
የጫና ዲፕሎማሲ (Coercive Diplomacy) በዓለም አቀፍ ግንኙነቶች ውስጥ በስፋት ሲከናወን ይስተዋላል። ይህ የዲፕሎማሲ ዓይነት በዋናነት የሚያተኩረው ጠላት ወይም ተቃዋሚ ባሕሪውን እንዲቀይር ወይም የተወሰኑ ፍላጎቶችን እንዲያከብር ለማስገደድ ሲሆን፣ ይህም ብዙውን ጊዜ የማስፈራሪያ ወይም የተመጠነ ኃይልን በመጠቀም ይከናወናል።
የጫና ዲፕሎማሲ በወታደራዊ እርምጃ እና በመደበኛ ዲፕሎማሲ መካከል ያለውን ሚዛን ጠብቆ የሚሄድ ሲሆን፣ ዋናው ዓላማው ሙሉ ጦርነትን ሳያስከትል ጠላት የተወሰኑ ለውጦችን በግድ ተቀብሎ እንዲፈጽም ለማድረግ ነው። ጫና የደረሰበት ሀገር ተገዢ ከሆነ ወደ ድርድር በመምጣት የኃያሉን ሀገር ጥቅም ባስጠበቀ መልኩ ስምምነት ይፈርማል።
የጫና ዲፕሎማሲ ዋና ዋና ገጽታዎች ውስጥ አንዱ በወታደራዊ ኃይል ማስፈራራት ነው። ይህ ማለት ጠላት ወይም ተቃዋሚ የተወሰኑ ፍላጎቶችን ካላከበረ ወታደራዊ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚችል የሚያሳይ ማስፈራሪያ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ጠላትን ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት ከመሞከር ይልቅ የተወሰኑ ፖሊሲ ለውጦችን በግድ እንዲቀይር ማድረግ ነው። ይህ ማለት የተወሰኑ ግቦችን ለማሳካት የሚያስፈልግ ጫና እና ማስፈራሪያ ነው።
የጫና ዲፕሎማሲ ማበረታቻንና ማስፈራራትን (carrot and stick) እያፈራረቀ የሚጠቀም ሲሆን ይህም የጠላትን አካሄድንና ውሳኔን ተለዋዋጭነት መሠረት የሚያደርግ ነው። ይህ ማለት ተቃዋሚው የተወሰኑ ድርጊቶችን ከፈጸመ ከመጣበት አደጋ የሚድን ወይም ማበረታቻዎች ሊያገኝ እንደሚችል በማሳየት እና ካልፈጸመ ደግሞ ከባድ አደጋ ሊያጋጥመው እንደሚችል በማሳየት ነው።
ይህ የጫና ዲፕሎማሲ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲከናወን አስገዳጅነት የሚጥል በመሆኑ ተቃዋሚው ለቀረበለት ጥያቄ አፋጣኝ ውሳኔ እንዲሰጥ የሚያስገድድ ነው። ካልሆነ ግን ከፍተኛ የኢኮኖሚ ወይም የወታደራዊ ጥቃት ሊደርስበት እንደሚችል ግዳጅ ይቀመጥበታል። የኢኮኖሚ ማዕቀቦች የጫና ዲፕሎማሲ አንዱ እና ዋና መሣሪያ ነው። ይህ ማለት ተቃዋሚው ሀገር የተወሰኑ ድርጊቶችን ካላከናወነ የኢኮኖሚ ጫናዎች ማለትም የንግድ እገዳዎች፣ የገንዘብ ማዕቀቦች እና የኢንቨስትመንት እገዳዎች ሊፈጠሩበት እንደሚችሉ የሚያሳይ ማስፈራሪያ ነው። የጫና ዲፕሎማሲ ግልጽ እና ሊደረስባቸው የሚችሉ ዓላማዎች አሉት። ይህ ማለት ጫና የሚያከናውነው መንግሥት ምን እንደሚፈልግ እና ተቃዋሚው ምን ማድረግ እንዳለበት ግልጽ ይደረጋል።
የጫና ዲፕሎማሲ በተለይም የኢኮኖሚ ማዕቀቦችን በሚጠቀምበት ጊዜ የሰብዓዊ መብቶችን ግምት ውስጥ ካላስገባ የሌሎች ወገኖችን ወቀሳ ትችት ይጋብዛል። ይህ ማለት ማዕቀቦች የሲቪል ሕዝቦችን እንዳይጎዱ ማድረግ ይጠይቃል። የጫና ዲፕሎማሲ ወታደራዊ ኃይልን ሊያካትት ይችላል፣ ነገር ግን ይህ ኃይል ተመጣጣኝ እና አስፈላጊ መሆን አለበት።
ይህ ማለት የኃይል አጠቃቀም የታለመውን ግብ ለማሳካት ብቻ መሆን አለበት እንጂ የተጋነነ ጉዳት የሚያመጣ ከሆነ በጠላትነት የተፈረጀው ሀገር ያልታሰበ ድጋፍ እንዲያገኝ ያግዘዋል። ይህ ማለት የማስገደድ ርምጃዎች ዓለም አቀፍ ደንቦችን የሚጥሱ ከሆነ የሌሎች ሀገሮችን ጫና ሊያስከትል ይችላል።
የጫና ዲፕሎማሲ ሲከናወን በዋናነት ብሔራዊ ጥቅምን በአነስተኛ ወጪ ለማስከበር ሲሆን እንደምክንያት ከሚቀርቡባቸው ጉዳዮች ውስጥ አንዱ እራስን መከላከል በመሆኑ የዓለም አቀፍ ሕግን ያልጣሰ ጫና መሆኑን ለማሳየት ይሞክራሉ። አሜሪካኖች እና ሌሎች ኃያላን ሀገራት በተለያዩ ሀገራት ውስጥ የሚያቋቁማቸው ወታደራዊ ሰፈሮች ይህንን የጫና ዲፕሎማሲ ለመተግበር ይጠቀሙበታል። ለምሳሌ ያህል በጅቡቲ በርካታ ታላላቅ ሀገሮች ወታደራዊ ሰፈር ገንብተዋል። እስካሁን ጦርነት ባያካሂዱም ለጫና ዲፕሎማሲ ይጠቀሙበታል። ወደፊት ግን በአካባቢው ላይ በሚነሳ የጥቅም ግጭት በመሀከላቸውም ወደጦርነት የሚያስገባ ሁኔታም ሊነሳ ይችላል።
የጫና ዲፕሎማሲ የሚያደርጉ ሀገራት የሚከተሉትን ጥቅሞች በማሰብ ነው። እነዚህም ሙሉ ጦርነትን በማስወገድ ዓላማን ለማሳካት፤ ወጪ ቆጣቢ በመሆኑ የሀብት ብክነትን ለመከላከል፤ ፈጣን ውጤቶችን ለማሳካት ነው። ለአብነት ያክል ኢራን የኒውክለር ቦምብ እንዳትሠራ የጫና ዲፕሎማሲ ስለተደረገባት የኒውክለር ኃይል ለሌላ ሥራ ብቻ እንድትጠቀም ገድቧታል።
በተቃራኒው ደግሞ የጫና ዲፕሎማሲ ማድረግ የተለያዩ ጉዳቶችን ሊያመጣ ይችላል። እነዚህም የጫና ዲፕሎማሲ ወደአልተፈለገ ግጭት ሊያመራና ሊስፋፋ ይችላል። ይህ ማለት ዛቻዎች ማድረግ ወደ ከፍተኛ ግጭት ሊያስከትል ይችላል፤ ሰብዓዊ ቀውሶችን በማምጣት የሲቪል ሕዝቦችን ሊጎዱ ይችላሉ፤ ዘላቂ ሰላም ያለማምጣት እና የቂም ፖለቲካ እንዲስፋፋ የማድረግ፤ የረጅም ጊዜ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶችንም ሊያበላሽ ይችላል። የጫና ዲፕሎማሲ የተወሰኑ ግቦችን ለማሳካት የሚያስችል ስልት ተደርጎ ይወሰዳል። ይህ ስልት ዛቻዎችን፣ የኢኮኖሚ ማዕቀቦችን፣ የወታደራዊ ማስፈራሪያዎችን እና በአጭር ጊዜ እንዲፈጸም ማስገደድን የሚያካትት እና ተቃዋሚውን የተወሰኑ ድርጊቶችን እንዲያከናውን ለማስገደድ ይረዳል። በመሆኑም የጫና ዲፕሎማሲ የሀገር ኃይልን እና የወታደራዊ ኃይልን (soft and hard power) አጣምሮ የሚሄድ ነው።
በሌሎች ሀገራት ላይ የሚከናወን የጫና ዲፕሎማሲ ሰብዓዊ መብት የሚጥስ ከሆነና ከፍተኛ ጉዳት በሰዎች የሚያደርስ ሲሆን የዓለም አቀፍ ሕግ የጣሰና ተቀባይነት የሌለው ነው የሚል ጩኸት ከዚህም ከዚያም ሊያመጣ ይችላል። በመሆኑም የጫና ዲፕሎማሲ ዝም ብሎ በድንገት የሚሠራ ሳይሆን ግራና ቀኝ አይቶ የሚወሰን ነው።
የጫና ዲፕሎማሲ የአንድ ሀገር የውጭ ፖሊሲ መተግበሪያ አማራጭ ዘዴ (Foreign Policy Tool) ሆኖ ያገለግላል። ሆኖም ግን ስኬታማ ሊሆንም ላይሆንም ይችላል። ስኬታማ ከሆነም የታሪክ ጠባሳ ሊያስከትልና የወደፊት ግንኙነትን ሊያሻክር ይችላል። ከኃያል ሀገር ለሚመጣ የጫና ዲፕሎማሲ በዋናነት ሁለት ምላሸ ሊያገኝ ይችላል።
የመጀመሪያው ጫናው የደረሰበት ሀገር የተጠየቀውን ሁሉ በመፈፀም የኃያል ሀገርን ፍላጎት ማሟላት ሲሆን ሁለተኛው አማራጭ አልቀበልም በማለት የመጣውን ሁሉ ለመቀበል ወይም የመጣውን ኃይል ለመቋቋም መሥራት ነው። ሁለቱም አማራጮች በዓለማችን ላይ ተከስተዋል፣ በመከሰትም ላይ ናቸው።
የመጀመሪያውን አማራጭ በምሳሌ ለማየት ያክል የሁለተኛው ዓለም ጦርነት ከመነሳቱ በፊት የጀርመን ናዚ መሪ የነበረው ሂትለር በበርካታ ሀገሮች ላይ የዲፕሎማሲ ጫና ያደርግ ነበር። ለአብነት ያክል በቀድሞ ስያሜዋ የምትታወቀው ቼኮዝሎቫኪያ ላይ የተደረገው ጫና በታሪክ ይጠቀሳል። ሂትለር ቼኮዝሎቫኪያን መያዝ በፈለገበት ወቅት ሱዴታን በምትባለው የቼኮዝሎቫኪያ ግዛት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች በዘር ጀርመናዊያን ስለሆኑ ሕዝቡንና መሬቱን ካልተሰጠኝ በሀገሪቷ ላይ ወረራ እፈጽማለሁ የሚል ከፍተኛ ዛቻ ያሳያል።
በዚህ ወቅት እንግሊዝና ፈረንሳይ የሂትለርን የመስፋፋት ፍላጎት ብንደግፍ በአገኘው ስለሚረካ ወደ ዓለም ጦርነት አንገባም በሚል ፖለቲካዊ ስሌት የጠየቀው እንዲሰጠው የሙኒክ ስምምነት በመፈፀም የልምምጥ ፖሊሲ (Appeasement Policy) ተከትለዋል። ከዚህም በተጓዳኝ ሂትለር የቼኮዝላቫኪያ መሪ የነበረውን ዶ/ር ኢሚል ሀቻ (Emil Hacha) ላይ ከፍተኛ የወረራ ዛቻ ያደርሰበታል።
በዚህ የተደናገጠው የቼኮዝሎቫኪያው መሪ በባቡር ወደ ጀርመን ይገባና ሂትለርን ያገኘዋል። ሂትለርም ከኢሚል ሀቻ የሚፈልገውን ሲነግረው ጀርመን ጦሯን ወደ ቼኮዝሎቫኪያ እየላከች እንደሆነ እና በሦስት ሰዓት ውስጥ ዋና ከተማ የሆነችው ፕራግ ድምጥማጧ እንደሚወጣ በመግለፅ የቼኮዝሎቫኪያ ግዛቶች ለጀርመን ሰጥቻለሁ ብለህ ከፈረምክ ብቻ ይህ አይፈጸምም አልያ ሕዝብህም ያልቃል የተፈለገው መሬትም ይያዛል በማለት ያስፈራራዋል።
በእድሜ ገፋ ያለው እና የልብ ሕመም የነበረበት ኢሚል ሀቻ ጫናውን መቋቋም አቅቶት ተዝለፍልፎ ይወድቃል። ሂትለርም የግል ሐኪሙን ዶ/ር ሞሬልን ይጠራውና የማንቂያ ሕክምና እንዲሰጠው ያደርገዋል። ኢሚል ሀቻ ወደቀልቡ ሲመለስ ሂትለር በድጋሚ አስጨናቂ የሆነውን ጥያቄውን ሲያቀርብ ኢሚል ሀቻ በድጋሚ ተዝለፍልፎ ይወድቃል። ተመሳሳይ ሕክምና ተደርጎለት ሲነቃ እንደገና ፈርም አልያ ሀገርህ ድምጥማጧ ይጠፋል ሲለው የግዳጅ ፊርማውን ይፈርምና የጀርመን ጦር ጥቃት እንዳያከናውን ይደረጋል።
ኢሚል ሀቻ ወደ ሀገሩ ሲመለስ ሁለት አስተያየቶች ገጠሙት፤ አንደኛው ከሀዲ የሆነ መሪ ሀገራችንን አሳልፎ ለጀርመን ሰጠ ሲሉት ሌሎች ደግሞ ኃያሉን ሂትለር ማስቆም ስለማይቻል የፕራግን እና አጠቃላይ የቼኮዝላቫኪያን ሕዝብ ከእልቂት የታደገ ጀግና መሪ ተብሎ ተወሰደ።
ያም ሆነ ይህ የሂትለር ጦር አይደለም ቼኮዝላቫኪያን ሌሎችንም የአውሮፓ ሀገራት በኃይል በመውረር የሁለተኛው ዓለም ጦርነት ተጀመረ። በጦርነቱም ጀርመን ተሸነፈችና በአሸናፊዎቹ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ ሩሲያ፣ እና ሌሎች አጋዥ ሀገራት በተቃራኒው ጀርመንን አስገዳጅ ውል አስገቧት፤ የጫና ዲፕሎማሲም አደረሱባት።
የጫና ዲፕሎማሲ የሚያከናውኑ ሀገራት በዓለም ላይ ያሉ ኃያል ሀገራት ወይም የቀጣናው ኃያል ሀገራት ሊሆኑ ይችላሉ (Global or Regional Hegemonic Powers)። ከዚህም በተጨማሪ እንደተባበሩት መንግሥታት እና የአውሮፖ ኅብረት ያሉ ዓለም አቀፍና አኅጉራዊ ድርጅቶችም የጫና ዲፕሎማሲ በማድረግ የአባል ሀገራትን ጥቅም ለማስጠበቅ ይሰራሉ።
በእነዚህ ተቋማት የሚደረጉ ማዕቀቦች/የኢኮኖሚ ጫና (Sanctions) ስኬት ካመጣላቸው ጫናውን የሚያነሱት ሲሆን በተለይ ከዓለም አቀፍ ሽብርተኝነት፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እና ሌሎች ከሰላምና ፀጥታ ጋር የተያያዙ ችግሮች እንዲቀረፉ ለማድረግ ይጠቀሙበታል። የኢኮኖሚ ማዕቀብ አንዱ የዲፕሎማሲ ጫና መፍጠሪያ እንደመሆኑ የንግድ ጦርነት (Trade War) እና ሌሎች ማዕቀቦችን በማድረግ የሚተገበር ነው።
በታሪክ ተመዝግቦ የሚገኘው በቻይና እና በእንግሊዝ መሀከል የተደረገውን የኦፒየም ጦርነት ማየት ይቻላል። በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በሁለቱ ሀገራት በነበረው የንግድ ልውውጥ ቻይና በጣም ተጠቃሚ ያደርጋታል። ይህ የተዛባ የንግድ ትርፍ ለመቀልበስ ይቻል ዘንድ እንግሊዝ የምታመርተውን ኦፒየም በስፋት የቻይና ገበያ እንዲገባ አልያ እንግሊዝ ቻይናን በጦር ኃይል እንደምትወጋት የጫና ዲፕሎማሲ ታከናውናለች።
ቻይና አልቀበልም በማለቷ እንግሊዝ ጦር ታዘምትባትና ቻይናን ታሸንፋታለች። በድጋሚ ቻይና እምቢተኝነት ስታሳይ በተመሳሳይ እንግሊዝ በጦር ኃይል ታስገድዳታለች። ይህ ሁለት ጊዜ የተከናወነ የኦፕየም ጦርነት ውጤት እስካሁን የቻይና ውርደት ተደርጎ በቻይናዎች ይታወሳል። ቻይናዎች ይህንን ታሪክ እንደብሔራዊ ቅሌት በመቁጠራቸው የቂም ፖለቲካ የፈጠረ ክስተት ሆኗል።
ሆኖም ግን ሁሉም የጫና ዲፕሎማሲ ይሳካል ማለት አይቻልም። ተቃራኒ ውጤትም ሊያመጣ ይችላል። ለአብነት ያክል የአውሮፓ ኅብረት ኢትዮጵያን በተመለከተ ሕገወጥ ስደተኞችን ለመቀበል ፈቃደኛ አይደለችም በሚል መነሻ ማንኛውም የኢትዮጵያ ዜጋ ወደ አውሮፖ ሀገር ለመጓዝ ሲፈልግ ቪዛ የሚያገኘው እንደበፊቱ በተቀላጠፈ ሁኔታ ሳይሆን አርባ አምስት/45/ ቀናት እንዲጠብቁ አድርጋለች።
በተመሳሳይም እንደሌሎች የአፍሪካ አገሮች የቅኝ ግዛትን የማታውቀውና ነጮችን ስታገኝ የፍርሃት ቆፈን የማይዛት ኢትዮጵያ የአውሮፓ ዜጎች ወደ ሀገራችን ለመግባት ሲፈልጉ አርባ አምስት/45/ ቀናት ለቪዛ እንዲጠብቁ አድርጋለች። ይህ ውሳኔ አውሮፓውያኖች ያልጠበቁት በመሆኑ አስደነገጣቸው (ሌሎች አፍሪካ ሀገሮች በዚህ ልክ አይደፍሩንም ስሜት)። አውሮፓውያን ያደረጉትን ጫና ሲያነሱ ኢትዮጵያም የምታነሳ ይሆናል። ይህ ማለት ግን ኢትዮጵያን ተጓዳኝ ዋጋ አያስከፍላትም ማለት አይደለም።
ይህንን መሰል ጫናን ያልተቀበለ አገር ችግሮቹን ለመቋቋም የሚያስችለው ረጅም ርቀትም ሊጓዝ ይችላል። ለምሳሌ ያህል በሰሜን ኮሪያ ላይ የጫና ዲፕሎማሲ ቢደረግባትም ጫናውን ተቋቁማ የኒውክለር ቦምብ ለመሥራት ችላለች። ይህንን በማድረጓ በተቃራኒው በደቡብ ኮሪያና በአካባቢው ሀገራት ላይ ጫና እየፈጠረች ትገኛለች። በእርግጥ የኒውክለር ቦምብ የሚሠሩ ሀገሮች ዓለምን የማጥፋት አቅም እንዳላቸው ከማሳየት እና ለጫና ዲፕሎማሲ ለመጠቀም ወይም የሌሎች ሀገሮችን የጫና ዲፕሎማሲ ለማስቆም ከማዋል ውጪ ብዙም ርቀት ሄደው መሣሪያውን አይጠቀሙበትም።
የጫና ዲፕሎማሲ በርካታ ዘርፎችን የሚያካትት ሲሆን አንዳንዴም ጫና የሚደረግበት የሀገር መሪ፤ ባለሥልጣናት እና ሕዝቡ ወደ ሀገራቸው እንዳይገቡ የሚገድቡበት አሠራር ይታያል። በቅርቡ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ትራምፕ የአስራ አንድ ሀገራትን ዝርዝር በማውጣት ዜጎቻቸው ወደ አሜሪካ መግባት የተከለከሉ መሆኑን ገልጿል። ከነዚህም ውስጥ የሰሜን ኮርያ፣ ኩባ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳንና፣ ሊቢያ ይገኙበታል። ከእነዚህም በተጨማሪ ሌሎች 32 ሀገራት በቀላሉ ቪዛ እንዳያገኙ ወይም ቪዛ ከጠየቁ ሁለት ወራት በኋላ እንዲሰጣቸው የሚል ውሳኔ አሳልፈዋል።
ከዚህም የከፋው ደግሞ የዩክሬኑን ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ ቀጥታ በሚተላለፍ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ላይ የረባ ልብስ ሳትለብስ እንዴት እኛ ጋር ትመጣለህ፤ ለነጩ ቤተመንግሥት ክብር የሌለህ ነህ፤ የሦስተኛ ዓለም ጦርነት ልታስነሳ ትፈልጋለህ፤ ያን ሁሉ ብር ሰጥተንህ ምን ፋይዳ አመጣህ እና የመሳሰሉት ክብረ ነክ ንግግሮች ወርደውበታል።
የሚያሳዝነው ደግሞ የትራምፕም ምክትልና ሌሎች ባለሥልጣናት በሀገር መሪው ዘለንስኪ ላይ የፈጠሩት ጫና ይታወሳል። ዘለንስኪ የልብ ሕመም ቢኖርበት እንደ ኢሚል ሀቻ ተዝለፍልፎ ሊወድቅም ይችል ነበር። ይህ የሚያሳየው ዲፕሎማሲ ከዝግ ስብሰባ አዳራሽ እየወጣ በይፋ ለዓለም ሕዝብ የሚታይበትና የፖለቲካ ጫና እየተፈጠረበት እንደሆነ ያሳያል ።
ከላይ እንደተጠቀሰው የጫና ዲፕሎማሲ ሁልጊዜ የተሳካ ውጤት አያመጣም። ሩሲያን እንደአብነት ለማንሳት ያክል በአሁኑ ወቅት በርካታ የምዕራብ ሀገራት የኢኮኖሚ ማዕቀብ በማድረግ ከዩክሬን ጋር ያለውን ጦርነት ለማስቆም እየሞከሩ ነው። ከዚህም አልፈው የመሣሪያ ድጋፍ ለዘለንስኪ በማድረግ ላይ ናቸው። ይህን ሁሉ ሲያደርጉ ሩሲያ የኒውክለር ቦምብ ባለቤት እንደሆነች እያወቁ ነው። ይህ የሚያሳየው ኒውክለር ቦምብ የጫና ዲፕሎማሲን እና የከፋ ግጭትን ለመመከት (Deterrence) እንጂ እንደክላሽና ብሬን ለመተኮስ እንዳልሆነ ያሳየናል።
ለማጠቃለል ያህል የጫና ዲፕሎማሲ በዓለም አቀፍ ግንኙነቶች ውስጥ አንዱ የዲፕሎማሲ አካል በመሆን በጥቅም ላይ ሲውል ይታያል። ይህ የዲፕሎማሲ ስልት ውስብስብ እና ተግዳሮች ያሉት ነው። የቂም ፖለቲካንም ሊያስከትል ይችላል። ይህ የዲፕሎማሲ ዘዴ በዋናነት የሚያተኩረው ጠላት ወይም ተቃዋሚ ባሕሪውን እንዲቀይር ወይም የተወሰኑ ፍላጎቶችን እንዲያከብር ለማስገደድ ሲሆን፣ ይህም ብዙውን ጊዜ የማስፈራሪያ ወይም የተወሰነ ኃይልን በመጠቀም ይከናወናል። የጫና ዲፕሎማሲ በዲፕሎማሲ እና በወታደራዊ ርምጃ መካከል ያለውን ሚዛን የሚጠቀም ሲሆን፣ ዋናው ዓላማው ሙሉ ጦርነትን ሳያስከትል ብሔራዊ ጥቅምን ለማስከበር ነው።
መላኩ ሙሉዓለም ቀ. በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የሥልጠና ዳይሬክተር ጄኔራልና ተመራማሪ
melakumulu@yahoo.com
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 13 ቀን 2017 ዓ.ም