
«የወደቁትን አንሱ» የበጎ አድራጎት ማኅበር መሥራችና ባለቤት ናቸው፡፡ «ሰው ወድቆ አይቀርም» እንዲሉ ፈጣሪ አንስቷቸው ዛሬ 27 ዓመታትን ያስቆጠረውና ከ762 በላይ የእሳቸውን መሰል ችግር የገጠማቸውን ዜጎች ለመደገፍ የበቃው ማኅበር መሥራችና ባለቤት ለመሆን በቁ። እሳቸው ራሳቸውም ደጋፊና የሚያነሳቸው አጥተው ጎዳና የወደቁ ሰው ነበሩ አቶ ስንታየሁ አበጀ፡፡
ትውልድና እድገታቸው ደቡብ ጎንደር ዞን እንዳርጌ ገብርኤል ገበሬ ማኅበር በምትሰኝ ትንሽ መንደር ነው። አቶ ስንታየሁ አበጀ ሕይወታቸው ውጣ ውረድ የሞላበት በረሃብና ጥምም በብርቱ የተፈተኑ ሰው ናቸው፡፡
ምን አልባት ፃድቃንና ሰማዕታት እንጂ ሰው ገጥሞት ይፈተንበታል ተብሎ በማይገመት በሽታም ቁም ስቅላቸውን ሲያዩ ኖረዋል፡፡ ወደ ኋላ መለስ ብለው እንዳጫወቱን በደምሳሳው ከልጆች ሞት በስተቀር የመጽሐፍ ቅዱሱ ፃድቁ ኢዮብ የተፈተነበትን ፈተና በሙሉ ተፈትነው አልፈውበታል ማለት ይቻላል፡፡ እንደ ኢዮብ በጽኑ ደዌ ተይዘው መላ ሰውነታቸው በቁስል ተወርሯል፤ ሥጋቸው እንደበሰበሰ ጨርቅ ተቦጫጭቋል፡፡ በአፍ በአፍንጫቸው ያልወጣ ፈሳሽ እንደሌለ ዛሬ ቆመው ያስታውሳሉ። በዚህ ምክንያት ተገፍተዋል፤ ተገልለዋል። እንደ ሰው ቢፈጠሩም እንደውሻ ከቤት ወጥተው ዱር የተጣሉበትም ጊዜ ብዙ ነበር፡፡ የአዕምሮ ጭንቀት፤ ጉበት፣ ኩላሊት እሳቸው እንደሚጠሩት «ፍሽሽት» የሆድ ስራይ ለ18 ዓመታት ቁም ስቅላቸውን ሲያሳያቸው ቆይቷል ፡፡
«ይሄም ቢሆን ምንነቱ ታውቆ መጠሪያ ስም ያገኘው በ1981 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ ከመጣሁ በኋላ ነው» ይላሉ። እኛ 500 ነን አንተ ብቻህን አትችለንም ይለኝ ነበር..የሚሉትና..ገና ከጨቅላነታቸው ጀምሮ እንደተፀናወታቸው የሚጠቅሱት ክፉ መንፈስ በፊናው አንዴ በሕልም፤ ሌላ ጊዜ በሚገዘግዝ በሽታ እየተመሰለ ሲያስፈራራቸው እንደነበር ይናገራሉ፡፡
ከዚህ ለመፈወስ ዘመናዊ ሕክምናን ጨምሮ ፀበል እና ሌሎች እምነቶችን ማዳረስ አልቀራቸውም፡፡ ከዛም አልፍ ብለው ጥንቆላ ሳይቀር ጎብኝተዋል። 18 ዓመታት በክፉ የሕመም ደዌ ሲሰቃዩ ኖሩ እንጂ ለስንታየሁ ጠንቋይ ጥቁር ዶሮ ግዛና ራስህ ላይ አዙረህ ጣለው፤ ደብተራ ደግሞ ነጭ በግ አርደህ በፈርሱ ታጠብ ያላቸው መፍትሔ አልሆናቸውም ፡፡
አቶ ስንታየሁ ግን ሁሉንም የፈውስ መንገድ ነው ያሉትን አዳርሰዋል። ..እነዚህ ሁሉ ጋር ብሄድም የእንጦጦ ኪዳነ ምሕረትን ከልጅሽ አማልደሽ አድኚኝ ብዬ መማፀኔን አልተውም ነበር.. ይላሉ። የትውልድ ቀያቸውን ለቅቀው ወደ አዲስ አበባ የመጡት የ24 ዓመት ወጣት ሆነው እንደነበርም ያስታውሳሉ፡፡ ወደዚህ ለመምጣት የገፋቸው የእናታቸው ሞት ብቻ ሳይሆን አባታቸው እሳቸውን ጨምሮ እናታቸው ትተውላቸው ወደ ማይመለሱበት የሄዱትን አምስት ልጆች መሸከም ባለመቻላቸው ጭምር ነው፡፡ እህል ባለበት ሀገር የሚበላ፤ ውሃ ባለበት የሚጠጣና የሚታጠቡበት፤ ቤት ባለበት የሚኖሩበት ቤት አጥተዋል፡፡ ሰውነታቸው እና ልብሳቸው ቆሻሻ በመሆኑ ሰዎች እንኳን ሊያስጠጓቸው ሊያይዋቸውም ተጠይፈዋቸዋል፡፡ አዲስ አበባ ከመጡም በኋላ አለኝ የሚሉትና የሚያርፉበት ዘመድ አዝማድ ስላልነበራቸው በቀጥታ አራት ኪሎ ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን ደጃፍ ነው የወደቁት፡፡ ታዲያ ልመናም ዘዴ ይጠይቃልና ተለምኖ እንደሚበላ ባለማወቃቸው ረሃብና ጥሙ አዲስ አበባም አልቀረላቸውም፡፡
«ይሄን ሁኔታዬን ለካ አንድ የሥላሴ ዲያቆን ይመለከት ነበር›› የሚሉት አቶ ስንታየሁ እዚህ በራብና ብርድ ደርቆ ከሚሞት በሚል ቤተክርስቲያኗ አጠገብ ከሚገኝ አንድ ሰው ቤት በረንዳ ላይ ለምኖ ያስተኛቸው ያስጠልላቸዋል። በዚህ ጊዜ ውስጥም ክፉው የሕመም ደዌ አለቀቃቸውም ነበር፡፡ ትንሽ ከሕመሙ ሲያገግሙ ዲያቆኑ በ30 ብር አንድ ሰው ቤት የጥበቃ ሥራ ያስቀጥራቸዋል፡፡ ወደዚሁ ውርጭና ቅዝቃዜውን ጨምሮ ብርዱ የማይቻለው የሚተኙበት በረንዳ ስር ከሰደደው ጽኑ በሽታቸው ጋር ተዳምሮ እጅ እግራቸው እንዳይንቀሳቀስ ተቆራመደ።
ይሄኔ በዘበኝነት የቀጠሯቸው ግለሰብ ከበረንዳውም አንስተው ወደ ጎዳና ጣሏቸው፡፡ ፈጣሪ ጥሎ አይጥልምና ጎዳና ላይ መውደቃቸውን ያዩ ዘበኝነት ይሠሩበት የነበሩ የአካባቢ ነዋሪዎች ያገኟቸዋል፡፡ ዘበኝነት ይሠሩበት የነበረው ቤት ባለቤት ወይዘሮ መንበረ ደምሴ አሜሪካ ሄደው በነበረበት አንድ ዓመት ከስድስት ወር ንብረታቸውን በሚገባ ጠብቆ ያቆየላት ነው በማለት ከጎዳና አንስተው ቀድሞ ይተኙበት ወደነበረው በረንዳ መለሷቸው፡፡ እዚህ መኝታቸው ለብርድ በማያጋልጣቸው ሁኔታ በሰዎቹ ተደልድሎ ነበርና ትንሽ ሲያገግሙ አሜሪካ ሄደው የነበሩት ወይዘሮ መንበረ ወደ ሀገር ቤት በመመለሳቸው በሌላ ሰው ቤት የጥበቃ ሥራ አስቀጠሯቸው፡፡
አቶ ስንታየሁ በተቀጠሩበት ቤት ቀድሞ ያውቋቸው ያልነበሩ ሙያዎችን መማራቸውንም ያስታውሳሉ፡፡ በግ ማረድ፤ ጥበቃና የመስተንግዶ ሥራ ከተማሯቸው ሙያዎች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ እዚህ ቤት ያስገቧቸው የቀድሞ አስጠጊያቸው ጋርም እየተመላለሱም የሚሠሩበት አጋጣሚ ነበር፡፡ መደበኛ ሥራቸው ጥበቃ ይሁን እንጂ ቀጣሪያቸው የእንጀራ አብሲት እና ጠጅ ያስጥላቸው፤ ቂጣ አስጋግረው ጠላ ያስጠምቋቸው እንደነበር ይናገራሉ። በአሠሪዎቻቸው ተደራራቢ ሥራ ጫና ምክንያት ድካም በረታባቸው፤ ሕመማቸው ዳግም ተቀሰቀሰና እንደተለመደው እጅና እግራቸው ሥራ አቆመ።
ሠርተው በቋጠሩት ጥሪት በአቅራቢያው በሚገኘው ሆስፒታል ሄደው ቢታከሙም መዳን ስላልቻሉ አሠሪያቸውን ፀበል ለመፀበል ብለው ፈቃድ ጠየቁ። ሆኖም ፍቃድ ሳይሆን ከቤት እንዲወጡ አድርገው አባረሯቸው፡፡ በፀበሉ ትንሽ ፈውስ አግኝተው ሲመለሱ አሠሪያቸው እንዲሠሩ ፈቀዱላቸው፡፡ ሆኖም አብረዋቸው ይሠሩ የነበሩ ሰዎች ለአሠሪያቸው አንዴ ፀበል ሌላ ጊዜ ሆስፒታል እያለ የሚመላለሰው ታሞ ሳይሆን እዚህ ቤት ሙያ በመልመዱ ከዚህ የተሻለ ገቢ የሚያስገኝ ሥራ እየፈለገ ነው በማለት ከአሠሪያቸው ጋር አጣሏቸው፡፡
በዚህ የተናደዱት አሠሪያቸው ከፀበል ተርበው በመምጣታቸው የለመኗቸውን ቁራሽ እንጀራ እን ሳይሰጡ አባረሯቸው፡፡ የአሠሪዎቻቸው ጎረቤቶች አሠሪያቸው ቤት የነበረውን ጓዝ እንኳን ሊያስቀምጡላቸው ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡ አንቋሽሸውና ፊት ነሷቸው። አቶ ስንታየሁ አሁንም እንደልማዳቸው ደጋግሞ ጎዳና ጎበኛቸው፡፡ ይሄን የሰሙት ከወደቁበት አንስተው ወደ አራት ኪሎ ቤታቸው አመጧቸው፡፡ በጣም ተርበው ስለነበርም እስከዛሬ አረሳውም የሚሉትን እና ራባቸውን ያስታገሰላቸው የበግ ቅቅል ሰጧቸው፡፡ እሳቸው ጋር እያኖሩ ከበሽታቸው ሲያገግሙም፤ «እኔ ደመወዝ ስለማልከፍልህ ሥራ እየሠራህ በትርፍ ጊዜ ታገለግለኛል» ብለው ከወደቁበት ያነሷቸው ወይዘሮ ከአንድ ዘይት ቤት አስገቧቸው፡፡ እዚህ በአሠሪያቸው ምክር ቀን ቀን እየሠሩ ማታ ማታ በመማር ስምንተኛ ክፍል ደረሱ፡፡ በተጨማሪም ደመወዛቸውን አጠራቅመው የልብስ ስፌት ሴንጀርም ገዙና ልብስም መስፋት ቀጠሉ፡፡ የራሴ የሚሉት ጥሪት በመቋጠራቸውም ይደርስብኛል ከሚሉት ከራብ፤ እርዛትና ጥማት ስጋት ተላቀቁ፡፡ ከነበረባቸው ሥራ ብዛት የተነሳ በአንድ ዓመት ውስጥ እያቋረጡ አምስት ጊዜ ትምህርት ቤት የተመዘገቡበት እንደነበርም ያስታውሳሉ አቶ ስንታየሁ፡፡
ሆኖም ትምህርት ቤት መግባታቸው ያገለግሉበት የነበረውን የአሠሪያቸውን ሰዓት በመሻማቱ አሠሪያቸው «አንተን ጠዋሪ ነኝ ወይ» ብለው አባረሯቸው፡፡ ልጆቻቸው እንዳያስወጧቸው ቢለምኗቸውም ሊመልሷቸው አልቻሉም፡፡ «የመከራ ጊዜ እናቴ ነዎት አታስወጡኝ ብላቸውም እንቢ አሉኝ፡፡ መታወቂያ ሊያወጡልኝ የነበረውም ሰርቆ ቢሄድስ ብለው ከለከሉኝ» ይላሉ፡፡ ከዚህ ቀደም መኪና ፈተህ ሰርቀሃል ብሎ በመጠርጠር ፖሊሲ ሊያስረኝ ሲመጣ «እንኳን መኪና ፈትቶ ሊሰርቅ መፍቻውንም አያውቀው የአክስቴ ልጅ ነው» ብለው ከስር ያዳኗቸው መሆኑን በማስታወስ ቢለምኗቸውም የሰው ልጅ ባስቀመጡት ቦታ አይገኝምና በጄ አላሉም ወይዘሮዋ።
በስተመጨረሻም ይሄን የታዘቡ አንድ ግለሰብ ያስጠጓቸውና ስንታየሁ ግለሰቡ ኪቺን እያደሩ አሁንም ለመኖር የሚያደርጉትን ጥረት ይቀጥላሉ፡፡ እሳቸው እንዳወጉን እዚህ የጤናቸውን ጉዳይ ለመከታተልም ጥሩ ጊዜ ያገኛሉ፡፡ ለሰባት ተከታታይ ዓመታት ፀበል ከመጠመቃቸው ባሻገር ለበሽታቸው መፍትሔ ለማግኘትም ጠንቋይ እና ደብተራ ቤት ለመሄድ የበቁት በዚህ ጊዜ ውስጥ እንደሆነም ያነሳሉ፡፡ ዘጠኝ ጊዜ የወሰዱት የአበሻ መድኃኒትም ቢሆን አልፈወሳቸውም፡፡ ሁለት ዓመት ከስምንት ወር ያህል ሲወስዱት የነበረውና በሐኪም የታዘዘላቸው መድኃኒትም የሰጣቸው ፈውስ አልነበረም፡፡
አሁን እንዴውም በሽታቸው ከፊቱ በጣም በበለጠ ሁኔታ ከሚገባው በላይ እየጠና መጣባቸው፡፡ ውሎና አዳራቸው ለቅሶ እና እህህ እያሉ ማቃሰት ሆነ። እንዲህም ሆኖ ያስጠጋቸው ሰውዬ አልፎ አልፎም ቢሆን ከጎናቸው ሆኖ አይዞህ ይልና ያስታምማቸው፤ ያጽናናቸውም ነበር። በዚህ ትንሽ ቢጽናኑም ማዕድ ቤቱን የሰጣቸው ሰውዬ ኮንዶሚኒየም ቤት ይደርሰውና ባዶ ቤት ጥሏቸው ይሄዳል። እዚህ ማዕድ ቤት ውስጥ የሚያገላብጣቸው ጠፍቶ ጠረናቸው ክፉኛ መቀየሩን፤ ሥጋቸው እስከ መበስበስ መድረሱን፤ ዓይጥ በቁማቸው ሊበላቸው መገደዳቸውንም ያወሳሉ፡፡ ሰዎች እየመጡ አልቆለታል፤ ዛሬም አልሞተም እንዴ ሲሏቸው የነበረ መሆኑንም ያስታውሳሉ፡፡ በሽታዬ እንዲህ ተባብሶ ሰውነቴን ከማበላሸቱ በፊት ላላምጥ አፌ ከትቻት የነበረችውን አንዲት የባቄላ ፍሬ የምታክል ምግብ ለሳምንታት ሳልውጣት በጥርሴ እንደነከስኳት ቆይቻለሁ ሲሉ የሕመምና ስቃያቸው ጊዜ ዛሬ ላይ ሆነው መለስ ብለው ያስታውሳሉ።
በከፍተኛ ሕመም እየተሰቃዩ ባሉበት ሁኔታ ውስጥ ሆነውም ይኖሩበት የነበረው ማዕድ ቤት በቀበሌ ይፈለግ ነበርና አቶ ስንታየሁ አሁንም ዕጣ ፈንታቸው ጎዳና ላይ ሆነ፡፡ እንደልማዳቸው አሁን ላይ 41 ቁጥር የአንበሳ አውቶቡስ ማዞሪያ አካባቢ የሚገኘው ገነተ ኢየሱስ ቤተክርስቲያን ወደቁ፡፡
«በሕመሜ ምክንያት ሦስት ጊዜ ጎዳና ወድቄ፤ ሦስት ጊዜ አንስተውኛል፡፡ አንስተውም እሳቸው ጋር ወስደው በማስታመም ሥራ ያስገቡኝ ነበር» የሚሏቸው ወይዘሮ እንኳን አድራሻቸውን ስለማያውቁ ሊደርሱላቸው እንዳልቻሉ ይናገራሉ፡፡ ቀንና ሌሊት ቤተክርስቲያኑ ደጃፍ ወድቆ በበሽታና በቁስል የተጎዳውና የቆሰለው ሰውነታቸውን አሁን ሲያስታውሱት ሕልም ይመስላቸዋል።
«በዚህ ሥፍራ ሆኜም የእውነቱን ሕልምና ቅዠትም ቢሆን አስተናግድ ነበር» የሚሉት አቶ ስንታየሁ በመጨረሻ ድንጋይ ተሸክመው ገነተ ኢየሱስ ቤተክርስቲያን ውስጥ በመግባት ሲፀልዩ ያዩት ራዕይ እንደነበረም ያስታውሳሉ፡፡
«ትንሽ ጊዜ ቆይ አድንሃለሁ» የሚል ድምፅ ሰሙ፡፡ ይህንንም ድምፅ አድምጠው ወደ ሥራ ሊቀይሩ ተነሱ፤ የእሳቸው መክሊት የወደቁትን ማንሳት እንጂ ምንኩስናም ሆነ ባህታዊነት አይደለም። በራዕይ የተገለጠላቸውን መከወን ነው። እንደእሳቸው የሚበሉና የሚጠጡት አጥተውና በክፉ የበሽታ ደዌ ተጠቅተው ጎዳና የወደቁና ክፉኛ የተጎዱ ስምንት ሰዎችን አንድ ብለው አነሱ፡፡ ዛሬ ዋናውና ባለ አራት ፎቁ ማዕከል በሚገኝበት 41 ኢየሱስ ከፍ ብሎና ራስ ካሣ ሰፋር እየተባለ በሚጠራው ማዕከል በሚገኘው በጎ አድራጎት ማኅበር መንከባከብ ጀመሩ፡፡
የወደቁትን አንስተው በመሰብሰብ ሥራው እየሰፋ መጥቶ አሁን ላይ በዚህ ማዕከልና በኪዳነ ምሕረት በውጭና በውስጥ የሚረዱ ሰዎች ቁጥር 762 ደርሷል። በማዕከሉ ያሉት ከመኝታና ምግብ ጀምሮ ሁሉንም አገልግሎት ያገኛሉ፡፡ የውጪዎቹ ከመኝታ በስተቀር ሁሉም ይደርሳቸዋል፡፡
ሦስቱም ዓይነት ተደጋፊ ወገኖች የንጽሕና መጠበቂያ፤ ነፃ የሕክምና አገልግሎት ምግብና አልባሳት ማግኘታቸው ያመሳስላቸዋል፡፡ በዚህ መልኩ ቃላቸውን የፈፀሙት አቶ ስንታየሁ ዛሬ ትዳር መሥርተው ሁለት ልጆች ቢወልዱም የወደቁትን ማንሳታቸውን አላቆሙም፡፡ ከሚያግዟቸው በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ጋር በመሆን በየጎዳናው እየዞሩ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ዜጎች በሙሉ ሲያፈላልጉ ይውላሉ፡፡
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 13 ቀን 2017 ዓ.ም