ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ያደመቀው የባሕል ስፖርቶች ፌስቲቫል ፍፃሜ

“ባሕላዊ ስፖርቶቻችን ለጠንካራ ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን” በሚል መሪ ቃል በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ሆሳዕና ከተማ ለተከታታይ ዘጠኝ ቀናት ሲካሄድ የቆየው 22ኛው የባሕል ስፖርቶች ውድድር እና 18ኛው የባሕል ስፖርቶች ፌስቲቫል ተጠናቋል።

ከትናንት በስቲያ በአቢዮ ኤርሳሞ ስታዲየም በተከናወነው ደማቅ የመዝጊያ ሥነ ሥርዓት አማራ ክልል አጠቃላይ አሸናፊ ሆኗል። ከውድድሮቹ በተጨማሪ ሲካሄዱ በነበሩ ፌስቲቫልና በልዩ ልዩ የባሕል ትርዒቶች ደግሞ፤ ኦሮሚያ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል፤ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ያሉትን ደረጃዎች በመያዝ አጠናቀዋል፡፡ ለአሸናፊዎቹ ክልሎችም የዋንጫና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።

በውድድሩ መጨረሻ እለት በአዲስ አበባ እና በኦሮሚያ ክልል ከ63-67 ኪሎ ግራም ክብደት የትግል ውድድር የፍፃሜ ጨዋታ ተካሂዷል። ኦሮሚያ ክልል የውድድሩ አሸናፊ ሲሆን፣ አዲስ አበባ 2ኛ ሆኖ ፈፅሟል። ቀደም ብሎ የደረጃውን ፍልሚያ ማሸነፉን ያረጋገጠው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ 3ኛ ሆኗል፡፡

በውድድሩ መዝጊያ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት፣ በባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ መኪዩ መሐመድ፤ “የባሕል ስፖርቶች ለአንድነታችን ፍቱን መድኃኒት በመሆናቸው፣ ወደ ክልሎችና ወደሌሎችም በማውረድ በየደረጃው ሊሠራባቸው ይገባል” የሚለውን ሀሳባቸውን አፅንዖት በመስጠት፤ የባሕል ስፖርቶች ማኅበራዊ ግንኙነትና መስተጋብር የማሳለጥ እና የማኅበረሰቡን ማንነት የመግለጽ ዕምቅ አቅም እንዳላቸው ገልፀዋል። ስፖርቶቹ ከባሕልነታቸው ባሻገርም የዘመናዊ ስፖርቶች መነሻና መሆናቸው ተገቢው እንክብካቤና ጥበቃ ሊደረግላቸው እንደሚገባ ጠቁመው፣ ሁሉም በተቻለው አቅም በኃላፊነት ሊሠራ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ሚኒስትር ዴኤታው፣ የባሕል ስፖርቶች ከጨዋታነት ባለፈ በፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥም የተረጋጋ የሕዝብ ለሕዝብና መንግሥታዊ የሕዝብ ግንኙነቶችን መፍጠር እንደሚያስችሉ ጠቅሰው፤ “የባሕል ስፖርቶች የተዛቡ ትርክቶችን በማረም ሂደት ውስጥ ከፍተኛ ሚና መጫወት እንደሚችሉ አብራርተዋል። የጋራ በሆኑ በርካታ ጉዳዮቻችን ውስጥ ገዥ ትርክቶችን ለማስረጽ ዓይነተኛ ጥቅም ስላላቸውም መንግሥት በዚህ ዘርፍ ሰፊ ሥራ ይሠራል” ብለዋል፡፡ አክለውም፤ በሆሳዕና ከተማ ሲደረግ የቆየው ውድድርና ፌስቲቫል፤ በሰላምና እጅግ አስደሳች በሆነ መንገድ ተጀምሮ ፍጻሜ መድረሱ፣ በበርካቶች የጋራ ልፋትና የእርስ በርስ ትብብር የተገኘ መሆኑን በመጥቀስ፤ በየዘርፉ ኃላፊነታቸውን የተወጡትን ሁሉ አመስግነዋል፡፡

“ውድድርና ፌስቲቫሉ የታለመለትን ዓላማ ሙሉ ለሙሉ አሳክቷል” ያሉት የባሕል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ሕይወት መሐመድ፤ በየዓመቱ የባሕል ስፖርቶች ውድድርና ፌስቲቫል መካሄዱ እሴቶቻችንን ከነበሩበት ለማሳደግ ማስቻሉ እንዲሁም ያለው ሀገራዊ ጠቀሜታ ከፍተኛ መሆኑን ገልፀዋል።

እንደ ፕሬዚዳንቷ ንግግር፣ የባሕል ስፖርቶቻችን ከስፖርታዊ ውድድርነት ባለፈ በሀገር ገጽታ ግንባታ ውስጥ አይተኬ ሚና አላቸው፡፡ ከሚሰጡን ማኅበረሰባዊ ፋይዳዎች ባሻገር፣ በቱሪዝም ልማት ውስጥ ከፍተኛ የገቢ ምንጭ ማስገኘት የሚችሉም ናቸው። የዘንድሮው ውድድር ኅብረ ብሔራዊ አንድነት የታየበት፣ የልምድ ልውውጥ የተደረገበት፣ እንዲሁም በብዙ ነገሮች የደመቁ የውድድርና ፌስቲቫል ቀናት እንደነበሩ የገለጹት ፕሬዚዳንቷ፤ የሆሳዕና ከተማ ሕዝብ እንግዳ ተቀባይነት ውስጥ አኩሪ ባሕላችን የታየበት እንደሆነ በመጥቀስ፤ የቀጣዮቹ ዓመታት አዘጋጆች ከዚህ ልምድና ተሞክሮ ሊወስዱ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ሌሊሶ በበኩላቸው ባደረጉት ንግግር፤ የባሕል ስፖርቶችን ለማኅበራዊ ትስስርና ለገጽታ ግንባታ መጠቀም የሚገባንን ያህል እንዳልተጠቀምንባቸው ጠቅሰዋል። አያይዘውም፤ እስከዛሬ የሄድንበትን መንገድና በመቀየር ለቀጣይ መሥራት እንደሚኖርብን ተናግረዋል። “በቀጣይ በጥናትና ምርምር የተደገፈ ሥራ በመሥራት፣ ለሰላምና ለአብሮነት የሚጠቅም ሕዝባዊ መሠረት ማስያዝ ይኖርብናል” የሚል ሀሳብም ሰጥተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም፤ የባሕል ስፖርቱን ለማሳደግ በቂ የሆኑ የማዘውተሪያ ስፍራዎችን መሥራት እንደሚገባም ጠቅሰዋል፡፡

በቀጣይ 2018 ዓ.ም 23ኛው የባሕል ስፖርቶች ውድድር እና የ19ኛው የባሕል ስፖርቶች ፌስቲቫል አዘጋጅ የሐረሪ ክልል እንደሚሆን ተጠቁሟል። የዘንድሮው የባሕል ስፖርቶች ውድድርና ፌስቲቫል አዘጋጅ የነበረችው የሆሳዕና ከተማ ደግሞ ቀጣዩን የብሔር ብሔረሰቦች ዓመታዊ በዓልን እንደምታስተናግድ ተጠቅሷል፡፡  በተለያዩ ውድድሮች ለአሸናፊዎች የዋንጫ፣ ሜዳሊያና የምስክር ወረቀት ተበርክቷል፣፣

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን  መጋቢት 9 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You