የሰላም አማራጭ በሮች እንዳይዘጉ

ኢትዮጵያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ኢኮኖሚዋን እና ማኅበራዊ መሠረቷን አደጋ ላይ የሚጥሉ በርካታ የውስጥ ግጭቶች ገጥመዋታል። በመንግሥት በኩል ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ ቢያቀርብም ምላሹ አጥጋቢ አይደለም። በውጤቱም ማኅበረሰቡ ለአደጋ ተጋላጭ ሆኗል። በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት የዘለቀውን አስከፊ ጦርነት ለማስቆም እንደ አውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር አቆጣጠር 2022 የተፈረመውን የሰላም ስምምነት (የፕሪቶሪያ ስምምነትን) ለማፍረስ በቅርቡ በትግራይ አንዳንድ መሪዎች የሚደረጉ ሙከራዎች ከቅርብ ግዜ ወዲህ ጋብ ያለውን አስጊ ሁኔታው እያባባሱት ነው። እነዚህ ድርጊቶች በሌሎች ክልሎች ካሉ ችግሮችና ግጭቶች ጋር ተዳምሮ በኢትዮጵያ ዳግም የማያባራ ግጭት ሊፈጠር ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሯል።

ዜጎች በዚህ መስቀለኛ መንገድ ላይ መቆማቸው ተገንዝቦ የጦርነት አስከፊ መዘዞችን በማስተዋል አፋጣኝ ውይይት፣ መረጋጋት እና ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ቁርጠኛ መሆን አስፈላጊ ነው።

እንደሚታወቀው ከ120 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ኢትዮጵያ ለግጭት እንግዳ አይደለችም። ሀገሪቱ በተለያየ ግዜ ለዓመታት የዘለቀ ውስጣዊ ግጭቶችን አሳልፋለች። ከእነዚህ ግጭቶች ውስጥ በጣም የቅርብ እና አውዳሚ የነበረው በሕዳር እንደ አውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር አቆጣጠር በ2020 የተቀሰቀሰው እና ለሁለት ዓመታት የዘለቀው የትግራይ ጦርነት ነው። ጦርነቱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል፣ ሚሊዮኖችን አፈናቅሏል፣ እንዲሁም አስተዳደራዊ ክልሎችን አፍርሷል። ከዚያ ሁሉ ደም አፋሳሽ ግጭት በኋላ እ.ኤ.አ በኖቬምበር 2022 የተፈረመው የፕሪቶሪያ ስምምነት ብጥብጡን ለማስቆም እና ለእርቅ መንገድ የሚጠርግ የተስፋ ብርሃን ነበር።

ይሁን እንጂ ከቅርብ ግዜ ወዲህ የሰላም ስምምነት ሂደቱ አፈፃፀም ደካማ መሆኑን እያየን ነው። ሰሞኑን የወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከትግራይ አካባቢ በፕሪቶሪያ የተደረሰውን ስምምነት የመተላለፍ እርምጃዎችን እያየን ነው። የትግራይ ኃይሎች ትጥቅ መፍታት እና የፌደራል ስልጣንን ወደ ክልሉ መመለስን ጨምሮ በሌሎች መሰረታዊ አፈፃፀሞች ላይ የሚታየው ከፍተት የሰላም መደፍረስ ምክንያት ሊሆኑ ተቃርበዋል። እነዚህ እውነታዎች ዳግም ውጥረቶችን እያባባሱ ነው። የክልሉ አመራሮች አለመስማማትና መከፋፈል ለዚህ ዋነኛ ምክንያት ነው። ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ እንደ አማራ እና ኦሮሚያ ያሉ ሌሎች ክልሎችም ውስጥ በመንግሥት ኃይሎችና የሰላም ጥሪን ባልተቀበሉ ኃይሎች መካከል ግጭት አለ፤ ይህ ሁኔታ የሀገሪቱን መረጋጋት እያወሳሰበ ነው።

የፕሮቶሪያ ስምምነትን መጣስ መዘዞች

የፖለቲካ ስምምነቶች የዓለም አቀፍ ግንኙነቶችን፣ ትብብርን፣ ሰላምን እና የጋራ ልማት የሚያጎለብቱ መሰረቶች ናቸው። ሆኖም እንዲህ ዓይነት ስምምነቶች ከተደረጉ በኋላ ሲጣሱ ውጤታቸው ከባድ ሊሆን ይችላል። በተለይ ዲፕሎማሲያዊ ውዝግብ፣ ኢኮኖሚያዊ አለመረጋጋት አልፎ ተርፎም ግጭት ያስከትላሉ። የፕሪቶሪያ ስምምነት መጣስም መሰል ችግሮችን ይዞ እንደሚመጣ ሊታመን ይገባል። ይህንን ጉዳይ በዝርዝር ከተመለከትነው የሚከተለውን አሉታዊ ጎን ያሳየናል።

የመጀመሪያው ዲፕሎማሲያዊ ውድቀት ነው። የፕሮቶሪያ ስምምነትን መጣስ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መሻከር ያስከትላል። እንደሚታወቀው በፖለቲካ ቡድኖች መካከል መተማመን አንዴ ከተሰበረ መልሶ ለመገንባት አስቸጋሪ ነው። በመሆኑም ይህ የሰላም ስምምነት ተግባራዊ እንዲሆን ጥረት ያደረጉ ዲፕሎማት፣ ኤምባሲዎች እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ከጥፋተኛው አካል ጋር (ስምምነቱን ከጣሰው) ወደፊት ስምምነት ለማድረግ ይጠነቀቃሉ። ይህ ማለት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለመሻከሩ ቀዳሚ ምክንያት ይሆናል።

ሁለተኛው የኢኮኖሚ ማዕቀብ ነው። ስምምነቶችን ሲጣሱ አሊያም ለመፍረሳቸው ምክንያት የሆነው አካል ላይ የኢኮኖሚ ማዕቀብ መጣልን ዓለም አቀፍ ሕግ ብዙ ጊዜ ይፈቅዳል። እነዚህ ማዕቀቦች የአንድን ሀገር ኢኮኖሚ ሊያሽመደምዱ ይችላሉ፤ ይህ ማለት ከንግድ ጀምሮ የዜጎች መተዳደሪያ እስከሆኑ ጥቃቅን ዘርፎች ላይ ጉዳት የሚያስከትል ይሆናል።

ሌላው ተአማኒነት ማጣት ነው። ስምምነትን የጣሰ ቡድን አሊያም የፖለቲካ ፓርቲ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን ተአማኒነት ሊያጣ ይችላል። ይህም በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ያለውን ተጽእኖ በመቀነስ ወደፊት በሚደረጉ ውይይቶች የመደራደር አቅሙን ሊያዳክም ይችላል። በመሆኑም የፕሪቶሪያ ስምምነትን ለመጣስ ሙከራ የሚያደርገው አካል ይህንን ታሳቢ ሊያደርግ ይገባል።

ወደ ግጭት ማደግ፡ በከፋ ሁኔታ፣ እንደ ፕሮቶሪያ ያለ ጉልህ ስምምነት መጣስ ወደ ወታደራዊ ግጭት ሊያድግ ይችላል። ታሪክ እንደሚነግረን በስምምነትና በጠረጴዛ ዙሪያ ያልተፈታ ዲፕሎማሲያዊ ውዝግብ ወደ ጦርነት ሊያድግ ይችላል። ይህም ከላይ በዝርዝር ለማንሳት እንደሞከርነው አስከፊ መዘዝ ያስከትላል።

ዓለም አቀፍ ሕግ ስምምነቶችን ስለመጣስ

የዓለም አቀፍ ሕግ በተለይም የቪየና የስምምነት ሕግ፣ ስምምነቶችን መመስረት፣ ማክበር እና ማቋረጥን ይቆጣጠራል። በዚህ ስምምነት መሰረት ‹‹ፓክታ ሳንት ሰርቫንዳ›› የሚል መርህ አለ። ይህ መርህ ‹‹ስምምነቶች መከበር አለባቸው›› የሚል ትርጉም ያለው ነው። መንግሥታትም ሆኑ የፖለቲካ ስምምነት አድራጊዎች የገቡትን የውል ቃል ኪዳን በቅን ልቦና የመወጣት ግዴታ እንዳለባቸው ይደነግጋል። ሆኖም ይህንን ተላልፈው ስምምነቶችን የሚጥሱ አካላት ካሉ

የመጣስ መዘዞች ይኖሩታል። አንዱ ወገን ስምምነቱን ከጣሰ ሌላው ወገን ስምምነቱን ማገድ ወይም ማቋረጥ፣ የማካካሻ ጥያቄ መጠየቅ ወይም እንደ ዓለም አቀፍ የፍትህ ፍርድ ቤት (ICJ) ባሉ ዓለም አቀፍ የሕግ አካላት በኩል ክስ በማቅረብ ውሳኔ እስከማሰጠት ሊደርስ ይችላል።

እንደ ፕሮቶሪያ የፖለቲካ ስምምነቶችን መጣስ ከዲፕሎማሲያዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ውድቀት፤ እስከ ሕጋዊ እርምጃዎችና ግጭት ድረስ ከፍተኛ ውጤቶችን ያስከትላል። ዓለም አቀፍ ሕግ እንደዚህ አይነት ጥሰቶችን የሚያወግዝበትና የሚያስከብርበት ማሕቀፎች አሉት። ለዚህ ነው ስምምነቶችን ማክበር እና አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ የመፍታትን አስፈላጊነት መገንዘብ የሚያስፈልገው። ከሁሉም በላይ ግን እርስ በዕርስ በተሳሰረ ዓለም ውስጥ የፖለቲካ ስምምነቶችን ማክበር ሕጋዊ ግዴታ ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፋዊ መረጋጋትን እና ብልጽግናን ለማረጋገጥ የሞራል ግዴታ መሆኑ ሊታመንበት ይገባል። ለሕዝቦች ሰላምና እረፍትን ለመስጠት የገቡትን ቃልኪዳን መወጣት ከምን ግዜውም በላይ በፕሪቶሪያ ስምምነት አድራጊዎች መካከል ሊከበር ይገባል።

ጦርነት-የሰው ዋጋ

የትግራይ ጦርነት ያስከተለውን አስከፊ መዘዝ ደግሞ ደጋግሞ ማስታወስ አስፈላጊ ነው። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን መረጃ ከሆነ ጦርነቱ ጅምላ ግድያ፣ ጾታዊ ጥቃት እና እንደ ሆስፒታሎች፣ ትምህርት ቤቶች እና የግብርና ተቋማት ያሉ ወሳኝ መሠረተ ልማቶችን መውደምን፤ አሰቃቂ ድርጊቶችን አስከትሏል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ቤታቸውን ጥለው ለመሰደድ ተገድደዋል።

የኢኮኖሚው ተፅዕኖም እንዲሁ በቀላሉ የሚታለፍ አይደለም። ጦርነቱ ንግድን አቋርጧል፣ ኢንዱስትሪዎችን ሽባ አድርጓል፣ ሀብትን ከልማት ፕሮጀክቶች መደገፊያ ውጪ አድርጓል። ኢትዮጵያና ዜጎቿ ከልማት እድገቷ ተደናቅፈው ሚሊዮኖች ወደ ድህነት እና የምግብ ዋስትና እጦት ተዳርገዋል።

ዳግም ወደ ግጭት ላለመግባት

ኢትዮጵያ ወደ ሌላ የግጭት አዙሪት ውስጥ ልትወድቅ እንደምትችል የቅርብ ጊዜ ሁኔታዎች እየጠቆሙ ነው። የፕሪቶሪያን ስምምነት የሚቃወሙ የትግራይ ክልል አንዳንድ መሪዎች ለዚህ ተጠያቂ ናቸው። ከዚሁ ጎን ለጎን በአማራ እና ኦሮሚያ ባሉ ሌሎች ክልሎች ውጥረቱ ተባብሶ የትጥቅ ግጭት እና የፖለቲካ አለመረጋጋት ተፈጥሯል። እነዚህ ችግሮች በአፋጣኝ ሊቆሙ ይገባል። የግጭት በሮች ተጠርቅመው የሰላም በሮች መከፈት ይኖርባቸዋል።

ከሰሞኑ እየታዩ ያሉ የግጭት ጠመቃዎች በጣም አሳሳቢ ናቸው። ድርጊቱ በሕወሓት መከፋፈል ምክንያት ደካማ አፈፃፀም ካለው ከፕሪቶሪያ ስምምነት በኋላ የተገኘውን አንፃራዊ ሰላም ከመቀልበስ ባለፈ ሀገሪቱን ወደባሰ ትርምስ ውስጥ እንድትገባ የሚያደርግ ነው። ክብሩን የሰው ልጅ ሕይወት ከመቅጠፍ ባለፈ የኢኮኖሚ ቀውሱ ዳግም ሊተካ የማይችል ነው። በተለይ በሁሉም የአፍሪካ ቀንድ አለመረጋጋት እና ሰብአዊ ቀውሶች መቀጠላቸውን ተከትሎ የጦርነትና የግጭት ጉሰማው ዳግም ማገርሸቱ ቃጣናውን ለማያባራ ቀውስ እንደሚዳርገው ሊታወቅ ይገባል።

የውይይት አስፈላጊነት

እነዚህን የግጭት አታሞዎች ለማስቆምና ፊት ለፊት ለመጋፈጥ ሰላማዊ ውይይት አስፈላጊ ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት፣ የክልል መሪዎች እና የዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ የግጭቶቹን መንስኤዎች በአግባቡ መለየት ይኖርባቸዋል። ቸግሮቹን ለመለየትና ለመፍታት፤ ለዘላቂ የሰላም መሰረት ለመገንባት በጋራ መስራት አለባቸው።

በመጀመሪያ ሁሉም ወገኖች ለፕሪቶሪያ ስምምነት ተፈፃሚነት ያላቸውን ቁርጠኝነት እንደገና ማረጋገጥ እና ውሎቹን ተግባራዊ ለማድረግ ተጨባጭ እርምጃዎችን መውሰድ ይጠበቅባቸዋል። ይህም የትግራይ ኃይሎች ትጥቅ መፍታትን ማረጋገጥ እና የሁሉም ባለድርሻ አካላት ቅሬታዎች ምላሽ መስጠትን ይጨምራል።

ሁለተኛ፣ መንግሥት ከሁሉም ብሔር ብሔረሰቦችና የፖለቲካ ቡድኖች ጋር በመሆን የቆዩ ቅሬታዎችን ለመፍታትና አገራዊ አንድነትን ለማጎልበት ሁሉን አቀፍ ውይይት ማድረግ አለበት። ይህ ውይይት ግልፅ፣ አሳታፊ እና ለኢትዮጵያ ተግዳሮቶች ዘላቂ መፍትሄዎችን በማፈላለግ ላይ ያተኮረ መሆን አለበት። ሦስተኛ፣ የዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ የኢትዮጵያን የሰላም ሂደት በመደገፍ ገንቢ ሚና መጫወት አለበት። ይህም ሰብአዊ እርዳታን መስጠትን፣ የልማት ተነሳሽነቶችን መደገፍ እና ዲፕሎማሲያዊ መንገዶችን በመጠቀም ውይይቶችን ማበረታታት ይጨምራል።

የመገናኛ ብዙሃን እና የሲቪል ማሕበረሰብ ሚና

እንደ ቢቢሲ እና አልጀዚራ ያሉ የመገናኛ ብዙሃን ግጭቱን አጋነው በመዘገብ እና ተፅዕኖውን በማሳደግ ረገድ ወሳኝ ሚና ተጫውተዋል። ነገር ግን መገናኛ ብዙኃን ስሜት ቀስቃሽ የሆኑ ዘገባዎችን በማስወገድ እና ዘገባው ለሰላም ግንባታ ጥረት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት የበኩላቸውን ማድረግ አለባቸው። የሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች፣ የሀይማኖት ቡድኖች፣ የወጣቶች ንቅናቄዎች እና የሴቶች አደረጃጀቶችም እንዲሁ ወሳኝ ሚና አላቸው። እነዚህ ቡድኖች በማሕበረሰቦች መካከል እንደ ድልድይ ሆነው ሊያገለግሉ፣ እርቅን ማሳደግ እና ለግጭት ሰላማዊ መፍትሄዎች መሟገት ይችላሉ።

ለሰላም የተደረገ ጥሪ

ኢትዮጵያ ወሳኝ ወቅት ላይ ትገኛለች። ዛሬ የሚደረጉ የሰላም ጥረቶችና የውይይት መድረኮች ሀገሪቱ ወደ ሰላምና ብልፅግና መሸጋገሯን ወይም ወደ ግጭትና ትርምስ መውደቋን ይወስናሉ። የሰሜኑ ጦርነት የሰጠን ትምህርት ግልፅ ነው፤ ጦርነት መከራና ውድመት ብቻ የሚያመጣ ሲሆን ውይይት እና ትብብር ግን ብሩህ ተስፋን ይሰጣል። ለዚህ ነው ከጦርነት ሰላምን፣ ከመለያየት ይልቅ ውይይትን፣ ከተስፋ መቁረጥ ይልቅ ተስፋን እንምረጥ የምለው። ምክንያቱም የኢትዮጵያ የወደፊት እጣ ፈንታ በእሱ ላይ የተመሰረተ ስለሆነ። ሰላም!!

ሰው መሆን

አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 15 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You