
የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናት ምርምር ማዕከል ያዘጋጀው አማርኛ መዝገበ ቃላት “ሥልጣን” የሚለውን ቃል አንድን ነገር ለማድረግ፣ ለመሥራት፣ ወይም ለማሠራት የሚያስችል መብት፤ የመንግሥት አስተዳደርን ወይም አመራርን በበላይነት ለማካሄድ የሚያስችል ኃይል፣ ሹመትና ኃላፊነት ሲል ይበይነዋል። “ሥልጡን” የሚለውን ቃል ደግሞ ንቁ፣ ቀልጣፋ፣ ጨዋ፣ ትሑት፣ ሥርዓት ያለው ብሎ ያፍታታዋል።
ሥልጣን ሥልጡን በሆነ መንገድ ሲመራ ነገር ይሰምራል። በምርጫ ተወዳድሮ የሕዝብን ይሁንታ በማግኘት ሥልጣን ላይ የወጣ ፓርቲ የሥልጣኑ ምንጭ የሆነውን ሕዝብ ሲያከብር ሥልጡን ይሆናል። የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በዚህ ሰሞኑን በማኅበራዊ ድረ ገጹ ባጋራቸው ሁለት መረጃዎች ሥልጣን ሲሠለጥን ምን መልክ እንደሚኖረው አስመልክቶናል።
የመጀመሪያው ጉዳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በፌስቡክ ገጻቸው በሀገራችን ያለውን የአፕል ልማት በተመለከተ ካሰፈሩት አጭር መልዕክት ጋር አያይዘው ከለጠፏቸው ፎቶዎች ጋር የሚያያዝ ነው። ከተለጠፉት ፎቶዎች መካከል ሁለቱ ከኢንተርኔት ላይ የተወሰዱ መሆናቸውን የሚገልጽ ትችት ተሰማ። በዚህ ጊዜ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ብዙዎችን ባስገረም ግልጸኝነት ኃላፊነት የተመላ ምላሽ በመስጠት የእርምት ርምጃ መውሰዱን አስታውቋል።
ጽሕፈት ቤቱ ለትችቱ በሰጠው ምላሽ ላለፉት ሰባት ዓመታት የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር የኮሙኒኬሽን ዘዴ ለየት ባለ መንገድ ግልጽነት እና ተደራሽነትን በማለም የተከናወነ መሆኑንና ዋነኛ ዓላማውም በልዩ አተያይ ሃሳቦችን፣ ለሥራ ተነሳሽነት የሚፈጥሩ ልምዶችን እና ተግባራትን በማካፈል ላይ እንደሚያተኩር በመግለጽ ይንደረደራል።
አልፎ አልፎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከክልሎች የሚገኙ የሥራ ሪፖርቶችን እንደሚያጋሩ ጠቅሶ፣ ይሁንና ከታችኛው የአስተዳደር እርከን ጀምሮ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር ደረጃ መረጃዎች በሚፈሱበት ሂደት አንዳንድ ትክክል ያልሆኑ አቀራረቦች በተለያየ እርከን በሪፖርቶች ሊካተቱ መቻላቸውን ከአፕል ፍራፍሬ ልማት ጋር ተያይዞ በተጋራው መልዕክት መረዳቱን ያትታል።
ለጥቆማ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የፌስቡክ ገጽ ከተጋሩ ምስሎች ውስጥ የተወሰኑት ከመስክ ከተገኙ እውነተኛ ፎቶዎች ጋር ተቀላቅለው ከክልል ከነበረ ልውውጥ እስከ ፌዴራል ደረጃ በመድረሳቸው ስህተቱ መፈጠሩን ያብራራል።
ቁልጭ ባሉ ቃላት ስህተት መፈጠሩን ከማመን ባሻገር የተሳሳቱ ምስሎቹን የያዘው ልጥፍ ከክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ገጽ ተነስቷል። ጉዳዩን ላይ እርምት እንዲወሰድ ያሳወቁ ዜጎችም ተመስግነዋል። ወደፊት ትክክለኛ መረጃ እና አቀራረብ የያዙ ዘገባዎች በሚዲያዎች እንዲቀርቡ ይደረጋል ሲል የተወሰዱ ርምጃዎችን ይገልጻል፤ ወደፊት ተመሳሳይ ስህተት እንዳይፈጠር ጥንቃቄ እንደሚደረግም ይጠቁማል።
ሥልጣን ሥልጡን በሆነ መንገድ ሲመራ መልኩ ከላይ የተገለጸውን ይመስላል። የጽሕፈት ቤቱ ምላሽ የሥልጡንነት ውሃ ልክ ከፍ ብሎ ታይቶበታል። ሌሎች መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ሊማሩበት የሚገባ ሥልጣኔ የገራውን ሥልጣን መልክ ያመላከተ ሰሌዳ ሆኖ ተሰቅሏል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ሌላም አበጀ ያሰኘው ተግባር ፈጽሟል። በፌስ ቡክ ገጹ ባጋራው ሌላ ልጥፍ ዜጎች በትምህርት፣ በጤና፣ በኢኮኖሚ ጉዳዮችና በሌሎች አምራች ዘርፎች ያሏችሁን ጥያቄዎች እና ማብራሪያ የሚሹ ጉዳዮችን እስከ ማክሰኞ መጋቢት 2 ቀን 2017 ዓ.ም. በዚህ ገጽ ይላኩልን። የሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተው ምላሽና ማብራሪያ ይሰጣሉ ብሏል። ጥያቄውን ተከትሎ ዜጎች በተጠቀሱት ዘርፎች ያሏቸውን ጥያቄዎች ከመልዕክቱ ስር አስፍረዋል።
ከአንድ ሳምንት ቆይታ በኋላ ጽሕፈት ቤቱ ባጋራው ሌላ መልዕክት ዜጎች ያቀረቧቸው ጥያቄዎች የሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎች የሰጡትን ምላሽና ማብራሪያ በዚህ ሳምንት እናቀርባለን ብሏል። ከመልዕክቱ ጋርም እድሳት በተደረገለት ብሔራዊ ቤተመንግሥት ቅጥር ግቢ ውስጥ በሚገኝ አረንጓዴ ስፍራ የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)፣ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር መቅደስ ዳባ እና የገንዘብ እና ኢኮኖሚ ሚኒስትር ዴኤታው እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ግማሽ ክብ ሠርተው ተቀምጠው የሚታዩበት ምስል ተጋርቷል። ከአንድ ቀን በኋላም ሚኒስትሮቹ በየዘርፋቸው ለተነሱ ጥያቄዎች የሰጧቸው ምላሾች በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን እንደሚቀርቡ የሚገልጽ ተንቀሳቃሽ ምስል ይፋ ሆኗል። በተንቀሳቃሽ ምስሉ ላይ ሚኒስትሮቹ በዜጎች ከተነሱላቸው ጥያቄዎች የተወሰኑትን እያነበቡ ታይተዋል።
ይህም ሌላ የሥልጣኔ መገለጫ ነው። አስፈጻሚው አካል በየጊዜው ከሕዝብ ለሚነሱ ጥያቄዎች በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምላሽ የሚሰጥበት አሠራር ብቻውን በቂ አይደለም። ዜጎች በየዘርፉ የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች በቀጥታ ለሚመለከተው አካል ማንሳት የሚችሉበት መሰል ዕድል መፈጠሩ አበረታች ነው።
ሥልጣን ላይ ያለው አካል ሲሠለጥን የመረጠውን ሕዝብ ያከብራል። ሥልጣን ፈላጭ ቆራጭነት፣ አምባገነንነት እና ማንአለብኝነት ሳይሆን ተጠያቂነትን የሚያስከትል ኃላፊነት መሆኑን ተረድቶ የመረጠውን ሕዝብ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጥያቄዎች ለመመለስ የነደፈውን ስትራቴጂ ለመተግበር ሥልጡን በሆነ መንገድ ይንቀሳቀሳል።
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ሁሉ በሌሎችም ተቋማት ሥልጣን መሠልጠን አለበት። ዜጎችም ሥልጣን ሲሠለጥን አብረን መሠልጠን ይጠበቅብናል። ሁሉን ነገር ተጠራጥሮ የትም አይደረስም። ዓይናችንን እጸጽን ብቻ ሳይሆን እንዲህ ያለውን መልካም ነገር ለማየት ማሠልጠን ይገባናል።
አርዓያነት ያላቸው መሰል አሠራሮችን ካላበረታታን በኖርንበትና በታመምንበት መንገድ እያነከስን ማዝገማችንን መቀጠል ዕጣችን ይሆናል። ወደኋላ እንዳንመለስ ተራማጅ አሠራሮችን ማበረታታትና እውቅና መስጠት ግድ ይለናል። ሥልጣን ሲሠለጥን “የነብርን ጭራ ከያዙ አይለቁም” ማለት እንጂ “ታጥቦ ጭቃ” ን መተረት ፍሬ አይሰጥም።
ተስፋ ፈሩ
አዲስ ዘመን ሐሙስ መጋቢት 11 ቀን 2017 ዓ.ም