
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አሰቃቂ ምስሎችን በፌስቡክና መሰል ማኅበራዊ ሚድያዎች መመልከት የየዕለት አጋጣሚ ሆኗል። እምነትን ከእምነት፤ብሔርን ከብሔር የሚያጋጩ፤ ባሕል እና እሴቶችን ዝቅ የሚደርጉ ሴቶችን የሚያሳንሱ፤ አረጋውያን እና አካል ጉዳተኞችን የሚንቋሽሹ መልዕክቶች በየማሕበራዊ ሚዲያው ሲለቀቁ ማየት የዕለት ተዕለት ክስተት ነው::
የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ባላቸው ሰፊ ተደራሽነትና ተሳትፎ ሳቢያ በጎም ሆኑ አሉታዊ መልዕክቶች በቀላሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩና በዓለም ዙሪያ ላሉ ሰዎች ለማዳረስ ያስችላሉ። የእነዚህ መልዕክቶች ዋነኛ መዳረሻ እና ተጠቂ ደግሞ ወጣቶች ናቸው::
የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር 130 ሚሊዮን ገደማ እንደሆነ ይገመታል። ከአጠቃላይ የሕዝብ ብዛት 24 በመቶ ያክሉ ከ13 እስከ 24 የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ ነው። በዚህ እድሜ ክልል ውስጥ ያለው ደግሞ ውሎ እና አዳሩ ከማሕበራዊ ሚዲያ ጋር የተያያዘ ነው::
ወጣቶች በከማሕበራዊ ሚዲያ ጋር የጠበቀ ቁርኝት ያላቸው በመሆኑ በማሕበራዊ ሚዲያ በሚለቀቁ በጎ ባልሆኑ መልዕክቶች መጠቃታቸው አይቀሬ ነው:: ይህ ደግሞ ለማሕበራዊ እና ለስነልቦናዊ ጉዳት በማጋለጥ ብቁ ሀገር ተረካቢ ዜጋ እንዳይኖር ያደርጋል:: የእርስ በርስ መቀራረብ እና አብሮነትን በሚያደፈርሱ መልዕክቶች አማካኝነት ወጣቶች ላልተጋ ጭንቀት እና አለመረጋጋት ስለሚጋለጡ ችግሩ ከእነሱም አልፎ ለቤተሰብ እና ለሀገርም የሚተርፍ ነው::
በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባሉና ፖለቲካዊ አለመረጋጋት በሚንጣቸው አገራት ውስጥ ማሕበራዊ ሚዲያን ለአሉታዊ ዓላማ የሚጠቀሙ ግለሰቦችና ቡድኖች እጅግ በርካታ ናቸው። አሁን አሁን ማሕበራዊ ሚዲያው ከሚታወቅባቸው ገጽታዎቹ የጥላቻ ንግግር አንዱ ነው::
“የጥላቻ ንግግር” ማለት በአንድ ሰው ወይም የተወሰነ ቡድን ላይ ያነጣጠረ፣ ብሄርን፡ ብሔረሰብንና ሕዝብን፣ ሀይማኖትን፤ ዘርን፣ ጾታን ወይም አካል ጉዳተኝነትን መሰረት በማድረግ ጥላቻን፣ መድሎን ወይም ጥቃትን የሚያበረታታ ንግግር ነው።
በዚህም በግለሰቦች፣ በማሕበረሰቦች እና በፖለቲካ ቡድኖች መካከል ያለውን ግንኙነት በማበላሸት ለግጭትና ለጥቃት መሳሪያ ሊሆኑ የሚችሉበት ዕድል ሰፊ ነው። ከዚህ አንጻር በሀገራችን ያለው ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ ነው::
በሀገራችን እየታየ ከሚገኘው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሚለጠፉ ሐሳቦች ጥላቻ አዘል፣ ግለሰብን ወይንም ቡድንን በብሔር እና በሃይማኖት የሚፈርጁና ብጥብጥ እና ሁከትን የሚሰብኩ ናቸው።
ዲጂታል ሚዲያው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዓለም አቀፍ ደረጃ በፍጥነት ያደገ፣ ከፍተኛ ተቀባይነት ያገኘ በቢሊዮን በሚቆጠሩ የዓለማችን ሰዎች ጥቅም ላይ የሚውል ነው። ይህ ማለት ደግሞ እራሱን የቻለ ማሕበራዊ፣ ሥነ ልቦናዊና አዕምሮአዊ ከፍተኛ ጉዳት ይዞ የሚመጣ ነው።
አሁን አሁን የማሕበራዊ ሚዲያ ሰፊ ቁጥር ላላቸው ታዳጊዎች የእለት ተእለት ሕይወታቸው አካል እየሆነ መጥቷል:: በማሕበራዊ ሚዲያ ላይ ያላቸው ግንዛቤ እና ጥገኝነት ከብዙ ጎልማሶች እጅግ የላቀ ከመሆኑ ባሻገር፣ ማሕበራዊ ሚዲያዎችንም በከፍተኛ ፍጥነት እየተጠቀሙ ነው።
ዓለም እጅግ ውስብስብና ዲጂታል እየሆነች በምትሄድበት እያንዳንዷ ቅጽበት የታዳጊዎችም ሕይወት እንደዚያ እየሆነ መሄዱ የሚጠበቅ ነው:: ይህ ደግሞ ዘግይቶም ቢሆን የአእምሮ ጤና መታወክ ያስከትላል::
እንደ ተመራማሪዎች ጥናት ከሆነ ማሕበራዊ ሚዲያ በታዳጊዎች ዘንድ እንደሱስ የመሆን እድሉ በጣም ሰፊ ነው:: ተመራማሪዎች በጥናታችን መሰረት አንዳንድ የአእምሮ ክፍሎች ታዳጊዎች ማሕበራዊ ሚዲያ ላይ በሚያገኟቸው “likes” ንቁ እንደሚሆኑና ይህ ደግሞ በመልሱ የማሕበራዊ ሚዲያ ፍላጎታቸው እንዲጨምር እንደሚያደርጋቸው ደርሰንበታል ይላሉ::
ታዳጊዎች በተለይም በማሕበራዊ ሚዲያ ላይ በሚለጥፏቸው የራሳቸው ፎቶዎች ላይ ብዙ (ላይኮችን) በሚመለከቱበት ጊዜ ከበርካታ የአእምሮ ክልሎቻቸው በተጨማሪ አበረታች የአንጎል አካል የሆነው ኒውክሊየስ አክመንስ ንቁ ይሆናል:: ይህ የአንጎል አካባቢ የምንወዳቸውን ሰዎች ፎቶ ስናይ ወይም ገንዘብ ስናሸንፍ ምላሽ የሚሰጠው ተመሳሳይ ክልል ነው::
በነገራችን ላይ ይህ የአእምሮ ክፍል በታዳጊነት ወቅት ይበልጥ ስሜታዊ መሆኑ ስለምን ታዳጊዎች በማሕበራዊ ሚዲያ ሱስ እንደሚጠለፉ አንዱ ማሳያ ነው:: ታዳጊዎች ማሕበራዊ ግንኙነቶችን ለማስፋት እና ጠቃሚ የቴክኒክ ክህሎቶችን እንዲማሩ ለመርዳት ማሕበራዊ ሚዲያዎች ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ ጥርጥር የለውም:: ጥያቄው ግን እነዚህ ማሕበራዊ ሚዲያዎች በታዳጊዎች ጭንቅላት ላይ ምን አይነት ተጽዕኖ ያሳድራሉ? የሚለው ነው::
ታዳጊዎች ለአእምሮ መጋለጥ የሚዳረጉት ብዙ ጊዜአቸውን ኦንላይን ስለሚያሳልፉ ብቻ አይደለም:: ይልቁንስ ኦንላይን የሚሆኑበትን ጊዜ መቆጣጠር ስለማይችሉ በዛ ያለ ጊዜ ኦንላይን ሆነው ባሳለፉ ጊዜ በዚህ በአእምሮ ጭንቀት የመጠቃት እድላቸው ሰፋ ይላል:: ብዙ ጊዜን ኦንላይን ማሳለፍ ደግሞ ዞሮ ዞሮ ለበርካታ የጤና እክሎች መዳረጉ አይቀሬ ነው::
ጥናቶችን መሰረት በማድረግ ስንመለከት በዓለም አቀፍ ደረጃ አምስት ቢሊዮን የሚሆን ሕዝብ የዲጂታል ሚዲያ ተጠቃሚ ነው:: በኢትዮጵያም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ዜጋ የዲጂታል ሚዲያ ተጠቃሚ ነው። ከሀገሪቱ የሕዝብ ቁጥር አብዛኛውን ድርሻ የሚይዘው ደግሞ በዚህ የሚዲያ ተፅዕኖ ውስጥ ያለ ወጣት በመሆኑ እንደሀገር ጉዳቱ ቀላል እንዳልሆነ እሙን ነው።
ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት ማሕበራዊ የትስስር ድረ ገጾችን ለሐሰተኛ መረጃና ለጥላቻ ንግግር ማስተላለፊያነት የሚጠቀሙ ሰዎችን ተጠያቂ የሚያደርግ ሕግ ማውጣቷ የሚዘነጋ አይደለም።
በአዋጁ ከተካተቱ ሕግጋት መካከል የጥላቻ ንግግርን በብሮድካስት፣ በሕትመት ወይም በማሕበራዊ ሚዲያ ወይንም በሌላ ተመሳሳይ ዘዴዎችን በመጠቀም ያስተላለፈ እስከ 2 ዓመት በሚደርስ እስራትና በ100 ሺህ ብር ይቀጣል የሚል ይገኝበታል።
በተላለፈው የጥላቻ ንግግር ምክንያት በግለሰብ አሊያም በቡድን ላይ ጥቃት ከደረሰ አልፎም መረጃው ከ5 ሺህ በላይ ተከታዮች ባሉት ገጽ ከተላለፈ ቅጣቱ እስከ 5 ዓመት ሊደርስ እንደሚችል አዋጁ ያትታል።
እስማኤል አረቦ
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 15 ቀን 2017 ዓ.ም