
ለብዙ ዜጎቻችን ሞት፣ የአካል ጉዳት፤ በከፍተኛ መጠን ለሚቆጠር የሀገር ሀብት ውድመት ምክንያት የሆነው በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ተከስቶ የነበረው ጦርነት በፕሪቶርያ የሰላም ስምምነት መቋጫ ማግኘቱ ይታወሳል። ስምምነቱ በትግራይ ክልል የጥይት ድምፅ እንዳይሰማ፤ ሕዝቡ ወደ ዕለት ተዕለት ሕይወቱ እንዲመለስ ያስቻለ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ እውቅና የተቸረው ስኬት ነው።
በርግጥ መንግሥት ከጦርነቱ በፊት አለመግባባቶች በሰላማዊ መንገድ በውይይት እና በድርድር የሚፈቱበትን ሁኔታ ለመፍጠር ረጅም መንገድ ተጉዟል። የሀገር ሽማግሌዎች ታዋቂ ሰዎችን እና የሃይማኖት አባቶችን ወደ ክልሉ በመላክ ችግሩ በሰላም እንዲፈታ ጥሯል። የግጭት ዋንኛ ሰለባ የሆኑ እናቶችን የሰላም መልዕክተኛ አድርጎ ሁኔታዎች ወደ ትጥቅ ግጭት እንዳያመሩ በስፋት ተንቀሳቅሷል።
በዚህ ሁሉ ጥረት ውስጥ ነገሮች ባልተገባ ሁኔታ፤ ሀገር እና ሕዝብን አክሳሪ ባደረገ መንገድ ተጉዘው ጦርነቱ ተቀስቅሷል። በጦርነቱ ብዙ ዜጎች ለሞት፤ ለተለያዩ የአካል ጉዳቶች፤ ቀላል ግምት የማይሰጠው የሀገር እና የሕዝብ ሀብት ለውድመት ተዳርጓል። ጦርነቱ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በሚኖሩ ዜጎች ላይ የፈጠረው የሥነልቦና ስብራትም እስከዛሬ በአግባቡ አላገገመም።
ጦርነቱ በብዙ ትውልዶች ከፍ ባለ መስዋዕትነት ተጠብቆ የኖረውን የሀገሪቱን ሕልውና ስጋት ውስጥ የጨመረ፤ ታሪካዊ ጠላቶቻችንን ጨምሮ የሀገሪቱ ብሩህ ነገዎች የሚያስጨንቃቸው ኃይሎች ክስተቱን እንደ መልካም አጋጣሚ ወስደው ለማትረፍ በስፋት የተንቀሳቀሱበት ነበር፤ አደጋውን ለመቀልበስ የኢትዮጵያ ሕዝብ የከፈለውም ዋጋ ቀላል እንዳልሆነ የአደባባይ ምስጢር ነው።
መንግሥት በጦርነት ውስጥ በነበረባቸው ወቅቶች ሳይቀር ችግሩን በሰላም ለመፍታት የተለያዩ ጥረቶችን አድርጓል፤ ቀድሞ ወደ ግጭት የገባው የሕወሓት ኃይል የሕልውና ስጋት ውስጥ በነበረበት ሁኔታ ችግሩ ለዘለቄታው በሰላማዊ መንገድ የሚፈታበትን አስቻይ ሁኔታ በማመቻቸት እና ለሰላም ቀድሞ ተገዥ በመሆን የፕሪቶርያ የሰላም ስምምነት ተግባራዊ እንዲሆን ከግማሽ መንገድ በላይ ተጉዟል።
ስምምነቱ ተግባራዊ ከሆነበት ዕለት ጀምሮም ስምምነቱ ላስቀመጣቸው የውሳኔ ሀሳቦች በግንባር ቀደምትነት ተገዥ በመሆን ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት በተጨባጭ አሳይቷል። ከስምምነቱ የውሳኔ ሀሳቦች ባለፈ መንገድ በመጓዝም ሰላም ምን ያህል ለሀገሪቱ እና ለሕዝቦቿ ብሩህ ነገዎች ወሳኝ አቅም እንደሆነ አሳይቷል።
ስምምነቱ ከተፈረመበት ዕለት አንስቶ ስምምነቱን ችግር ውስጥ ሊከቱ የሚችሉ ጠብአጫሪ ድርጊቶችን በሆደ ሰፊነት ከማለፍ ጀምሮ፤ ያልተገቡ የጥፋት አዝማሚያዎችን እና ትንኮሳዎችን በትዕግስት በማለፍ የሰላም ስምምነቱ የሚጠበቀውን ውጤት እንዲያመጣ ረጅም መንገድ ተጉዟል። ዳግም በትግራይ ምድር የጥይት ድምፅ እንዳይሰማ በመፈለግም ብዙ ተፈትኗል።
የትግራይ ሕዝብ ጦርነቱ ከፈጠረው የሥነ ልቦና እና ኢኮኖሚ ስብራት እንዲያገግም በቢሊዮን የሚቆጠር ሀብት መድቦ ተንቀሳቅሷል። ሕዝቡ ወደ ቀደመው የዕለት ተዕለት ሕይወቱ እንዲመለስ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ብዙ ሀብት አፍስሰው ሕዝቡን ተጠቃሚ ማድረግ እንዲችሉ ሠርቷል። ቢሮዎች መደበኛ ሥራቸውን እንዲያቀላጥፉም የሚቻለውን አድርጓል።
መንግሥት በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቀዬያቸው እንዲመለሱ፤ የታጠቁ ኃይሎች በፕሪቶርያው ስምምነት መሠረት ተገቢውን ሥልጠና ወስደው ወደ ማኅበረሰቡ እንዲቀላቀሉ ለማድረግ ከዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ጋር በመሆን ሰፋፊ ጥረቶችን አድርጓል።
ይህም ሆኖ ግን በሕወሓት መካከል በተፈጠረ የሥልጣን ይገባኛል ክፍፍል እና ክፍፍሉ በፈጠረው የጠላትነት ፍረጃ የመንግሥት ጥረቶች የሚጠበቀውን ያህል ውጤት ማምጣት አልቻሉም። በተለይም በሕወሓት ውስጥ የተፈጠረው ጽንፈኛ ኃይል ጥረቶቹ ውጤታማ እንዳይሆኑ የተለያዩ አሰናካይ ምክንያቶችን በማቅረብ የትግራይን ሕዝብ የሰላም ፍላጎት የፖለቲካ መቆመርያ ካርድ አድርጎታል።
ይህ አንጃ በፕሪቶርያው ስምምነት መሠረት የተዋቀረውን፤ በጊዜው የሁሉንም ይሁንታ ያገኘውን የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር እንቅስቃሴ እግር በእግር እየሄደ ከማሰናከል ባለፈ ተፈናቃዮች ወደ ቀዬአቸው እንዳይመለሱ፤ ወደሰላማዊ ሕይወት መግባት የሚፈልጉ ታጣቂዎች የፈለጉትን እንዳይሆኑ ፈተና ሆኖባቸዋል። ለዚህ ደግሞ ሰሞኑን የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንት ጌታቸው ረዳ ለጋዜጠኞች በግልጽ ቋንቋ አመልክተዋል ።
አቶ ጌታቸው እውነታውን ወደ አደባባይ ይዘውት ይምጡ እንጂ ጉዳዩ ከሁሉም በላይ ለትግራይ ሕዝብ የተሰወረ አይደለም። በተለይም የትግራይ ወጣት የጦርነቶች ዋነኛ ገፈት ቀማሽ ከመሆኑ የተነሳ በንቃት የሚከታተለው እና ከእርሱ የተሰወረ እንዳልሆነ ይታመናል።
የትግራይ ወጣት አሁን ላይ ከሁሉም አብልጦ ለሚፈልገው ሰላም እና ልማት፤ ራስን የመሆን እና ራስን አሸንፎ የመውጣት መሻት የፕሪቶርያው ስምምነት ዋስትናው ነው። ትናንት ባልተገባ ጦርነት ምክንያት ከአጠገቡ ያጣቸውን የእድሜ አቻዎቹን ሆነ፤ ተስፋቸውን የተነጠቁ የትግራይ ወላጆችን የልብ ስብራት ሊጠግን የሚችለው ይሄው ስምምነት ነው።
የትግራይ ሕዝብ በተለይም የትግራይ ወጣት ስምምነቱ ተግባራዊ እንዲሆን ከሁሉም በላይ ስምምነቱ እንዳይተገበር ፈተና ሆነው ያሉ ኃይሎችን በቃችሁ ሊላቸው፤ በሚገባቸው ቋንቋ ሊነግራቸው ይገባል። በትግራይ ወጣት ደም እና በሕዝብ መከራ እና ስቃይ የሥልጣን ቁመራ የያዙ ኃይሎችን በቃችሁ እኛን ለራሳችን ፈቃድ ተዉን ሊላቸው ይገባል። ይህን በማድረግም ከውስጥም፤ ከውጪም በትግራይ ሕዝብ ላይ የተደገሰውን የጥፋት ድግስ መቀልበስ ይቻላል !
አዲስ ዘመን ሐሙስ መጋቢት 11 ቀን 2017 ዓ.ም