ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ወደ ናንጂንግ አቅንተዋል

የዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮና ከነገ በስቲያ በቻይና ናንጂንግ ይጀመራል። ከዓለም አትሌቲክስ ዋና ዋና ውድድሮች መካከል አንዱ የሆነው የቤት ውስጥ ሻምፒዮና በተወሰኑ ርቀቶች የሩጫ እና የሜዳ ተግባራት የዓለም ክዋክብት አትሌቶች ይፎካከሩበታል። 264 ሴቶችና 312 ወንዶች በአጠቃላይ 576 አትሌቶች የሚካፈሉበት ይህ ሻምፒዮና ባለፈው ፓሪስ ኦሊምፒክ ሜዳሊያ ያጠለቁ 20 አትሌቶችን ማፎካከሩ ይበልጥ ትኩረት እንዲስብ አድርጎታል።

በቤት ውስጥ ሻምፒዮና በርካታ ሜዳሊያ በመሰብሰብ ተፎካካሪ ከሆኑ ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ስትሆን፣ በሻምፒዮናው ኢትዮጵያን የሚወክለው ቡድንም ሌሊቱን ወደ ስፍራው ማቅናቱን ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ይጠቁማል። ፌዴሬሽኑ የካቲት 27 ቀን 2017 ዓ.ም ይፋ ባደረገው ዝርዝር መሠረት ኢትዮጵያን በሻምፒዮናው የሚወክለው ቡድን በ800 ሜትር ሴቶች እና በ1ሺ500 ሜትር እንዲሁም 3ሺ ሜትር ርቀቶች በሁለቱም ፆታዎች 14 አትሌቶችና ሁለት አሠልጣኞችን ያካተተ ነው።

ኢትዮጵያ በሴቶች ብቻ በምትሳተፍበት የ800 ሜትር ፉክክር የወርቅ ሜዳሊያ የምትጠብቅ ሲሆን፣ አትሌት ጽጌ ድጉማ፣ ሃብታም ዓለሙንና ንግሥት ጌታቸው ተሳታፊ ይሆናሉ። ኢትዮጵያ እምብዛም ውጤታማ ባልሆነችበት ርቀት ከቅርብ ዓመት ወዲህ በኦሊምፒክ ጭምር የብር ሜዳሊያ ማጥለቅ የቻለችው የ24 ዓመቷ ወጣት አትሌት ጽጌ ድጉማ የወቅቱ የርቀቱ ኮከብ ነች። በድንቅ አሯሯጥ ልምድ ያላቸውን አትሌቶች ጭምር በማሸነፍ አስደናቂ ብቃት ላይ የምትገኘው ጽጌ ድጉማ ከፓሪሱ ኦሊምፒክ የብር ሜዳሊያ በተጨማሪ በ2023ቱ የግላስኮ የቤት ውስጥ ሻምፒዮና እንዲሁም በአፍሪካ ጨዋታዎች በርቀቱ ለኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳሊያዎችን ማስመዝገቧ ይታወሳል።

የተያዘውን የውድድር ዓመት በድንቅ ብቃት የጀመረችው ጽጌ በሦስት የቤት ውስጥ የዙር ውድድሮች በአሸናፊነት በማጠናቀቅ ከፍተኛ ነጥብ ካስመዘገቡ አትሌቶች መካከል አንዷ ነች። ይህም ናንጂንግ ላይ ሁለተኛውን የቤት ውስጥ ሻምፒዮና የወርቅ ሜዳሊያ እንድትታጭ አድርጓታል። በተመሳሳይ በቤት ውስጥ የዙር ውድድሮች ጥሩ ጊዜ ያሳለፈችውና በርቀቱ የካበተ ልምድ ያላት ሃብታም ዓለሙ እንዲሁም ንግሥት ጌታቸው የሜዳሊያ ተፎካካሪዎች እንደሚሆኑ ይጠበቃል።

ሌላኛው ኢትዮጵያ ከፍተኛ የአሸናፊነት ግምት ያገኘችበት ርቀት በሴቶች 1ሺ500 ሜትር ሲሆን፤ በመካከለኛና ረጅም ርቀት የመም ውድድሮች ስኬታማዋ አትሌት ጉዳፍ ፀጋይ ለድል ትጠበቃለች። በሦስት የመድረኩ ተሳትፎዎቿ የወርቅ፣ የብርና የነሐስ ሜዳሊያዎችን ያጠለቀችው ጉዳፍ፤ እአአ በ2021 ሌቪን ላይ ያስመዘገበችው 3:53.09 ሰዓት የርቀቱ የዓለም ክብረወሰን ነው። በተደጋጋሚ የራሷን ሰዓት ለማሻሻል ጥረት አድርጋ ባይሳካላትም ሦስት ፈጣን ሰዓቶችን በማስመዝገብም ብቸኛዋ አትሌት ናት። የዘንድሮውን የውድድር ዓመቱ በቤት ውስጥ የዙር ውድድር ሌቪን ላይ የጀመረችው ጉዳፍ ፈጣን ሰዓት ማስመዝገቧ የሚታወስ ሲሆን፣ ናንጂንግ ላይም ኮከብ እንደምትሆን ይጠበቃል።

በርቀቱ ከጉዳፍ በተጨማሪ ሌላኛዋ ብርቱ አትሌት ድርቤ ወልተጂ በዋናው የዓለም አትሌቲክስ ቫምፒዮና ያሳየችውን ብቃት ትደግማለች ተብሎ ይጠበቃል። በሌቪን የቤት ውስጥ ዙር ውድድር ያሸነፈችው ወጣቷ አትሌት፤ በዙር ውድድሮች 800 እና 1ሺ500 ሜትር ድንቅ ተሳትፎ ከነበራት ወርቅነሽ መሰለ ጋር በመሆን ለተጨማሪ ሜዳሊያ ይፋለማሉ።

በዘንድሮው የቤት ውስጥ ዙር ውድድር አስደናቂ ብቃት በማሳየት ከፍተኛ ነጥብ አስመዝግባ በቀጥታ በናንጂንግ ሻምፒዮና በቀጥታ የመግቢያ ካርድ ካገኙት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች መካከል ሁለተኛዋ ፍሬወይኒ ኃይሉ ናት። በኦስትራቫ እና ሌቪን አሸናፊ የሆነችው አትሌቷ በ3ሺ ሜትር ሴቶች ቡድኑን ትመራለች። ቤልግሬድ ላይ በ800 ሜትር የብር እንዲሁም በግላስኮ በ1ሺ500 ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት የነበረችው አትሌቷ አሁን ደግሞ በሌላኛው ርቀት ድሉን በድጋሚ በእጇ እንደምታስገባ ይጠበቃል። ከሳምንታት በፊት ማድሪድ ላይ አሸናፊ የነበረችው ብርቄ ኃየሎም እና ጽጌ ገብረሰላማም ቀላል ግምት የማይሰጣቸው አትሌቶች ናቸው።

በወንዶች በኩል በበርሚንግሃም እና ቤልግሬድ 1ሺ500 ሜትር የወርቅ ሜዳሊያዎችን ያጠለቀው አትሌት ሳሙኤል ተፈራ ዘንድሮም ኢትዮጵያን ይወክላል። በማድሪዱ የዓለም የቤት ውስጥ የዙር ውድድር አሸናፊ የነበረው መለሰ ንብረትም የርቀቱ ተጠባቂ አትሌት ነው።

ጠንካራ አትሌቶች ከተካተቱባቸው ርቀቶች መካከል አንዱ የሆነው የ3ሺ ሜትር ወንዶችም ኢትዮጵያ ሜዳሊያ የምታሳካበት እንደሚሆን ይጠበቃል። በፓሪስ ኦሊምፒክ 10ሺ ሜትር የብር ሜዳሊያ አሸናፊው አትሌት በሪሁ፣ ቡድኑን ይመራል። በውድድር ዓመቱ በበርካታ ውድድሮች ተሳትፎ አቅሙን ያጠናከረው ጌትነት ዋለ እና በቱሪን እና ሌቪን የዙር ውድድሮች ሁለተኛ ያጠናቀቀው ወጣቱ አትሌት ቢንያም መሐሪም የቻምፒዮናው ብርቱ ተፎካካሪ ይሆናል።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 10 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You