
ግብርና የሀገራችን ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው። ምክንያቱም የግብርና ምርቶች የምግብ ዋስትናችን ማረጋገጫዎች ናቸው፣ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ የኢኮኖሚያችን ምንጭ ናቸው። ከየትኛውም ዘርፍ በላቀ ሁኔታ የሥራ እድል ፈጣሪዎችም ናቸው። ሌሎችንም የሥራ እድል ፈጣሪ ዘርፎችን መጥቀስ ቢቻልም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ የተሰማራው ግን በዚሁ በግብርና ሥራ ላይ ነው። ስለዚህ ግብርና ሁለመናችን ነው ልንለውና ትኩረት ልንሰጠው የግድ ይላል።
ግብርና በሀገራችን በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ ነው። በዚህም አመርቂ የሚባሉ ውጤቶችን ማየት ተችሏል። ይሄ ውጤትም በቀጣይ በተጠናከረና በተሻለ መልኩ ከተሠራበት ተስፋ ያለው መሆኑን አመላካች ነው። ይሁን እንጂ ዛሬም ድረስ የግብርና ሥራችን ከበሬና ገበሬ እምብዛም አለፍ ያለ አይደለም። ዘመናዊ ትምህርትን የቀሰመው፣ በኢንቨስትመንት ዘርፉ የተሰማራውና አቅም ያለው በዘርፉ በስፋት ሲሰማራበት ብዙ አይታይም። በመሆኑን የአርሶ አደሩ ገቢ ከእጅ ወደ አፍ ከመሆን አላለፈም። ከጎተራ ተርፎ ገበያውን አላጥለቀለቀም። ከፍተኛ ገቢ ሊያስገኝ የሚገባው ለውጭ ገበያ የሚቀርበው የግብርና ምርት ዝቅተኛ መጠን ያለው ነው።
አሁን አሁን በምርታማነቱ በግንባር ቀደምትነት እየተጠቀሰ ካለው የእርሻ ሥራችን ውጤት መካከል ስንዴ፣ ሩዝ እና ቡና ተጠቃሾች ናቸው። በመጠነኛ ደረጃ ደግሞ የቅባት እህል ፣ ቅመማ ቅመም … እንዲሁ የሚጠቀሱ ናቸው። ከእነዚህ ዓይነቶች አለፍ ብሎ ሀገርን የሚያስጠራ በውጭ ገበያው ተጠቃሽ የሆነ የግብርና ምርት የለም። ይህ ለምን ሆነ ብሎ መጠየቅ ደግሞ በተለይ ጉዳዩ ከሚመለከተው አካል የሚጠበቅ ይሆናል። ለም መሬት፣ ውሃ፣ የወጣት ጉልበት፣ እውቀትና ልምድ ባለው ሀገር፤ መልክዓ ምድሩና የአየር ንብረቱ ለእርሻ ሥራ ተስማሚ በሆነ ሀገር ላይ በግብርና ምርቶች ተወዳዳሪና ተመራጭ አለመሆን በእጅ ያለን ወርቅ እንደ መዳብ እንደ መጠቀም ይቆጠራል።
ኢትዮጵያ ወደ 130 ሚሊዮን የሚጠጋ የሕዝብ ቁጥር ያላት ሀገር ናት። አብዛኛው ዜጎቿም ወጣቶች መሆናቸው በሀገሪቱ ምንም ዓይነት እድገትን ለማስፋፋት፣ ልማትን ለማፋጠን፣ ቴክኖሎጂን ለመተግበር ችግር ይሆናል ተብሎ አይታሰብም። ጉልበት ያለው ዜጋ (የወጣቱ ቁጥር) ሰፊ መሆኑ ደግሞ የግብርና ሥራውን ለማዘመንና ለማስፋፋት ጥሩ እድል ሊፈጥር እንደሚችል ይታመናል። ይሁን እንጂ እስካሁን ድረስ በሚፈለገው ልክ ምርታማነት አድጓል ማለት አይቻልም። ዘመናዊ ቴክኖሎጂን የሚጠቀመው አርሶ አደር ቁጥር ብዙ አይደለም። ትምህርት ቀመሱ የአርሶ አደር ልጅ የሚናፍቀው ከተሜነትን ብቻ ነው።
በአካባቢው ላይ በተለያየ የግብርና ሥራ ላይ በመሰማራት ውጤታማ መሆን እንደሚችል አርቆ እያሰበ አይደለም። የግብርና ሥራን ያልተማረ ማኅበረሰብ ሥራ፣ እርሻውም በበሬና ገበሬ ብቻ አድርጎ የሚያስበው ጥቂቱ አይደለም። አርሶ አደሩም ከዘልማዳዊው አስተራረስ ለመላቀቅ እየተጋ አይደለም። በራሱ ጥረትና ልፋት የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ለመሆን የሚያደርገው ሙከራ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ከዛ ይልቅ የመንግሥትና የሌሎች ርዳታ ሰጪዎችን ድጋፍ በመናፈቅ ላይ ተጠምዷል። በአርሶ አደር ሕብረት ሥራ ማህበራት ተደራጅተው ለገበያ ተፈላጊ የሆኑ ምርቶችንም በማምረት ላይ የተሰማሩት፣ እንዲሁም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን የሚጠቀሙ እና ምርታማነትን በሚያሳደጉ ሥራ ላይ የተሰማሩት አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ናቸው።
አሁን ባለው ሁኔታ ደግሞ የሕዝብ ቁጥር መጨመርን ተከትሎ የእርሻ መሬት ዕጥረት እያደገ በመምጣቱ በአነስተኛ መሬት ላይ ከፍተኛ ምርት ማምረት የግድ ይላል፡፡ ለዚህ ደግሞ የሌሎቹ የግብርና ምርት ማሳደጊያ ግብዓቶች (ዘመናዊ የአመራረት ስልት፣ የጸረ አረምና ጸረ ተባይ መድኃኒት አቅርቦት፣ ምርጥ የሰብል ዘር እና ሌሎች) መጠቀም ያስፈልጋል። እዚህ ላይ የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ጉልህ ድርሻ አለው። ይህም በመሆኑ የሀገራችን የአፈር ማዳበሪያ ፍላጐት ከዓመት ዓመት እየጨመረ መጥቷል። ለአብነት የ2008 በጀት ዓመት አቅርቦት 850 ሺህ ሜትሪክ ቶን የነበረው፤ በ2013 በጀት ዓመት አቅርቦት ወደ አንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን አድጓል፡፡ ዘንድሮ ደግሞ ይህ ቁጥር በከፍተኛ መጠን ጨምሯል። የዋጋ ለውጥም አስከትሏል።
ለዘንድሮ የምርት ዘመን (2017/18) የተገዛው የማዳበሪያ መጠን ካለፈው የምርት ዘመን (2016/17) የማዳበሪያ ግዥ ጋር ሲነጻጸር የአራት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ኩንታል ብልጫ አለው። ለዘንድሮ የምርት ዘመን 24 ሚሊዮን ኩንታል ገደማ ማዳበሪያ የሚያስፈልግ ሲሆን ይህም በአንድ ቀን 150 ሺ ኩንታል ማዳበሪያ ከወደብ ላይ እየተነሳና ወደ ሀገር ውስጥ እየገባ ይገኛል፡፡ ይህንንም ለእያንዳንዱ አርሶ አደር እንዲደርሰው እየተደረገ ነው። ሌላው ቀርቶ የሰላም መደፍረስ ችግር ባለባቸው ክልሎች ጭምር አርሶ አደሩ ምርታማነቱ እንዳይቀንስ ማዳበሪያ እንዲያገኝ ከጸጥታ አካላት ጋር በጋራ እየተሠራ ይገኛል። በዚህ ላይ መንግሥት ከፍተኛውን የዋጋ ድጎማ በማድረግ ነው አርሶ አደሩ የአፈር ማዳበሪያ ተጠቃሚ እንዲሆን በመደረግ ላይ ያለው።
ከዚህም በተጨማሪ የአርሶ አደሩን ምርታማነት የሚያሳድጉ እንደ ኩታ ገጠም አስተራረስ ዘዴን መተግበር በመጀመሩ በምርታማነት ላይ የመጣው ለውጥ ቀላል አይደለም። ይህም የእርሻ ቦታን ከብክነት ማዳን አስችሎናል፤ የአርሶ አደሩን ጉልበት በመቆጠብ ረገድ አግዞናል። የምርት ብክነትን መከላከል እንዲሁም በአግባቡ የእርሻ ቦታዎችን በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን በተሻለ መጠን ለማሳደግ አንዱ ዘዴ በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ይታመናል።
ሌላው ምርታማነትን የሚያሳድገው አርሶ አደሩን የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ እንዲሆን ማስቻል ነው። በግብርና ሜካናይዜሽንን አነስተኛና መካከለኛ የእርሻ መሳሪያዎችን መጠቀም የግድ ይላል። አርሶ አደሩ በግሉ እንዲሁም በሕብረት በመደራጀት አነስተኛና መካከለኛ የእርሻ መሳሪያዎችን መጠቀም አማራጭ የሌለው መፍትሔ ነው። አሁን ባለው ሁኔታ መንግሥት በተወሰነ መጠንም ቢሆን አርሶ አደሩ የግብርና ሜካናይዜሽን አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆን ሥልጠና በመስጠትና የማሽነሪ አቅርቦት ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛል።
የግብርና ሜካናይዜሽንን በመጠቀም በኩል በተለይ በኦሮሚያ ክልል አበረታች የሆነ ለውጥ ታይቷል። በዚያው ልክም ምርታማነትን የማሳደግ ሥራ በስፋት በመሠራት ላይ ነው። ከፍተኛ መጠን ያለው የስንዴ ምርትን ማምረት ተችሏል። ስንዴ ይመረትባቸው ባልነበሩ ቦታዎች ጭምር ስንዴን የማምረት፤ እንዲሁም የበጋን ስንዴ ጨምሮ በዓመት ከአንድ ጊዜ በላይ በመስኖ ማምረት ወደ ባሕልነት መሻገር ችሏል። በመሆኑም ከፍተኛ መጠን ያለው የስንዴ ምርት ለገበያ እየቀረበ ይገኛል። በዚህ በአንድ በኩል ሀገር በሌላ በኩል ደግሞ አርሶ አደሩ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ መሆን ችሏል። ይሄ አበረታች ውጤት ቀጣይነት እንዲኖረው በክልሉ መንግሥትም ለአርሶ አደሩ የእርሻ ትራክተሮችን ጨምሮ የተለያዩ የግብርና ግብዓቶችን በማቅረብ ላይ ነው። ሰሞኑን እንኳን የክልሉ መንግሥት አንድ ሺህ 402 የእርሻ ትራክተሮችን ከነመገጣጠሚያቸው ለአርሶ አደሮች፣ የሕብረት ሥራ ማኅበራትና ዩኒየኖች አስረክቧል፡፡ ይህንንም የተረከቡት 143 አርሶ አደሮች፣ 12 የሕብረት ሥራ ማኅበራት እና 42 ዩኒየኖች ናቸው።
የግብርናውን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ሜካናይዜሽን ትልቁን ሚና ይጫወታል፡፡ የግብርና ሜካናይዜሽን አገልግሎትን ማስፋፋት ግብርናን ለማዘመንና የምርት ጥራትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው። ግብርናውን ለማዘመን በሚደረገው ርብርብ ሜካናይዜሽን ከሌሎች የግብርና ግብዓቶች ጋር ተዳምሮ ለዘርፉ እድገት እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ ነው፡፡ የአርሶ አደሩን ችግር በመፍታት፣ የአነስተኛ ይዞታ አርሶ አደሮችን ምርታማነት ለማሳደግ ወሳኝ ነው፡፡
አርሶ አደሩ በሀገር ውስጥ በአነስተኛ ዋጋ በብዛትና በቅርበት የቴክኖሎጂ ውጤት የሆኑ የእርሻ መሳሪያ፣ የሰብል ማጨጃ የመሳሰሉ የፈጠራ ሥራዎች የሚያወጡትን በገንዘብና በቴክኒክ መደገፍ እና ማበረታታት አንዱ ሥራ መሆን አለበት። ይህም የፈጠራ ባለቤቶችን ለተሻለ ሥራ ከማነሳሳቱ ባሻገር ሌሎች የፈጠራ ባለሙያዎችን በግብርና ሜካናይዜሽን ፈጠራ ሥራ ላይ እንዲነሳሱ ያደርጋል፡፡ ሥራውን ወደ አርሶ አደሩ ለማውረድ እና የተሻሻሉ፣ ውጤታማና ተደራሽ የሆኑ የግብርና ሜካናይዜሽኖችን ተግባራዊ ለማድረግ ያግዛቸዋል።
የግብርና ኤክስቴንሽን ሥርዓት ምርትና ምርታማነት እድገት፣ የምግብና ሥርዓተ ምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ እንዲሁም ገበያ ተኮር የግብርና ኤክስቴንሽን ሥርዓት፣ ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ወሳኝ ተግባር ነው። ለዚህም የግብርና ኮሌጅ ሚና ከፍ ያለ ነው። የግብርና ሥራችንን በእውቀት አስደግፎ በተሻለ መልኩ መሥራት ከተቻለ አሁን ካለውም በላይ ውጤታማ መሆን ይቻላል። አሁን ባለው ጅምር ሥራ እንኳን በሁሉም የግብርና ሥራ የሚታይ፣ የሚዳሰስና የሚጨበጥ ለውጥ መመዝገብ ችሏል። ለመጣው ለውጥ ከአርሶና አርብቶ አደሩ ግንባር ቀደም ሚና ጎን ለጎን የልማት ጣቢያ የሚተካ ሚና አለው። በቀጣይም ይሄንኑ ማጠናከር የግድ ይላል። ሀገር የምታደገውና የምትለወጠው በተወሰኑ አካላት ጥረት ብቻ ሳይሆን ጉዳዩ የሚመለከተው አካል ሁሉ በያገባኛል ስሜት፣ በእውቀትና በቅንነት ሲተባበር እና መሥራት ሲችል ነው።
የግብርና ገጠር ልማት አሁናዊ ሁኔታዎችን ያገናዘበ ፖሊሲና ስትራቴጂን መከተል ግብርናውን ለማዘመን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። በኢኮኖሚ የገጠመንን ስብራት ማሻሻያ ተደርጎ መታሰቡም ለግብርና ወሳኝነት አለው፤ ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ኢኮኖሚ ግብርና ቁልፍ ሴክተር በመሆኑ ያለንን የተፈጥሮ ጸጋና የሰው ሀብት መጠቀም አለብን። ይህንን ተግባራዊ በማድረግና እየተመዘገበ ያለውን ለውጥ በማስቀጠል የምግብ ሉዓላዊነታችን ማረጋገጥ ያስፈልጋል።
የግብርና ፖሊሲውን ግብ ማሳካት በእውቀትና በብቃት መመራት አለበት። ግብርና ለሁሉም ዘርፍ ምሰሶ ነው። ስለዚህ በእውቀትም፣ በቴክኖሎጂም፣ በሰለጠነ የሰው ኃይል እና በግብዓት መደገፍ ይኖርበታል። አርሶና አርብቶ አደሩን ማሰልጠን ብቁና በቂ የልማት ባለሙያዎችን ማፍራትና አርሶ አደሩ እንዲደገፍ ማድረግ ከዚህ ቀደም ከነበረው በላቀ መልኩ ትኩረት ማግኘት ይኖርበታል።
አሁን ባለንበት የግሎባላይዜሽን ዘመን የንግድ ሥራ የተቋማት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የእያንዳንዱ ሀገር ጉዳይ ሆኗል፡፡ በአደጉት ሀገሮች ትልቁ የዲፕሎማሲ ሞተር የንግድ አጋርነት ጉዳይ ነው። ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ በዓለም ገበያ በተሻለ ብቃት ተወዳዳሪ መሆን የምትችለው በአብዛኛው በግብርና ምርት ውጤቶች ነው፡፡ ስለሆነም በቀጣይ ከ10 ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ አኳያ በግብርናው ዘርፍ ላይ በሰው ኃይል፣ በግብዓት አቅርቦትና በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ልዩ ትኩረት በመስጠት በዓለም ገበያ ተወዳዳሪነትን ማሳደግ ይጠበቅብናል። የግብርና ምርትና ምርታማነት ማሳደግ ለኢኮኖሚያችን ዋልታ ነው፡፡ በምግብ ራስን ለመቻል ዋነኛው መሠረት ነው። ስለዚህ ልዩ ትኩረት ያስፈልገዋል። በአገኘነው ውጤት ሳንኩራራ ያጣነውን ለማግኘት ሌት ተቀን መሥራት ይጠበቅብናል። ዓለም ያደገችው በሥራና በሥራ ብቻ ነው። ሰላም!
አዶኒስ (ከሲኤምሲ)
አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 3 ቀን 2017 ዓ.ም