶች መሠረተ ልማት ማሻሻል ሕዝባዊ ንቅናቄ ከተጀመረ ጀምሮ ባለፉት ጊዜያት ከ39 ቢሊዮን ብር በላይ ሀብት ሕዝቡ አሰባስቧል ነው ያሉት። በዚህም 5 ሺህ 957 ቅድመ አንደኛ፣ አንድ ሺህ 738 የአንደኛ እና መካከለኛ፣ 268 የሁለተኛ ደረጃ አዳዲስ ትምህርት ቤቶች ተገንብተዋል ብለዋል።

31 ሺህ 252 ትምህርት ቤቶች ጥገና እና እድሳት ተደርጎላቸው የመማር ማስተማር ሥራውን እንዲያከናውኑ መደረጉንም አንስተዋል።

በግጭት ውስጥም ሆኖ በአማራ ክልል ብቻ የትምህርት ለትውልድ የትምህርት ቤቶች መሠረተ ልማት ማሻሻል ሕዝባዊ ንቅናቄ ከ2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ ሀብት በማሰባሰብ አዳዲስ የትምህርት ቤቶች ግንባታ እና የነባር ትምህርት ቤቶች ጥገና መከናወኑን ገልጸዋል።

“ትምህርት ቅንጦት ሳይሆን መሠረታዊ ሰብዓዊ መብት ነው” ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ ሕጻናት ወደፊት ዕጣ ፈንታቸውን የሚገነቡበት፣ ችሎታቸውን የሚከፍቱበት ቁልፍ መሣሪያ እና ድልድይ ነው ብለዋል። ነገር ግን በብዙ የዓለም ክፍሎች የሚካሄድ ግጭት እና ጦርነት ይህን መብት እየጣሰ ነው ብለዋል።

የትጥቅ ግጭት የሚያስከትለው ተፅዕኖ ከፍተኛ ነው፣ ትምህርት ቤቶች ይወድማሉ፤ መምህራን ይፈናቀላሉ፣ ቤተሰቦች ከመኖሪያቸው ይለቃሉ፣ በብዙ ዘመን እና ድካም የተገነባውን የኅብረተሰቡን መዋቅር የሚያፈርስ እና የሕጻናት እና ወጣቶችን ብሩህ የወደፊት ተስፋ የሚሸረሽር እንደሆነም አመልክተዋል።

በኢትዮጵያ ግጭት ብሎም ሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ አደጋ በተከሰተባቸው ክልሎች በርካታ ሕጻናት እና ወጣቶች ከትምህርት ገበታ ውጭ ሆነዋል ያሉት ሚኒስትሩ፤ በዚህ ዓመት እንደ ሀገር ወደ ትምህርት ቤት መምጣት ከነበረባቸው ውስጥ ከ7 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሕጻናት ከትምህርት ገበታ ውጭ መሆናቸውን መረጃዎች ያሳያሉ ብለዋል።

በአማራ ክልል ብቻ አሁን ባለው ግጭት ምክንያት ከአራት ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ሆነዋል ነው ያሉት። ከ3 ሺህ 700 በላይ ትምህርት ቤቶች ከመማር ማስተማር ሥራው ውጭ ሆነዋል ነው ያሉት። የዚህን ክፉ ተግባር ውጤት ምንነት ከዛሬም በላይ ገና ወደፊት ይገለጣል ብለዋል።

ትምህርት የረጅም ጊዜ ሥራ ነው ያሉት ሚኒስትሩ ትምህርት በአንድ ዓመት እና በሁለት ዓመት ሲቋረጥ የሚፈጠረው የሥነ ልቦና ጫና እጅግ ከባድ ነው ብለዋል።

እነዚህ ልጆች ወደ ትምህርታቸው ተመልሰው ቢገቡም እንኳን የደረሰባቸው የሥነ ልቦና ቀውስ ትምህርት የመቀበል አቅማቸውን እንደሚጎዳው ነው የተናገሩት። በተጨማሪም በግጭት ጊዜ ያለፈውን ትምህርት ለማካካስ አስቸጋሪ ይሆናል ብለዋል። እንደምንም አካክሰው እንኳን ትምህርታቸውን ቢቀጥሉ በዕድሜ ከነሱ ካነሱ እና ከታናናሾቻቸው ጋር መማራቸው ጫናውን የጎላ ያደርገዋል ነው ያሉት።

ግጭት የልጆቻችንን የወደፊት ዕድል ክፉኛ እንዳያበላሽ መጠንቀቅ፤ በግጭቶች አካባቢ ያሉ ትምህርት ቤቶች ዓለም አቀፍ ሕግጋት እንደሚያዙት ከማንኛውም ወገን ጥቃት እንዳይደርስባቸው እና ልጆች ትምህርታቸው እንዳይሰናከልባቸው ማድረግ ይገባል ብለዋል። ይሄን ለማድረግ የወላጆች እና የአካባቢው ማኅበረሰብ ሚና ከፍተኛ መሆኑንም አመላክተዋል።

እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በኢትዮጵያዊነቱ ብቻ ጥራት ያለው ትምህርት እንዲያገኝ በማድረግ ብቁ እና ብቃት ያላቸው፣ ሥነ ምግባር የተላበሱ ትውልዶችን ማፍራት እንችላለን ማለታቸውን አሚኮ ዘግቧል።

“ትምህርት ለትውልድ” የትምህርት ቤቶች መሠረተ ልማት ማሻሻል ሕዝባዊ ንቅናቄ የተሳካ እንዲሆን በክልሉ ያሉ ነዋሪዎች፣ የቀድሞ ተማሪዎች፤ ታዋቂ ግለሰቦች፣ በውጭ ሀገር የሚኖሩ የክልሉ ተወላጆች፣ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ ባለሀብቶች፣ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ የልማት ድርጅቶች በትውልድ ቦታቸው አስተዋፅዖ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ማክሰኞ መጋቢት 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You