ባሕር ዳር – በችግሮች ውስጥ አልፎ ውጤት የማስመዝገብ አብነት !

በመደመር ዕሳቤ ያለፉ ወረቶቻችን ለዛሬ መሠረቶቻችን ናቸው በሚል አቅጣጫ ቅርሶችን ከመፍራት ወደ ማፍራት የተሸጋገርንበት ዘመን ላይ እንገኛለን፡፡ ያለፉት እሴቶቻችንን በዛሬ ላይ በማከል የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያውያን የጋራ ግብ እና የጋራ ሕልም ያለን ሕዝቦች ነን፡፡

ይህንኑ መነሻ በማድረግ ከለውጡ ወዲህ መንግሥት አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻ ግንባታዎች በስፋት በማከናወንና ነባር ቅርሶችን በማደስ ለቱሪዝም ዘርፉ መጠናከር የማይተካ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል፡፡ እንደ ሀገርም ኢኮኖሚውን ወደ ፊት ያሻግራሉ ብሎ ተስፋ ከጣለባቸው የግብርና፤ ኢንዱስትሪ፤ ማዕድንና ቴክኖሎጂ ጋር በአንድነት የቱሪዝም ዘርፉ የመሪነት ሚና እንዲኖረው ተደርጓል፡፡

ይህንኑ ሀገራዊ ራዕይ መሠረት በማድረግም ሀገራዊ ለውጡ ዕውን ከሆነበት 2010 ጀምሮ የተፈጥሮ ሀብቶችን በማወቅ፤ በመለየት፤ በማልማትና መመጠቀም ረገድ እመርታዊ ለውጦች ታይተዋል፡፡ በዚህም የተዘነጉ ከተሞች ጭምር ዛሬ የመታየት እና የመጎብኘት ዕድል አግኝተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በከተሞች ምሥረታ ሂደት ረጅም ታሪክ ያላት ሀገር ነች፡፡ ሆኖም የከተሞቹ አመሠራረት እውቀትን ተከትሎ እና አስፈላጊው መሠረተ ልማት ተሟልቶ የተቆረቆሩ ባለመሆናቸው፤ ለኑሮም ሆነ ለሥራ ምቹ ሳይሆኑ ዘመናት ተሻግረዋል፡፡ ይህንኑ ችግር ከመሠረቱ ለመቅረፍም መንግሥት የኮሪዶር ልማት ፕሮጀክትን ይፋ በማድረግ ከተሞች ውብ እና ለኑሮ ተስማሚ እንዲሆኑ በርካታ ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡

በአሁኑ ወቅት በበርካታ ከተሞች የኮሪዶር ልማት እየተከናወነ ሲሆን፣ የኮሪዶር ልማቱም ከተሞች ለኑሮ እና ለሥራ ተስማሚ እንዲሆኑ እና በተጓዳኝም የቱሪዝም ማዕከል እንዲሆኑ በር የከፈተ ነው፡፡ ይህ ዕድል ከገጠማቸው ከተሞች አንዷ የሆነችው የባሕር ዳር ከተማ ተፈጥሮ ባደላት ውበቷ ላይ የኮሪዶር ልማቱ ተጨማሪ ውበትን አላብሷታል፡፡

የአማራ ክልል ዋና ከተማ እና የጣና ዳር ፈርጥ የሆነችው ባሕር ዳር ተፈጥሮ ካደላት ውበት ውጪ ይሄ ነው የሚባል እድሳት ሳይደረግላት ዘመናትን ተሻግራለች፡፡ በዚህም ምክንያት ውበቷ ከጊዜ ጋር እያረጀ መጥቷል፡፡ ሆኖም በአሁኑ ወቅት ከተማዋ በተፈጠረላት የኮሪዶር ልማት ተፈጥሮ እና የሰው ጥበብ ተዋሕደው ባሕር ዳርን ይበልጥ ውበቷን እያወጡት ነው።

ባሕር ዳር ተፈጥሮ ከለገሳት ውበት ባሻገር በኮሪደር ልማቱ የተከናወኑት የመንገድ እና የመዝናኛ ማዕከላት ግንባታ ከተማዋን አዲስ ውበት አላብሷታል፤ ዳግም የተወለደች ያህልም ታይታ የማትጠገብ ውብ የንግድ እና የቱሪስት መዳረሻ ለመሆን በቅታለች፡፡ በዛፍና በቁጥቋጦ ተሸፍኖ የነበረው የጣና ውበት በኮሪደር ልማቱ ተገልጦ ለከተማዋ አዲስ ውበት አላብሷታል፡፡ ተዳፍኖ የቆየው የጣና ውበት በስምንት አቅጣጫ ተከፍቶ ከከተማዋ የትኛውም አካባቢ የሚታይ ፀዳልን አጎናጽፏታል፡፡

ጣና ለዘመናት የነበረ ውበት ነው፡፡ ባሕር ዳር የጣና ሐይቅና የዓባይ ወንዝ መገናኛ ናት። ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ያስቆጠሩ የዘንባባ ዛፎች አሏት። በአጠቃላይ ባሕር ዳር ተፈጥሮ ፀጋዋን ያፈሰሰችባት እና ውበቷን ያርከፈከፈችበት ውብ ስፍራ ብትሆንም ዘመኑን የሚዋጅ ውበት ሲታከልበት በነባር ዕሴቶቻችን ላይ አዳዲስ ዕሴቶችን በመጨመር ብልፅግናን ማረጋገጥ እንደሚቻል ባህሕር ዳር ቋሚ መዘክር መሆን ችላለች፡፡

ባሕር ዳር ከተፈጥሮ መስሕቧ ባሻገር በጣና ዙሪያ ያሉት ታሪካዊ ሥፍራዎች፤ ከጣናና ከዓባይ ጋር ተያይዘው የተሠሩት ወደቦችና መናፈሻዎች፤ የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም፣ የዓባይ ዘመናዊ ድልድይ እና ሌሎቹም ልማቶች ባሕር ዳርን የ22ኛው መክዘ የንግድና ቱሪዝም ማዕከል ያደርጓታል፡፡ ይህቺ ካሏት ውብ የተፈጥሮ መስሕቦችና ታሪካዊ ስፍራዎች ባሻገር የኮሪዶር ልማቱ የፈጠረላት ዕድል ከተማዋ ታይታ የማትጠገብ የቱሪስት መዳረሻ እንድትሆን ያደርጋታል፡፡

ታዲያ ባሕር ዳር ይህን ሁሉ ስኬት የተጎናጸፈችው ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ ሆኖላት አይደለም፡፡ በክልሉ በነበረው ግጭት እና አለመረጋጋት ባሕር ዳር በችግር ውስጥ ብታልፍም ፈተናው ሳይበግራት እና የተጀመሩ ሥራዎች ለአፍታም ሳይስተጓጎሉ ውጥኗን ከዳር ማድረስ ችላለች፡፡ እንደ አዲስም ለመወለድ በቅታለች፡፡ ይህም ከተማዋን አይበገሬነት ተምሳሌት እንድትሆን እና በችግሮች ውስጥ አልፎ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚቻል ማሳያ ያደርጋታል፡፡

አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 10 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You