በጥላቻ እና በጨለምተኝነት የተቃኘ ፖለቲካ ይብቃን !

ፖለቲካ ሳይንስ ነው። ሳይንስ ደግሞ በማስረጃ እና በመረጃ ላይ የተመሠረተ በመርሕ እና በሀሳብ ልዕልና የሚመራ ነው። ይነስም ይብዛም የሕዝብን ፍላጎት እና የመሆን መሻት ታሳቢ የሚያደርግ፤ ለዚህም የሚገዛ ነው። ከዚህ ውጪ ያለ የፖለቲካ እሳቤም ሆነ ከእሳቤው የሚመነጭ ተግባራዊ እንቅስቃሴ የችግር እና የኪሳራ ምንጭ ከመሆን ያለፈ ጠቀሜታ አይኖረውም። ይኖረዋል ብሎ ማሰብም አንድም አላዋቂነት፤ ከዚያም ካለፈ የፖለቲካ ቁማርተኝነት ባሕሪ መገለጫ ነው።

ዓለማችን በቀደሙት ዘመናት የተለያዩ የፖለቲካ አስተሳሰቦችን ተቀብላ አስተናግዳለች፤ ከትናንት በመማር ዛሬን የተሻለ ያደረጉ የፖለቲካ እሳቤዎችን አመንጭታለች። በትውልድ መካከል ባለ የዕውቀት ሽግግር ዛሬ ላይ ከትናንት የተሻለች ዓለም መገንባት ችላለች። ዛሬም ነገን ከዛሬ የተሻለ ለማድረግ ከፍ ባለ መነሳሳት ዘርፈ ብዙ የጥናት እና ምርምር ሥራዎችን እያከናወነች ትገኛለች። ይህም ነገ ላይም በተመሳሳይ መልኩ ይቀጥላል ።

የሀገራት ዕድገት እና ሥልጣን፤ ዓለም ተስፋ የሚያደርጋቸው የተሻሉ ነገዎች የተፈጠሩት እና ሊፈጠሩ የሚችሉት ከዚህ ተጨባጭ እውነታ ነው ። ይህንን እውነታ በአግባቡ መገንዘብ ለአንድ ሀገር ዕጣ ፈንታ ወሳኝ ነው። በተለይም ራሳቸውን የአንድ ሀገር፤ ማኅበረሰብ ሆነ ቡድን የፖለቲካ ውክልና አለን ብለው የሚያስቡ ግለሰቦች እና ቡድኖች ውክልናቸው ትርጉም እንዲኖረው በዚህ እውነታ የተገራ ማንነት መፍጠር ይጠበቅባቸዋል።

ዘረኝነት እና ከፋፋይነት፤ ጥላቻ እና ጨለምተኝነት መሠረት ያደረጉ የፖለቲካ አስተሳሰቦች እና አስተሳሰቦቹ የሚወልዷቸው የትኛውም አይነት ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች፤ የጥፋት ምንጭ ከመሆን ያለፈ ውጤት አይኖራቸውም። ለዚህም በተለያዩ ወቅቶች በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ተከስተው ዓለምን ብዙ ያልተገባ ዋጋ ያስከፈሉ በራስ ወዳድነት፣ በጥላቻ እና በጨለምተኝነት የተቃኙ የፖለቲካ አስተሳሰቦችን ማስታወስ ተገቢ ነው። ከፋሺዝም፤ ከናዚዝም እና መሰል የተዛቡ የፖለቲካ አስተሳሰቦች በስተጀርባ የነበሩ የጥላቻ እና የራስ ወዳድነትን አስተሳሰቦችን ማስታወስ በራሱ በቂ ነው።

ዓለም ከነዚህ የተዛቡ አስተሳሰቦች በብዙ ተምሮ ዛሬ ሚዛናዊ በሆነ የፖለቲካ አስተሳሰብ ላይ ትገኛለች። ሚዛናዊነት የዓለም ፖለቲካ መገለጫ ከመሆን አልፎ ባህል ከሆነ ውሎ አድሯል። ይህም አሁን ላለው የዓለም ሰላም እና መረጋጋት ያለው አበርክቶ መተኪያ የሌለው እንደሆነም በዘርፉ የተሰማሩ ምሑራን በአጽንዖት የሚናገሩት እውነታ ነው። ዘመኑን የሚዋጅ የሚያሻግር የፖለቲካ አስተሳሰብ መሠረት እንደሆነም ይታመናል።

እኛም እንደሀገር ከዚያም አለፍ ሲል የብዙ ሥልጣኔ እና የረጅም ዘመን የሀገረ መንግሥት ምሥረታ ታሪክ ባለቤት እንደሆነ ሕዝብ በአንድም ይሁን በሌላ ሀገራዊ የፖለቲካ እሳቤዎቻችን ለዚህ ዓለም አቀፋዊ እውነታ የተገዛ መሆን እንዳለበት ይታመናል። መንደርን ይሁን ጎጥን፤ ከዛም አልፎ ሀገር እና ሕዝብን እወክላለሁ የሚል ፖለቲካኛ የፖለቲካ ስብዕናው በዚህ እውነታ የተገራ ሊሆንና ሚዛናዊነትን የፖለቲካ ሕይወቱ መርሕ እና ባህል ማድረግ ይጠበቅበታል ።

በተለይም የሕዝባችን ሃይማኖታዊ ባህላዊ እና ማኅበራዊ እሴቶቹ ለሚዛናዊነት እና ታማኝነት ትልቅ ስፍራ የሚሰጡ፤ ራስወዳድነትን፣ ማስመሰል እና ቅጥፈትን አብዝተው የሚያወግዙ፤ ለሌላው መኖርን እና መሰጠትን በስፋት የሚሰብኩ፣ በብዙ መከራ እና ጨለማ ውስጥ ሳይቀር ነገን በተስፋ መጠበቅን በእምነት የሚያስተምሩ፣ በየዘመኑ ተስፈኛ ትውልድ መፍጠር ያስቻሉ ናቸው። የዛሬም ሆነ የትናንት የይቻላል መነቃቃታችንም የዚሁ እውነታ አንዱ መገለጫ ነው።

ለእነዚህ የሕዝባችን ሀይማኖታዊ ባህላዊ እና ማኅበራዊ እሴቶቹ ያልተገዛ የፖለቲካ እሳቤ ከመሠረቱ ሕዝባችንን የሚመጥን አይደለም። ውዥንብር እና ግርግር ከመፍጠር የዘለለ የሕዝባችንን ነገዎች ብሩህ፤ የመሆን መሻቱን ተጨባጭ ማድረግ አያስችልም። የፖለቲካ መድረኮቻችን መማማሪያ እና መተራረሚያ እንዳይሆን ፈተና ከመሆን ያለፈም ፋይዳ አይኖረውም።

እንደ ሀገር በተፈጠረው አስቻይ ሁኔታ የማኅበረሰብም ሆነ የቡድን ውክልና ወስደው ሀገራዊ ፖለቲካው ውስጥ በመሳተፍ ላይ የሚገኙ ግለሰቦችም ሆኑ ቡድኖች፤ እንወክለዋለን የሚሉት ሕዝብ ከእነርሱ የሚጠብቀው ከትናንት የሚያሻግረው የፖለቲካ አስተሳሰብ እና ለዚያ የሚሆን ቁርጠኝነትን እንጂ በጥላቻ እና በጨለምተኝነት የተቃኘ፤ በራስ ወዳድነት እና በአሉባልታ የተገራ የፖለቲካ አስተሳሰብ አይደለም። ዘመኑን በሚመጥን እሳቤ ከትናንት የሚዋጀውን እንጂ ትናንት ላይ ተቸንክሮ የሚያስቆዝመውን አይደለም።

የወከለን ሕዝብ ማኅበረሰባዊ እሴቶቹ እና ከዚህ የሚመነጨው ማንነቱ፣ ለሚዛናዊነት እና ታማኝነት ትልቅ ስፍራ የሚሰጥ፤ አሉባልታን፣ ማስመሰል እና ቅጥፈትን የሚጠየፍ፤ ለሌላው መኖርን እና መሰጠትን የሚሰብኩ፣ በብዙ መከራ እና ጨለማ ውስጥ ሳይቀር ነገን በተስፋ በእምነት የሚጠብቅ መሆኑን ለደቂቃ ልንዘነጋው አይገባም።

አዲስ ዘመን ዓርብ መጋቢት 12 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You