
ተፎካካሪነት በመርህ የሚገዛ እና ውጤትን ታሳቢ ያደረገ፤ ከሁሉም በላይ ተሽሎ መገኘትን የሚጠይቅ ነው። በየትኛውም ዘርፍ የሚደረግ ፉክክር የመመዘኛ ስሌት አለው፤ በአንድም ይሁን በሌላ ተፎካካሪውን የሚያተርፍ፤ የመፎካከሪያ መድረኩን ቀጣይነት የሚያስጠብቅ፤ የመፎካከርን ማሸነፍና መሸነፍ እንዳለ ለመቀበል የሁሌ ዝግጁነት የሚፈልግ ነው።
በተለይም በፖለቲካ መድረክ ላይ የሚታይ ተፎካካሪነት፤ ሀገር እና ሕዝብን ከማስተዳደር ጋር የተገናኘ ኃላፊነትን ተቀብሎ መንቀሳቀስን የሚጠይቅ በመሆኑ በከፍተኛ ጥንቃቄ የሚመራ እና በብዙ ዝግጁነት የሚሰላ ነው። የፉክክር መድረክ ድንገት በተፈጠረ አጋጣሚ በሞቅታ የሚገባበት ነገር አይደለም።
በብዙ መገራት እና በመገራት ውስጥ ባለ ዝግጁነት የሚቀላቀሉት፤ የአንድን ሀገር እና ሕዝብ ከዚያም አልፎ የቀጣይ ትውልድን እጣ ፈንታ መወሰን የሚያስችል የኃላፊነት መገራት፤ ከፖለቲካ ዲስኩር እና ማነብነብ ባለፈ ለያንዳንዱ ዜጋ የዕለት ተዕለት ሕይወት ኃላፊነት ወስዶ መንቀሳቀስን የሚጠይቅ ነው።
ከተለመደው የፖለቲካ ሴራ እና መጠላለፍ ወጥቶ፤ ለሕዝብ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ከፍ ባለ የሃሳብ ልዕልና መገለጥን፤ የሕዝብን ሆኖ የመገኘት መሻት በሚመጥን ደረጃ ራስን ማዘጋጀት፤ ለዚህ የሚሆን የማያቋርጥ የማንነት ግንባታ የሚጠይቅ፤ ከትናንት አክሳሪ የፖለቲካ ባህል እና ባህሉ ከፈጠረው የጥፋት መንገድ መራቅን የሚፈልግ ነው።
በተለይም የአሁናዊው ዓለም የፖለቲካ እሳቤ እና እሳቤው እየፈጠረው ካለው መልከ ብዙ ፍላጎቶች አኳያ፤ አንድን ሀገር እና ሕዝብን ለመምራት እና ለማሻገር የሚደረግ የፖለቲካ ፉክክር /መነሳሳት ሀገራዊ አካባቢያዊ እና ዓለም አቀፋዊ እውነታዎችን በአግባቡ ተገንዝቦ ወደ ስኬት መጓዝ የሚያስችል ሰፊ እውቀት እና ጥበብን የሚጠይቅ ነው።
ከእያንዳንዱ አሉታዊም ሆነ አዎንታዊ ክስተቶች ማትረፍ በሚያስችል ሁለንተናዊ ዝግጁነት የገዘፈ የፖለቲካ ሥብዕና፤ በሕዝብ መሻት የተገራ የሰከነ ማንነት፤ ትናንትን በአግባቡ ተረድቶ እና ተቀብሎ፤ ነገን ዛሬ በመሥራት ራስን እና ትውልድን ከትናንት ፈተናዎች ማሻገር የሚያስችል ሁለንተናዊ ዝግጁነት ይፈልጋል።
የፖለቲካ መድረክ የተወዳዳሪነት እሳቤ፤ ሀገር እና ሕዝብን የተሻለ ተጠቃሚ የማድረግ፤ የሕዝብን መሻት ወደሚጨበት የነገ ሕይወት የመለወጥ መነሳሳት የሚንጸባረቅበት፤ ለዚህ የሚሆን የግለሰቦች እና የቡድኖች /ፓርቲዎች ቁርጠኝነት የሚደመጥበት እና የሚታይበት ሰላማዊ የፉክክር መድረክ ነው።
የሃሳብ ልዕልናን መሠረት በማድረግ የራስን እና የቡድንን ፍላጎት ለሀገር እና ለሕዝብ አሳልፎ መስጠትን፤ በሀገር እና በሕዝብ ጉዳይ በኃላፊነት መንፈስ በጋራ መንቀሳቀስን፤ ከጠላትነት ይልቅ አጋርነትን፤ ከመገፋፋት ይልቅ መሰባሰብን፤ ከመካሰስ ይልቅ መተራረምን መርህ አድርጎ መንቀሳቀስን የሚጠይቅ ነው።
በተለይም እንደኛ ባሉ በተሳሳተ የፖለቲካ ባህል ረጅም ዘመናትን በግጭት እና በሰላም እጦት ለማሳለፍ ለተገደዱ ሀገራት ፖለቲከኞች፤ የፖለቲካ የፉክክር መድረኮችን የአዲስ የፖለቲካ ባህል ግንባታ ዕድል፤ ከግጭት አዙሪት ለዘለቄታው መውጫ መንገድ አድርገው ሊወስዱት ይገባል።
እንደ አንድ ፖለቲካኛ ሀገር እና ሕዝብን ተጠቃሚ በማድረግ የራስን አዎንታዊ ዐሻራ አስቀምጦ በታሪክ ውስጥ የደመቀ ስፍራ ለማግኘት፤ ከሁሉም በላይ ከትናንት አክሳሪ የፖለቲካ አስተሳሰቦች ራስን መግራት፤ የሀገር እና ሕዝብን፤ ከዚያም አልፎ የቀጣይ ትውልድን እጣ ፈንታ መወሰን የሚያስችል ኃላፊነት ለመውሰድ የሚያስችል ዝግጁነት መፍጠር ያስፈልጋል።
በፖለቲካ የሐሰት ዲስኩር በሴራ እና በተዛነፈ ትርክት የሚፈጠር የፖለቲካ ተቀባይነት ቀናትን አልፎ ሀገር እና ሕዝብን ማሻገር የሚያስችል አቅም የለውም። ከዚያ ይልቅ የሕዝብን የመሆን መሻት በማቀጨጭ ወዳልተፈለገ ድባቴ እና ተስፋ መቁረጥ የሚወስድ ነው። ከዚህ ያልተገባ፤ ዘመኑን ከማይመጥን የፖለቲካ አካሄድ ራስን መግታትም የሕዝባዊነት አልፋና ኦሜጋ ነው!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 14 ቀን 2017 ዓ.ም