ጉብኝቶቹ የልማት አቅሞች ናቸው !

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶክተር) ባለፈው ሰሞን የምሥራቅ ሐረርጌ አካባቢዎችን፣ ሐረር እና ድሬዳዋ ከተማን ጎብኝተዋል፡፡ ቀደም ሲልም በምዕራብ ሸዋ የአምቦ ከተማን እና የመከላከያ ኢንዱስትሪዎችን እንዲሁም ሌሎች የተለያዩ አካባቢዎችን ጎብኝተዋል፡፡ ሰሞኑን ደግሞ በባሕር ዳር ጉብኝት አድርገዋል፡፡

በምሥራቅ ኢትዮጵያ ጉብኝታቸው በየአካባቢዎቹ እየተካሄዱ የሚገኙ ውጤታማ የግብርና፣ የኢንዱስትሪ፣ የከተማ ልማትና የሀገር መከላከያ የልማት ሥራዎችን ተመልክተዋል፡፡ የልማት ሥራዎቹ አበረታች መሆናቸውን በመግለጽም ለሀገር ልማት ያላቸውን ፋይዳም አስታውቀዋል፡፡ የየአካባቢዎቹ አስተዳደርና ሕዝብ በልማት ሥራዎቹ እያከናወኑ ያሉትን ተግባር አርዓያነት ያለው መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በምሥራቁ የሀገሪቱ ክፍል በግብርናው ዘርፍ በሴፍቲኔት ይተዳደሩ የነበሩ ወገኖች በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት እያከናወኑ ያሉት ሰፊ ሥራ፣ የመከላከያ ተቋማት በቤቶችና በመሳሰሉት ልማቶች፣ በኢንዱስትሪው ዘርፍም እንዲሁ በግራናይትና በብረታ ብረት ልማት ዘርፍ እየተከናወኑ ያሉትን ሥራዎችን ተመልክተው አድንቀዋል፡፡

በአማራ ክልል ባሕር ዳር ከተማ ባደረጉት ጉብኝትም ከተማዋ ያላትን የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ እያከናወነች ያለችውን የኮሪዶር ልማት ተመልክተው አድንቀዋል፡፡ የተፈጥሮና የሰው ጥበብ ተዋደው የባሕርዳርን ውበት ይበልጥ እያወጡት መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ልማቱን በፈተና ውስጥ የተካሄደ ሲሉም ገልጸውታል፡፡ ባሕር ዳር ለፈተና የተወረወረን ድንጋይ ለግንባታ ተጠቅማለች ሲሉም ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በክልሎች የሚካሄዱ የልማት ሥራዎችን በተለያዩ መንገዶች እንደሚከታተሉ ይታሰባል፡፡ የልማት ሥራዎቹን በግንባር ቦታው ላይ ተገኝተው መመልከታቸውና ስለተመለከቷቸው የልማት ሥራዎችም አድናቆታቸውን መቸራቸው ትርጉሙ ብዙ ነው፡፡

በጉብኝታቸው ስለተመለከቷቸው የልማት ሥራዎች በሚያስተላልፏቸው መረጃዎች መላ ኢትዮጵያውያንም በየአካባቢው ያለው ልማት እንዴት እየተፈጸመ እንዳለ መረዳት የሚያስችሉ ናቸው፡፡ ከዚህም ክልሎች ከተማ አስተዳደሮችና ሌሎች የአስተዳደር እርከኖችና ሕዝቡና ባለሀብቶች ብዙ ተሞክሮ እንደሚቀስሙ ይጠበቃል፡፡

እነዚህን ሥራዎች በዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት፣ ግምገማና በመሳሰሉት በዝርዝርም ባይሆን መድረስ እንደሚቻል ቢታወቅም፣ ዓይን አይቶ ልብ ይፈርዳል እንዲሉ አፈፃፀማቸውን ቦታው ላይ ተገኝተው መመልከታቸው የየከተሞቹ አመራርና ሕዝብ የጀመሩትን ሥራ ይበልጥ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ተጨማሪ አቅም ሆኖ ሊያገለግል ይችላል፡፡ በየአካባቢዎቹ በከተማ አስተዳደሮችና በነዋሪዎች ምን ያህል ሥራዎች መሬት ላይ ወርደው እየተሠሩ መሆናቸውን በቅርበት ለመረዳት ይጠቅማል፡፡ ክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮች፣ ተቋማትና ሕዝቡ ልማታቸው በመሪያቸው መጎብኘቱ ልዩ ደስታ የሚፈጥርባቸው ከመሆኑ በተጨማሪ ለልማት ይበልጥ እንዲነሳሱ ያደርጋቸዋል፡፡

እነዚህን የልማት ሥራዎች ተመልክተው የሚሰጧቸው አስተያየቶች በሌሎች አካባቢዎች ለሚካሄዱ ተመሳሳይ የልማት ሥራዎች መፋጠን የበኩላቸውን አስተዋፅዖ ያበረክታሉ ተብሎም ይታመናል፡፡ ገና ብዙ ልማት የሚጠበቅ እንደመሆኑ የየአካባቢዎቹ አስተዳደሮችና ሕዝቦች ለልማቱ ይበልጥ እንዲነሳሱም ለማድረግም ይጠቅማል፡፡

ሪፖርቶች ተጨባጭ ስዕል የማያሳዩ እንደመሆናቸው እንዲህ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚያደርጉት ልማቶቹ በተካሄዱባቸውና በሚካሄዱባቸው ቦታዎች ተገኝቶ ያሉበትን ደረጃ፣ ያመጡትን ለውጥ መመልከት ስለልማቱ ለመመስከር ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡

በጉብኝት ወቅት የሚገኝ እውነታ ከሪፖርትም ሆነ በግምገማ ወቅት ከሚገኝ መረጃ ይልቅ በእጅጉ የሚናገር እንደመሆኑ ይህን እውነታ ለማግኘት ያስቻለ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ መሰል ጉብኝቶችን በማድረግ ይታወቃሉ፤ ይለያሉም፡፡ በዚህም በርካታ አካባቢዎች በመገኘት የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል፤ ከየአካባቢው ሕዝብ ተወካዮች ጋርም መክረዋል፡፡ እነዚህ ጉብኝቶች ደግሞ በአንዴ የቀሩ አይደሉም፤ ቀጣይነት ያላቸው ናቸው፡፡ ይህም መሆኑ ሥራዎችን ከዳር ለማድረስ ሲደረግ ለቆየው ጥረት ትልቅ ድጋፍ ሆኖ አገልግሏል ተብሎ ይወሰዳል፤ እየተደረገ ላለው ጥረትም ሌላ ትልቅ አቅም በመሆን ያገለግላል፡፡

በጉብኝታቸው ደግሞ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮችን፣ ሚኒስትሮችን ጭምር ይዘው ይሄዳሉ፡፡ ይህም ለክልሎች ጥሩ ተሞክሮ ከመሆኑ በተጨማሪ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮችም በራሳቸው ተከታታይነት ያለው ጉብኝት በማድረግ በየክልሎቻቸው የሚካሄዱ የልማት ሥራዎችን በአካል ተገኝተው እንዲመለከቱና ሥራዎቹን ከሪፖርትና ግምገማ ባሻገር መመልከት እንዲችሉ መንገድ ያሳያል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝቶች የየአካባቢው አስተዳደሮች፣ ሕዝብና አልሚዎችም ጭምር መንግሥት ከአጠገባቸው መሆኑን ይበልጥ እንዲገነዘቡ ማድረግ ያስችላሉ፡፡ ክልሎች፣ ተቋማትና ሕዝቡ የሚሠሩት ለራሳቸው አካባቢ ብቻ ሳይሆን ለሀገርም ለመላው ሕዝብም መሆኑን እንዲረዱና ሥራቸውን ይበልጥ ሰፋ አርገው አጠናክረው እንዲቀጥሉ ለማድረግ ይጠቅማል፡፡

ሌሎች የክልል፣ የከተማ፣ የዞን የወረዳና የቀበሌ እንዲሁም የተቋማት አመራሮችም ተመሳሳይ የጉብኝት መርሐ ግብሮች በቋሚነት በማዘጋጀት አርሶ አደሮች፣ የከተማ ነዋሪዎችና ባለሀብቶች ሥራዎቻቸውን እያከናወኑ ያሉበትን ሁኔታ መቃኘት ይኖርባቸዋል፤ እርግጥ ነው አንዳንድ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች ሰፋፊ ጉብኝቶችን ያደርጋሉ፡፡ ሁሉም ይህን በዘላቂነት ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡

ይህም ልማቱ የት እንደደረሰ በአካል ተገኝተው ለመረዳት እንዲሁም የልማቱ አጋርነታቸውን ለማረጋገጥ ያስችላቸዋል፡፡ የፕሮጀክቶቹን ችግሮችን ለመፍታት፣ የስኬቶችን ምስጢርም ተረድቶ ሌሎች ፕሮጀክቶች ተሞክሮ ለመቅሰም ትልቅ አቅም ይሆናል!

አዲስ ዘመን መጋቢት 14 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You