አዲስ አበባ፦ የዜግነት እውቅና ተነፍጓቸው በስደት በተለያዩ ሀገራት ይኖሩ ለነበሩ ኢትዮጵያውያን ማንነታቸውን የሚያረጋግጥ ሰነድ ወይም ፓስፖርት እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡ በኢትዮጵያ ለሚኖሩ ለ1ሺህ 247 የተለያዩ አገራት ዜጎች ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ እንዲያገኙ መደረጉም ተገልጿል፡፡
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም ትናንት በሳምንታዊ መግለጫው በተለያዩ ምክንያቶች ከአገራቸው ወጥተው በደቡብ አፍሪካ፣ በሱዳንና በመካከለኛው ምሥራቅ ለዓመታት ዜግነታቸው እውቅና ተነፍጎት ‹‹እንደ አገር አልባ›› ይኖሩ ለነበሩ ከ40ሺ በላይ ኢትዮጵያዊያን እውቅና እንዲያገኙ መደረጉን ገልጸዋል፡፡
ቃል አቀባዩ ኢትዮጵያውያኑ በተጠለሉበት አገር የመኖሪያ ፈቃድ ለማግኘት ሲሉ የሌላ ሁለተኛ አገር ዜጋ ሆነው የቀረቡና የትውለደ ኢትዮጵያዊ መታወቂያ ተከልክለው በችግር ውስጥ የቆዩ መሆናቸውን አስረድተው፤ ተገቢው ማጣራት እየተደረገ መታወቂያ የመስጠቱ ተግባር እንደሚቀጥልና ከተያዘው በጀት ዓመት ጀምሮ የአሠራር ለውጥ መደረጉን ገልጸዋል፡፡
ቃል አቀባዩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በተለያዩ ሀገሮች በእስር ላይ የሚገኙ 2ሺ250 ዜጎች ተፈትተው ወደ አገር ቤት እንዲመለሱ ጥረት ማድረጉን፤ እስከአሁንም 450 ዜጎች ከሳዑዲ አረቢያ ጂዳ መመለሳቸውን፣ 450 ዜጎች ደግሞ ዛሬ ወደ አገር ቤት እንደሚመለሱ፣ የተቀሩትም በሳምንት ጊዜ ውስጥ ወደ ሀገራቸው እንደሚገቡ ጠቁመዋል፡፡
እንደ ቃል አቀባዩ ማብራሪያ የሠሩበት ደሞዝ ያልተከፈላቸውም ደመወዛቸው እንዲከፈላቸው በተደረገው ጥረት በጂዳ ሚሲዮን አማካኝነት ብቻ 1ሚሊዮን 600ሺ ብር ክፍያ እንዲፈጸም ለማድረግ ተችሏል፡፡ ሚኒስቴሩ በውጭ ያሉ ዜጎች ደህንነት እንዲረጋገጥና መብታቸው እንዲከበር በትኩረት በመሥራት ላይም ይገኛል፡፡
ቃል አቀባዩ አያይዘው እንደገለጹት ለኢትዮጵያ አስተዋጽኦ ያደረጉ በኢትዮጵያ ለሚኖሩ የውጭ ዜጎች፣ ራስ ተፈሪያኖችና ቤተ እሥራኤላዊያን 460 አመልካቾች እንደ ግሪክ፣ ጣሊያን፣ አርመን የመሳሰሉ ከኢትዮጵያ ጋር የረጅም ጊዜ ትስስር ያላቸውና በከፍተኛ ኢንቨስትመንት ላይ የተሰማሩ አገራት ዜጎች ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ አግኝተዋል፡፡ 688 ቤተ አሥራኤላዊያንና 99 የራስ ተፈሪያኖችም የዚህ ዕድል ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡
ኢትዮጵያ ይህንን በማድረጓ በኢንቨስትመንትና ቱሪዝም መስኮች ትልቅ ውጤት እንድታገኝ ከማስቻሉ በተጨማሪ የኢትዮጵያ የባህል አማባሳደሮች ሆነው ለሌሎች በማስተዋወቅ ከፍተኛ ድርሻ እንደሚወጡ ቃል አቀባዩ ገልጸዋል፡፡
አዲሱ ገረመው