
ወጣት ቃልኪዳን አሳዬ ይባላል፤ ልደትና እድገቱ፣ የትምህርቱም ጅማሬ በገጠራማው የሀገራችን ክፍል ከሆኑ፤ ነገር ግን በትጋታቸው ውጤታማ ከሆኑ ወጣቶች አንዱ ነው:: ወጣት ቃልኪዳን፣ ይሄንን ሲያስረዳ ”በብዙ ችግር አልፈን በጥረታችን ነው እንጂ፣ እንደ ከተማ ልጆች ሁሉም ተመቻችቶልን ተምረን አይደለም ውጤታማ የሆንነው፤” ይላል::
ወጣት ቃልኪዳን እንደሚለው፣ ገጠር ላይ የሚያስተምሩ መምህራን ከመኖሪያ ቤት ችግር ጀምሮ ደሞዝ በወቅቱ አይደርሳቸውም፤ ከዚህ የተሻገሩ ሌሎችም ብዙ ችግሮች አሉባቸው:: በተለይ ቀደም ብሎ አንድ መምህር ሁሉንም የትምህርት ዓይነት ከማስተማሩ አንፃር መሰላቸትና መድከም በስፋት ይስተዋላል::
የመማሪያ ክፍል ጉዳይም ቢሆን ብዙም ለመማር ማስተማሩ ሂደት በቂና ምቹ የማይሆኑባቸው አጋጣሚዎችም አሉ:: ለምሳሌ፣ በአንድ ክፍል ከ50 በላይ ተማሪ ተጨናንቆ የሚማርበት አግባብ መኖሩ መምህራን ሁሉንም ተማሪ በእኩል የሚያበቁበትን እድል የሚያቀጭጭ ነው:: በመሆኑም ብቁ በመሆንና ያሰበበት የመድረስ ዓላማ የሰነቀ ተማሪ፣ በዚህ መካከል የራሱን ጥረት የማድረግ ከፍ ያለ ግዴታ ውስጥ ይገባል::
ወጣት ቃልኪዳንም፣ በእንደዚህ የመማር ማስተማር አውድ ውስጥ ያለፈ፤ የሚፈልግበት ቦታ ለመድረስም ከፍ ያለ ኃላፊነትና ጫናን መቀበል የግድ በሚልበት የገጠሩ አከባቢና ትምህርት ቤት ያለፈ ቢሆንም፤ ከመጀመርያው ጀምሮ ራሱን ለማብቃትና ያሰበበት ለመድረስ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል::
”ጥረቴ ትምህርቶችን ሸምድዶ አንደኛ የሚወጣ የደረጃ ተማሪ ለመሆን ሳይሆን እውቀት ለመጨበጥ ብቻ ነበር” የሚለው ወጣት ቃልኪዳን፤ እውቀት ከጨበጠ ደረጃው የትም አይሄድብኝ የሚል እምነት እንደነበረውም ያስረዳል:: ይሄ ትጋቱም አብሮት አድጎ የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን አጠናቅቆ ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ሲመረቅ በተመረቀበት ትምህርት ክፍልና ከዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ ነጥብ በማምጣት በሁለት ወገን የወርቅ ተሸላሚ እንዳደረገውም ይናገራል::
ሌላዋ ወጣት ብስራት እጅጉ በበኩሏ፤ በመማር ማስተማር ሂደቱ ከሚስተዋሉ በርካታ ችግሮች ጋር የመምህራን የሥነምግባር ችግር ሲታከልበት፣ ተማሪዎች የሚፈለገውን እውቀትና ክህሎት ይዘው እንዳያድጉ ይሆናሉ:: ይሄ ደግሞ ተማሪዎች በትምህርት ቦቶች ካሉባቸው እግሮች በተጓዳኝ ከመምህራኖቻቸው የሚፈለገውን እውቀት እንዳያገኙ ስለሚያደርጋቸው የራሳቸውን ከፍ ያለ ጥረት ለማድረግ ይገደዳሉ:: እሷም ይሄ ችግር ከገጠማቸው ተማሪዎች መካከል አንዷ ናት::
በግል ጥረቷ ታግዛ በመማር ውጤታማ መሆን በመቻሏ ዛሬ በትልቅ የሥራ ኃላፊነት ላይ ተመድባ በመንግሥት መሥርያ ቤት እያገለገለች የምትገኘው ወጣት ብስራት፤ ትምህርት ቤቶች ለመማር ማስተማር ሂደቱ ራሳቸውን ምቹ ማድረግ፤ ጥቂት የሥነምግባር ጉድለት ያለባቸው መምህራንም የብዙሃኑን ስም ከሚያጠለሽ ተግባራቸው እንዲታረሙ የሚያስችል ሥራ ማከናወን እንደሚገባ ትመክራለች::
እነዚህን ሁለት ስኬታማ ወጣቶች ተሞክሮ ለማሳያነት አቀረብን እንጂ፤ የመማር ማስተማሩን ሂደት የሚያውኩ እና ተማሪዎችን የሚያጋጥሙ በርካታ ተግዳሮቶች በትምህርት ተቋማት ውስጥና አካባቢዎች ላይ የመታየታቸው ጉዳይ የአደባባይ ምስጢር ነው:: ይሄ ደግሞ በተማሪዎች ብቻ ሳይሆን፣ በትምህርት ጥራትም ሆነ አጠቃላይ በማሕበረሰቡና በማሕበረሰብ ግንባታ ሂደቱ ላይ ጉልህ አሉታዊ ተጽእኖ ማሳደሩ እሙን ነው::
ለዚህ ማሳያ ከሚሆኑ ወጣቶች መካከል ልምዷን ያከፈለችን ደግሞ፣ ቦሌ መሰናዶ ትምህርት ቤት እስከ አስረኛ ክፍል እንደተማረች የነገረችን ራሄል ቦንሳ ናት:: ወጣት ራሄል የትምህርት ቤት ቆይታ ጊዜዋን እያስታወሰች እንደነገረችን፤ ተወልዳ ያደገችው አዲስ አበባ ከተማ ካዛንቺስ እንደመሆኑ፣ እስከ 10ኛ ክፍል ያለ ትምህርቷን በቦሌ መሰናዶ ትምህርት ቤት ነው የተማረችው::
ከአንደኛ ደረጃ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ያለውን ትምህርቷን የተከታተለችበት ይህ ትምህርት ቤት ታዲያ፤ በወቅቱም የተግባር ትምህርት ለመቅሰም እንኳን የሚያስችል የተሟላ ቤተሙከራ አልነበረው ታስታውሳለች:: ከዚህ ውጪ በጥቂት መምህራን የሚታይ የሥነምግባርና የአቅም ችግር፤ እንዲሁም በአንንዳንድ መምህራን ዘንድ የሚታየው የኢኮኖሚያዊ (የቤትና ሌላም) ችግሮች፤ በትምህርት ቤቶች ከባቢ የሚታዩ ያልተገቡ እንቅስቃሴዎችና ሌሎችም በመማር ማስተማሩ እና በተማሪዎች ውጤታማነት ላይ ጉልህ ጫና ነበራቸው::
“ትምህርት መጨረሻ የሌለው ቢሆንም እኔ በሳይንሱ መስክ ፕሮፌሰር እስከምሆን ሳላቋርጥ የመማር ሕልም ስለነበረኝ ራሴን ለማብቃት እጥር ነበር” የምትለው ራሄል፤ በአንድ አጋጣሚ ከመምህሯ ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ምክንያት ትምህርቷን ከአስረኛ ክፍል አልፋ ላለመግፋት እንደተገደደችም በቁጭት ታነሳለች:: ከዚህ በኋላ አረብ ሀገር በመሄድ (ያውም በአስቸጋሪው የእግርና የባሕር ጉዞ) በስደት መሄዷን፤ በሂደትም ወደ ጀርመን አምርታ ትዳር መስርታና ልጆች ወልዳ መኖር መጀመሯን ትናገራለች::
በዚህ መልኩ በመማር ማስተማር ሂደቱ ላይ የሚታዩ ችግሮችን እና አጠቃላይ ተጽዕኖውን አስመልክቶ የተለያየ ባለድርሻዎችን አነጋግረናል:: ከእነዚህ መካከል፤ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ አንዱ ነው:: በጉዳዩ ዙሪያ የቢሮው ምክትል ኃላፊ ዶክተር ታምራት ይገዙ እንደሚናገሩት፤ ክልሉ የትምህርት ጥራት እንደ ሀገርም እንደ ክልልም በሰፊው አደጋ ላይ ከወደቀባቸው ክልሎች አንዱ ነበር:: የዚህ ምክንያት ደግሞ በክልሉ ደረጃቸውን ያልጠበቁ ትምህርት ቤቶች በብዛት መኖር መሆኑ ተገምግሟል:: በክልሉ እንደ ትልቅ የመማር ማስተማር ተግዳሮት የሚታየውም ይሄው ደረጃቸውን ያልጠበቁ ትምህርት ቤቶች መኖር ነበር::
እንደ ኃላፊው ገለጻ፤ ቢሮው “በትምህርት ለትውልድ” እንዲሁም “አንድ መጽሐፍ ለአንድ ተማሪ”በሚል ኢንሼቲቭ ከ940 ሚሊዮን ብር በላይ በማሰባሰብ ችግሩን ለመፍታት ሲሰራ ቆይቷል:: ከተሰባሰበው ውስጥ 470 ሚሊዮን ብሩ በዓይነት፤ በጉልበት፤ በእውቀት የተሰባሰበ ነው:: 200 ሚሊዮን ብሩ “አንድ መጽሐፍ ለአንድ ተማሪ” በሚለው የተሰባሰበ ሲሆን በርካታ ደረጃቸውን ያልጠበቁ ትምህርት ቤቶችን ከደረጃ አራት ወደ ደረጃ ሦስት፤ከደረጃ ሦስት ወደ ደረጃ ሁለት እንዲያድጉ ለማድረግ ውሏልም ይላሉ::
በሀብቱ መጽሐፍት በሌለባቸው ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች መጽሐፍት እንዲያገኙ የተደረገበት ሁኔታ መኖሩንም ተናግረዋል:: የመንግሥትም ድጋፍ ታክሎበት ከአራተኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል መጻፍ ታትሞ መሰራጨቱን አንስተዋል:: አሁን ላይ የመጽሐፍት ጥምርታ ስርጭት አንድ ለሦስት መድረሱንም ተናግረዋል:: ሁለተኛው ፌዝ ከቅድመ አንደኛ እስከ ሦስተኛ ክፍል ያለ መጽሐፍ ጨረታ ላይ መሆኑን ነግረውናል:: በቅርቡ ታትሞ ይሰራጫል፤ ከሰባት እስከ ስምንት ያለው መጽሐፍም እንዲሁ በቀጣይ ይታተምና ተማሪ እጅ ይደርሳልም ብለዋል::
“በክልሉ የማስተማር ስነ ዘዴ ስልጠና ያልወሰዱ በርካታ መምህራን አሉ” የሚሉት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፤ ቢሮው የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለመማር ማስተማር ምቹ እንዲሆኑ ከማመቻቸት ባሻገር ተማሪዎች ውጤታማ እንዲሆኑ፤ ሁሉንም መምህራን ለማብቃት በቅንጅት እየሰራ ስለመሆኑም ያስረዳሉ::
ሥራውን በክልሉ ከሚገኙ አራት የፌዴራል ዩኒቨርሲቲዎች እና ሁለት የመምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጆች ጋር እየተሰራ ስለመሆኑም አንስተዋል:: ይሄም በ2017 በጀት ዓመት ትምህርት ዘመን የትምህርት ጥራት ክፍተትን በመሙላት መሻሻል እንዲያሳይ ማገዙንም ተናግረዋል::
የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ብርሃነመስቀል ጠና በበኩላቸው፣ ዩኒቨርሲቲው በትምህርት ዩኒቨርሲቲ ደረጃ ከተቋቋመ ጀምሮ በኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ ጥራት ያላቸው መምህራን፤ የትምህርት ባለሙያዎችና መሪዎችን እያሰለጠነ መሆኑን ይናገራሉ:: በተለይ መምህራንን ሲያሰለጥን የቆየበትና እያሰለጠነ የሚገኝበት መንገድ እስካሁን የትምህርቱ ዘርፍ ሲገጥሙት የነበሩ ተግዳሮቶችን የሚፈታና የትምህርትን ጥራት በተገቢው ሁኔታ ማስጠበቅም የሚያስችል ነው:: ዩኒቨርሲቲውም አሁን ላይ በተለይ ከመምህራን ጋር ተያይዞ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት በሀገር አቀፍ ደረጃ የትምህርት ስነ-ምህዳሩን ለማሻሻል የታለሙ ተነሳሽነቶችን በግንባር ቀደምትነት ለመተግበርም የሚያግዝ ነው::
“ለመምህራን እየሰጠነው ያለው ስልጠና ከመምህራን ጋር ተያይዞ ከዚህ ቀደም የሚነሱ እንዲሁም የፊቱን ያህል ጎልተውም ባይሆን አሁንም እየተነሱ ያሉ ክፍተቶችን የሚሞላ ነው፤” ይላሉ::
ከስልጠናው ጎን ለጎን ዩኒቨርሲቲው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የትምህርት ጥራትን ማስጠበቅ፤ እንዲሁም ዘርፉ የሚገጥሙትን ተግዳራቶች ለመፍታት የሚያስችል፤ ፖሊሲን ለማውጣትና ለመተግበር ግብዓት የሚሆን ምርምር ላይ እየሰራ ስለመገኘቱ ያነሳሉ:: እስካሁን ይሄን መሰል ፋይዳ ያላቸው በርካታ ምርምሮችን ማበርከቱንም በማሳያነት ይጠቅሳሉ::
እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ፣ በአካባቢው ለሚገኙ የማሕበረሰብ ክፍሎች ሕይወታቸውን በተሻለ መምራት የሚችሉበት አገልግሎት እየሰጠ ነው:: ይሄ ደግሞ የአጠቃላዩን ትምህርት ዘርፍ ካለበት ተግዳሮት በማሻገር ውጤታማ ማድረግን ታሳቢ ያደረገ ነው:: ሆኖም ሁሉንም ዓይነት ተልእኮውን ዩኒቨርሲቲው ብቻውን ሊወጣው አይችልም:: የትምህርቱ ዘርፍም በባህርይው የአንድ ተቋም ብቻ ሳይሆን የሁሉንም ተቋም ተሳትፎ የሚጠይቅ ነው:: ከዚህ አንፃር በዘርፉ የሚጠበቀውን ለውጥ ለማምጣት ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ መሥራቱ የግድ የሚል እና አስፈላጊም ሆኖ ተገኝቷል::
መሆኑም አጋር አካላት ከዩኒቨርሲቲው ጋር በቅንጅት ለመሥራትና ለውጥ ለማምጣት ፈጣን ምላሽ መስጠት ይጠበቅባቸዋል:: ትምህርት ቤቶች፤ ትምህርት ቤቶችን የሚመሩ አካላትም ለመማር ማስተማሩ ሂደት ፈተና የሆኑ ተግዳሮቶችን በመፍታት እንዲሁም እግረ መንገዳቸውን የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ በየፊናቸው የግድ የየራሳቸውን ጠጠር በመጣል መትጋት ይጠበቅባቸዋል::
በትምህርት ሚኒስቴር የአጠቃላይ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አየለች እሸቴ እንደሚናገሩት፤ በኢትዮጵያ መማር ማስተማር ሂደቱን ከሚገጥሙት ተግዳሮቶች መካከል አንዱ ደረጃቸውን ያልጠበቁ ትምህርት ቤቶች መኖራቸው ስለመሆኑ ይናገራሉ::
እንደ ሚኒስትር ዲኤታዋ ገለጻ፤ የትምህርት ቤቶች ከደረጃ በታች መሆን እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በቂና ብቁ መምህራን አለመኖር፤ ያሉትም የማስተማር ሥነዘዴ ዝግጅት ክፍተት ያለባቸው መሆናቸው፤ ለመምህራን የሚሰጠው የሥራ ላይ ሥልጠና አናሳ መሆን፤ የትምህርት ግብዓት በበቂ አለመሟላት፤ የተማሪዎች የትምህርት ፍላጎት እና ራስን ለማብቃት የሚደረግ ጥረት ዝቅተኛ መሆንም አሁን ላይ እንደ ሀገር የመማር ማስተማሩን ሂደት በብርቱ እየፈተኑ ያሉ ሌሎቹ ተግዳሮቶች ናቸው::
በተለይ በከተሞች አካባቢ የሚታየው የመምህራን የመኖርያ ቤት ጉዳይ ተደማሪ ችግር መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ እነዚህ የመምህራን የስነ-ምግባር ችግርን ጨምሮ ተግዳሮቶቹ ተደማምረው ከትምህርት ቤት ጀምሮ እስከ ግለሰብ፤ ማሕበረሰብ፤ትምህርት ተቋማት፤ ትምህርት ዘርፍና ሀገር ድረስ አሉታዊ ተጽእኖ የሚያሳድሩ ስለመሆናቸውም ያስረዳሉ:: ትምህርት የሁሉም ዘርፍ መሰረት እንደመሆኑ በኢኮኖሚው፤ በማሕበራዊው፤ በፖለቲካዊውና በሌሎች መስኮች ላይ ሊያሳድሩት የሚችሉት ተጽዕኖ በቀላሉ ታይቶ የሚታለፍ እንዳልሆነም ያብራራሉ::
እንደትምህርት ሚኒስቴርም በተለይ ከመምህራን ጋር ተያይዞ ዘርፉን የሚገጥሙትን ተግዳሮቶች ለመፍታት እና የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ባለፈው ክረምት ብቻ ከ50 ሺህ በላይ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህራን የሥራ ላይ ሥልጠና እንዲወስዱ ተደርጓል ይላሉ:: በተጨማሪም በአሁኑ ጊዜም የመምህራን የቅድመ ሥራ ላይ ሥልጠና በዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም በ38ቱ የመምህራን ትምህርት ኮሌጆች እየተሰጠ ስለመገኘቱም ይጠቅሳሉ:: ለመምህራኑ እየተሰጡ ካሉ የሥራ ላይ ስልጠና ርዕሰ ጉዳዮች መካከል ከማስተማር ስነ- ዘዴ እና ስነ- ምግባር ጋር የተያያዙ እንደሚገኙባቸውም ያወሳሉ::
እንዲህ ዓይነቱ የመምህራን የሥራ ላይ ሥልጠና በፍጥነት በሚለዋወጥ ዓለም ውስጥ ተማሪዎች ችሎታና ብቃት እንዲያገኙ፤ አምራች ዜጋ መሆን የሚያስችላቸውን እውቀት፣ እንዲጨብጡ ለማስቻል ብሎም የትምህርትን ጥራት ለማስጠበቅ ዓይነተኛ መፍትሄ ስለመሆኑም ያነሳሉ:: የመምህራን የመኖርያ ቤት ችግርም በተለያየ መንገድ እንዲፈታና በመማር ማስተማሩ ላይ የራሱ የሆነ አሉታዊ ተጽእኖ እንዳያሳድር ተሰርቷል፤ እየተሰራም ይገኛል ብለዋል::
እንደ ሚኒስትር ዴኤታዋ ማብራሪያ፤ በትምህርት ሚኒስቴር በተለይ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ መምህራንን ከማብቃት ባሻገር ከሌሎች ዘርፎችና ተቋማት ጋር በትብብር መሥራትም አስፈላጊ መሆኑ ታምኖ እየተሰራበት ይገኛል::
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 15 ቀን 2017 ዓ.ም