የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ በኅብረት ሥራ ማኅበራት ሲተረጎም

ዜና ትንታኔ

አዲሱ የግብርናና የገጠር ልማት ፖሊሲ ተግባራዊ መሆን የግብርናው ዘርፍ እንደ ሀገር ያለውን ድርሻ ከፍ እንዲል ከማስቻሉም በላይ ሌሎች ዘርፎችን ከማሳደግና ከማጠናከር አንጻር የማይተካ ሚና አለው:: በተለይም ለኅብረት ሥራ ማኅበራት የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ እንደሆነ ይገለጻል:: ለመሆኑ ይህ ፖሊሲ የኅብረት ሥራ ማኅበራትን ከምን አንጻር ተጠቃሚ ያደርጋቸዋል ስንል በዘርፉ የሚሠሩ ባለድርሻ አካላትን አነጋግረናል::

የኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ሺሰማ ገብረሥላሴ፤ ስለተሻሻለውና አዲሱ የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ የኅብረት ሥራ ማኅበራትን ከማጠናከር አንጻር በርካታ ሀሳቦችን ይዞ እንደመጣ ይናገራሉ:: በ1994 ዓ.ም የነበረው የገጠር ልማትና ግብርና መምሪያ ፖሊሲ ስትራቴጂና ማስፈጸሚያ ስልት የኅብረት ሥራ ማኅበራት መርሆዎችን በአብዛኛው ያከበረ አልነበረም:: በነፃ የመደራጀት መብት አይሰጣቸውም:: የአባላት ባለቤትነትንም አይፈቅድም:: ለመግባትና ለመውጣትም ፍላጎትን አይጠይቅም:: ከሁሉም በላይ ደግሞ የውጭ አካላት ጣልቃ ገብነት በስፋት የሚታይበት ነበር:: አዲስ የወጣውና የተሻሻለው የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ ግን ብዙ መብቶችን የሰጠና ተጠቃሚነታቸውን የሚያረጋግጥ ነው ይላሉ::

እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ የግብርና እና ገጠር ልማት ፖሊሲው ለኅብረት ሥራ ማኅበራት በርካታ ጠቀሜታ አለው:: አንዱ በሚሠሩባቸው የአገልግሎት ዘርፎች ላይ የተጠናከረና ቀጣይነት ያለው ተግባር እንዲያከናውኑ ማስቻሉ ነው:: ሌላው የግብርናና የገጠር ልማት ፖሊሲን እውን ማድረግ ዘላቂና ቀጣይነት ያለው የኅብረት ሥራ ማኅበራትን ተሳትፎ ያረጋግጣል:: ሰፊ የሥራ ዕድል ለመፍጠርም ያስችላል:: ማኅበራቱ በገቢ እድገታቸውም ከፍ እንዲሉ ያግዛቸዋል:: በገጠር ሰፊና ዘላቂ ሥራ እንዲያከናውኑም ያደርጋቸዋል:: በተለይ የግብርና ግብዓቶችን ተጠቅመው አምራች ለሚሆኑ፤ አቅርቦት ላይ ለሚሠማሩ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ከፍተኛ አስተዋፅዖ ይኖረዋል::

ፖሊሲው በአገልግሎት ዘርፉ ትራንስፖርት፣ ንግድና ስርጭት ዙሪያ ሰፊ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ዕድል የሰጣቸው ነው:: በሌላ በኩል ኅብረት ሥራ ማኅበራት በዋናነት ዓላማቸው አድርገው የሚሠሩት የሕዝብ አቅምን በማሰባሰብ ለጋራ ጥቅም መንቀሳቀስ ነውና ፖሊሲው ይህንን የሚያረጋግጡበት ዕድል እንደሰጠም አንስተዋል::

ፖሊሲው ኅብረት ሥራ ማኅበራትን ለቁጠባና ብድር እንዲሁም ለገጠር ፋይናንስም ምቹ መደላደል የሚፈጥርላቸው ነው:: ለአብነት ኅብረት ሥራ ማኅበራት የግብርና ምርት ማሳደጊያ፤ የግብዓትና ቴክኖሎጂዎች አቅርቦት ስርጭትን የሚያሳልጡ፤ የሀገር ውስጥና የውጪ ንግዶችን ግብይት በአግባቡ እንዲመሩ የሚያደርጉ፤ የግብርና ሜካናይዜሽን ግብይትና አቅርቦትን የሚያፋጥኑ ስለመሆናቸውም በዝርዝር አስቀምጧል:: አርሶና አርብቶ አደሮችን በማደራጀት ምርቶቻቸውን በማሰባሰብና በማከማቸት የመጋዘን አገልግሎት የሚሰጡ፤ የምርት ደረጃ የመለየትና የማሸግ አገልግሎት በመስጠትም ምርቶቻቸው ጥራቱን የጠበቁ እንዲሆኑላቸው የሚያደርጉ ስለመሆናቸውም ፖሊሲው እውቅና ሰጥቷልና በስፋት የሚጠቀሙበትን ዕድል ያመቻቸ ስለመሆኑም ተናግረዋል::

ኢንቨስትመንትን እንዲያሰፉ የፋይናንስ አማራጮች እንዲጠቀሙ ዕድል የፈጠረ፤ በአባላት ጥቅም ላይ ተንተርሰው የሚጓዙ እንዲሆኑ፤ የአባሎቻቸውን አቅም አሰባስበው በአግባቡ የሚመሩና የሚጠቀሙ፤ እንዲሁም አባሎቻቸው እንዲጠቀሙ እሴት የመጨመር መብት የሰጣቸው ነውና ጠቀሜታው ለኅብረት ሥራ ማኅበራት ብዙ እንደሆነም ይገልጻሉ::

በግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የግብርና ፖሊሲ ጥናትና የምግብ ሥርዓት ዳይሬክተር አቶ ረታ ዋቅጋሪ በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ የፖሊሲው ዋና ዓላማ የአርሶአደር ገቢን፤ ኑሮን በማሻሻል ግብርናውን ማሻገርና ምርታማነትን ማሳደግ እንዲሁም ድህነትን በመቀነስና የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ግብርና የኢኮኖሚ ዕድገት የመሪነት ሚናውን እንዲወጣ ማስቻል ነው:: ከዚህ አንጻርም ፖሊሲው ሲዘጋጅ ግብርናው አካታች እንዲሆን ተደርጎ ነው:: አካታች ሲባል ደግሞ የግል ባለሀብቱንና የኅብረት ሥራ ማኅበራትን ከፍተኛ ሚና እንዲጫወቱ ዕድል በመስጠት ነው::

በቀደመው ፖሊሲ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ምርትን ከማቅረብና ገበያን ከማረጋጋት ውጪ ሌሎች ዘርፎች ላይ እንዲሳተፉ አይፈቅድም ነበር:: በተቀጠረና በሠለጠነ የሰው ኃይልም አይመሩም:: የማኅበረሰቡን ተጠቃሚነት እያረጋገጠ የገቢ ምንጮቹን እያየና አዋጭነት ባለው መልኩ እንዲሠሩም ዕድል የሚሰጥ አልነበረም:: የቁጥጥር ሥራቸው ደካማ በመሆኑ የሀብት ብክነት የሚያጋጥማቸው ነበሩ:: አሁን ግን እነዚህ ሁሉ ታይተው መፍትሔ እንዳገኙ ጠቅሰዋል:: የተሻሻለው ፖሊሲ 10 ዋና ዋና ጉዳዮችን ለይቶ እንዳስቀመጠና ከእነዚህ ውስጥም አንዱ ለኅብረት ሥራ ማኅበራት የሰጠው መብት እንደሆነም አመላክተዋል::

የኅብረት ሥራ ማኅበራት ከፍታዎች ብሎ ከአስቀመጣቸው ተግባራት መካከልም የመጀመሪያው ኅብረት ሥራ ማኅበራት ማደግና ዘመናዊ አሠራር ውስጥ መግባት አለባቸው የሚለው ነው:: ሌላው ከውጪ አካል ተፅዕኖ የተላቀቁና ራሳቸውን የቻሉ ገለልተኛ ተቋም መሆን አለባቸው ይላል:: የኅብረተሰቡን አገልግሎት የሚያሳልጡ እንዲሆኑም አቅጣጫ ያስቀምጣል ብለዋል::

ተወዳዳሪና በቅጥር የሚሠራ የሠለጠነ የሰው ኃይል እንዲኖራቸውና በዚያ ሊመሩ እንደሚገባም የሚያስቀምጥ ነው:: በኅብረት ሥራ ማኅበራት ውስጥ በዋናነት የሚሳተፉት አነስተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች በመሆናቸው የሼር መጠናቸው ትንሽ ነው:: በአነስተኛ ካፒታል ደግሞ በኢኮኖሚው ውስጥ ተወዳዳሪ መሆን አይቻልም:: ስለሆነም ፖሊሲው እንዲዋሓዱና ገቢያቸውን እንደያጠናክሩ ዕድል ይሰጣል:: ከዚያም ባሻገር ድጋፍ እንዲደረግላቸውም ይፈቅዳል:: በዚህም ተወዳዳሪና በገቢያቸው ያደጉ እንዲሆኑ ያግዛቸዋልም ይላሉ::

እንደ አቶ ረታ ማብራሪያ፤ ፖሊሲው ኅብረት ሥራ ማኅበራት በብዙ የሥራ ዘርፎች ውስጥ ተሳታፊ የሚሆኑበትን ዕድልም ሰጥቷቸዋል፡ በእሴት ጭመራ፤ በብድርና በቁጠባ፤ በመሠረተ ልማት አገልግሎት በስፋትና በጥራት እንዲሳተፉ አቅጣጫ የተቀመጠበት ነውም:: ሌላው የፋይናንስ ምንጫቸውን እንዲያሰፉ ዕድል ሰጥቷቸዋል:: አንዱ የራሳቸውን ገቢ እንዲያሰፉ ሲሆን፤ ሌላው የባንክ ብድር በስፋት እንዲያገኙ የሚያደርግ ነው:: ከዚህ አንጻርም ያሉት ባንኮች በቂ ሆነው ካልተገኙ ተጨማሪ ባንኮች ጭምር እንዲቋቋሙ ይፈቅዳል:: ይህም የኅብረት ሥራ ባንክ ወይም የገጠር ባንኮች ላይ የተመረኮዘ ነው::

ፖሊሲው የኅብረት ሥራ ማኅበራት ኦዲትና ኢንስፔክሽን እንዲሁም እውቅና አሰጣጥ እንዲጠናከር የሚፈቅድ ሲሆን፤ ይህ ዕድል በኅብረት ሥራ ማኅበራት ውስጥ ተዓማኒነትን ከመፍጠር፣ ካፒታላቸውን ከመጠበቅ ፣ በአግባቡ ከመመራት እንዲሁም ገቢያቸውን እንዲያሳድጉ ከማስቻል አኳያ የማይተካ ሚና ይኖረዋል ሲሉም አቶ ረታ አብራርተዋል::

ቀደም ሲል በነበረው አሠራር ኅብረት ሥራ ማኅበራት ሲቋቋሙ ከ10 እስከ 50 በሚደርሱ አርሶአደሮች ነበር:: ይህ ደግሞ በገቢ የሚጠናከሩበት ሁኔታ አነስተኛ እንዲሆን አድርጎታል:: አሁን ግን እነዚህ ሁኔታዎች በመፈታታቸው ከ110 ሺህ በላይ ማኅበራት በሀገራችን ውስጥ እንዲኖሩ ዕድል ሰጥቷል:: በዚህ ውስጥም ወደ 28 ሚሊዮን ሕዝብ መደራጀት ችሏል::

ሁለቱም የዘርፉ ባለድርሻ አካላት እንዳሉት፤ ፖሊሲው በተቀመጠው ልክ መተግበር ከቻለ የኅብረት ሥራ ማኅበራት በውጭው ዓለም እንደምናየው በኢኮኖሚው ውስጥ ከፍተኛ ሚናን እንዲጫወቱ ይሆናሉ:: በተለይም ደግሞ በግብርናና ገጠር ሽግግር ሂደት ውስጥ በእሴት ጭመራ፤ ምርት ማሳደግና ምርት ግብይት እንዲሁም የአገልግሎት አቅርቦት ውስጥ አዎንታዊ ሚናን እንዲጫወቱ ያደርጋቸዋል:: ማኅበረሰቡን ጠቅመው የራሳቸውን የገቢ ሁኔታ በማሳደግ ኢኮኖሚው ለሀገር እድገት አስተዋፅዖ እንዲኖረውም ያስችላሉ::

ጽጌረዳ ጫንያለው

አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 10 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You