አዲስ አበባ፡- የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የአባሎቹን ጥራት በማሻሻልና አቅም በማሳደግ ህብረተሰቡ የሚረካበት፤ በክህሎትና በእውቀት የዳበረ አገልግሎት መስጠት የሚያስችለውን አደረጃጀት እየሠራ መሆኑን አስታወቀ፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀልና ትራፊክ አደጋ ምክትል ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳስታወቁት፤ ኮሚሽኑ በቀደሙት ዓመታት ከህዝባዊ ወገንተኝነትና ለሰላም በቁርጠኝነት ከመሥራት አኳያ ይታይበት የነበረውን ችግር መፍታት ያስችለው ዘንድ ስርነቀል የሆነ አደረጃጀት እያካሄደ ይገኛል፡፡ በተለይም አመራሮቹን በመለወጥ የተሻለ አደረጃጀት መፍጠርና ማስፋት ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ ነው፡፡
ህበረተሰባችን በሰላም ወጥቶ ለመግባት ገና ለገና ምን እሆናለሁ ብሎ መጨነቅና ማሰብ የለበትም፡፡ የሰላሙ መሠረት እኛ መሆናችንን በተግባር ማረጋገጥም ይጠበቅብናል ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ፤ በተለይም ባለፉት ዓመታት ከፍተኛ መዳከም የታየበትን የማህበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎት በአዲስ መልክ በማደራጀት ለህዝቡ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ኅብህረተሰቡ ጥሩ ተቀባይነት ያላቸውን ጨዋ ፖሊሶች የመመደብ ሥራ የሪፎርሙ አካል መደረጉን ምክትል ኮሚሽነሩ ጠቅሰው፤ ብቃት ያላቸውና ማዕረጋቸው በመኮንንነት ደረጃ ያሉ አባላትን የመመደብ አዲስ አቅጣጫ መጀመሩንና የፖሊስ አባላቱን በቅርቡ ለህብረተሰቡ የማስተዋወቅ ሥራ እንደሚሠራ አመልክተዋል፡፡
ከቀድሞው በተሻለ መልኩ የደመወዝ ደረጃ አከፋፈሉን ሳቢ በማድረግ በትምህርት፣ በአቅምና በብቃቱ ተወዳደሪ የሆነ የፖሊስ አባል እንዲመደብ የሚደረግ መሆኑን የገለጹት ምክትል ኮሚሽነሩ፤አዲሱ አደረጃጀት ከዚህ ቀደም ይነሳ የነበረውን ቅሬታ በበዙ መልኩ ይፈታዋል የሚል እምነት እንዳላቸው አስገንዝበዋል፡፡
ኮሚሽኑ እያደረገ ያለው ሪፎርም በዋናነት በሰው አዕምሮ ላይ የሚሠራ በመሆኑ አመላከት የመቀየር ሥራ በአንድ ጀንበር የሚከናወን አለመሆኑን የጠቀሱት ምክትል ኮምሽነሩ፤ ከዚህ ቀደም በአንዳንድ የፖሊስ አባላት ዘንድ መደብደብ መብት ተድርጎ የሚሠራበትን አካሄድ ለማስቆም የአስተሳሰብ ቀረፃው ላይ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ባለፉት አምስት ወራት ብቻ በተደረገው ዘመቻ ፍተሻና ጥቆማ 1ሺ599 ሽጉጦች፣ 28ሺ209 የተለየዩ ዓይነት ጥይቶች፣18ሺ717 የክላሽ ጥይቶችና በርካታ መሳሪያዎች መያዛቸውን ተናግረዋል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሣሥ 5/2011
ማህሌት አብዱል