
ሀገር በአንድ ትውልድ አትሠራም፤ አልተሠራችምም። ይልቁንም በዘመን ሂደት ውስጥ ቀደምቶች ለተከታዮቻቸው እያበጁና እያቀኑ ያስረክባሉ። ተቀባዮችም ከቻሉ አልቀው ሠርተውና አበልፅገው፤ ካልቻሉ ደግሞ ባለበት ጠብቀው በማቆየት ለተተኪዎች ያቀብላሉ። እንዲህ እንዲህ እያለ በትውልዶች ቅብብሎሽ ሀገር ትሠራለች፤ ትለማለች፤ ትበለፅጋለች፤ በሙሉ ሉዓላዊነት ሰገነት ላይ ትቆያለች።
ይሄን በማድረግ ሂደት ደግሞ የወጣቶች ሚና ከፍ ያለ ነው። ምክንያቱም ወጣትነት ትኩስ ኃይልና ሞራል ብቻ ሳይሆን፤ እውቀትና ክህሎት ማከማቻ ወቅት ነው። ለዚህም ነው አንድ ሀገር እንድትሠራም ሆነ እንድትፈርስ ሲፈለግ ቀድሞ የወጣቱ ኃይል ላይ ትኩረት የሚደረገው።
ኢትዮጵያም እንደ ሀገር፣ ኢትዮጵያውያንም እንደ ሕዝብ በዚህ መልኩ ወጣቱን የሀገር ልማትና እድገት አቅም፤ የሰላም፣ የነፃነትና ሉዓላዊነትም ማዕከል በማድረግ ለሺሕ ዓመታት የዘለለ ጊዜን መዝለቅ ተችሏል። ዛሬም ቢሆን ኢትዮጵያ የወጣት ሀገር ከሚባሉ ቀዳሚ ሀገራት መካከል አንዷ እንደመሆኗ፤ ልማቷን፣ ሉዓላዊነቷም በእነዚሁ ወጣቶች ላይ የተመሠረተ ነው።
ወጣቱም፣ የወጣትነት ትኩስ ኃይልነትም ሆነ የፈጠራና የብልፅግና አቅም መሆኑን በተግባር እየገለጠ ይገኛል። መንግሥትም ለወጣቱ በሰጠው ልዩ ትኩረት የወጣቱን ኃይልነት፤ የእውቀትና ክህሎት መፍለቂያነት፤ የሀገር ክብርና ሉዓላዊነት አቅምነት በልኩ እንዲገለጥ እያደረገ ይገኛል። ይሄ ደግሞ ወጣቱን ለሀገራዊ ክብር፣ እድገትና ብልፅግና፤ በጥቅሉም የተሟላ ሉዓላዊነት ያለውን አበርክቶ አውጥቶ እንዲጠቀም የሚያስችለው ነው።
ይሁን እንጂ ከትናንት እስከ ዛሬ ከዚህኛው መንገድ በተቃራኒው የሚራመዱ፤ ወጣቱን የልማት ሳይሆን የጥፋት ፍላጎታቸው መጠቀሚያ ሊያደርጉ የሚተጉ ግለሰቦችና ቡድኖች አልታጡም። እነዚህ ግለሰቦችና ቡድኖች ታዲያ፤ ወጣቱን በሀገርና ሕዝብ ልክ ሳይሆን፤ በራሳቸው ጥቅምና ፍላጎት ልክ እየቀረጹ መጠቀሚያ ማድረግ ዋነኛ መገለጫቸው ነው።
ለዚህ መንገድ ጥሩ ማሳያ የሚሆኑት ደግሞ፣ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ የዘለቀን ዘመን ትውልድን በጦርነት ውስጥ እየማገዱ በሥልጣን ላይ የመቆየት፣ ሀብት የመፍጠር እና የግልና የቡድን ፍላጎቶቻቸውን በማሟላት የተጠመዱ ጥቂት የሕወሓት አንጃዎች ናቸው።
እነዚህ አንጃዎች ትናንት በነፃነት ስም አንድን ትውልድ ያልተገባ ዋጋ አስከፍለዋል። በኋላም ለሥልጣናቸው መደላድል እንዲሁ ሌላ ትውልድ ዋጋ አስከፍለዋል። በቅርቡም ሀገርና ሕዝብ ያዋለደውን ለውጥ ተላምዶ መራመድ ተስኗቸው ሦስተኛ ትውልድ ወጣትን ያልተገባ መስዋዕትነት አስከፍለዋል።
እዚህ ጋ ልብ ሊባል የሚገባው፤ እነዚህ አንጃዎች በወጣቶች መስዋዕትነት ላይ ራሳቸውን የሚገነቡ፤ ሞትና መከራ የማይጋፈጡ፤ በአዛውንትነት እድሜያቸውም ስለ ወጣቶች ለውጥና እድገት ሳይሆን ስለራሳቸው ድሎትና ምቾት ሲሉ በአስር እና በመቶ ሺዎች ታዳጊ ወጣቶችን ወደ እሳት የሚነዱ ናቸው።
ከሰሞኑም እንዲሆን እየሠሩ ያሉት ይሄንኑ ነው። ይሄ ደግሞ ከሁለት ዓመታት ደም አፋሳሽ ጦርነት በኋላ በፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት መሠረት ሰላማዊ አየር የታየበትን የሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢ፤ በተለይም የትግራይ ክልል ዳግም ወደ ጦር አውድማነት የመቀየር አካሄዳቸው ነው።
ይሄ አካሄድ፣ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል የሚከወን አይደለም። ይልቁንም የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት እየፈጠረው ያለው ሰላም እረፍት የነሳቸው፤ ጥቅማቸውን ያሳጣቸው፤ በሕዝቡ ዘንድ የተጠያቂነት መንፈስ እየፈጠረባቸው መሆኑን የተገነዘቡ ጥቂት አፈንጋጭ የሕወሓት አዛውንቶች ስብስቦች ሕልውና ሲባል የሚከወን ነው።
ይሄን መሰሉ አካሄድ ግን ዛሬ ላይ የትግራይ ሕዝብና ወጣት የሚሻው አይደለም። ለዚህም ነው በተለይ ወጣቱ ዛሬ ላይ ሰላምና ልማትን፣ እድገትና ሠርቶ መበልፀግን እየተመኘው። ወጣቱ ለዚሁ ነው ለእኩይ ተግባራቸው ተገዢ መሆንን አምርሮ እየተጠየፈ ያለው። የለውጥ እንጂ የጥፋት አቅም መሆንን እያወገዘ የሚታየው።
ዛሬ ላይ ወጣቱ ጦርነት ሳይሆን ሰላምን ነው የሚሻው። ድህነት ሳይሆን፣ እድገትን ነው የናፈቀው። አጥቶ መሰደድና መከራ መቀበልን ሳይሆን፣ በሀገሩ ሠርቶ መለወጥን በሚችልበት መንገድ ላይ መራመድን መምረጡ። እነዚህ አንጃዎች ግን ይሄ የወጣቱ ምኞትና ሕልም አይታያቸውም። ምክንያቱም እነርሱ ሰላም ሰፍኖ ሕዝቡ ፊቱን ወደ ልማት ከመለሰ፤ ግፍና በደላቸው ገዝፎ በሕዝብ ዘንድ የሚፈጠረውን ጥያቄ መመለስ፤ በሕዝብ ፊት መቆምም፤ ከተጠያቂነትም ማምለጥም አይችሉም።
እናም ከተጠያቂነት ለማምለጥም፤ የራስ ፍላጎትና ጥቅምን ለማስቀጠልም ሲሉ፤ ወደ ንስሐ በመቅረቢያ ብሎም የእርቅ ሽማግሌ በመሆኛ የእርጅና ዘመናቸውም ወጣቱን ከሰላም የማናጠል፤ ወደ ጦርነትም የመማገድ ሕልምና ትልም ይዘው ከውጪ ኃይሎች ጋር ጭምር ተባብረው እየሠሩ ይገኛሉ።
ይሄ ደግሞ በዚህ ወቅት በኢትዮጵያ ምድር፣ በትግራይም ክልል ሊሆን የማይገባው ብቻ ሳይሆን፤ ወጣቱም እንዲሆን የማይፈልገው ጉዳይ ነው። ዛሬ ወጣቱ ጦርነት ሳይሆን ሰላምና ልማትን ነው የሚሻው። ይሄን የወጣት ሕልምና ምኞት ነው መንግሥትም ተገንዝቦ እየሠራና ውጤት እየታየ ያለው።
በመሆኑም ከዚህ በተቃራኒ የሚጓዙ፤ በእርጅና ዘመናቸውም በወጣቱ ደም ለመነገድ የሚተጉ አንጃዎች ከዚህ መንገዳቸው ሊመለሱ ይገባል። ምክንያቱም ጊዜው ወጣቱን ለጦርነት ሳይሆን ለሰላምና ልማት ተግባር ማስቀደምን አብዝቶ የሚሻ ነው። ሊታሰብም፣ ሊሆንም የሚገባው ይሄው ወጣቱን ለልማት ማስቀደምን የሃሳቦችና የተግባራት ሁሉ ቀዳሚ ማድረግ ነው።
አዲስ ዘመን መጋቢት 9 ቀን 2017 ዓ.ም