“ሰላምን ፈልጉ…፤”

በዚህ ዓምድ በምጽፋቸው መጣጥፎች ማሳረጊያ ላይ ሁሌም ሻሎም። አሜን። ሰላም ይሁን። እላለሁ ሰላም ግን እንደ መሻቴ እንደ መፈለጌ እውን አልሆን እያለ ዛሬ ላይ ደርሰናል። በኦሮሚያና በአማራ ክልል የተቀሰቀሰው ጦርነት ያሳጣን ሰላም ሳያንስ ላለፉት ሁለት ዓመታት አንጻራዊ ሰላም ሰፍኖበት የቆየው የትግራይ ክልል ሰሞነኛ ውጥረት ደግሞ በእንቅርት ላይ ቆረቆር ሆኖ ተከስቷል። በቀጣናው ያለው ውጥረት ከዚህ ጋር ተጃምሎ አኅጉሩን ከፍ ሲልም ዓለማቀፍ ማኅበረሰቡን እያሳሰበ ይገኛል። መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ ምዕራባውያን መግለጫም የችግሩን አሳሳቢነት አደባባይ ያወጣ ነው። ከሁሉም በላይ ደግሞ ኢትዮጵያውያንን እያስጨነቀ ነው። ሰሞነኛው የኢሰመኮ እና የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት መግለጫም ይሄን ሀገራዊ ስጋት ታሳቢ ያደረገ ነው።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በትግራይ ክልል በሁለት የሕወሓት ቡድኖች መካከል የተፈጠረው ውጥረት የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት “በተሟላ መልኩ እንዳይፈጸም” የሚያደርግና የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ስጋት የሚፈጥር በመሆኑ በሰላም እንዲፈታ አሳስቧል። በፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት መካከል ሲካሄድ የነበረው ጦርነት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶርያ ጥቅምት 2015 ዓ.ም በተፈረመ የሰላም ስምምነት መቋጨቱን ተከትሎ በክልሉ የተቋቋመውን ጊዜያዊ አስተዳደር በሚመራው ሕወሓት አባላት መካከል በዋናነት የፓርቲው ጉባኤ መካሄድ አለበትና የለበትም በሚል ጉዳይ በሁለት ጎራ ተከፋፍለዋል።

በሕወሓት ሊቀመንበር (ዶክተር) ደብረጽዮን የሚመራው ቡድን ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ምርጫ ቦርድና የኢትዮጵያ መንግሥት እውቅና የነፈገውን “የመዳን ጉባኤ” ያካሄደ ሲሆን የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር በነበረውና የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንት በሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው ጉባኤን በመቃወም ሳይተሳፍ ቀርቷል። ሁለቱ ቡድኖች ከእዚያን ጊዜ ጀምሮ እርስ በርሳቸው በመግለጫ መወጋገዛቸው የተለመደ ቢሆን አቶ ጌታቸው መጋቢት 1 ቀን 2017 ዓ.ም በሦስት የትግራይ ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች ላይ እግድ ከጣሉ በኋላ ውጥረት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል።

ኢሰመኮ በመግለጫው አቶ ጌታቸው እግድ ከጣሉ በኋላ “የሕወሓት ተወካይ መሆናቸውን የሚገልጹት አካላት በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች የጊዜያዊ አስተዳደሩን የመንግሥት ተቋማት ለመቆጣጠር እንቅስቃሴ ማድረጋቸውን ተከትሎ ከክልሉ ነዋሪዎች ዕለታዊ እንቅስቃሴ ባሻገር በሰዎች ሰብዓዊ መብቶች ላይ አደጋ እና ሥጋት ፈጥረዋል” ብሏል። ኢሰመኮ እግዱን ተከትሎ በተነሳው ግርግር በክልሉ ሰዎች መቁሰላቸውን፣ መታሰራቸውና በመቀሌና በአዲግራት የአስተዳዳሪዎች ቅየራ መደረጉን ጠቅሷል። የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋር ምክር ቤትም በዚያ ሰሞን ባወጣው መግለጫ፤ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደርና የሕወሓት አመራሮች የገቡበት ውጥረት ወደ ሌላ ጦርነት ከማምራቱ በፊት የፌዴራል መንግሥት መፍትሔ ሊያበጅለት ይገባል ሲል አሳስቧል፡፡

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋር ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን አየለ፣ ‹‹ሀገርን የሚያስተዳድረው መንግሥት፣ እንደዚህ ዓይነት ችግሮች የሚፈቱበት መንገዶችንና አማራጭ ሃሳቦችን ሰፋ አድርጎ በማጤን መፍትሔ መፍጠር አለበት፤›› ብለው እንደሚያምኑ ለሪፖርተር ገልጸዋል። ለዚህም ሁለቱ አካላት ውይይቶች የሚያደርጉበትን መንገድ ሊያመቻች ይገባል ሲሉ ተናግረዋል። የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደርና ሕወሓት ከገቡበት የሥልጣን ሽኩቻ ወጥተው፣ ችግራቸውን በድርድር መፍታት አለባቸው ያሉት ሰብሳቢው፣ ከፌዴራል መንግሥት ባሻገር፣ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፣ ልሂቃን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ሌሎች አካላት ጣልቃ በመግባት ወደ ጦርነት የሚደረገው ሂደት እንዲገታ የበኩላቸውን እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

በትግራይ ክልል ባለፉት ዓመታት በነበረው የእርስ በርስ ጦርነት እንደ ሰሜን ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገር ነው የተጎዳነው ብሎ መገንዘብ እንደሚያስፈልግ የጠቀሱት ኃላፊው፣ የክልሉ ማኅበረሰብ የሰላምና የልማት እንጂ የጦርነት ድምፅ መስማት እንደማይገባው አስገንዝበዋል። በክልሉ ያሉ አመራሮች ከግል ፍላጎት ወጥተው ለማኅበረሰቡ ቅድሚያ ሊሰጡ ይገባል ሲሉም አክለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) በበኩሉ፣ ፌዴራል መንግሥት በትግራይ ክልል የሚታየውን ውጥረት በአስቸኳይ ሊያስቆም ይገባል ሲል መጋቢት 5 ቀን 2017 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ጥሪውን አቅርቧል። ፓርቲው በመግለጫው፣ ከፕሪቶርያው ሥምምነት በኋላ አንፃራዊ ሰላም እየታየበት የነበረው የትግራይ ክልል ሁኔታ፣ የፌዴራል መንግሥቱ በስምምነቱ መሠረት ታጣቂ ኃይሎችን ትጥቅ የማስፈታት ኃላፊነቱን በአግባቡ ባለመወጣቱና አካታች የሆነ ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት አለመመሥረቱን ተከትሎ፣ ሕወሓት የእርስ በርስ ፍትጊያ ውስጥ ገብቶ በትግራይ ክልል ውጥረት ነግሷል ብሏል፡፡

በሕወሓት ውስጥ የተፈጠረውን የውስጥ የሥልጣን ሽኩቻ ተከትሎ በክልሉ ያሉ የታጠቁ ኃይሎች እየሄዱበት ያለው ግጭት ቀስቃሽ ሕገወጥ እንቅስቃሴ ግን፣ በጠቅላላው እንደ ሀገር በተለይ ደግሞ በትግራይ ክልል ውስጥ በሚገኙ ንፁሓን ዜጎች ላይ የሚያመጣውን ምጣኔ ሀብታዊ፣ ማኅበራዊ፣ የሰላምና የደኅንነት አስከፊ አደጋ አሳሳቢ እንደሆነ ፓርቲው ገልጿል። ኢዜማ፣ የሕወሓት አመራሮች ምንም ሳይፀፀቱ ሥልጣንን ጠቅልሎ በመያዝ ግብግብ ውስጥ ገብተው ለሌላ ዙር ግጭት የሚጋበዙ ከሆነ በተለይ በትግራይ ውስጥ ያሉ ዜጎች ሊረዱት የሚገባው መሠረታዊ ጉዳይ፣ ይህ ስብስብ በምንም ዓይነት ሁኔታ ለማኅበረሰቡ ጥቅም የቆመ እንዳልሆነ ነው ብሏል፡፡ በዚህ የፖለቲካ ሥልጣን ጥምን ለማርካት በሚደረግ መገፋፋት ውስጥ ባለመሳተፍ እንዲሁም ግጭት የሚቀሰቅሰውን የትኛውንም ኃይል በግልጽ በመቃወም የክልሉ ነዋሪ በአንፃራዊነት ያገኘውን ሰላም ሊያስጠብቅ ይገባል ሲልም ፓርቲው አሳሰቧል፡፡

በተለይ የፌዴራል መንግሥቱ ጉዳዩ እዚህ ደረጃ ከመድረሱ በፊት በክልሉ የተፈጠረውን ትርምስ በሰላማዊና ሕጋዊ መንገድ ሊያስቆም ሲገባ ይህን አለማድረጉ ሳያንስ፣ አሁንም ራሱን እንደሩቅ ተመልካች በመቁጠር በጉዳዩ ላይ ተጨባጭ መፍትሔ እንዲመጣ እየሠራ እንዳልሆነ የገለጸው ኢዜማ፣ የፕሪቶርያው ስምምነትን በአግባቡ እንዲፈጸም ባለማድረጉ ንፁሓን ዜጎች በሕይወታቸውና በአካላቸው ዋጋ እየከፈሉ መምጣታቸው ተገቢነት የሌለው ተግባር መሆኑን አውቆ አሁንም ለጉዳዩ ተገቢ ትኩረት በመስጠት ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ በሚያስችል ሕጋዊና ሰላማዊ መንገድ ብቻ የመንግሥትነት ሚናውን እንዲወጣ አሳስቧል፡፡

በግሌ ቱባ ቱባ የእርቅ ማዕዶች እያሉን፤ የሦስቱ አብርሃማዊ እምነቶች ተከታይ ሆነን ለምን ሰላም እራቀን ስል እብሰከሰካለሁ። እቆጫለሁ። ፖለቲካችንስ በዚህ ደረጃ ወርዶ ለምን ቀውስ ቀፍቃፊ ሆነ ስል ግራ እጋባለሁ። አጥጋቢ መልስ ስለማላገኝ የሰላም ምንጭ ወደሆነው እምነት መመለስን መርጫለሁ። አዎ ወደ ሦስቱ አብርሃማዊ እምነቶች። ወደ ክርስትና፣ ይሁዲና እስላም። እዚህ ላይ እነዚህ እምነቶች ራሳቸው የውዝግብና የግጭት ምንጭ እንዲሆኑ የሚደረጉ ተደጋጋሚ ጥረቶችን ዘንግቸው አይደለም። ነገር ግን ከዚህ በላይ ግዘፍ የነሱ ስለሆነ ዛሬም ከዚህ ክፉ ቀን መውጫችን እነሱ ናቸው ብዬ አምናለሁ።

በእነዚህ አብርሃማዊ እምነቶች ሰላም የማዕዘን ድንጋይ ነው። የወንጌላቸው አልፋም ኦሜጋም ሰላም ነው። በዚህ መነሻና ማንጠሪያነት ሰላምን ከታላቁ መጽሐፍ አንጻር እንመርምር። “ሰላምን ፈልጉ ስለ እርስዋም ወደ እግዚአብሔር ጸልዩ” ይለናል ታላቁ መጽሐፍ። እንደ አብርሃማዊ እምነቶች ተከታይ እውን ሰላምን እየፈለግን ነው፤ መልሱን እኔን ጨምሮ ለእናንተ ልተወው። ከስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ስለ ሰላም ያነበብሁትን ጽሑፍ ላጋራችሁና በሰላም ሁለንተናዊነት ላይ ተነጋገሩ። ተወያዩ። ተጠያየቁ።

ሰላም ‹‹ተሳለመ›› ከሚለው የግዕዝ ግስ የተገኘ ሲሆን ትርጒሙም መፋቀር፣ መዋደድ ማለት ነው። ሰላም በሕይወት ስንኖር ልናጣቸው ከማይገቡ ነገሮች የመጀመሪያው ነው። ሰላም የፍጥረታት ሁሉ የሕይወት መርሕ ነው። ሰላም/ፍቅር/ የሕግ ሁሉ ፍጻሜ ነው። ሰላም የሕይወት ማጣፈጫ ቅመም ነው። በማንኛውም ጊዜ እና ቦታ ለማኅበራዊ ኑሮ መሠረቱ ሰላም ነው። ሰላምን በዋጋ መተመን በወርቅ በብር መግዛት አይቻልም። ሰው እርስ በርስ በሰላም በፍቅር በአንድነት የማይኖር ከሆነ ምሥጢረ ሥጋዌን /የአምላክን ሰው መሆን/ ምሥጢራዊነት አለመረዳት ነው። ክርስቶስ ሰው የሆነው የሰውን ዘር ሁሉ ለማዳን ነውና። ከሦስቱ የቀጰዶቅያ አባቶች አንዱ ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሳርያ የክርስቶስ ልደት የመላው ሰው የልደት ቀን ነው። በማለት አስረድቷል። ስለዚህ ክርስቶስ ሰው የሆነው ለሰው ልጆች ሁሉ ሰላም ነው፡፡

ቤተ ክርስቲያንም ሁልጊዜ በአስተምህሮዋ በቅዳሴዋ ‹‹ሰላም ለኵልክሙ/ሰላም ለሁላችሁ ይሁን›› እያለች ትሰብካለች። ሰላም የተጀመረው በጥንተ ተፈጥሮ ነው። መላእክት ከተፈጠሩ በኋላ ሁሉም መላእክት ማን ፈጠረን እያሉ በተረበሹ ሰዓት መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል በያለንበት እንጽና /አትረበሹ/ ተረጋጉ በማለት የመጀመሪያውን የሰላም ብሥራት አብሥሯል። ስለዚህ የሰላም አስተማሪ ቤተ ክርስቲያን ናት። አባቶቻችን ስለ ሰላም ብዙ ጽፈዋል፣ ብዙ መሥዋዕትነት ከፍለዋል፡፡

ስለ ሰላም ከአባቶቻችን ምን እንማራለን?

እንደ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ያሉ አባቶቻችን ከሰው አልፎ ከአራዊት ጋር ኑረው አሳይተውናል። እኛ ግን መኖር ያቃተን ከአራዊት ጋር ሳይሆን ከወንድሞቻችን ጋር ነው። ቅዱስ ያሬድ ስለ ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ እንዲህ ብሏል ‹‹ዮሐንስ ምስለ ቶራት በገዳም ልሕቀ›› /ዮሐንስ ከቶራዎች ጋር በገዳም አደገ/። ቅዱስ ዮሐንስ ከልጅነቱ ጀምሮ የኖረው በበረሃ ነው በልጅነቱም ያጠባችው ቶራ የምትባል የዱር እንስሳ ነች። ብዙውን ጊዜ የኖረው በበረሃ ነው። ታዲያ የአባቶቻችን አካሄድ ይህ ሁኖ እያለ እኛ እንዴት ከራሳችን ጋር መኖር ያቅተናል።

ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅን ራሱ ጌታችን ከሴቶች ከተወለዱት መካከል እንደ ዮሐንስ መጥምቅ አልተነሳም ብሎ መስክሮለታል። እነ አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ የኖሩት ከአንበሳ ጋር ነው ዕድሜያቸውን በሙሉ የጨረሱት በተጋድሎ ነው። እነ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ የኖሩት ከነብሮች ጋር ነው። የአባቶቻችን አካሄድ ይህ ሁኖ እያለ እንዴት ከወገኖቻችን ጋር መኖር ያቅተናል። አባታችን አብርሃም ዘመኑን በድንኳን ኑሮ አሳለፋት። እኛ ደግሞ ሰባ ወይም ሰማንያ ዘመን ተሰጥቶን አብሮ መኖር አቃተን። ዓለሙኒ ኃላፊ፣ ንብረቱኒ ኃላፊ፣ ፍትወቱኒ ኃላፊ፣ እስመ ኵሉ ኃላፊ ውእቱ ተብሎ የተፈጸመውን የእግዚአብሔር ቃል ተገንዝበን ሁሉም ነገር ኃላፊ መሆኑን መረዳት ተሳነን። አብሮ መኖርም አቃተን፡፡

ሰላምን በተግባር የሚገልጽ ሰው፡-

ክርስትና የሚያስተምረው በቃላት መዋደድን ወይም የአንደበትን ፍቅር አይደለም በድርጊት የሚታይ በሥራ የሚተረጎመውን ሰላም ነው። ውስጣዊ የማፍቀርን ባሕርይ ግልጽ የሚያደርገው ደግሞ ተግባር ነው። በአሁኑ ሰዓት በአንዳንድ የሀገራችን ቦታዎች ሰላም ጠፍቶ ኀዘን በዝቷል። ሰላምን የያዘ ሰው የሥነ ምግባርን ሕጎች አይተላለፍም፤ የሰውን ሕይወት አያጠፋም፤ ሰው የተባለውን ሁሉ አይጠላም፤ የሌላውን ሀብት እና ንብረት አይመኝም፤ የሰውን መልካም ስም አያጎድፍም ሌላው ሰው ባለው ነገር አይቀናም፤ ራሱን ብቻ አይወድም፤ በማንም ሰው ላይ ክፉ ሥራ አይሠራም፤ በራሱ ላይ ሊደርስበት የማይፈልገውን በሌላው ላይ እንዲደርስ አይፈልግም፤ በሀብቱ እና በጤንነቱ ጊዜ የሚወደውን ወንድሙን በችግሩ እና በሕመሙ ጊዜ አይጠላውም አይንቀውም አያገለውም፡፡

የሰላም ትሩፋቶች፦ ሰላማዊ መሆን በጎነት ነው። ጻድቁ ኢዮብ እንዲህ ይለናል። ‹‹አሁንም ከእርሱ ጋር ተስማማ፣ ሰላምም ይኑርህ፣ በዚያም በጎነት ታገኛለህ።”›› ሰላማዊ መሆን ከእግዚአብሔር ጋር መኖር ነው። ያለ ሰላም እግዚአብሔርን ማስደሰት አይቻልም። ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ከሁሉ ጋር ወደ ሰላም ሩጡ››፤ ሰላማዊ ሰው መሆን ፍላጎትን ማሳኪያ መንገድ ነው። ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ ‹‹ትእዛዜን ብትሰማ ኑሮ ሰላምህ እንደ ወንዝ፣ ጽድቅህም እንደ ባሕር ሞገድ በሆነ ነበር ዘርህም እንደ ባሕር አሸዋ የሆድህም ትውልድ እንደ ምድር ትቢያ በሆነ ነበር፡፡›› በማለት እንደተናገረው፣ ሰላማዊ መሆን ለራስም ለሌሎችም ደስታን መፍጠር ነው። ቅዱስ ዳዊት ‹‹የዋሆች ግን ምድርን ይወርሳሉ በብዙም ሰላም ደስ ይላቸዋል›› እንዲል። ሰላማዊ መሆን ከመለያየት ይልቅ አንድነትን ማምጣት ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ወንድሞች ሆይ ሁላችሁ አንድ ንግግር እንድትናገሩ በአንድ ልብ እና በአንድ ሐሳብም የተባበራችሁ እንድትሆኑ እንጂ መለያየት በመካከላችሁ እንዳይሆን በክርስቶስ ስም እለምናችኋለሁ›› በማለት በአፅንዖት ይመክረናል፡፡

ስለ ሰላም ምን እናድርግ? ጸሎት ስናደርግ ሰላም እንዲሆን ሁሉም መጸለይ አለበት። ነቢየ እግዚአብሔር ኤርምያስ ‹‹ሰላምን ፈልጉ ስለ እርስዋም ወደ እግዚአብሔር ጸልዩ›› እንዲል። ነቢዩ ዘካርያስ ‹‹እውነትን እና ሰላምን ውደዱ›› ብሏል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ‹‹ሰላምን እንያዝ››። ቅዱስ ዳዊት ደግሞ ‹‹ሕይወትን የሚፈቅድ ሰው ማን ነው? በጎ ዘመንን ማየት የሚወድ ማነው? አንደበትህን ከክፉ ከልክል፣ ከንፈርህም ሽንገላን እንዳይናገር፣ ከክፉ ሽሽ፣ መልካምንም አድርግ፣ ሰላምን ሻት ተከተላትም። ቅዱስ ያሬድም ‹‹ጥቅምን መሠረት ሳያደርግ ባልንጀራውን የሚወድ ከእግዚአብሔር ነው›› እንዳለ። (ድጓ)

በተቀደሰ ሰላምታ ሰላም መባባል በዕለት ከዕለት ኑሯችን ሰላምን መተግበር /ሰላምታ መለዋወጥ/ ጠብ ጫሪ፣ ነገር ፈላጊ አለመሆን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በየትኛውም ቦታ በሔድንበት ሁሉ ሰላም መባባል እንዳለብን ሲያስተምረን ‹‹ወደ ማንኛውም ሰው ቤት ስትገቡ ሰላምታ አቅርቡ፡፡›› ‹‹አስቀድመህ ከወንድምህ ጋር ታረቅ በኋላም መጥተህ መባህን አቅርብ›› ብሏል። ቅዱስ ጳውሎስም ‹‹እንግዲያስ ሰላም የሚቆምበትን እርስ በርሳችንም የምንታነጽበትን እንከተል›› እንድናለን፡፡

በአሁኑ ጊዜ በሀገራችን ሰላምን ከሚነሱ ምክንያቶች አንዱ ዘረኝነት ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘረኝነት በእግዚአብሔር ዘንድ የሚያስቀጣ ነው። ሙሴ ኢትዮጵያዊቷን በማግባቱ እኅቱ ማርያም እና ወንድሙ አሮን ተቃውመው ነበር። እነዚህ ሰዎች የሙሴን ድርጊት በመቃወማቸው እግዚአብሔርን አስቆጡት እግዚአብሔርም ተቆጥቶባቸው ሄደ ደመናውም ከድንኳኑ ተነሣ እነሆም ማርያም ለምጻም ሆነች ተብሎ እንደተጻፈ። ቅዱስ ጳውሎስ ዘረኝነትን ደጋግሞ አውግዞ አስተምሯል። የሰው ልጅ ሁሉ አንድ እንደሆነ አንድነትን አሟልቶ እና አስፍቶ አስተምሯል፡፡

‹‹አይሁዳውያንና አረማውያን አለየም አንዱ ጌታ የሁሉ ጌታ ነውና፣ እኛ ሁላችንም በአንድ መንፈስ አንድ አካል ለመሆን ተጠምቀናል አይሁድ ብንሆን፣ አረማውያንም ብንሆን፣ ባሪያዎች ብንሆን፣ ነፃዎችም ብንሆን ሁላችን አንድ መንፈስ ጠጥተናልና። ‹‹ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋልና አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም። ወንድም ሴትም የለም ሁላችሁም በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና›› እንዲል።

ማንም ሰው ራሱ ስለፈለገ አልተወለደም። ራሱም ስለመረጠ ከፈለገው ጎሣ አልተወለደም። ማንም ሰው ስለፈለገ ጥቁር ወይም ነጭ አይሆንም። ሰው ሁሉ አንድ ነው። ልዩነት ከቤታችን ጀምሮ አለ። አንዱ ቀይ፣ አንዱ ጥቁር፣ አንዱ ቀይ ዳማ፣ አንዱ ጠይም ወ.ዘ.ተ ይሆናል። ልዩነት ከስምም ጀምሮ ከቤት ይጀምራል። ስለዚህ ልዩነት ያለ የሚኖር ጉዳይ ነው። ግን ይህ ልዩነት ለጠብ የሚዳርግ አይደለም። ሰላማዊ ሰው አለመሆን በማኅበራዊ ሕይወት የሚያስከትለው ችግር መንግሥተ እግዚአብሔርን አለማግኘትን ያስከትላል። ሰላምን የሚያደፈርሱ ሰዎች በአምላክ መንግሥት ሥር እንዲኖሩ አይፈቀድላቸውም። ነቢየ እግዚአብሔር ሚክያስ ‹‹በመኝታቸው ላይ በደልን ለሚያስቡ ክፋትንም ለሚያደርጉ ወዮላቸው›› ቅዱስ ዳዊት ‹‹ዐመፃን የወደዳት ግን ነፍሱን ጠልቷታል››

ሻሎም ! አሜን።

በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን) fenote1971@gmail.com

አዲስ ዘመን መጋቢት 14 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You