ባለፉት ሰባት ዓመታት የተመዘገቡ ውጤቶች ለኢትዮጵያ ብልፅግና መሠረት የጣሉ ናቸው!

መንግሥት በሕዝብ ቅቡልነት ማጣቱን ተከትሎ በ2010 ዓ.ም አዲስ የለውጥ መንግሥት በኢትዮጵያ ዕውን ሆነ። ውሎ ሳያድርም የለውጡ መንግሥት ሀገሪቱ ለዘመናት የገጠማትን የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ስብራት መጠገን የሚያስችሉ ርምጃዎችን መውሰድ ጀመረ።

በተለይም በፖለቲካ አስተሳሰባቸው ምክንያት ለእስር ተዳርገው የነበሩ እስረኞችን መፍታት፤ ሀገር እንዳይገቡ ማዕቀብ ተደርጎባቸው የነበሩ ፖለቲከኞችና ታዋቂ ግለሰቦች ወደ ሀገር እንዲገቡ መፍቀድ፤ አሳሪ የነበሩ የሚዲያ፤ የሰብዓዊ መብቶች፤ የሽብር እና የግብረሠናይ ድርጅቶችን ሕጎች ማሻሻል እና የፖለቲካ ምኅዳሩን ማስፋት የመሳሰሉ አዎንታዊ ርምጃዎችን በመውሰድ የለውጡን ጅማሮ አብስሯል።

የሕዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያውያን የአይበገሬነት ዓርማ ነው። የዓድዋ ድልን ያህል ክብር የሚሰጠው ነው። ሆኖም የለውጡ መንግሥት ከመምጣቱ አስቀድሞ ይህ ግዙፍ ግድብ በነበሩ ብልሹ አሠራሮች ምክንያት ወደ መክሰም እና መኮላሸት አደጋ ውስጥ ገብቶ ነበር። ለውጡ እውን ባይሆን ኖሮ ብዙዎች የሚጓጉለት እና የዘመናት የቁጭት ምንጭ የሆነው ዓባይ ግድብ መክኖ መቅረቱ አይቀሬ ነበር።

ሆኖም የለውጡ መንግሥት የነበሩ ችግሮቹን ነቅሶ በማውጣት እና አዳዲስ የአሠራር ስልቶችን በመቀየስ የዓባይ ግድብ ዳግም ነፍስ እንዲዘራ አስችሏል። ሁለት ተርባይኖች ወደሥራ እንዲገቡ በማድረግ ከኢትዮጵያ አልፎ ለቀጣናው ሀገራት ብርሃን መፈንጠቅ ችለዋል።

የለውጡ መንግሥት ሲነሳ አብሮ ስሙ እንዲነሳ ከሚያደርጉት ተግባራት ውስጥ አንዱ እና ዋናው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ነው። መርሐ ግብሩ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረኮች ጭምር ስሟ በበጎ ጎኑ እንዲነሳ ከማድረጉም በተጨማሪ የሀገሪቱን ደን ሽፋን ከ3 በመቶ ወደ 23 በመቶ እንዲያድግ አስችሏል።

ከዚሁ ጎን ለጎንም የሀገሪቱን ገጽታ እና የቱሪስት ፍሰት የሚያሳድጉ ሥራዎችንም በመሥራት ኢትዮጵያ በጎብኚዎች ተመራጭ ሀገር እንድትሆን የተሠራውም ሥራ የብዙዎችንም ቀልብ የገዛ ነው። በገበታ ለሸገር ፕሮጀክት የአንድነት፤ የወንድማማችነትና የእንጦጦ ፓርኮች ከአዲስ አበባ አልፈው የሀገር ኩራት ለመሆን በቅተዋል። በገበታ ለሀገር ደግሞ የኮይሻ፤ የጎርጎራና የወንጪ ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያ መለያ ለመሆን በቅተዋል። የኮሪዶር ልማቱም ከከተሞች አልፎ የገጠሪቱ ኢትዮጵያ ውበት እና ድምቀት ለመሆን በቅቷል።

ከእነዚህ ዓይነ ግቡ ሥራዎች ባለፈም ባለፉት ሰባት ዓመታት እመርታዊ ለውጥ ከመጣባቸው ሥራዎች አንዱ ግብርና ነው። የለውጡ መንግሥት እውን እስከ ሆነበት ጊዜ ድረስ በአጠቃላይ የነበረው ዓመታዊ ምርት ከ300 ሚሊዮን ኩንታል ብዙም የዘለለ አልነበረም። ባለፉት አምስት ዓመታት ጤፍን በክላስተር ማረስ በመቻሉ ምርቱ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ዓመታዊ ምርቱ 639 ሚሊዮን ኩንታል ሊደርስ ችሏል። ዘንድሮ ይህንን ምርት ወደ 800 ሚሊዮን ኩንታል ለማሳደግ የግብዓት እና የሙያ ድጋፎች እየተደረጉ ነው።

ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ስንዴ ሸማች ከሆኑ ሀገራት ውስጥ በግንባር ቀደምትነት የምትታወቅ ሀገር ነበረች። በየዓመቱም እስከ 107 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ በማስገባት 1 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ወጪ ስትገፈግፍ ኖራለች። ሆኖም ባለፉት ዓመታት መንግሥት ለስንዴ ምርት በሰጠው ትኩረትም ኢትዮጵያ ስንዴን ከውጭ ማስገባት ከማቆሟም ባሻገር ወደ ውጭ መላክ ጀምራለች። ይህ ጥረቷም በዓለም ላይ ስንዴ በማምረት ተጠቃሽ ከሆኑ 18 ሀገራት ተርታ አሰልፏታል። የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ከ35-40 በመቶ የሚሸፍነው ቡናም ምርታማነቱ ጨምሯል። በዘንድሮው የበጀት ዓመትም ከቡና ብቻ 2 ቢሊ ዮን ዶላር ገቢ ይጠበቃል ።

የለውጡ መንግሥት ከሠራቸው ሥራዎች አንዱ ለዘመናት የቆየውን ኢኮኖሚ መዋቅር መቀየር ነው። በ2010 ዓ.ም የሀገሪቱ አጠቃላይ የሀገር ውስጥና የውጭ ብድሮችን የዕዳ መጠን 1.5 ትሪሊዮን ብር ወይም 52 ነጥብ 57 ቢሊዮን ዶላር ነው። ይህ ደግሞ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ቅርቃር ውስጥ መግባቱን የሚያመላክት ነበር።

ይህንኑ ከግምት ውስጥ በማስገባት የለውጡ መንግሥት ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሞችን በመቅረጽ የሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት ከገባበት ቅርቃር እንዲወጣ የማይተካ ሚና ተጫውቷል። ኢትዮጵያ ለዘመናት ስትከተለው የቆየውን በውጭ ሀገራት ላይ የተንጠለጠለውን የኢኮኖሚ አቅጣጫ በመቀየር ዜጎች ባላቸው ፀጋ ላይ ተንተርሰው ሀገራቸውን እንዲለውጡ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል።

በተሠሩ ሥራዎችም የሀገሪቱ የዕዳ መጠን ከ26 ቢሊዮን ዶላር ወደ 13 ቢሊዮን ዶላር እንዲወርድ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙ አስተዋፅዖ አድርጓል።

በአጠቃላይ ባለፉት ሰባት ዓመታት የለውጡ መንግሥት እንደ ሀገር ስብራት አጋጥሞት የነበረውን የፖለቲካ እሳቤ ከመለወጥ ጎን ለጎን የኢኮኖሚ ስብራቶችን ለመቀየር የሠራቸው ሥራዎች ፍሬ ማፍራት ጀምረዋል። እነዚህን ሁሉ ውጤታማ ሥራዎችም ኢትዮጵያ ወደ ተሟላ ብልፅግና እንደሚወስዷት ያለመለክታሉ!

አዲስ ዘመን ሐሙስ መጋቢት 25 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You