የፍጥነት መንገድ ፕሮጀክት ግንባታውን የማፋጠን ጥረት

የሞጆ ሃዋሳ የፍጥነት መንገድ አካል የሆነው የሞጆ ባቱ የፍጥነት መንገድ ግንባታ ተጠናቅቆ ወደ ሥራ ከገባ ቆይቷል፡፡ የዚህ መንገድ ሁለተኛ ምእራፍ የባቱ-አርሲ ነገሌ የፍጥነት መንገድ ፕሮጀክት ግንባታ በአሁኑ ጊዜ አየተፋጠነ ይገኛል።

የዚህ ቀጣይ ክፍል የሆነው የባቱ-አርሲ ነገሌ የፍጥነት መንገድ ግንባታ ዋና የአስፓልት ሥራ እስከ መጪው ነሐሴ ወር 2017 ዓ.ም ድረስ እንደሚጠናቀቅ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር አስታውቋል።

የአዲስ አበባ ሞያሌ – ናይሮቢ – ሞምባሳ የፍጥነት መንገድ ኮሪደር አካልና 10 ሺህ ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው ከግብጽ ካይሮ እስከ ደቡብ አፍሪካ ኬፕታውን ድረስ የሚዘልቀው “የትራንስ አፍሪካን ሃይ ዌይ” መንገድ ክፍል የሆነው ይህ የሞጆ – ሃዋሳ የፍጥነት መንገድ ፕሮጀክት በተለያዩ ምዕራፎች ተከፋፍሎ ሲገነባ ቆይቷል።

ፕሮጀክቱ ግንባታው ሲጠናቀቅ ትልቅ ሀገራዊ እና አህጉራዊ ፋይዳ እንዳለው ከኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የተገኘ መረጃ ይጠቁማል። መንገዱ ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ የሚካሄድበት፣ በየአካባቢው የሚገኙ የቱሪዝም ሥፍራዎችን ተደራሽ የሚያደርግ ነው።

የሞጆ ሃዋሳ – የፍጥነት መንገድ ግንባታ በአጠቃላይ 3000 ያህል ለሚሆኑ ሠራተኞች የሥራ እድል መፍጠሩን እንዲሁም የባቱ- አርሲ ነገሌ የመንገድ ክፍል ብቻ ለ700 ሰዎች የሥራ እድል መፍጠሩን የኢትዮጰያ መንገዶች አስተዳደር መረጃ አመልክቷል።

በኢትዮጵያ የመንገዶች አስተዳደር የባቱ አርሲ ነገሌ የፍጥነት መንገድ ግንባታ ያለበትን ደረጃ ሰሞኑን ለጋዜጠኞች አስጎብኝቷል፡፡ በዚህም በርካታ በግንባታ ላይ የሚገኙ ማሳለጫዎች፣ ድልድዮች፣ የአስፓልት ግንባታ እንቅስቃሴዎች ተጎብኝተዋል።

የሞጆ ሃዋሳ የፍጥነት መንገድ ፕሮጀክት ማናጅመንት ፅህፈት ቤት ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር አዲስሕይወት ታደሰ በወቅቱ እንደተናገሩት፤ ፕሮጀክቱ አሁን 85 በመቶ አፈፃፀም ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ከዋናው መንገድ ሥራ ጋር የተያያዘውን ሥራ እስከ ነሐሴ 2017 ዓ.ም መጨረሻ ለማጠናቀቅ ታቅዷል።

የፍጥነት መንገድ ዋናው ሥራ ከአስፓልት ሥራው ጋር የተያያዘ ብቻ አይደለም፤ የክፍያ ጣቢያዎች ግንባታ የተሻጋሪ መንገዶች መሠረተ ልማት እና የሲስተም ዝርጋታ ሥራዎች መኖራቸውንም ኢንጂነሩ ጠቁመዋል።

ኢንጂነር አዲስ ሕይወት እንደተናገሩት፤ የባቱ-ሃዋሳ የፍጥነት መንገድ ፕሮጀክት ርዝመት 57 ነጥብ ስድስት ኪሎ ሜትር ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ የአፈር ስራው 99 በመቶ ተጠናቅቋል።

ፕሮጀክቱ ከ200 በላይ የውሃ መፋሰሻ ቱቦዎች ግንባታ ይካሄድበታል። መሻጋገሪያዎች ሙሉ ለሙሉ ተጠናቅቀዋል። 54 በመቶ የመጀመሪያውና ሁለተኛው የአስፓልት ንጣፍ ስራ ተጠናቅቋል። አስፋልት ያልነካው ሶስት ኪሎ ሜትር ብቻ ነው። የ35 ኪሎ ሜትሩ የመጨረሻ የአስፓልት ንጣፍ ስራም ተጠናቅቋል። ቀሪው ስራም በፍጥነት እየተሰራ ይገኛል።

መንገዱ እግረኞች እና ከብቶች የሚያልፉበት መሿለኪያ እና መሸጋገሪያዎችም አሉት። የመሿለኪያው ግንባታም 100 በመቶ ተጠናቅቋል፤ መሸጋገሪያዎቹ ደግሞ 80 በመቶ ላይ ደርሰዋል። ሁለት ማሳለጫዎች ተካተው እየተሰሩ ይገኛሉ። እነዚህም የቡልቡላ ማሳለጫ እና የላንጋኖ ማሳለጫ ናቸው።

የባቱ -አርሲ ነገሌ የፍጥነት መንገድ ፕሮጀክት ሙሉ በሙሉ በዓለም ባንከ ድጋፍ በአራት ነጥብ ስድስት ቢሊየን ብር እየተሰራ ይገኛል፡፡ እስካሁን የዓለም ባንክ ለፕሮጀክቱ ከመደበው አራት ነጥብ ሶስት ቢሊየን ብር አለማለፉን ኢንጂነሩ ጠቅሰው፣ በጥሩ አፈጻጸም ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ኢንጂነር አዲስ ህይወት እንደገለፁት፤ የመንገዱ የአስፓልት ንጣፍ ሥራ በሦስት ደረጃ እየተከናወነ የሚገኝ ሲሆን፣ በእስካሁኑም የመጀመሪያው Dense Bituminous Macadam (DBM) ንጣፍ ሥራ 53 ኪሎ ሜትር፣ የሁለተኛው 52 ኪሎ ሜትር እንዲሁም የመጨረሻው ደግሞ 35 ኪሎ ሜትር የሚሆነው ሥራ ተገባድዷል።

የዚህ ፕሮጀክት ግንባታ ሙሉ በሙሉ ከከተማ ውጪ የሚያልፍ ሲሆን፣ ከከተማዎች ጋር የሚያስተሳስሩ አገናኝ መንገዶች የሚሠሩለት ይሆናል።

የፍጥነት መንገዱ በ90 ሜትር የመንገድ ወሰን ውስጥ የሚገኝ ሆኖ ያለው አጠቃላይ የጎን ስፋት 31 ነጥብ 6 ሜትር ይሆናል። የአገናኝ መንገዶቹ ደግሞ በገጠር 10 ሜትር እና በከተማ ደግሞ 22 ነጥብ 5 ሜትር ስፋት ያላቸው ናቸው።

ከፍተኛ የሥራ እንቅስቃሴ ከሚታይበት ሳይቶች አንዱ የሆነው የቡልቡላ ማሳለጫ የሚገነባበት ቦታ፣ ከቡልቡላ አላጌ እና የቡልቡላ ከተማን አስተሳስሮ በሚገኘበት ሥፍራ ላይ ነው።

የዚህም ማሳለጫ አብዛኛዎቹ የአፈር ሙሊት ሥራዎች ተጠናቅቀው ሌሎች የክፍያ መንገድ ሥርዓትን ለማስተናገድ የሚጠቅሙ የክፍያ ጣቢያዎች ግንባታ ጎን ለጎን እየተሠሩ ይገኛሉ።

የማሳለጫ መግቢያና መውጫ ራምፖች፣ ድልድዮች፣ ከተማ ድረስ የሚገባ ሁለት ኪሎ ሜትር ማገናኛ መንገድ ጭምር ከዋናው መንገድ ጋር ተያይዞ ጎን ለጎን እየተሠራ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ መንገዱን ተረክቦ ሲያስተዳድር ከሚጠቀማቸው ቢሮዎች፣ ጋራዦች፣ ከትራፊከ ማዕከላት፣ ከከባድ ጭነት መለኪያ ሚዛኖች ጋር ተያይዞ የሚሠሩ ሥራዎች ጭምር አካቶ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።

የአስፓልት ሥራዎች ግንባታው ከንጋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ እስከ ምሸት ሁለት ሰዓት ድረስ እየተሠሩ መሆናቸውን ጠቁመው፣ የጸጥታ ኃይሎችም የአካባቢውን ደህንነት እየጠበቁ መሆናቸው የዚህ ቀጣይ ክፍል የሆነው የባቱ-አርሲ ነገሌ የፍጥነት መንገድ ግንባታ ዋና የአስፓልት ሥራ አስከ መጪው ነሐሴ ወር 2017 ዓ.ም ድረስ እንደሚጠናቀቅ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር አስታውቋል።

በዚህ የፍጥነት መንገድ ፕሮጀክት ግንባታ ከወሰን ማስከበር ሥራ ጋር ተያይዞ ተግዳሮቶች መኖራቸውን ጠቁመዋል። በአዲሱ አዋጅ መሠረት የወሰን ማስከበር ሥራ የክልል ኃላፊነት መሆኑ ችግሮቹን ለመፍታት እንደሚያስችል ይታመናል ። የክፍያ ከመፈጸም፣ ልኬት ከማከናወን፣ አርሶ አደሮችን ከማስነሳት ሥራዎች ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮች የሚፈቱ ከሆነ ዋናውን የመንገድ ሥራ እስከ ነሐሴ ወር ለማጠናቀቅ መታቀዱን ጠቁመዋል።

የዋናው መንገድ ግንባታ ቢያልቅም የፍጥነት መንገዱ ለአገልግሎት ክፍት የሚሆነው ተያይዘው መሠራት ያለባቸው የክፍያ፣ የደህንነት ሲስተም ዝርጋታዎች ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቁ ነው ያሉት ኢንጂነሩ፣ አጠቃላይ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቅቆ ለትራፊክ ክፍት ለማድረግ መታቀዱን ገልፀዋል።

በኢትዮጵያ የፍጥነት መንገድ ግንባታ የመጀመሪያው የአዲስ አበባ አዳማ የፍጥነት መንገድ ሲሆን፣ ይህም ከ10 ዓመት ተገንብቶ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ ሌላው ከድሬዳዋ እስከ ደወሌ ያለው መንገድ ነው። የሞጆ ሃዋሳ የፍጥነት መንገድ ሶስተኛው መንገድ ሲሆን፣ በአራት ክፍሎች ተከፋፍሎ የሚገነባ ነው፡፡ አጠቃላይ ርዝመቱም 202 ኪሎ ሜትር ነው።

የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታው ሰባት ዓመታትን መውሰዱን መስከረም 2014 ዓ.ም ላይ ለትራፊክ ክፍት መደረጉም ተጠቁሟል፡፡ ከአርሲ ነገሌ-ሃዋሳ የፍጥነት መንገድ ግንባታ በጥሩ አፈጻጸም ላይ እንደነበረ አስታውሰው፣ ከአበዳሪ ተቋም ጋር ተያይዞ መቋረጡንም ገልፀዋል። ችግሮቹን ለመፍታትም ከሚመለከተው አበዳሪ አካል እና የመንግሥት ቢሮዎች ጋር የቅርብ ውይይቶች እየተደረጉ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

የዚህ አካል የሆነው የሞጆ መቂ – ባቱ መንገድ ግንባታ ከሶስት ዓመታት በፊት ተጠናቅቆ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።

የመንገድ ኮሪደሩን ከነባሩ መንገድ ጋር በማስተያየት ተጠቃሚዎች የሚያነሱትን አስተያየት ለመቀበል ተችሏል። የዚህ መንገድ ተጠቃሚ የአካባቢው ነዋሪዎች እና አሽከርካሪዎች መንገዱ ከትራፊክ መጨናነቅ እንዲሁም ይህን ተከትሎ ሊደርስባቸው ከሚችል አደጋ የታደጋቸው መሆኑን በመግለጽ ደስተኞች መሆናቸውን ይገልጻሉ።

አሽከርካሪ ፈይሳ በለጠ፣ ከሃዋሳ አዲስ አበባ፣ አዳማ እንዲሁም ቡታጀራ መስመር ላይ ይሠራል። የፍጥነት መንገዱ በሙሉ ተጠናቅቆ አገልግሎት ቢጀምር የጉዞ ሰዓት እንደሚያሳጥር እና እንግልት እንደሚቀንስ ይገልፃል።

ነባሩ የሞጆ ባቱ መንገድ አጭር ሆኖ ለአሽከርካሪ ነፃነት የማይሰጥና በትራንስፖርት ፍሰቱ ላይ ተግዳሮት የሚሆኑ እግረኛ፣ ባጃጅ፣ የአህያ ጋሪና የመሳሰሉት የሚበዙበት መሆኑን አመልከቶ፣ በዚህ የተነሳም በጉዞ ሰዓት ላይ ፈተና ሆኖ መቆየቱን አስታውሷል። አዲስ መንገድ እንኳ ቢገነባ ከብት፣ ግመል፣ ፍየልና የመሳሰሉት እክል እንደሚፈጥሩ ተናግሯል፡፡

በአጥር በተከለለው የፍጥነት መንገድ መንቀሳቀስ የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው ጠቁሟል። የፍጥነት መንገድ ፕሮጀከት ለተሽከርካሪ ምቾት እንዳለው ጠቅሶ፣ እስከመጨረሻ እስከ ሃዋሳ ድረስ ያለው ገንብቶ ለትራፊክ ክፍት ማድረግ እንደሚገባ አመልክቷል።

የሞጆ ባቱ የፍጥነት መንገድ በብዙ መልኩ እየጠቀመ ነው የሚሉት የባቱ ከተማ አካባቢ ነዋሪው አቶ ዶሬ ሮባ፣ የፍጥነት መንገዱ በስፋት ከተሠራ በኋላ አደጋ ቀንሷል ይላሉ። ቀደም ሲል በድሮው መንገድ ከባቱ ከተማ አዲስ አበባ ለመሄድ በመንገድ ላይ መንገላታት እና መዘግየት በስፋት ይስተዋል እንደነበር አስታውሰዋል። ተሽከርካሪዎች በየከተማው ገብተው ይቆማሉ፣ ታማሚ ይዘን ስንሄድ መንገድ ላይ ሊሞትብን ይችላል፣ አሁን ግን በፈጣን መንገዱ አዲስ አበባ ከሁለት ሰዓት በታች በፍጥነት መድረስ እየተቻለ ነው ይላሉ። በፍጥነት የታሰበው ቦታ እና ጉዳይ ለመድረስ የፍጥነት መንገዱ ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ መንገዱ ወደ ግንባታ ሲገባ ለልማት ተነሺዎች ተገቢው ካሳ መከፈሉን ጠቅሰው፣ ተነሽዎችም በዚህ ኑሯቸውን ማሻሻል መቻላቸውንና በልማቱ ደስተኛ መሆናቸውን አስታውሰዋል።

ቀደም ሲል በ2012 ዓ.ም በመንገድ መጣበብ የተነሳ በደረሰው የትራፊክ አደጋ ባጃጅ ውስጥ ስምንት ሰው መሞቱን አስታውሰው፣ አሁን ግን የፍጥነት መንገድ መገንባቱ ችግሩን እንደሚቀርፍ ጠቁመዋል።

የኩንሃ ኢንጂነሪንግ እና ማማከር አማካሪ ኢንጂነር አሸናፊ ገዛኸኝ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ በዚህ የፍጥነት መንገድ ፕሮጀክት በዲዛይንና በግንባታው ላይ ጥራት እና ደረጃውን መጠበቅ ላይ ቁጥጥር የማድረግ ሥራዎች ይሠራሉ። ለፕሮጀክቱ ግንባታ ሥራ ላይ የሚውሉ ግብአቶችን የሚያሟሉ ዲዛይን ላይ ጥቅም ላይ ይውላል።

ፕሮጀክቱ የፍጥነት መንገድ ከመሆኑ አኳያ ከሌሎቹ ፕሮጀክቶች ለየት ያለ ደረጃቸውን የጠበቁ የጥራት ቁጥጥር እና የዲዛይን ሲስተሞች ጥቅም ላይ ይውሉበታል። ይህም መንገዱ ከፍተሻ የተሽከርካሪ ትራፊክ የሚያለፍበት እንደመሆኑ ምን ያህል ተሽከርካሪ ይሄድበታል፣ በምን ዓይነት የአየር ንብረት የሚለው፣ ለምን ያህል ጊዜ አገልግሎት ይሰጣል ፣የሚለው የሙቀት መጠን ተለክቶ ዝቅተኛውና ከፍተኛው ተለክቶ ታውቋል። በዚህም መስፈርቶች ከተለየ በኋላ አስፋልቱን ጨምሮ ያንን መቋቋም የሚችሉ ከባድ የትራፊክ ጭነት፣ ያለውን የአየር ሁኔታ ሊያሟሉ የሚችሉ ማቴሪያሎች ይመረጣሉ። አግሪጌቱም ከመፈጨቱ በፊት ጠበቅ ያለ የቁጥጥር ሥራ አለው። በተፈጥሮውም /ለግንባታው የሚያስፈልገው ድንጋይ የሚገኝበት ሥፍራ/ ኳሪው ሲመረጥ የተሻለ ይመረጣል። ሲፈጭም እንደዛው እነዚህ ብቃታቸው በአየር ንብረቱ እና የትራፊክ ፍሰቱ ላይ ተመስርቶ ይፈተሻል።

መንገዱ አገልግሎት ላይ ሲውልም ሊያጋጥሙት የሚችሉ የአስፋልት መዘርጠጥ፣ መሰንጠቅ እንዲሁም የአካባቢ ሁኔታ ዝናብ፣ ፀሐይ ሲፈራረቅ የመፈርፈርና የመሳሰሉት ሁኔታዎች ሁሉ ላቦራቶሪ ውስጥ ለመፈተሽ የሚያስችሉ ልዩ ዘመናዊ መፈተሻ መሣሪያዎች ጥቅም ላይ መዋላቸውን ገልፀዋል።

የአዲስ አበባ – ሞጆ – ሞያሌ – ላሙ – ሞምባሳ ትራንስ ኢንተርናሽናል ሀይዌይ አንድ አካል የሆነው ይኸው የመንገድ ኮሪደር-የባቱ ከተማ፣ የአዳሚ ቱሉ እና አርሲ ነገሌ ወረዳዎች ብሎም ከ17 በላይ ቀበሌዎችን የሚያስተሳስር ነው። በተጨማሪም በመስመሩ ላይ የሚገኙትን የእርሻና የኢንዱስትሪ እንዲሁም የቱሪስት መስህብ የሆኑ ቦታዎችን ለማገናኘት ያስችላል። የፍጥነት መንገዱ ግንባታ የሀገራችንን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ትስስር በማጠናከር ረገድ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው መንገድ ነው።

በኃይሉ አበራ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 13 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You