ተጠባቂዎቹ የ3ሺህ ሜትር ድሎች

የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ቻምፒዮና ትናንት በቻይናዋ የባህል ከተማ ናንጂንግ ተጀምሮ ነገ ይጠናቀቃል። ኢትዮጵያውያን አትሌቶችም ዛሬ ከሰዓት በኋላና ነገ ሜዳሊያ የሚያጠልቁባቸው ውድድሮች ይጠበቃሉ።

3ሺህ ሜትር ሴቶች

ዛሬ ከሰዓት በኋላ 8:15 በሚካሄደው የሴቶች 3ሺህ ሜትር ፍፃሜ በድንቅ አቋም ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያዊት አትሌት ፍሬወይኒ ኃይሉ በዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ግላስጎ ላይ የወርቅ ሜዳሊያ ባጠለቀች በዓመቱ ሌላ ወርቅ ለማጥለቅ ተቃርባለች።

የ24 ዓመቷ ኮከብ በግላስጎው ተመሳሳይ ቻምፒዮና በ1500 ሜትር ስታሸንፍ በውድድር ዓመቱ በቤት ውስጥ ፉክክሮች አንድም ሽንፈት አልገጠማትም። ዘንድሮም የውድድር ዓመቱ ለወጣቷ አትሌት የተለየ አይደለም። የተለየ የሚያደርገው አምና ከተወዳደረችበት 1500 ሜትር ከፍ ብላ በ3000 ሜትር መወዳደሯ ነው። ፍሬወይኒ 2025 የውድድር ዓመትን በአንፃራዊነት ለእሷ አዲስ ወደሆነው 3000 ሜትር ፉክክር አተኩራ ብትጀምርም የተሻለ ልምድ ካላቸው አትሌቶች ልቃ ነው መታየት የቻለችው።

ባለፈው የፈረንጆች የካቲት ወር ኦስትራቫ ላይ ባደረገችው ውድድር 8:24:17 የሆነ የራሷን ምርጥ ሰዓት አስመዝግባለች። ከዘጠኝ ቀን በኋላም ሌቪን ላይ ከኦስትራቫው የተሻለ 8:19:98 በማስመዝገብ በየጊዜው ብቃቷ እየተሻሻለና እያደገ እንደሚሄድ አሳይታለች። ይህ ሰዓቷም በቤት ውስጥ ውድድር ታሪክ ሦስተኛው ፈጣን ሰዓት ሆኗል። በሌቪኑ ውድድር የተሻለ ፈጣን ሰዓት ከማስመዝገቧ ባሻገር የሦስት የተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ቻምፒዮኗን ኢትዮጵያዊት አትሌት ጉዳፍ ፀጋይ ማሸነፏ በራስ መተማመኗን ይበልጥ አሳድጎላታል።

በዚህ ቻምፒዮና የቅርብ ተፎካካሪዋ ጉዳፍ ትኩረቷን በ1500 ሜትር ብቻ በማድረጓ ፍሬወይኒ ወርቁን ለማጥለቅ በብርቱ የሚፈትናት ተፎካካሪ አለ ማለት ይከብዳል። የተለየ ነገር ካልተፈጠረ በቀር በርካቶች ከውድድሩ አስቀድሞ ወርቁን አጥልቀውላታል።

ፍሬወይኒ እርግጠኛ በሚባል ደረጃ ለወርቅ ሜዳሊያው ብትታጭም ወጣቷ ኢትዮጵያዊት አትሌት ብርቄ ኃየሎም ተፎካካሪዋ ትሆናለች። ብርቄ ፍሬወይኒና ጉዳፍ ተከታትለው በገቡበት የሌቪኑ ፉክክር ሦስተኛ ሆና ስታጠናቅቅ ያስመዘገበችው 8:25:37 ሰዓት የዓለም ከ20 ዓመት በታች ክብረወሰን ሆኖ መመዝገቡ ይታወቃል።

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ካለፉት 11 የዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና የሴቶች 3000 ሜትር ውድድር ዘጠኙን ማሸነፋቸው ዘንድሮም ናንጂንግ ላይ ዓለም የተለየ ታሪክ እንዳይጠብቅ አድርጎታል።

3ሺህ ሜትር ወንዶች

ከዓለም ቻምፒዮና እስከ ኦሊምፒክ ያላጠለቀው የወርቅ ሜዳሊያ የለም። በአውሮፓ የአትሌቲክስ ቻምፒዮናዎችም ያልተቀዳጀው ድል አይገኝም። በደማቅ አትሌቲክስ ሕይወቱ ጉዞ ያላሳካው አንድ ነገር ግን አለ። ይህም የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ቻምፒዮና የወርቅ ሜዳሊያ ነው። ኖርዌዣዊው ኮከብ አትሌት ጃኮብ ኢንገብሪግስተን ከወቅቱ የመካከለኛና ረጅም ርቀት ፈርጦች አንዱ መሆኑ አያከራክርም።

ቀረኝ የሚለውን የቤት ውስጥ ቻምፒዮና ወርቅ ለማጥለቅም ዛሬ ቀን 8:35 የሚካሄደውን ውድድር በጉጉት እየጠበቀ ይገኛል። በቤት ውስጥና ከቤት ውጭ የተለያዩ የዓለም ክብረወሰኖችን እያነከተ የግሉ በማድረግ ላይ የሚገኘው ጃኮብ በዘንድሮው የዓለም ቻምፒዮና ከአንድም ሁለት ወርቅ አልሞ ታሪክ ለመሥራት ቆርጧል። በ1500 እና 3000 ሜትሮች ሁሉንም ድል ጠራርጎ ለመውሰድ ትልቅ ግምት የተሰጠውም ይህ የ24 ዓመት ኮከብ ነው።

ጃኮብ ባለፉት ሦስት የአውሮፓ የቤት ውስጥ ቻምፒዮናዎች በ1500 እና 3000 ሜትር ጥምር ወርቆችን ማጥለቅ ለምዷል። ከቤት ውጪ የአውሮፓ ቻምፒዮና ላይም ያለው ታሪክ ተመሳሳይ ነው። ይህም ካለው አስደናቂ ወቅታዊ ብቃት አንፃር በዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና ለጥምር ድል ቢታጭ አያስገርምም።

ቅልጥመ ረጅሙ ኖርዌዣዊ ኮከብ በዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና 2022 ቤልግሬድ ላይ በ1500 ሜትር ተሳትፎ የብር ሜዳሊያ ነበር ያጠለቀው። የያኔው ጃኮብና የአሁኑ ግን በብቃት ረገድ በብዙ ይለያያሉ። በፓሪሱ ኦሊምፒክ የ5000 ሜትርን ወርቅ ካጠለቀ ወዲህ ፉክክሩ ከሰዓት ጋር ሆኗል። ከጥቂት ወራት በፊት ሌቪን ላይ የ1500 እና የማይል የቤት ውስጥ የዓለም ክብረወሰኖችን የጨበጠው ጃኮብ የ3000 ሜትር የዓለም ክብረወሰንም በእጁ ይገኛል።

ጃኮብ ናንጂንግ ላይ ጥምር ወርቅ ካሳካ ከጀግናው አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሤ ቀጥሎ ሁለተኛው ታሪካዊ አትሌት ይሆናል። ኃይሌ እኤአ 1999 ማባሺ ጃፓን በተካሄደው የዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና ላይ በ1500 እና በ3000 ሜትር ወርቅ ማጥለቁ ይታወሳል። ጃኮብም የጀግናውን የኃይሌን ታሪክ ለመጋራት ጉጉት እንዳለው ተናግሯል።

ያም ሆኖ ኖርዌዣዊው ብቸኛውን የኃይሌን ታሪክ ለመጋራት ኢትዮጵያውያን ወጣት ከዋክብት ዛሬ ይፈቅዱለታል? የጃኮብ ትልቁ ፈተና ይህ ነው። ይህን ጥያቄ ለመመለስ በውድድሩ ከሦስት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ጋር ብርቱ ትግል አድርጎ ማሸነፍን ይጠይቃል።

በፓሪስ ኦሊምፒክ የ10000 ሜትር የብር ሜዳሊያ አሸናፊው ወጣት ኮከብ በሪሁ አረጋዊ ብቸኛውን የኃይሌ ታሪክ የማስጠበቅ አቅሙም ብቃቱም ያለው ታታሪ አትሌት ነው። የዓለም ከ20 ዓመት በታች ክብረወሰን ባለቤት ቢኒያም መሀሪ ሌላኛው ተስፋ የተጣለበት ኢትዮጵያዊ ወጣት ሲሆን የ3ሺህ መሰናክል ስፔሻላስቱ አትሌት ጌትነት ዋለም ከፊት የሚሰለፍ ብርቱ ተፎካካሪ ነው። ሦስቱም ኢትዮጵያውያን ኮከቦች በ3000 ሜትር የቤት ውስጥ ውድድር ከ7:30 በታች ማጠናቀቅ የቻሉ አትሌቶች መሆናቸው የአሸናፊነት ግምት ለተሰጠው ጃኮብ መንገዱ ጨርቅ እንደማይሆንለት ጠቋሚ ነው።

ቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 13 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You